አንዱዓለም አራጌና እስክንድር ነጋ ታሰሩ

(UDJ) — ዛሬ ከቀኑ አሰር ሰዓት (10፡00) አከባቢ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አንዱዓለም አራጌ በአገዛዙ የደህንነት ሰዎች ታስሮዋል፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ተይዞዋል፡፡ አንዱዓለምና እስክንድር ከሌሎች ሁለት የአንድት ፓርቲ አባለት ጋር ከቀኑ 8፡30 ገደማ ጀምሮ አንድነት ፓርቲ አከባቢ በሚገኝ ካፍቴሪያ አከባቢ እሰከ 9፡30 ገደማ አብሮ ሲጫዎቱ ነበር፡፡

አንድነት ፓርቲ የራሱን ስትራቴጂ ነድፎ፣ በጠራ የትግል አቅጣጫና በከፍተኛ የትግል ሞራል በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ ትግሉም የራሱ ዋጋ እንደሚያስከፍል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ትግሉ አምባገነኖች ሊቀለበሱት ወደማይችሉበት ደረጃ በተቻለ ፍጥነት ማድረስ ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም አንድነት በጀመረው የሠላማዊ ትግል መንገድ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ ለሚደረገው ትግል፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህብረት በመነሳት በሀገራችን አምባገነንነት ለአንዴና ለመጨረሺያ ጊዜ እንዲያበቃ መታገል ያስፈልጋል፡፡