የአለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድቤት የሱዳኑን ፕሬዝዳንት አልባሺርን ለማሳሰር ያወጣው የዕሥር ትዕዛዝ መለስ ዜናዊ “ነግ በኔ” እንዲል አድርጎታል ሲል በዊኪሊክ ላይ ሾልኮ የወጣው የአሜሪካ የምስጢር ሠነድ አጋለጠ

የሱዳኑ ፕሬዝዳንት አልባሽር ከሥልጣን ይወገዱ ዘንድ መለስ ዜናዊ ፍላጎት እንዳለው ለአሜሪካ ባለሥልጣናት መናገሩን ይፋ አድርጎ የነበረው የአሜሪካ ኤምባሲ መረጃ፤ አልበሽር ዳርፉር ውስጥ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት በአለም አቀፍ ፍርድቤት እንዲከሰሱ መደረጉ አስደንግጦታል ማለቱን ዊኪሊክስ ይፋ ያደረገው መረጃ አጋለጠ።

ዊኪሊክስ ይፋ እንደ አደረገው የአሜሪካ ምስጢር መረጃ፤ የአለም አቀፉ ፍርድቤት አልባሽር ላይ የመሰረተው ክስ በሱዳን ውስጥ አለመረጋጋትን ከመፍጠር አልፎ ወደ ኢትዮጵያ በመዝለቅ የጸጥታ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ብሎ መለስ ዜናዊ እንደሚሰጋና በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸሙት ጭፍጨፋዎችና በተለይም በኦጋዴን ክልል ለደረሰው የዘር ፍጂት ወንጀል በሃላፊነት ያስጠይቀኛል የሚል ፍርሃት እንደለቀቀበት አረጋግጦአል።

መለስ ዜናዊ በአንድ በኩል በሱዳን ውስጥ የአስተዳደር ለውጥ እንዲኖር የአልበሽር መንግሥት ላይ መዘመት አለበት በማለት አመሪካኖችን እንደሚያግባባ ያጋለጠው መረጃ፤ በጋምቤላ፤ በኦጋዴንና በድህረ ምርጫ 97 በአገራችን የተለያዩ ቦታዎች የተፈጸመው ጭፍጨፋ ዳርፉር ውስጥ ከደረሰው ሰቆቃ ጋር አቻነት እንዳለው በዚህም ምክንያት የአልበሽር ለአለም አቀፍ ፍርድቤት መቅረብ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ለመለስ ዜናዊም እንደማይቀርለት ማሳየቱን የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚያምኑበት ግንዛቤ መፍጠሩን ለማረጋገጥ ተችሎአል።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ህዝባችንን በጠነከረ የብረት አለንጋ እየገረፈ ለመግዛት ካለው ፍላጎት የተነሳ ለአለም አቀፍ ፍርድቤቱ እስከዛሬ ምንም እውቅና እንዳልሰጠና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍርካ ህብረት አማካይነት የፍርድቤቱን ውሳኔ የማጣጣል ዘመቻ እንዲከፍት አድርጎታል።