መድረኩ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ አደረገ – አዋሳ፣ መቀሌ፣ ጅማና ባህር ዳር ይቀጥላሉ
መስክረም 8 ቀን 2003 ዓ.ም
አዲሱ አመት በገባ በአንድ ሳምንት ዉስጥ፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ መስክረም 8 ቀን 2003 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ በሚገኘው የመብራት ኃይል አዳራሽ፣ ከአምስት ሺሆች በላይ በተገኙበት፣ መድረክ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ማድረጉን ከስፍራዉ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
ትላንት አርብ መስከረም 7 ቀን እና ዛሬ መስከረም 8 ቀን ጠዋት፣ በትልቁ የተዘጋጀ የብርቱካን ሚደቅሳን ፎቶ በመያዝ፣ የመድረኩ አባላትና ደጋፊዎች በአዲስ አበባ አራቱ ማእዘናት ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ ወያኔ/ኢሕአዴግ 99.6% አሸነፍኩ ብሎ እራሱን በአለም አቀፍ ደረጃ ካዋረደበትና ከመንግስቱ ኃይለማሪያም ኢሰፓ ጋር ከተመሳሰለበት ምርጫ በኋላ፣ ይህ አይነቱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሲደረግ የመጀመሪያው እንደሆነ የደረሰን ዘገባ ይገልጻል።
በስብሰባዉ በአብዛኛዉ የተገኙት ወጣቶች ሲሆኑ ስብሰባዉን የመራዉ ተወዳጁ ወጣት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ አንዱዋለም አርጌ ነበር። ኢንጂነር ግዛቸዉ ሽፈራዉ፣ አቶ ገብሩ አሥራት፣ ዶር መራራ ጉዲና እንዲሁም በርካታ የመድረክ አመራር አባላት የተገኙ ሲሆን፣ የመክፈቻ ንግግሩንም ያደረጉት፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እስክትፈታ ድረስ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን የሚመሩት፣ ምክትል ሊቀመንበሩ ኢንጂነር ግዛቸዉ ነበሩ።
ኢንጂነር ግዛቸዉ የትግሉ ባለቤት ሕዝቡ እንደሆነ በማሳሳብ፣ ውጤት እንደሚጣ ከተፈለገ፣ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቁርጥኝነት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በተለይም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለፍትህ ለነጻነትና ለእዉነት ስትል የታሰረቸዉ ወ/ት ብርቱካን እንድትፈታ፣ መነቃነቅ እንዳለበት የገለጹት ኢንጂነር ግዛቸዉ «ብርቱካን ሚደቅሳ በአስቸኳይ መፈታት አለባት» የሚል ጠንካራና ስሜት አዘል ንግግር በተናገሩ ጊዜ፣ በስብሰባዉ የነበረዉ በሺሆች የሚቆጠረዉ ሕዝብ ከመቀመጫዉ ተነስቶ፣ በጭብጨባና በፉጨት ድጋፉን እንደሰጠ፣ ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳም ያለዉን ትልቅ ፍቅርና ሶሊዳሪቲ እንዳሳየም ከዘጋቢዎቻችን ለመረዳት ችለናል።
ከኢንጂነር ግዛቸዉ አጭር ንግግር በኋላ የመድረክ አመራር አባላት ከሕዝብ የሚቀርቡ አስተያየቶች ያዳመጡ ሲሆን ለቀረቡትም ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። ከሕዝቡ ከተሰጡት ጥያቄዎችን አስተያየቶች መካከል፡
«ለምን ወደ ሕዝቡ አትገቡም? ለምን ወደ ገጠሩ በስፋት አትንቀሳቀሱም ?»
«ምርጫዉን ማን እንዳሸነፈ እናዉቃለን። ማንን እንደመረጥን እናወቃለን። ኢሕአዴግ ህዝብ መረጠኝ ብሎ ቢያወራ ብዙ አያስጨንቃችሁ። ስራችሁን ሥሩ»
አብራችሁ በዘር ሳትከፋፈሉ በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር መሰባሰባችሁ አስደስቶናል። አንድነታችሁን የበለጠ አጠናክሩ። የበለጠ ተባበሩ። እንደገና ተከፋፍላችሁና ተጣልታችሁ አታሳዝኑን»
«በሰላም ኢሕአዴግ ስልጣን ይለቃል ብላችሁን አሁንም ታምናላችሁ ወይ ? »
መድረኩ በአዲሱ አመት በአዲስ አበባ የጀመረዉን ህዝባዊ እንቅስቃሴ በመቀጠል በአዋሳ፣ በመቀሌ፣ በጂማና በባህር ዳር ታላላቅ ህዝባዊ ስብሰባዎ በማዘጋጀት ከህዝቡ ጋር እንደሚነጋገርና ሕዝቡን የበለጠ የማደራጀት ሥራዉን እንደሚቀጥልም ለማወቅ ችለናል።