«አገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና ፍትሕ የሚሰፍንባት ሀገር ትሁንልን!» ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በስዊድን ያደረጉት ንግግር

መልካም አዲስ ዓመት/እንቁጣጣሽ!

ከአስቸጋሪ የእስር ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የማከብራትን የዛሬዋን እንቁጣጣሽ ከምወዳችሁ በስዊድን እና አካባቢዋ ከምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ላሳልፍ በመቻሌ ደስታዬ ለከት የለውም።

ስለዚህም በዚህ በደመቀ በዓል ላይ እንግዳ ሆኜ እንድገኝ የጋበዘኝን በስዊድን የኢትዮጵያውያን ማኅበርን እጅግ አድርጌ ላመሰግን እወዳለሁ። ከዚህም በላይ ከእስር ሰንሰለት ወጥቼ የዛሬዋ የነፃነት ቀን የእኔ እንድትሆን አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ከፍተኛ ተጋድሎ ስታደርጉ ለቆያችሁ ወገኖቼ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እግዚአብሔር ይስጥልኝ!

አዲስ ዓመት ሲመጣ ሁላችንም መጪውን ዘመን በአዲስ ተስፋ፣ በአዲስ ጉልበት እና በአዲስ ሃሳብ መቀበልን እናስባለን። ይህ ነገር በእኛ ባህል ብቻ ያለ ተግባር አይመስለኝም። እዚህ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ህዝቦችም የሚያደርጉት ይህንኑ ነው። በእኛ ዘንድ ግን ዕሳቤው ትንሽ ለየት ያለ ይመስለኛል። እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ የዓመታት መፈራረቅ ያላስቀረው፣ የመከራና የስቃይ ታሪክ ባለቤቶች በመሆናችን በአዲሱ ዘመን አዲስ ነገርን ለማየት እየተመኘንም እንኳን በጭንቅላታችን ጀርባ ’ምን ዋጋ አለው እንደድሮው ነው’፣ በማለት ስናንጎራጉር ኖረናል። ይህን የሚያሳየኝን የባህል ትውስታዬን ላካፍላችሁ።

ሁላችሁም እንደምታውቁት እንቁጣጣሽ በዓል ከማንም በላይ ለሕፃን ሴት ልጆች የፈንጠዝያ ጊዜ ነው። እኔም እንደማንኛውም ሕፃን የእንቁጣጣሽ ቀን ነግቶ እስከአየው አያስችለኝም ነበር። መንጋቱ አይቀርምና በበዓሉ ቀን ትንሽዋን ከበሮአችንን ይዘን በመንደራችን እንዞራለን። ከሀሴቴ ብዛት ልቤ በአፌ የምትወጣ ይመስለኝ ነበር። ይህን የልጅነት ደስታ ደመና የሚያጠላበት ነገር ግን አላጣሁም። ዜማው ተጀምሮ አበባየሆሽ ለምለምን ስንቀባበል በዘፈኑ አጋማሽ ላይ አንድ ግጥም ትመጣለች፣ …

ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው፣
ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው፤
ከጎኔም ጎኔን ኩላሊቴን፣
እናቴን ጥርዋት መድኃኒቴን፤ …

በልጅነት ዕዝነ ሕሊናዬ፣ የዛችን ሴት በጉልቻ የደቀቀ ጎን አስብ ነበር። እናም ይከፋኛል። የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የሀገራችንን ጎን ካነከተው፣ ቅስሟን ከሰበረው፣ ካለፈ ስቃይ ትዝታችን አያላቅቀንም። ይዘነው ወደ መጪው ዓመት መጓዛችን የማይቀር መሆኑንም እናስባለን።

በአንድ በኩል አይፈረድብንም። ዓለም የት በደረሰበት በዚህ ዘመንም እንኳን፣ ዛሬም የሀገራችን ልጆች በልቶ ማደር ወደ ጠፍር የመምጠቅን ያህል ርቆባቸዋል። ምን አልባትም አንዳንዶቹ ዛሬ በዓል መሆኑንም ዘንግተውት ይሆናል። በረሃብ ጣር ተይዘዋልና። ይኸውስ የተፈጥሮ ፍርጃ ነው እንል ይሆናል። ለነገሩ የተፈጥሮ ሳይሆን፣ ሀገሪትዋን ለዓመታት የተፈናጠጡባት የገዥዎችዋ ችግር ነው። ይባስ ተብሎ «አገርህ ላይ በስላም ልትኖር የምትችለው፣ አስብ ያልንህን ስታስብ፣ ተናገር ያልንህን ስትናገር፣ አድርግ ያልንህን ስታደርግ ብቻ ነው» ተብሎ ኩሩ ኢትዮጵያዊ አንገቱን ተሰንጎ ይኖራል። ይህን እምቢ ያለውንም ማሰር ሰለቸኝ በሚለው፣ በእርግጥ ግን ሰልችቶት በማያውቀው ሥርዓት እስር ቤቶች ይበሰብሳል።

ዛሬ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ሊኖሩበት ቀርቶ ሊያዩት በሚያፀይፈው የስታሊኑ ጉላግ አምሳያ በሆነው በማዕከላዊ እስር ቤት ታፍጋ አዲስ ዓመትን ታሳልፋለች። ጥፋትዋ ጠንካራ ሰብዕናዋ፣ እንደሰው ለመኖር መወሰንዋ ነው። የፖለቲካ እስረኛ የሆኑት የሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ታሪክም ከዚህ የተለየ አይደለም።

ወገኖቼ! ሀገራችን የዓመታት ሰቆቃ እግራችንን ሊጎትተን፣ መልካምን ነገር ለሀገራችን ከማለምና ከመመኘት ሊያቆመን አይገባም። የሰው ልጅ ታሪክ እንዳሳየን እንደዚሁ እልህን ያስጨረሱ፣ የዜጎችን ልብ ያሸነፉ የመሰሉ ቁጥር የለሽ ታሪካዊ ሁኔታዎች በትክክለኛው ወቅትና ጊዜ እንዳልነበሩ ሆነው ተቀያይረዋል። ለወገኖቻችን እንግልት ምክንያት የሆኑትን ክስተቶች ደጋግሞ በመንገዳችን እያመጣ ተስፋችንን የተፈታተነው ጊዜ በሌላው ተራ ደግሞ ለትውልድ እፎይታ የሚሆንን እውነታ አምጥቶ ያለፈውን ሁሉ ተረት ያደርገዋል።

ይህ የሚኖነው ግን የሁሉ ሀብት የሆነውን ጊዜ ቁጭ ብለን ስንጠብቀው አይደለም። ጊዜን፣ አዲስ ዓመትን የእኛ አጋር፣ የበጎ ተግባር አስፈፃሚ ልናደርገው የምንችለው፤ ከዛሬ አሻግረን የተሻለን ነገን እስካለምን ለህልሙም እውንነት እስከጨከንን ጊዜ ብቻ ነው።

የምወዳችሁ ኢትዮጵያውያን! ይህ አዲስ ዓመታችን ልብን አዝሎ ያው እንደድሮ ነው የማለት ወቅት ሊሆን አይገባም። ለሀገራቸው የፍትሕና የነፃነት በጎ ሃሳብ አጥርተው አስበው፣ የሀገራቸውንና የራሳቸውን መፃዒ ዕድል በራሳቸው እጅ አስገብተው፣ በሀገራቸው ለዘላለም የተተከለ ይመስል የነበረውን፣ ዜጎችን ያስጎነበሰውን የየሀገራቸውን ሥርዓት ለሁልጊዜ እንደቀየሩት ህዝቦች ሁሉ፣ በአዲስ ተስፋ፣ በአዲስ ሃሳብ ለሀገራችን በአንድነት የምንሠራበት ዘመን ሊሆን ይገባል።

በስዊድንና አካባቢው ነዋሪ ለሆናችሁ ወገኖቼ፣ እንዲሁም በሀገር ቤትና በውጭ ሀገር ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ። ሀገራችን ኢትዮጵያም ሠላምና ፍትሕ የሚሰፍንባት ሀገር ትሁንልን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!