አቡጊዳ – እቶ አንዱዋለም እና አቶ እስክንድር ከሌሎች ተከሳሾች ጋር ፍርድ ቤት ቀረቡ

መስክረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም

የአንድነት ለዲሞርካሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አንዱዋለም አርጌ፣ እዉቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባላት አቶ አስማማዉ ብርሃኑን እና አቶ ናትናዔል ጨምሮ አምስት ኢትዮጵያዉያን ፣ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 4 ቀን ከሰዓት በኋላ፣ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ገለጸ።

«መረጃ የበለጠ ለማሰባሰብ ቀናቶች ያስፈልጉኛል» ብሎ ፖሊስ በጠየቀዉ መሰረት፣ የፖሊስ/አቃቢ ሕግን ጥያቄ አንድም ጊዜ ዉድቅ አድርጎ የማያዉቀዉ ፍርድ ቤት፣ እንደተጠበቀዉ፣ ለአቃቢ ሕግ 28 ቀናት በመስጠት ቀነ ቀጠሮዉ እንዳራዘመ ለማወቅ ችለናል።

አምስቱ እስረኞች ለየብቻ ጉዳያቸው የታየ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ እስረኞች የሚሉት ነገር ካለ እንዲናገሩም እድል ሰጧል።

አቶ አንዱዋለም አርጌ የሚናገሩት እንዳለ ፍርድ ቤት ላቅረበላቸዉ ጥያቄ «መናገር የምፈልገዉ ይሄ በኔ ላይ የሚደረገዉ ነገር ፓርቲዬን ለማዳከም ነዉ። ብትፈልጉ አሁን የሞት እርምጃ ልትወስዱብኝ ትችላላችሁ። ለመብቴና ለነጻነቴ ከመቆም ወደኋላ አልልም» የሚል ምላሽ እንደሰጡ በስፍራዉ የነበሩትን በመጥቀስ ምንጮቻችን ይገልጻሉ።

ፍርድ ቤቱ «ለምን እንዲህ ትላለህ ? ይሄ ፍርድ ቤት ለዜጎች ሰብዓዊ መብት የቆመ ነዉ » በሚልበት ጊዜ፣ አቶ አንዱዋለም «ይህ ፍርድ ቤት ለዚያ እንዳልቆመ አዉቃለሁ» ሲሉ በኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓት ሳይሆን ፍርደ ገምድልነትና ኢፍትሃዊነት እንደሰፈነ ለማሳየት ሞክረዋል።

የአንድነት ፓርቲ የአምስት አመት እቅድ አዉጥቶ በስፋት በአገሪቷ ክልሎች ሁሉ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀስ ያለ፣ በሕግ እዉቅና የተሰጠዉ ደርጅት ነዉ። ላለፉት ጥቂት ወራት ፍኖተ-ነጻነት የሚል ጋዜጣ በማተም፣ ሕዝብን በከተማና በገጠር ለመድረስ እየሞከረ ሲሆን፣ በሕዝብ ዘንድም ያለዉ ተቀባይነት እያደገ የመጣ ድርጅት ነዉ።

ከሶስት አመታት በፊት የዚሁ ድርጅት ሊቀምንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በተመሳሳይ ሁኔታ በግፍና በጭካኔ፣ ሕገ ወጥ በሆነ ተግባር መታሰሯ፣ በዚያም በነፍሰ ገዳዮች ላይ ያልደረሰ፣ ስድስት ወራት በጨለማ ቤት ዉስጥ የመቀመጥ ቶርቸር እንደተፈጸመባት ይታወቃል።