አረመኔው የወያኔ አገዛዝ የጸረ ሽብርተኝነት ህጉን ህጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈኛ እያዋለው ነው ሲል አንድነት መግለጫአ አወጣ

በፍርሃት ሸምቀቆ ውስጥ ገብቶ እንደቆሰለ አውሬ ያገኘውን ሁሉ በመናከስ ያለው አምባገነን የወያኔ አገዛዝ የአንድነት ፓርቲ ም/ል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊን እንዲሁም የሌሎችንም የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ማሰሩን አስመልክቶ የፓርቲው አመራር አካላት በትናንትናው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፣ የአቶ አንዱአለም አራጌ፣ የአቶ ናትናኤል መኮንን፣ የአቶ አሳምነው ብርሀኑ እና የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መታሰር፣ ዘረኛው ወያኔ የጸረ ሽብርተኝነት ህጉን ህጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈኛ እያዋለው መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።

የአንድነት የፓርቲ አመራሮች በመግለጫቸው እንደጠቀሱት ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በአንድነት ፓርቲ ላይ በሽብርተኛ ስም ጥቃት የሰነዘረበት ፓርቲው እየተጠናከረና የህዝብ አመኔታን እያገኘ በመምጣቱ ነው ብለዋል።

እንደ አንድነት መግለጫ ወያኔ በእነ አቶ አንዱአለም ላይ የወሰደው እርምጃ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ከፍተኛውን አመራር እየያዙና ብቃታቸውን እያስመሰከሩ የመጡትና እየመጡ ያሉትን ወጣቶች ከትግል ሜዳው በማሸሸት፣ በእንጭጩ ለማስቀረት መሆኑም አመራሮቹ መናገራቸው ተገልጹአል።

አንድነት በመግለጫው መጨረሻም ህዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ መከበር በመታገል ትግሉን ሊቀለበስ ወደ ማይችልበት ደረጃ የማድረስ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቦአል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና ዘረኛው አገዛዝ በሽብር ድርጊት ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ጋዜጠኛና የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላትን ሀሙስ እለት ፍርድ ቤት እንዳቀረባቸው ተያይዞ የደረሰን ዜና አምለክቱአል፡፡ ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዷለም አራጌ፣ የመላው ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /መኢዴፓ/ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንን እና አቶ አሳምነው ብርሃኑ ሀሙስ ከቀኑ 9፡00 እስከ 11፡00 ሰዓት ድረስ በአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ችሎት እንደቀረቡ ታውቁአል፡፡

በዘረኛውና አረመኔው አገዛዝ በሽብር ተግባር የተወነጀሉት አምስት ግለሰቦች በተናጥል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን በችሎቱ በመጀመሪያ እንዲቀርብ ያደረገው የፌዴራል ፖሊስ ማንም ሰው ወደ ችሎቱ እንዳይገባ ሆን ብሎ በማገዱ የእስክንድር ቤተሰቦች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ሰዎች የክስ ሂደቱን ሳይከታተሉ ቀርተዋል፡፡

በሁለተኛው ግለሰብ ችሎት ላይ የታሳሪ ቤተሰቦችና ጋዜጠኞች ጭሀትና ብሶታቸውን በመግለጻቸው ችሎቱ ክፍት እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ ክሱን እንዲከላከል ሲጠየቅ፡- ወያኔ በአሁኑ ጊዜ በግልጽ የአፈና ሥራ እየሰራ ነው፣ እኔ ምንም ወንጀል አልሰራሁም በአንፃሩ እኔ ላይ አገዛዙ ወንጀል እየሰራብኝ መብቴን የሚያስከብርልኝ አካል ስላጣሁ፣ ይህ ፍርድ ቤትም በነፃነት ይሰራል የሚል እምነት ስለሌለኝ እስከ ሞት ፍርድ ድረስ የፈለጋችሁትን ልታደርጉኝ ሁሉ በእጃችሁ ነውና የፈለጋችሁትን ወስናችሁ ልታስታዉቁኝ ትችላላችሁና አልከላከልም” ብሏል፡፡ በችሎቱ ላይ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለቱ ፍርድ ቤቱ 28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ለጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

የጋዜጠኛ እስክንድ ነጋ ባለቤት ጋዜጠኛ ሠርካለም ፋሲል በከረንት አፌይርስ የመወያያ ክፍል ባደረገችው አጭር ቃለ ምልልስ፣ ረቡእ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ልጃችንን ከትምህርት ቤት በማምጣት ላይ ሳለ ነበር እስክንድርን ከመንገድ የያዙት፣ በጊዜው ደውሎ መያዙን ነግሮኝ የ5 ዓመት ህጻን ልጃችንን ለእኔ እስኪያስረክበኝ እንኳ አልጠበቁትም እጁ ላይ ካቴና ሲያስገቡ፣ እኔ ስደርስ ልጃችን መሬት ወድቆ ያለቅስ ነበር ብላለች፡፡ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለኢቪዥን ረቡእ ወደ 11፡30 ሰዓት አካባቢ ላይም ወደ 15 የሚጠጉ ፖሊሶችና ሲቭል ለባሾች ወደ ቤታችን መጥተው በመበርበር እስክንድር የፃፋቸውን ወረቀቶች፣ ሲዲዎችና ላፕቶፕ ኮምፒውተር ይዘው ሄደዋል ብላለች፡፡