አቡጊዳ – የወያኔ ታጣቂዎች የአንድነትን መሪ አቶ አንዱዋለም አርጌን አሰሩ !
በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይመራ የነበረዉና በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኝ የመጣዉ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ሆነዉ ከዚህ በፊት ያገለገሉት እና አሁን ደግሞ በሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊነት የሚሰሩት፣ ወጣት አንዱዋለም አርጌ፣ በገዢዉ ፓርቲ የደህንንት ሰዎች፣ አዲሱ አመት በገና በሁለት ቀናት ዉስጥ፣ ዛሬ፣ ታግተዉ መወሰዳቸዉን ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
አቶ አንዱዋለም የሚመሩት፣ የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል፣ ላለፉት ሁለት ወራት በየሳምንቱ፣ ፍኖተ እንጻነት፣ የተሰኘ ጋዜጣ በማሳተም፣ በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ዉጭ ከፍተኛ ሕዝባዊ ቅስቀሳዎች ከማድረግ በተጨማሪ፣ በየጊዜዉ ገዢዉ ፓርቲ በሚያራምዳቸዉ ጎጂ ፖሊሲዎች ዙሪያ፣ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ፣ ከወቀሳነት አልፈዉ መፍትሄ አመላካች የሆኑ፣ መግለጫዎችን እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል።
አቶ አንዱዋለም በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ከመሆናቸዉ በፊት፣ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት አካባቢ በምትገኝ ካፌቴሪያ ከሥራ አጋሮቻቸዉ ጋር ያወሩ የነበረ ሲሆን፣ «የፍርድ ቤት ወረቀት ይዘናል» ብለዉ ታጣቂዎች እርሳቸዉን አፍነዉ ከመዉሰዳቸው በቀር በምን ምክንይት ወደ እሥር እንደተወሰዱ የሚታወቅ ነገር የለም።
አንጋፋዉ አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ ጋዜጠኞች ዉብሸት ታዬ እና ርዮት አለሙን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን ከግንቦት ሰባት ጋር ሰርታቹሃል በሚል መሰረተ ቢስ ክስ መታሰራቸው ይታወቃል።
አቶ አንዱዋለም ከሰላማዊ ትግል ዉጭ መፍትሄ የለም ብለዉ የሚያምኑ፣ የሰላማዊ ትግል አርበኛ እና በሰላማዊ ትግል፤ የሚታገል አንጋፋ ድርጅት አመራር አባል ናቸዉ።
አቶ አንዱዋለም በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅትም የቅንጅት ከፍተኛ አመራር አባል የነበሩ ከነብርቱካን ሚደቅሳ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ጋር ለሁለት አመት በቃሊቲ የታሰሩ ፣ ወጣት፣ ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸዉ።