አቡጊዳ – አቶ አንዱዋለም በባለቤታቸዉ እና በአባታቸዉ ተጎበኙ
ከትላንትና ወዲያ «በሽብር ሥራ ተሰማርተሃል» በሚል ወደ ማዕክላዊ የተወሰዱት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት እና የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ፣ አቶ አንዱዋለም አርጌ፣ በባለቤታቸው እና በአባታቸዉ ዛሬ እንደተጎበኙ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
የአቶ አንዱዋለም ባለቤት እና የአቶ አንዱዋለም አባት ፣ አቶ አንዱዋለምን ካነጋገሩ በኋላ ፣ አቶ አንዱዋለም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፣ በመንፈስ ጠንካራ እንደሆኑ ገልጸዋል።
«በአቶ አንዱዋለም እና በሌሎች ላይ መረጃ አግኝቻለሁ» ያለዉ ፖሊሲ፣ ዛሬ ወደ አቶ አንዱዋለም ቤት በመሄድ፣ ሰፊ ብርበራ እንዳደረገም ለማወቅ ችለናል።
ፍርድ ቤቱ 28 ቅናት እንዲሰጠዉ የጠየቀዉ ፖሊስ፣ ምንም አይነት መረጃ ማግኘት ስለማይችል፣ በነዚሁ ቀናት ዉስጥ የፈጠራቸዉን መረጃዎች በየቤታቸዉ ሊያስቀምጥ እንደሚችል የሚጠረጥሩ ጥቂቶች አይደሉም። በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸዉ አንድ ተንታኝ ሲናገሩ «ገዢዉ ፓርቲ በዉሸት የታወቀ ነዉ። የቴዲ አፍሮ ጊዜ መረጃ ሲያጡ የሆስፒታል ወረቀትን እንደገና አሰርዘዉ ያቀረቡ ሰዎች ናቸዉ። አሁንም እነእስክንድርን ለማሰር፣ በየቤታቸዉ መረጃዎች ማስቀመጣቸዉ አይቀርም» በማለት የገዚዉ ፓርቲ የደህንነት አባላትን የሚያሳዩትን ትያትር ለማሳየት ሞክረዋል።