አቡጊዳ – የአንድነት ፓርቲ የነ አንዱዋለምን መታሰር አጥብቆ አወገዘ – ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጠ

ፓርቲዉ ዛሬ በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ለሰላምና ለዲሞክራሲ በሚታገሉ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉ ተግባር እጅግ በጣም አሳፋሪና አሳዛኝ እንደሆነ ጠቅሶ ፣ መሰረት በሌለዉ በሽብር ክስ የታሰሩ ሰላማዊ ዜጎች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ ዜጎችን የማሰፈራራትና የማወክ ጸረ-ዲሞክራስያዊ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።

ጠንካራ ተቃዋሚዎች ላይ ኢፍትሃዊ እርምጃ በመዉሰድ የሚታወቀዉ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ፣ ሰሞኑን በነአንዱዋለም አርጌ ላይ የወሰደዉ እርምጃ፣ የአንድነት ፓርቲ ለማዳከም ብሎም የፓርቲዉ አባላት እና ደጋፊዎችን ለማደናገጥ ሆን ተብሎ ታስቦ የተደረገ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ይህን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የአንድነት ፓርቲ ያልታሰሩ የአመራር አባላት፣ ፓርቲዉ ከመቼዉም በበለጠ ትግሉን እንደሚያጠናክር፣ አባላቱም ለአላማቸው የቆረጡና የጨከኑ እንደሆነም አረጋግጧል። የገዢዉ ፓርቲ የሰሞኑ እኩይ ተግባር፣ አንድነትን የበለጠ ያጠናከረና የሚያጠናክር እንጂ የሚያዳክም እንዳልሆነም የአመራር አባላቱ ገልጸዋል።

የአንድነት አፓርቲ በመግለጫዉ በአገር ዉስጥ ሆነ ከዓገር ዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከዝምታ ወጥቶ የሚደረገዉን ፈታኝና ትዕግስት አስጨራሽ ሰላምዊ ትግልን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርቧል።

በዚህ ጋዜጣዊ መገለጫ ወቅት፣ የአገር ዉስጥ እና የአገር ዉጭ ጋዜጠኞች የተገኙ ሲሆን፣ ኤምባሲዎቻቸዉን ወክለዉ በርካታ ዲፕሎማቶች ፣ የአንድነት ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የአንድነት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አመራር አባላት፣ የብርሃን ለዲሞክራሲና ለፍትህ አመራር አባላት እና የመድረክ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ