የግንቦት7 አላማ ምንነት፤ ለምንና እንዴት በሚል ርዕስ ከታተመው የግንቦት7 መጽሃፍ የተወሰደ
ሰው፣ እውቀትና ነጻነት
ነጻነት ከማናቸውም ነገር ቀድሞ ከራስ የማንነት ግንዛቤ ከሚመጣ እውቀት የሚመነጭ ነው፡፡ ይህ እውቀት ደግሞ የሰው ልጆች ብቻ ተፈጥሮ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍጥረትን ተራ በተራ ብንወስድ፣ ድንጋይን የመሳሰሉ ህይወት የሌላቸው ግኡዛን ስለራሳቸው ምንም እውቀት እንደሌላቸው እንረዳለን፡፡ ብዙ ቋጥኞች በአንድ ላይ ተከማችተው በሚገኙበት ሁኔታ አንዱ ቋጥኝ ስሌላው አጠገቡ ስለሚገኝ ቋጥኝ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ አበቃ ድንጋይ ድንጋይ ነው፡፡ እጽዋትም፣ ፊታቸውን ጸሃይ ፍለጋ ወደ ጸሃይ መውጫና መጥለቂያ የሚያዞሩ ወይም ውሃ ፈለጋ ስራቸውን በመቶ ሜትሮች ከምድር በታች አስገብተው የሚያስሱ፣ ሲነኳቸው የሚሸማቀቁ ቢኖሩም በተፈጥሯቸው ከድንጋይ የሚለያቸው ነገር የለም፡፡ አንድ ዛፍ አጠገቡ ስላለው ዛፍ እውቀት የለውም፡፡ ወይም ከዛፉ እግር ስር ስለበቀለችው ጽጌረዳ ውበት አይደነቅም፡፡ ግንዱን ተደግፋ ስለምትታከከው ላም ወይም መጥረቢያውን ስሎ ሊገነድሰው ስለሚጠጋው ዛፍ ቆራጭ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ዛፍ ዛፍ ብቻ ነው። የተለየ ሌላ ተፈጥሮ ወይም ምንነት የለውም፡፡ ከዛፉ ስር ያቆምናት ላምም ከዛፉ የተሻለ ከባቢያዊ የደመነፍስ እውቀት ቢኖራትም፣ ተፈጥሮዋ ከዛፉ ብዙ ልዩነት የለውም፡፡ በማሽተትና በማጣጣም አካባቢዋን ማወቅ ብትችልም በማሽተትና በማጣጣም አቅሟ ላይ ማሰላሰልና መመራመር አትችልም፡፡ በአንድ ቃል ስለላምነቷ የምታውቀው ነገር የላትም፡፡ የራስ ግንዛቤ የሚባል ነገር የላትም፡፡ የሚቀልባት ባለቤቷ አንድ ቀን ሊያርዳት እንደሚችልና ህልውናዋም ሞት በሚባል ፍጻሜ እንደሚጠናቀቅ አታውቅም፡፡ ይህ ራስን የማወቅ፣ ራስን ከአካባቢ፣ ከእንስሳውና ከእጽዋቱ፣ ከቋጥኙና ከድንጋዩ ለይቶ እኔ የሚል የራስ ግንዛቤ ያለው ሰው ብቻ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት ብቻ ሳይሆን፣ ከጎኑ ካለው ሌላው ሰው ጭምር ራሱን የሚለይ፣ የራስ ማንነትና የተለየ የግለሰብነት ግንዛቤና ስሜት ያለው ልዩ ፍጥረት ነው፡፡
አንዳንድ ሃይማኖቶች ይህ የሰው ልጅ የራስ እውቀት ከፈጣሪው ያገኘው ልዩ ተፈጥሮ ነው ይላሉ። ይህንንም ሲያስረዱ የሰው ልጅ፣ ከሌሎች ፍጥረታት ብቻ ሳይሆን ከጎኑ ካለው ሌላው ሰው ጭምር ራሱን የሚለይ፣ የራስ ማንነትና የተለየ የግለሰብነት ግንዛቤና ስሜት ያገኘው ፈጣሪው ልዩ አድርጎ ስለፈጠረው መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ከእምነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የተለያዩ ፍልስፍናዎችም ሰውን ልዩ የሚያደርገው ተፈጥሮው ወይም ባህርይው ይህ ማንነቱን በራሱ ለይቶ ለማወቅ ያለው ነጻነት መሆኑን ይስማማሉ፡፡
ቀደም ብለን እንደ ጠቀስነው ድንጋይ በድንጋይነቱ ከታሰረበት የድንጋይነት ማንነቱ ራሱን ነጻ ማድረግ የማይችል በመሆኑ በድንጋይነት ለዘልአለም ይቀጥላል፡፡ እጽዋትና እንስሳትም እንደዚሁ፡፡ ሰው ግን በአንድ በኩል በተሰራበት ንጥረ ነገር፣ በስጋነቱና በፈራሽነቱ፣ ከድንጋዩ ከጽዋቱ ከእንስሳው የማይለይ ቢሆንም፣ እንዲህ አይነቱን አካለዊ ሰውነቱን ጨምሮ ስለማንነቱ የራስ ገንዛቤ አለው፡፡ ‹‹እኔ፣ እኔ ነኝ አንተም እርስዋም አይደለሁም፡፡ ያ ጠረጴዛም ወይም ብርጭቆ አይደለሁም›› የሚል ደመነፍሳዊ ያልሆነ ግንዛቤ አለው፡፡ ሰው እራሱን ካገኘበት የተፈጥሮ ትርምስ ራሱን መንጥቆ ማውጣት የሚችል ተፈጥሯዊ ነጻነት ባይኖረው፣ ራሱን ከአካባቢው ለይቶ የእኔነት ግንዛቤ ሊኖረው አይችልም ነበር፡፡ ከፍጥረት ጋር አንድ ሆኖ የፍጥረትን ረቂቅነት፣ ቀለምና ቅርጽን መለየት የማይችል ከየትኛውም ፍጥረት ልዩነት የሌለው የተፈጥሮ አካል ሆኖ ይቀበር ነበር፡፡ ሰው እንደ ድንጋዩ፣ ዛፉና ላሟ እራሱን ከተሰራበት አካላዊ ተፈጥሮ ነጻ ማድረግ ባይችል ኖሮ እነሱኑ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡
የሰው ልጅ ነጻነቱ አካላዊ ካልሆነው ሌላው የሰው ልጅ ተሰጥኦ ከህሊናው ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ የሰው ልጅ ህሊናን ከነጻነት ለይተን ማሰብ አንችልም፡፡ ይህ ማለት ነጻነትና ሰውነት በማይበጣጠሱ ክሮች የተተበተቡ ናቸው ማለት ነው፡፡ ይህ የራስ እውቀት ጅማሮ ግን ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን አስቀድሞ የሰው ልጅ በተላበሰው ነጻነት ራሱን ማወቅ በመቻሉ የመጣ ነው፡፡ ነጻነት ሰው ከሆንን በኋላ የሚሰጠን ወይም የምንላበሰው ባሀርያችን ሳይሆን የሰውነት መለያችን ነው፡፡ ሰው መሆናችንን ማወቂው ብቸኛው ነገር ነጻነት ነው፡፡ ይህ እውቀት፣ ይህ ነጻነት የሰው ልጆችን ከአንስሳት የተለዩ ልዩ ፍጥረቶች ለመሆናቸው ማስረጃ በመሆን ሲያኩራራቸው ይታያል፡፡ ይህ እውቀትና ነጻነት ግን የሚያኩራራና የሚያስደስት ብቻ ሳይሆን በግልባጩም ለሰው ልጅ እዳና እርግማን በመሆን የከፍተኛ ሃዘን መከራና ጣር ምንጭ ጭምር ነው፡፡
የነጻነት እርግማን፣ የእውቀት እርግማን
የተለያዩ እምነቶች ‹‹የሰው ልጅ ስለራሱና ስለአካባቢው ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ፍላጎቱ ጠንካራ በመሆኑም በራሱ ፍላጎትም ሆነ፤ በሰይጣን እየተገፋ ፈጣሪው አታድርግ ያለውን ከማድረግ አልተመለሰም። የድርጊቱን ውጤት ለማወቅ ስለሚጓጓ፤ ፍላጎቱን ከማሳካት የሚያግደው አንዳችም ሃይል የለም። ነጻ ተፈጥሮው የፈጣሪውን ትዕዛዝ እንኳ እስከመጣስ ያደርሰዋል። በዚህም ምክንያት የሰራው ሁሉ እየተባረከለት ከሚኖርባት፣ ረሃብ፣ ችጋርና በሸታ የሚባል ነገር ከማይታወቅበት፣ ፍጥረታት ሁሉ ለጥቅሙ ብቻ ከተፈጠሩባት ገነት/ጄኔት ከተባለ ስፍራ ወደ አደገኛይቱና በውስጧም ያሉ ፍጥረታት ሁሉ በጥረቱ ካላሸነፋቸው በስተቀር ሊጎዱት ወደሚችሉባት ምድር መጣሉን ይነግሩናል፡፡ ‹‹ሰው ራሱን አወቀ፣ እርቃኑን መሆኑን ተረዳ። ሟችና ፈራሽ መሆኑን ተገነዘበ። ያለማንም ድጋፍ በራሱ ድካምና ጥረት ማስኖ የሚኖር ለራሱ እንዲወስን በውሳኔውም ወደ ጽድቅና ኩነኔ ወደ ገነት/ጄኔትና ገሃነም የሚጓዝ ፍጥረት መሆኑን ተገነዘበ፡፡ ሆኖም ፈጣሪው ሰውን ከገነት/ጄኔት አውጥቶ ወደ ምድር ሲወረውረው፣ያሻውን ማድረግና መፍጠር እንዲችል ካደረገው ከነጻነቱ ጭምር ጋር ነው፡፡ ይህንን ነጻነቱን በመጠቀም በሚሰራው ግን ይጠየቅበታል›› ይላሉ፡፡
የተለያዩ ፍልስፍናዎችም ሰው በራሱ ምርጫና ውሳኔ ኖሮ የሚሞት ፍጥረት መሆኑን ያስረዱናል፡፡ ነጻ ፍጥረት በመሆኑ ጥሩና መጥፎውን የሚለየው በራሱ ነጻ ጥረት እንጂ አስቀድሞ ከተደነገገበትና ማምለጫ በሌለው አሳሪ ህግ አለመሆኑን ያብራራሉ፡፡ የሰው ልጅ ለሚፈጽመው ድርጊት በሙሉ ከራሱ ውጭ ሌላ የሚጠየቅ ሃይል የለም፡፡ ሰው እንደ ድንጋይ እንደዛፍና እንስሳ አስቀድሞ በተወሰነ ባህርይ የታሰረ አይደለም፡፡
ሰው በርጩማ አይደለም። በርጩማ ለመቀመጫነት ታስቦ የተሰራ ነው። ሰው እንደ በርጩማ ምን አገልግሎት እንደሚኖረው አስቀድሞ ታስቦ፤ የተጠረበ አይደለም፡፡ ሰው ምን መሆን እንደሚገባው በህይወት መንገድ ላይ የሚገጥሙትን ፈተናዎች ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት እየወሰነ፣ በነጻነቱ በሚወስነው ውሳኔ እራሱን ደግሞና ደጋግሞ እንደአዲስ እየፈጠረ የሚኖር ፍጥረት ነው፡፡
ሰው እንደሙቀጫ ወይም ዘነዘና ምን መሆን እንደሚገባውና ለምን መገልገያነት እንደተፈጠረ አስቀድሞ አልተደነገገም፡፡ የሰው ልጅ ያለቀለት የምንነቱ መገለጫ ይዞ ያልመጣ መሆኑን የሚስረዱን የፍልስፍና ዘርፎች እንደሚሉት ከሰው ባህርይ የማይቀየር ያለቀለት ሆኖ ከሰው ጋር የሚመጣ ነገር ቢኖር ነጻነቱ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው መምህር፣ መለዮለባሽ፣ ማጅራትመቺ፣ በጎአድራጊ፣ የመሆን እጣውን በህይወቱ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ሊቀይራቸው ይቻለዋል። በሰውነቱ ይዞት የመጣውን የራስ ግንዛቤና ነጻነቱን ግን እንዳሻው ሊቀይረው አይችልም፡፡ ነጻነት ማለት ሰውነት፣ ሰውነት ማለት ነጻነት ነው፡፡ ሰውን ከነጻነቱ ውጭ ማሰብ አይቸልም፡፡ ያለነፃነት ሰው የሚባለውን ፍጡር ማሰብ አይቻልም። “ነጻነት ለሰው ልጅ የማይመለጥ እጣ፤ የማይመለጥ እርግማን ነው” የሚባለውም ለእዚህ ነው፡፡
ነጻነትና ሞት፤ የነጻነት ፍራቻ
የሰው ልጅ የፍጥረቱ ባህርይ ነጻነትን የተላበሰ መሆኑን አትተናል፡፡ ሌላው ሰውን ልዩ የሚደርገው ነገር አስቀድሞ የራሱን መጨረሻ ማየትና በፍጻሜው ላይ ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት መሆኑ ነው፡፡ አስቀድሞ ሟች መሆኑን አውቆ የሟችነትን የማይመለጥ እጣና እርግማን ተሸክሞ ይኖራል፡፡ ብዙዎቻችን ስለነጻነት ካለን ቀና አመለካከት በመነሳት የሰው ልጅ ከነጻነት ጋር እንዲህ በጥብቅ መተሳሰሩ ታላቅ ጸጋ ነው እንል ይሆናል፡፡ ይሁንና የነጻነት ጉዳይ በተለምዶ ከምናውቀው የሃገር ነጻነት፣ የመናገርና የመጻፍ ነጻነት ባሻገር ብዙ መዘዞችን ተሸክሞ የሚመጣ መሆኑን ስንረዳ ብዙዎቻችን ስለነጻነት ጸጋ መሆን ያለን አመለካከት ይቀየራል፡፡ ነጻነት የሚያማልሉ ገጽታዎች ያሉትን ያህል እንደሬት የሚመሩ ገጽታዎችም ያሉት ነው።
ነጻነት በህይወታችን ለምንወስዳቸው ማናቸውም ውሳኔዎች መሰረት ነው፡፡ ነጻነት በምንለብሰው ልብስና በምንመገበው የምግብ አይነት በሚደረግ ምርጫ የሚገለጽ የውሳኔ ነጻነት ብቻ ቢሆን ብዙ ባላስጨነቀን ነበር፡፡ የሰው ልጅ ግን ተራ በሆኑ ፍለጎቶቹ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በህይወቱ ላይ ከፍተኛ መዘዝ የሚስከትሉ ምርጫዎችንና ውሳኔዎችን እንዲወስን ይገደዳል፡፡ ሰው ማለቂያ አልባ ውሳኔዎችን እየወሰነ የውሳኔዎቹ መዘዝ በጎም ይሁኑ መጥፎ ተቀብሎ የሚኖር ፍጥረት ነው፡፡
ሰው በአንድ በኩል በማናቸውም ጉዳይ ላይ የመወሰን ነጻነት እንዳለው ያውቃል፡፡ ይህ ውሳኔ ጠንከር ያለ መዘዝ ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰጥ ከሆነ ደግሞ የበለጠ ይሸበራል፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ በሥራው ቦታ ጠባይ፣ በአለቃው ጠባይ፣ በሚሰራው ሥራ ዓይነት፣ የማይወደውን ሥራ ለአመታት ሲሰራ ቆይቶ “አሁንስ በቃኝ” ለማለት ሲነሳ በጭንቅላቱ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ “ይህን ሥራ አቁሜ ምን እሆናለሁ?” ይላል፤ ሌላ የሚስደስተው ሥራ በቀላሉ የሚያገኝ ከሆነ ግን ችግር አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ምንም ሥራ የማያገኝ ከሆነ የውሳኔው መዘዝ ግልጽ ይሆናል፡፡ ‹‹ይህንን ሥራ አቁሜ ምን እበላለሁ? የቤት ኪራይስ ምን እከፍላለሁ?›› ወዘተ ማለት ይጀምራል፡፡ ልጆችና ቤተሰብ ካለው ደግሞ ችግሩ የበለጠ ይወሳሰባል። በሥራው በጣም የተንገፈገፈ ከሆነ “ከእዚህ ሥራ ለምን ተርቤ አልሞትም? ለምንስ በረንዳ አላድርም?” የሚሉ አማራጮች በጭንቅላቱ መመላለስ ይጀምራሉ፡፡
የሰው ልጅ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት በተላበሰው ፍጹማዊ ነጻነቱና ውሳኔውን ተከትሎ በሚመጣው መዘዝ መሃል ተወጥሮ የሚኖር ፍጥረት ነው፡፡ የሰው ልጅ ከላይ ከጠቀስነው ምሳሌ እጅግ አስከፊ መዘዞች ያሉትን ውሳኔዎች የሚወስንበት ሁኔታዎች በህይወቱ ያጋጥመዋል፡፡
በአለም መገናኛ ብዙሃን ሁሌም ተደጋግሞ የሚታየው በቻይናው ታይናማን እልቂት ጊዜ ታንክ ፊት ቆሞ ታንኩን አላሳልፍም ያለው ወጣት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ታንኩ ፊት የመቆምና ያለመቆም ውሳኔ የመኖርና ያለመኖር ውሳኔ ነው፡፡ ከታንኩ ፊት እቆማለሁ ብሎ መወሰን ከሞት ጋር ፊት ለፊት መፋጠጥን ያስከትላል፡፡ ይህ ሁኔታ እንደዚህ ዓይነቱን አስፈሪ ውሳኔ የመወሰን ነጻነት የሰው ልጆች በሙሉ የተላበሱት መሆኑን ያሳየናል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎቻችንም ከየትኛውም ታንክ ፊት መቆም እንደምንችል ይጠቁመናል፡፡ ከታንኩ ፊት መቆም ለአንድ ቻይናዊ ወጣት ብቻ የተሰጠ እንዳልሆነ ያመላክተናል፡፡ የሰው ልጅ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚፋጠጠው ስፋቱ ማለቂያ ከሌለው ነጻነቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከገዛ ሞቱ ጋርም ይሆናል፡፡ ነጻነትና ሞት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው የሚባለውም ለእዚህ ነው፡፡ ነጻነቱ ገደብ የሌለውን ነገር ለመፈጸም የሚያስችለው መሆኑን ሲረዳ ይህም ማለት ሞት የሚስከትልበትን ድርጊት መፈጸምን የሚጨምር መሆኑን ሲያውቅ ሞቱን ብቻ ሳይሆን ነጻነቱንም ጭምር መፍራት ይጀምራል፡፡ ሞትን ስንሸሽ እንደምንኖር ሁሉ ነጻነታችንን ስንሸሽ የምንኖር ፍጥረቶች የሚያደርገን ይህ ሃቅ ነው፡፡
ይህ የነጻነት ፍራቻ ብዙዎቻችን ህሊናችን የማይቀበለውን ድርጊት እንድንፈጽምና የማንፈልገውን ህይወትና ኑሮ እንድንኖር የሚያደርገን ዋናው ምክንያት ነው፡፡ የውሳኔያችንን መዘዝ ለመቀበል ድፍረቱን ስናጣ፣ በሰውነታችን የተላበስነው፣ ሁኔታዎችን የመቀየርና እምቢ የማለት ነጻነት ያለን ፍጥረት መሆናችንን መካድ የተለመደ ነው፡፡ ያለንበትን ሁኔታ ለመቀየር ምርጫ የሌለን አድርገን እራሳችንን ማየት እንጀምራለን፡፡ ነጻነትን የመሰለ ሰውን ከምንም ነገር የሚለየውን ባህርይ መላበሳችንን እንክዳለን፡፡ ለራሳችን እየዋሸን ምንም አይነት የሰብአዊነት ሞራል የሌለው ኑሮ እንኖራለን፡፡ ይህ ድርጊታችን እጅግ አስገራሚና ከራሳችን ጋር እንድንፋጠጥ በሚያደርጉ ዝንባሌዎች እንደሚገለጽ ቀጥሎ የምናየው ይሆናል፡፡
እቃ ወይም ባሪያ የመሆን ፍላጎት
ሰብአዊ ማንነታችንና ህሊናችን የተሰራበት ድርና ማገሩ ነጻነት ነው፡፡ ከፍጥረታት ራሳችንን ለይተን ማየት ካስቻለን ግንዛቤ አንስቶ ለትንሹም ለትልቁም ድርጊት ለምናደርገው ውሳኔ መሰረቱ ነጻነት ነው፡፡ ነጻነት ነዝናዛ ነው፡፡ ነጻነታችን በራሳችን በግላችን ውሳኔ ከመወሰንና ወደፊት ከመራመድ ውጭ ምርጫ የሌለን መሆናችን ያለማቋረጥ ያሳስበናል፡፡ ይህ ነጻነት ‹‹በል ሰው በመሆን መኩራት ብቻ አይደለም እንደሰው ኑር›› የሚል የማያቋርጥ ፈተና ከፊታችንን ይደነቅራል፡፡ አንዳንዱ ፈተና የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ሃገር በውጭ ወራሪ እጅ ወድቃለች። ይህ ወራሪ እየረገጠ በገዛ ሃገርህ ሁለተኛ ዜጋ አደርጎ ሊገዛህ የመጣ ነው፡፡ ሃብትና ቅርስ የሌለህ፣ የአምስት ህጻናት አባት ነህ፡፡ ለእናትህ አንድ ልጅ ነህ፡፡ ከአባትህ ሞት በኋላ የምትወዳት አቅሟ የደከመ እናትህ የምትጦረው ባንተ ነው፡፡ ይህን ሁሉ የቤተሰብ ሃላፊነት ትተህ፣ ለቤተሰብህ ለሃገርህ ነጻነት ለመታገል፣ በዚህ ትግልም የተነሳ እንደወጣህ ለመቅረት እንደምትችል እያወቅህ ነጻነቴን እመርጣለሁ ትላላህ ወይስ የቤተሰብን ሃላፊነት ምክንያት በማድረግ አንተንም የምትወዳቸውን ልጆቸህንና ቤተሰቦችህን በባርነት ማኖርን ትቀበላለህ፡፡ ነጻነታችን እንዲህ አይነቱን አሰቃቂ ምርጫ ይዞ የሚመጣባቸው ወቅቶች አሉ፡፡
በእንዲህ አይነቱቶቹ ፈታኝ ወቅቶች የሚቀርቡልን አማራጮች ስቃያችንን የሚያበዙ ይሆናሉ፡፡ ጭንቀታችን ሲበዛ ሁኔታውን በድፍረት ተቋቁመን አንዱን በመምረጥ ፈንታ የሰውነት እጣችንን መራገም እንጀምራለን፡፡ እኛ ከመወሰን ይልቅ አንዳች ሌላ ፍጥረት እንዲወስንልን እንመኛለን፡፡ እንዲህ አይነቱ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ብዙ ጊዜ ሰዎች ሲገቡ ምነው ‹‹ጆሮዬ ባይሰማ፣ አይኔ ባያይ፣ ባልተፈጠርኩ፣ ምነው ድንጋይ ባደረገኝ›› የሚሉ ስሜቶች በውስጣቸው መንሸራሸር ይጀምራል፡፡ እራሳችንም ሆንን ባቅራቢያችን የሚገኙ ሌሎች ሰዎች እንዲህ ስንል በተደጋጋሚ እንደመጣለን፡፡ ይህ ምኞት ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ቀደም ብለን እንደጠቀስናቸው፣ ድንጋይ፣ ዛፍና ላም ሆኜ በተፈጠርኩ የሚል ምኞት ነው፡፡ እነዚህ ፍጥረታት ከነጻ ፍጥረትነት የሚመጣ ጭንቀት እንደሌለባቸው ስለምናውቅ እነሱን ለመሆን መመኘታችን ነው፡፡ ይህ ምኞት ሰው በነጻነቱ የተነሳ የሚደርስበትን ስቃይ ለመቋቋም ሲያዳግተው የሚገባበት ምኞት ነው፡፡ ለብዙዎቻችን ይህ ምኞት፣ በምኞት ደረጃ የሚቀር ጉዳይ ሳይሆን በህይወታችን ደግመን ደጋግመን በስራ የምንተረጉመው ምኞት ሆኖ ይገኛል፡፡ ሌሎች ጥቂት ምሳሌዎችን እንውሰድ፤
በጦር ሜዳ ላይ ህጻናትንና አረጋውያን ነፍሳቸውን ለማዳን የተደበቁበትን ቤተ/አምልኮት ‹‹በእሳት አጋይ›› የሚል ትእዛዝ ከበላዩ የሚሰጠው ወታደር ትእዛዙን ሳያንገራግር ይፈጽማል፡፡ ከፈጸመ በኋላ ግን ለምን እንዲህ አይነት ግፍ ትፈጽማለህ? ለሚለው ጠያቂው የሚሰጠውን የተለመደ ምላሽ በደንብ ካጤንነው በጣም የሚገርም ነው፡፡ ምላሹ ‹‹እኔ ወታደር ነኝ፡፡ ትእዛዝ ሲሰጠኝ መፈጸም አለብኝ። ሌላ ምን ምርጫ አለኝ›› ነው የሚለው፡፡ ይህ ወታደር ግን ምርጫ ነበረው፡፡ አለቃውን አልታዘዝም በማለት ከፈጸመው ግፍ መቆጠብ አንዱ ምርጫ ነው፡፡ ሌላው ንጹሃንን መረሸን ነው፡፡ የመጀመሪያው ምርጫ በአለቃው ትእዛዝ መረሸንን ያስከትላል፡፡ ሁለተኛው ምርጫ ንጹሃንን በመፍጀት የገዛ ህይወቱን ማትረፍ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ምርጫም ስናየው ቀላል ይመስላል እንጂ እንደ መጀመሪያው ምርጫ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹ህይወቴን ለማትረፍ ስል ህጻናትንና አሮጊቶችን ልፍጅ የሚል ግልጽ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ማንም ሰው አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ሺህ ጊዜ ነጻ ቢሆን ይህንን ነጻነቱን ተጠቅሞ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች የሚገዛ የራሱ የሆነ ማእቀብ ያለው ፍጥረት ነውና፡፡ ‹‹ሰው ነጻ ነው። ማናቸውንም ውሳኔ መወሰን ይችላል›› ስንል ለውሳኔው መስፈርት ወይም መመዘኛ የለውም ማለት አይደለም፡፡
የእያንዳንዱ ተናጠል ግላዊ ውሳኔ ወደድንም ጠላንም ስለ ሰው ልጆች ተብሎ የሚወሰን ውሳኔ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ “በሌላው ላይ የምትወስነው ውሳኔ በራስህም ላይ እንዲወሰንብህ የምትፈቅደው ነውን?” የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ የጠቀስነው ወታደር ‹‹አዎን ሌላ ወታደር ህይወቱን ለማቆየት ሲል እናቴን ልጆቼን ወዘተ ሊገድል ይችላል የሚል ፈቃድ ለሌላው ወታደር እንዲሰጠው ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ ማለፍ የማይቻል ፈተና ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ከላይ የጠቀስነው ወታደር እፊቱ ከቀረቡለት ሁለት አማራጮች መሃከል አንዱን መምረጥ ሲጨንቀው፣ እስከናካቴው የመወሰን መብት የሌለው ፍጥረት ሆኖ መቅረብን ህሊናው ይመርጣል፡፡
ሰውነቱ የሚገለጸው ልክ ለመጻፊያነት ታስቦ እንደተሰራ ብእር ይመስል፣ እራሱን ለወታደርነትና ለትእዛዝ ተቀባይነት ብቻ የተሳራ አድርጎ በማቅረብ ‹‹ወታደር ነኝ ሌላ ምን ማደርግ እችላለሁ›› ይላል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው ይህ ሰው አፈጣጠሩ ከብእሩ የተለየ ነው፡፡ እንዳውም በየጊዜው በሚወስዳቸው ውሳኔዎች እራሱን እየፈጠረ የመሄድ ነጻነት ያለው ሃያል ፍጥረት ነው፡፡ በሰጠነው ምሳሌ ግን እራሱን ከብእሩ የተለየ አድርጎ አያቀርብም፡፡ ብእር ሰሪው በሰራው ብእር እንደሚጽፍበት ሁሉ ይህም ወታደር እራሱን ልክ እንደጠመንጃ እንደቦንብ አለቆቹ ሊገለገሉባቸው እንሚችሉባቸው ሌሎች መሳሪያዎች ራሱን ግኡዝ ነገር አድርጎ ያቀርባል፡፡ ይህንን ነው በርካታ ፈላስፎች ‹‹በእያንዳንዱ የሰው ፍጥረት ውስጥ ነጻነት የሚፈጥረውን ሽብር ለመሸሽ ሲባል እቃ የመሆን ፍላጎትና አደጋ አለ›› የሚያስብላቸው፡፡
እኛ ከምንወስን ሌሎች እንዲወስኑልን፣ የሚወስንልን ከጠፋም እኛ ራሳችን ውሳኔ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ መወሰን የማንችል ፍጥረቶች አድርግን የምንቀመጥበትን ህሊናዊ ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ ህሊና ካለው ፍጥረትነት ወደ ግኡዝ ፍጥረትነት፤ ወደማይለማና የማይሳማ ፍጥረትነት ወደ እቃነት ወደ ባርያነት የመቀየር ሌላ ግፊት፣ ሌላው ከሰው ልጆች የማይለየው ባህርይ ነው፡፡
እውነታው ግን አንድ ግለሰብ ከማናቸውም እራሱ ለራሱ በህይወቱ ከሰጣቸው ማህበራዊና ግለሰባዊ ሚናዎቹ አስቀድሞ ሰው ነው፡፡ ወታደር ነኝ፣ አባት ነኝ የድርጅት አባል ነኝ ወዘተ የሚባሉ ሚናዎች ከሰውነታችን በኋላ የመጡ እኛው ለእኛው የሰጠናቸው ናቸው፡፡ ስንፈጠር የግንቦት 7 አባላት እንድንሆን ምርጫ ሳይኖረን የተፈጠርን አይደለንም፡፡ የግንቦት 7 ድርጅትን ተሰባስበን የፈጠርነው፣ አበላቱ የሆንነው እኛው ነን፡፡ ይህ ድርጅት በሰውነታችን ልንቀበለው የማይገባውን ውሳኔ ወስኖ ስናገኘው ምን ማድረግ ይቻላል? የድርጅት ውሳኔ ነው፤ እኔም የድርጅት አባል ነኝ የሚሉ አቋሞች ይዘን ከተገኘን፣ ከላይ ስለወታደሩ ባነሳነው ምሳሌ ወታደሩ ከወሰደው አቋም የተለየ አይሆንም፡፡ ይህ አካሄድ ነጻነት ካለው ፍጥረትነት ራስን ወደ እቃነት የመቀየር አቋም ነው፡፡
ከላይ የጠቀስነው በሰው ተፈጥሮ ውስጥ ያለውን እቃ/ግኡዝ የመሆን ዝንባሌ የሚያበረታቱ ሌሎች ተጨማሪ ግፊቶች አሉ፡፡ ‹‹ራሳችንን እቃ የማድረግ ዝንባሌ ይዘን እንደምንፈጠርና ህይወትም ከእዚህ ዝንባሌ ጋር የሚደረግ የማያቋርጥ ትግል ነው›› ያልነው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሌላው የሰው ልጆች ተፈጥሮ ሌላውን ሰውን እንደ እቃ የማየት ዝንባሌን የሚካትት መሆኑን መረዳት ይገባናል፡፡ ይህ እውነታ የሚመነጨው ስለፈለግነው ሳይሆን ሁኔታዎች በእዚህ መንገድ ተዘጋጅተው የተቀመጡ በመሆናቸው የመጣ ነው፡፡ ይህን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት እያንዳንዳችን ከፊታችን ወይም ከጎናችን ያለውን ሌላ ሰው እንመልከት፡፡
ይህ ሰው በካበቢያችን እንዳለ መረዳት የምንችለው በዙሪያችን እንዳሉ እቃዎች እንደ ጠረጴዛው እንደ ወንበሩ ሲከሰት ብቻ ነው፡፡ በቀለሙ፣ በቅርጹ፣ ከእኛ በተወሰነ ርቀት በመገኘቱ በሚኖረን ግንዛቤ ነው አንድን ሰው በአጠገባችን በአካል ለመኖሩ የመጀመሪያውን ግንዛቤ መያዝ የምንችለው፡፡ ይህ ማለት እያንዳንዱ ሰው በአቅራቢው ያለውን ሌላ ሰው በቅድሚያ የሚያውቀው በራሱ ውስጥ በሚያገኛቸው ስሜቶች አማካይነት አይደለም ማለት ነው፡፡ መጀመሪያ በአካባቢው እንደሚያያቸው ሁሉም ነገሮች እቃዎችና ፍጥረቶች ነው የሚያየው፡፡ የሰውነት ትርጉም፣ ክብር፣ ወገንተኛነትና ወዘተ የተለያዩ እሴቶች ለእዚህ በቅድሚያ በአካልነት ላየነው ሰው የምናላብሰው መጀመሪያ እንደማንኛውም ነገር አጠገባችን ያለ ነገር መሆኑን ከተገነዘብን በኋለ ነው፡፡
ሌላውም ሰው እኛን የሚመለከተው እንደዛው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ ሰው አትኩሮ ሲመለከተን እንረበሻለን፡፡ የሚረብሸን ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ተመልካቹ እንደ ሰብአዊ ፍጥረት ሳይሆን እንደእቃ እየመረመረኝ ነው ከሚል ስጋት ነው፡፡ ሁሉን ነገር በቅድሚያ በግኡዝነት እንድናይ የሚደርገን አፈጣጠራችን በሰዎች መሃከል መኖር የሚገባውን ግንኙነት በሁለት ሰብአዊ ፍጥረቶች መሃከል በእኩልነት ሊኖር የሚገባው ግንኙነት እንዳይሆን አጥብቆ ይከላከላል፡፡ አንዱ ሌላውን እንዳልባሌ እቃ እንዳሻው ለማድረግ የመሻት ዝንባሌ ስለሚኖረው በሰዎች መሃከል ሚዛኑን የጠበቀ ሰብአዊ ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ ፈተና ነው፡፡
ይህ ተፈጥሯችን በአጠገባችን የምናየው ሰው፣ ከሌሎች ፍጥረቶች ሁሉ የተለየ እንደኛው በሰብአዊ ባህርያት የተሞላ ፍጥረት መሆኑን በምናውቅበት ወቅትም የማይለቀን ነው፡፡ ስለዚህም ከሰውነታችን ጋር የተጎናጸፍነውን ነጻነት ሊያጠፋ የሚፈልገው በውስጣችን ያለ ወደ ግኡዝነት/እቃነት የመቀየር ዝንባሌ ብቻ ሳይሆን ከውጭም አንዳችን ሌላውን በእቃነት የማየትም ዝንባሌ ይዘን የምንመጣ ፍጥረቶችም በመሆናችን ጭምር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
እንግዲህ ከዚህ በላይ እንዳየነው ከውስጣችንም ይሁን ከውጭ በስብአዊ ነጻነታችን ላይ የሚካሄደው ወረራ ቀላል አይደለም፡፡ ይህንን ወረራ ለመመከት በሚገባ ካልተዘጋጀን፣ በራሳችን ምርጫ ይሁን ወይም በሌሎች ውሳኔ ከነጻነት ወደ ባርነት የምናደርገውን ሽግግር የሚስቆመው አይኖርም፡፡ የሰው ልጅ ለነጻነቱ ሁሌም ዘብ ይቁም የሚለው አባባል ለሰውነቱ ዘብ ይቁም ከሚለው አባባል ልዩነት የሌለው መሆኑን ልንረዳ ይገባናል፡፡
ሌሎች የነጻነት ፈርጆች፣ ማህበራዊና ዜጋዊ መብቶች ከዚህ ሰብአዊ ነጻነት የሚቀዱ ናቸው፡፡ ለእነዚህ መብቶቻችን መከበር የምናደርገው ትግል ለሰውነታችን ከምንሰጠው ክብር ጋር የተሳሰረ መሆኑን በሚገባ ስንረዳና ስናወቅ በቀላሉ ባርያ/እቃ አድርገው እንዳሻቸው ሊያደርጉን ለሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች እጅ አንሰጥም፡፡ እኛም ብንሆን ሌላውን ሰው፣ በተመሳሳይ ሰብአዊ ክብሩን ገፈን እቃ/ባርያ አድርገን እንድናይ በውስጣችን የሚፈልቀውን ግፊት በቀላሉ ስድ አንለቀውም፡፡
የነጻነት ክህደትና የሽንገላ ህይወት
ነጻነታችን እራሱ አስፈሪ ሆኖ ስናገኘው ለገዛ ነጻነታችን ሃላፊነት ወስደን ከመፋጠጥ ነጻነት እንደሌለን አድርግን ማስመሰል እንደምንመርጥ አትተናል፡፡ እንዲህ አይነቱ አመለካከት እጅግ በርካታ ለሆንነው ሰዎች በውሸት ወይም በሽንገላ የተሞላ ህይወት እንድንኖር ያደርገናል፡፡ ነጻነትን ያክል ሰው የሚያደርገንን ታላቅ ጸጋ አስገፍፈንና ተገፈን ምንም እንዳልሆንን አስመስለን ለማለፍ እንሞክራለን፡፡ ችግሩ ግን የነጻነት ጉዳይ የምርምርና የጥናት ውጤት ሳይሆን ሰው ሆኖ ከመፈጠር ጋር የተያያዘ እርግማን በመሆኑ ሁላችንም እራሳችንን እያጭበረበርን እንደሆነ እናውቀዋለን፡፡
የነጻነትን ጉዳይ ፍርፋሪ እየለቀመ በውርደት የሚኖረው የኔ ቢጤ ያውቀዋል፡፡ የወያኔን ጌቶቹን አይንና ጆሮ ፈርቶ የሚኖረውም የዩኒቨርስቲ አስተማሪ ያውቀዋል። ‹‹እኔ አንድ ደሃ የእግዜር ለማኝ ነኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?” የሚለው ደሃ በውስጡ የሚንቀለቀለውን በነጻነትና በእኩልነት ስብእናው ተከብሮ እንዲኖር ያለውን ማምለጫ የሌለውን ሰብአዊ ፍላጎቱን ቢፈልግ እንኳን ማጥፋት አይችልም። ከእዚህ ፍላጎት መሸሽ ካልሆነ ማምለጥ አይቻልም፡፡ በተመሳሳይም ‹‹እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፡፡
ሳይንቲስት ነኝ፤ ኢኮኖሚስት ነኝ፤ ሃኪም ነኝ፤ ቄስ ነኝ፤ አርቲስት ነኝ፤ ነጋዴ ነኝ” የሚለው ዜጋ የነጻነቱን ጉዳይ የፖለቲካ ሰዎች ሥራ አድርጎ ሲተወው የሚሰራውን ያውቃል፡፡ እራሱን ለገዛ ነጻነቱና ስብእናው ከመታግል እያሸሸ እንደሆነ ያውቃል፡፡ ሆድ ሲውቅ ዶሮ ማታ ነውና ለራሱ እየቀጠፈ እንደሆነ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኛው እውነቱን አትጻፍ ሲባል፤ ነጋዴው ‹‹ጫማ ስመህ ጉቦ ሰጥተህ እቃህ ከጉምሩክ ይለቀቃል›› ሲባል፤ ፕሮፌሰሩ ‹‹ተማሪዎችህን እኛ ከፈቀድነው ውጭ ጥያቄ ማንሳት ውይይት እንዲያደርጉ ማድረግ አትችልም›› ሲባል፤ ተማሪው ‹‹ለከፍተኛ ትምህርትና ሥራ ለመቀጠር የመለስ ዜናዊ ጀሌ የግድ መሆን አለብህ›› ሲባል፣ አንድ ዜጋ በዘሩ እየተለየ ጥቃት ሲደርስበት፣ በእምነቱ የተነሳ ሲዋረድ፤ እየተገፈፈ ያለው ከስብእናው ጋር የመጣውን ነጻነቱን ነው፡፡ ከነጻነቱ ጋር የመጣውን ስብእናውን ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን የነጻነት ማስከበር ሥራ ለፖለቲከኞች መተው የሚቻለው ራስን በከፍተኛ ማጭበርበር በመሙላት ብቻ ነው፡፡ በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ በእንዲህ አይነቱ የራስ ማጭበርበር የተሞላ የውሽት ህይወት የምንኖረው ብዙዎች ነን፡፡
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሃገራቸውን ለቀው በሚሊዮኖች የሚሰደዱት በፖለቲካ ሆነ በኢኮኖሚ ምክንያት በሃገራቸው መኖር ስላልቻሉ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በየጊዜው የመጡ አምባገነን መሪዎች እንደቆሻሻ እየጠረጉ አያት ቅድመ-አያቶቻችን የደም መባ ገብረው በነጻነቷ ታፍራ እንድተቆይ ካደረጓት ሃገር እንዳላባረሩን፣ ብዙዎቻችን ስደትን በምርጫችን የገባንበት ጉዳይ አድርገን የምናይበት ህሊና በፍጥነት እንገነባለን፡፡ ለአሳፋሪ የስደት ህይወት ከተዳረግን ጥቂት አመታት በኋላ የምናገኘውን የሌላ ሃገር ዜግነት ለነጻነታችን መቆም ባለመቻላችን በተነጥቅነው ዜግነት ምትክ ተክተን፣ ለስደት በበቃንበት ሃገር የቆየነው ዘመን ገና አንድ ትውልድ ሳይሞላው፣ ‹‹እኔ አሜሪካዊው፣ እኔ እንግሊዙ እኔ ጀርመኑ›› ስንል ምንም እፍረት አይሰማንም፡፡ ይህ እፍረት ማጣት ሌላው ራስን የማጭበርበር ውጤት ነው፡፡
ቀደም ብለን በእዚህ ጽሁፍ መጀመሪያ እንደጠቀስነው እኛ ኢትዮጵያውያን ከየትኛውም ነጻነት በላይ ትልቅ ቦታ ሰጥተነው የኖርነው የሃገራችንን ነጻነት ነው፡፡ ቀደምቶቻችን ለሺህ አመታት አይችሉት ፈተናዎችን ችለው፣ አይከፍሉት መስዋእትነት ከፍለው እንዳቆዩልን የሃገር ነጻነትና ከውጭ ወራሪዎች ነጻ ሆኖ የመገኘት ነጻነት በላይ የሚያኮራን ቅርስ የለንም፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሌላም ቅርስ የለንም፡፡ ይህንን ሃገር ለዝንተ አለም ቀደምቶቻችን እየወደቁና እየተነሱ ልጆቻቸውን በየሜዳው እየበተኑ በየዱሩና በየጫካው እየወደቁ ለእኛ ለልጆቻቸው እንዳስረከቡ እናውቃለን፡፡ እኛም ብንሆን ይህንን ሃገር ሲቻል ከቀደምቶቻችን በተሻለ ካልሆነም እንደነበረ ለመጪው ትውልድ ከማስረከብ የላቀ የትውልድና የታሪክ አደራ እንደሌለብን እናውቃለን፡፡
ስለሃገራችን ስናስብ የማናመልጠው ሃቅ ቢኖር እኛ መርጠን የተወለድንበት ቦታ አለመሆኑን ነው፡፡ ወላጆቻችንን አልመረጥንም፣ የተወለድንበትን ቤተሰብ፣ አልመረጥንም፣ ቋንቋችንን አልመረጥንም፣ የቆዳችንን ቀለም፣ የአካላችንን ቅርጽ አልመረጥንም፡፡ ለብዙዎቻችን ከሃገራችን ጋር ያለን ቁርኝት የጠበቀ የሆነው ለሃገራችንና ወገናችንም ለምንለው ኢትዮጵያዊ የተለየ ስሜት እንድንይዝ የሚያደርግን ይህ ነው፡፡
ቀደም ብለን የጠቀስነው የፈረንጆቹን ፓስፖርት የወረሰውና እራሱን የፈረንጆቹ ዜጋ አድርጎ የወሰደው ወገናችን ነገ እነዚህ ፈረንጆች ኢትዮጵያን ቢወሩ፣ በሌሎች ሃገሮች ላይ የሚጠቀሟቸውን አስከፊ መሳሪያዎች በደሃ ኢትዮጵያውያን ላይ ቢያዘንቡ ምን ስሜት እንደሚሰማው ለማወቅ ጠንቋይ መቀለብ አይኖርብንም፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያውያን ወንድና ሴት አትሌቶች ከሌሎች ሃገር ዜጎች ጋር ሩጫ ሲፎካከሩ በቴሌቪዥን ስናይ የሚሰማንን እናውቃለን፡፡ የዜግነት ፓስፖርት የሰጡን ፈረንጆች እንዲያሸንፉዋቸው አንመኝም፡፡ እኛ ብቻ አይደለንም። ገና ያልተረገዙ ልጆቻችን ከፎቴው ጠርዝ ላይ ተቀምጠው ልባቸው እየመታ የአትሌቶቻችንን አሸናፊነት ሲመኙ ማለም አያዳግተንም፡፡
ነገር ግን ከላይ የጠቀስነው የፈረንጅ ዜግነት በማግኘቱ ፈረንጅ ነኝ የሚለውም ሆነ፤ ሌላውም በፈረንጆች ሃገር ተምሮ በአንድ ትልቅ ዩኒቨርስቲ አንቱ የተባለ ፕሮፌሰር የሆነው፣ ወይም ነግዶ ብዙ ሃብት ያካበተና በትልቅ ቤት የሚኖረውና ውድ መኪና የሚያሽከርክረው ስደተኛ የሚሰማው የክንዋኔ ኩራት ራስን በመሸንገል ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ ከማንነቱና ከምንነቱ ጋር በብዙ ክሮች የተተበተበበትን የቋንቋው፣ የመልኩና የታሪኩ መሰረት ከሆነችው በብዙ ፈተና ቀደምቶቹ ካስረከቡት ሃገር ተገፍቶ ወጥቶ፣ ቀደምቶቹ ለእራሱ ያስረከቡትን ሃገር እሱም ለልጆቹ ማስረከብ በማይችልበት ሁኔታ ተቀምጦ በፈረንጅ ሃገር ተገኘ የሚለው የህይወት ድል በየትኛውም የክንዋኔ መለኪያ ቢላከ ባዶ ድል መሆኑን ልቡ ያውቀዋል፡፡
‹‹ስለሃገርና ስለወገን ጉዳይ አታንሱልኝ ብሎ›› ቤቱን ግን ኢትዮጵያን በሚያስታውስ ቅርጻ ቅርጽ ሞልቶ፣ ጥሬ ስጋና ክትፎ እየበላ፣ በሺ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች አስጉዞ ባስመጣቸው ታቦቶቹ ስም በሰራው ቤተስኪያን በየሳምንቱ ጸሎት የሚደርሰው ፣ በየመስጊዱ ዱአ የሚያደርገው፣ ሸሚዝና ከረባቱ ሳይቀር ወጥ ወጥ እየሸተተ ሥራ የሚገባው ኢትዮጵያዊ ማንን ነው የሚያታልለው? ኢትዮጵያውያን በየደረሱበት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ከሃገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር በአንቀልባ አዝለው እንደሚጓዙ እያወቅን የኢትዮጵያ ጉዳይ አይመለከተንም ሲሉ ብንሰማቸው ልንገረም አይገባም፡፡ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በራሱ ከነጻነት ስሜት ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ስለምናወቅ ሽሽታችን ከሃገራችን ሳይሆን ከነጻነታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይመለከተኝም የሚለው አባባል ለኢትዮጵያ ያለን ጥላቻ ሳይሆን ለገዛ ነጻነታችን ያለንን ፍራቻ የሚረጋግጥ ነውና፡፡
ከእዚህ በላይ የተባለው ሁሉ የሚያሳየው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ነጻነታችንን በመሸሽ የምንመራው ህይወት በሃሰትና በራስ ሽንገላ የተሞላ ህይወት መሆኑን ነው። ይህ የሃሰት ህይወት ከትላልቅ የሃገር ጉዳይ አንስቶ እስከ ተራ ህይወታችን ድረስ ይዘልቃል፡፡ የሃሰት ህይወት ደግሞ በማንኛውም መመዘኛ ኢሞራላዊ የሆነ እንደሰው ነጻ ሆኖ ከተፈጠረ ሃያል ፍጡር የማይጠበቅ ነው፡፡
ነጻነትና ባህል
በሃገራችን ውስጥ ከእዚህ በላይ የጠቀስነውን የነጻነት ምንነትና ትርጉም ለማሰላሰል የቻልንበት ማህበራዊና ምሁራዊ ሁኔታ አናገኝም፡፡ የተናጠል ጥረቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሃገራችን ለዘመናት የኖረው አፋኝ የፖለቲካና ባህላዊ ሁኔታ ይህ በግለሰብ ደረጃ ሊሰማን ስለሚገባው ሰብአዊ ነጻነት እድል የማይሰጥ በመሆኑ ህብረተሰባችን ለእንዲህ አይነቱ የነጻነት አመለካከት ባእድ ሆኖ ኖሯል፡፡ በእምነት ደረጃ ሰው አስቀድሞ እጣውና ውሉ የተሰመረ እንደሆነ እየተነገረን፣ በግል ጥረት ልንደርስበት የምንችለውን ክንዋኔ አንኳሰን እንድናይ ስንሰበክ ነው የኖርነው፡፡
በራስህ ውሳኔ ኑር ተብሎ ከገነት/ጄኔት ሰው ተገፍትሮ መውጣቱን የሚያስተምሩን ሃይማኖቶቻችን ሳይቀሩ፣ ፈጣሪ ሰው በውሳኔው እራሱን እየፈጠረ እንዲኖር የሰጠውን ብይን የሚቃረን ትምህርት ሲያስተምሩን ኑረዋል፡፡ በሃገራችን ሆነ በውጭ ሃገር ከምናየው ተጨባጭ ማስረጃ ውጭ እጣችን አስቀድሞ የተደነገገ ምንም ብናደርገው የማንቀይረው ተደርገን ስንሰበክ ኖረናል፡፡ መሳፍንቱ መሳፍንት እንደሆኑ ከነድሎታቸው፣ ገበሬውም ገበሬ እንደሆነ ከነዝተቱ ለዝንተአለም እንደሚኖሩ፣ ደህነትንና መብት ረገጣን በሰውነታችን ልናምጽባቸውና ልናሸንፋቸው የምንችል ጉዳዮች እንዳልሆኑ ሲነገረን ቆይተናል፡፡
የፖለቲካ ሥርዓቱም ሰውን በእቃና በባሪያ ደረጃ ከማየት ውጭ ስለራሳቸውም ይሁን ስለሌው ነጻነት ቀደም ብለን የጠቀስነውን ግንዛቤ ባልያዙ ድውያን እጅ በተከታታይ በመውደቁ ከመሪዎች ወደ ህዝብ ሊወርድ የቻለ የነጻነት ቡራኬ አልታየም፡፡ ከታች ወደ ላይ ነጻነትን ለማስከበር የተደረጉ አመጻዎች ለዘመናት በሽንፈት የተጠቃለሉበት ወይም አሸናፊው ነጻ አውጭ ነኝ ባይ ወደ ሌላ ባራያ ገዥነት የተቀየረበት ሁኔታ በመከሰቱ፤ በህብረተሰባችን ውስጥ ምንም ነገር አይቀየርም የሚል አመለካከት እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡ ተረትና ምሳሌዎቻችን በሙሉ፣ እነ ጎመን በጤናን፣ አጉል መፈራገጥ ለመመላለጥ የመሳሰሉት፣ ነገሮችን አትነካካ የምትቀይረው ነገር የለም የሚለውን አመለካከት የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡
ህብረተሰባችን በአዛዠና በታዛዥ በጌታና በሎሌ ግንኙነት ተተብትቦ ለረጅም ዘመን የኖረ በመሆኑ ይህንኑ የእዝ ሰንሰለት የሚያንጸባርቁ አመለካከቶች ናቸው በሃገራችን ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩት፡፡ በቃን ብለው የተነሱ ዜጎች በየጊዜው የገጠማቸውን ስቃይና መከራ ለዘመናት ሲያስታውስ የሚኖር ትውልድ አበሳው ሲበዛበት፣ ማመጽን ሳይሆን ምንም ማድረግ አይቻልም ወደሚል የራስ ሃላፊነትና የየራሱን ሰብአዊ የድርጊት ነጻነት መካድ ውስጥ ይገባል፡፡ ማለቂያ የሌላቸውን ምክንያቶች በመደርደር እንደ አንድ ሃገር ዜጋ ብቻ ሳይሆን እንደሰው ልንቀበለው የማይገባንን እጅግ አሳፋሪ ሃገራዊና ማህበራዊ ሁኔታ ተቀብለነው መኖር የምንችለው ለእዚህ ብቻ ነው፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የሰብእና መራከስ ውርደትና አሰቃቂ ድህነት እያየን እንዳላየን ማለፍ የምንችለው ቀደም ብለን እራሳችንን ከሰውነት አውርደን በእቃነት ለማስቀመጥ በመቻላችን ብቻ ነው፡፡ ራሳችንን በእቃነት ለማስቀመጥ ፍላጎቱ እስካለን ድረስ ደግሞ በእቃነት ሊያስተናግዱን ዝግጁ የሆኑ ሌሎች ሰዎች ሁሌም እንዳሉ መረዳት ይኖርብናል፡፡ መብታችንን ከሚገፉት በላይ መብታችን በተለያዩ ምክንያቶች እንዲገፈፍ የፈቀድነው ግለሰቦች ነን በቅድሚያ ተወንጃይና ተወጋዥ መሆን የሚገባን፡፡ ከግል ሰብብ አንስተን በባህልና በማህበረስብ ከወረስናቸው ዝንባሌዎች ጭምር አንዳቸውም ለነጻነታችን ላለመታገል ምክንያት መሆን እንደማይችሉ ግን እናውቃለን፡፡ የሚቀረን ይህንን እውቀት ከምር ወስደን በተግባር መተርጎም ብቻ ነው፡፡
ዜግነትና ነጻነት
የዜግነት ነጻነት ለሁላችንም በእኩልነት ከተላበስነው ሰብአዊ ነጸነት የሚመነጭ ነው። የዜግነት ነጻነት የምንላቸው የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና ሌሎች መብቶች በሙሉ የሰብአዊ ነጻነታችን ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ እነዚህን መብቶች ማንም እንዲገፋቸው ልንፈቅድለት የማንችለው ይህ ገፈፋ በቀጥታ ሰው አይደላችሁም የሚል መልእክት ስለሚያስተላልፍ ነው፡፡ ለእነዚህ መብቶች የሚደረግ ትግል ሰብአዊ ፍጡርነትን ለመከላከል የሚደረግ ትግል ነው፡፡
የዜጎች ነጻነት ግን ከዚህም ሰብአዊ ማንንት ጋር ከተሳሰረ ጉዳይ በላይ ሌላም ተጨማሪ ትርጉም አለው፡፡ ሰው የሚኖረው በማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ ማህበረሰብ ማለት ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ የሰው ማህበር ማለት ነው፡፡ በእዚህ ማህበረሰብ ሰዎች ተሰባስበው የሚያደርጉት ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሁሉንም በእኩልነት በሚያዩ በጋራ ስምምነት የተደረሰባቸው ውሎችና ህጎች አማካይነት ነው፡፡ በእነዚህ የእኩልነት ውሎች ስር እያንዳንዱ ዜጋ በነጻነት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በተከበረባቸው ቦታዎች በመሉ የሰው ልጅ የተረጋጋና የበለጸገ፣ ለሰው ልጆች ስቃይ የሚጨነቅ ማህበረሰብ መፍጠር የተቻለበት ሁኔታ እንዳለ እናውቃለን፡፡
ዜጎችን እኛ እናውቅልሃለን በሚል የጥቂቶች ፈላጭ ቆራጭነት ስር አስገብተው የሚገዙ ስርአቶች በሞራል ኪሳራ የተሞሉ ብቻ አይደሉም፡፡ በሁሉም መስኩ መከራ አምራቾች ጭምር ናቸው፡፡ ይህ ሃቅ እኛ የግንቦት7 አባላት ለዜጎች ነጻነት እንድንቆም የሚያደርገን ተጨማሪ ምክንያት ነው፡፡ ነጻነት በማይከበርብት ሁኔታ የሚራከሰው ሰብአዊነት ብቻ ሳይሆን ማህበረሳባዊነትም ጭምር ነው፡፡ በሃገራችን የዜጎች የፖለቲካ ነጻነት እንዲከበር የግንቦት 7 ንቅናቄ ዋነኛው አጀንዳው አደርጎ የሚታገለውም ለእዚህ ነው፡፡ የፖለቲካ ነጻነት ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ የሚገልጸው የመጨረሻው ክፍል ከእዚህ የሚቀጥለው ነው፡፡
የፖለቲካ ነጻነት
‹‹የፓለቲካ ነፃነት›› የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ልንተረጉመው እንችላለን፡፡
- የተሟላ የፓለቲካ ነፃነት መኖር በግለሰብ ሉዓላዊነት ላይ የጉልበት ጣልቃ-ገብነት አለመኖር ማለት ነው፡፡ የግለሰብ ሉዓላዊነት ደግሞ አንድ ሰው ችሎታውን ተጠቅሞ ፍላጎቶቹን የማሟላት ተፈጥሮአዊ መብት ነው፡፡ እናም የፓለቲካ ነፃነት መኖር ይህ መብት በሰው ወይም ሰው በፈጠረው ተቋም አለመገደቡን ያመለክታል፡፡
- የፓለቲካ ነፃነት ማለት አንድ ግለሰብ ተፈጥሮአዊ ችሎታውን ሙሉ በሙሉ ተጠቅሞ ፍላጎቶቹን ለማሟላት የሚያስፈልገው ኃይል እና/ወይም ሥልጣን እና/ወይም ግብዓቶች ተሟልተውለታል ማለት ነው፡፡
የመጀመሪያው ትርጉም ግለሰብ ሰው በመሆኑ በተፈጥሮ የተጎናፀፈውን ፀጋ በተግባር ላይ ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት በጉልበት የሚገታው አለመኖሩን ሲገልፅ (negative liberty)፤ ሁለተኛው ደግሞ ሰው የመሆንን ፀጋ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የሚያስፈልጉ ነገሮች ተሟልተው መገኘታቸው ላይ (positive liberty) ያተኩራል:: የመጀመሪያው ትርጓሜ ግለሰብ በተናጠል ሁለተኛው ደግሞ ግለሰብን በማኅብረሰብ ውስጥ የሚያዩ በመሆናቸው በሁለቱ መካከል ልዩነቶች ቢኖሩም ሁለቱም ትርጓሜዎች በነፃ ማኅበረሰብ ውስጥ ሰዎች በግልም ሆነ በጋራ ያሏቸውን ያልተገደቡ ሰፊ መብቶችን ይመለከታሉ፡፡
የፓለቲካ ነፃነት መሰረቱ የሰው በሰው መጨቆን፣ መገዛት፣ መገደድ አለመኖርን ነው፡፡ የፓለቲካ ነፃነትን በተሟላ ሁኔታ ለመጠቀም ደግሞ የመኖርን፣ የመማርን፣ በነፃነት የማሰብን የመሳሰሉ መሰረታዊ መብቶች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ የፓለቲካ ነፃነት እጦት የሚፈጠረው በአብዛኛው ሥልጣን በጥቂቶች እጅ በገባ ጊዜ ነው ፡፡ ስለሆነም ለፖለቲካ ነፃነት አስፈላጊ ከሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው ሥልጣን በጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እጅ እንዳይገባ ማድረግ ነው፡፡ የፓለቲካ ነፃነት አይነቶች ብዙዎች ቢሆኑም የሚከተሉትን ለአብነት መግለፅ ይበቃል፡፡
- የመሰብሰብ ነፃነት፣
- የመደራጀት ነፃነት
- የመማር ነፃነት
- ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት
- የእምነት ነፃነት
- የመናገር ነፃነት
- የፕሬስ ነፃነት
- የሃሳብ ነፃነት
- የአካዳሚ ነፃነት
- የፆታ ነፃነት
- ራስን የመከላከል ነፃነት
- መሪዎችን የመምረጥ ነፃነት
የፖለቲካ ነፃነትና ማኅበራዊ እድገት በበርካታ መንገዶች የተያያዙ ናቸው፡፡ ነፃነት ዜጎች በተፈጥሮ ያገኙትን እና/ወይም በትምህርትና ልምድ ያካበቱትን ችሎታ ፍላጎታቸውን በሚያረካ መንገድ የመጠቀም እድላቸውን ስለሚያሰፋ ምርምርንና ፈጠራን ያዳብራል፡፡ ነፃነት የሰው ልጅን ምኞቶች ያሳድጋል፡፡ የፍላጎቶች ማደግ ደግሞ አዕምሮን ለማሰብ፣ ለመመራመርና ለፈጠራ ያመቻቻል፡፡ ለነፃ ማኅበረሰብ ማበብ ችግርና ያልተሟሉ ምኞቶች የስኬት ምንጮች ናቸው፡፡ በመሆኑም የነፃነት መኖር ዘላቂ ለሆነ እድገት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እድገት ያለ ነፃነት ትርጉሙ አነስተኛ ነው፡፡ በቁሳዊ ምቾት ቢንበሸበሽም፣ ሰው ሰብዓዊ ክብሩን ከተነፈገ፣ ይዋል ይደር እንጂ ራሱን ጌቶቹ ከሱ ምን እንደሚፈልጉ ሳያውቅ በመድለብ ላይ እንዳለ ፍሪዳ አድርጎ መቁጠሩ የማይቀር ነው፡፡
ሰውን ቁሳዊ ምቾት ብቻ አያኖረውም። ማኅበራዊና መንፈሳዊ ምቾቶችንም ይፈልጋል፡፡ እንዲያውም የሰው ልጅ ራሱን ባበቃ (ማለትም ባሳደገ) መጠን ለማኅበራዊና መንፈሳዊ ምቾቶች ያለው ክብር እየበዛ፤ ለቁሳዊ ምቾቶች ያለው ክብር ደግሞ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ታላላቅ መሪዎች ለክብራቸው፣ ለዓላማቸው፣ ለድርጅታቸው ሲሉ መራብን፣ መጠማትና መሰቃየትን ብቻ ሳይሆን መሞትንም በደስታ የሚቀበሉት።
ማጠቃለያ
ከእዚህ በላይ በስፋት የቀረበው ጽሁፍ በአጭሩ መጭመቅ ይቻላል፡፡ የነጻነት ጉዳይ ሰው የሚደርግን ከሌለው ሁሉ ፍጥረት የሚለየን ወደ እዚህ ምድር ስንመጣ አብሮን የመጣ የተፈጥሮአችን አካል ነው፡፡ ይህንን ነጻነት ከሰው መግፈፍ አይቻልም፡፡ ሰው ነጻ መሆኑን ማስቆም የሚቻለው አንድም ሰውየውን በመግደል ወይም ኮማ ውስጥ በመጨመር ብቻ ነው፡፡ የሰው ልጅ ነጻነት በማህበረሰብ ከመደራጀቱ አስቀድሞ በሰውነቱ የመጣ ነጻነት ነው፡፡ ይህ የተፈጥሮ ነጻነት ገደብ የሌለው በስፋቱ ታላቅነት በውቅያኖስ ላይ ለብቻው እንደተጣለ ሰው ባለቤቱን የሚያሸብር ነው፡፡
በማህበረሰብ ውስጥ በፖለቲካ በኢኮኖሚ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ የምንጥላቸው የነጻነት ገደቦች ሁላችንም በተናጠል በተፈጥሮ ባገኘነው ነጻነት እንጓዝ ብንል የሚከተለውን ቀውስ ለመከላከል ነው፡፡ እነዚህ ገደቦች ደግሞ ሁላችንም በስምምነት የደረስንባቸው ውሎች ውጤቶች መሆናቸው ከሰብአዊ ክብራችን ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ እኛ ያልተስማማንበትን የነጻነት ገደብ ላድርግባችሁ የሚል አምባገነን ከመጣ የማይዋጥልንም ለእዚሁ ነው፡፡ ዛሬ በሃገራችን የሚካሄደውን የነጻነት ትግል ልዩ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ህዝብ የእዚህ አይነቱ ነጻነት ባለቤት መሆኑን የተረዳበት፣ በላዩ ላይ የተዘፈዘፉ ዘረኞችና አምባገነኖች እንደ ከዚህ ቀደሙ ገዥዎች ከሰማይ የወረዱና ምንም ሊያደርጋቸው የማይችል አድርጎ የማያይበት ምእራፍ ላይ የደረሰበት መሆኑ ነው፡፡
ይህ አዲሱ የነጻነት እይታ የሚያስጨንቅ ነው እናዳልነው ሁሉ የሚያስደስትም ነው። የመከራችንና የዘረኛ አምባገነኖች ቀን ማጠሪያ መቃረቡን የሚያመላከት ነውና፡፡ ሌላ ዙር የባርነት ሥርዓት በሃገራችን ሊመጣ የማይችል መሆኑን የሚጠቁም ነውና፡፡
እያንዳንዱ የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ አባል ነፃነት ሰው የመሆናችን መታወቂያችን መሆኑን በመረዳት ከነፃነቱ የሚያስበልጠው ምንም ነገር የለም ተብሎ ይታመናል:: የግንቦት 7 አበላትን የዚሁ የነጻነት ትግል ግንባር ቀደም ታጋዮች የሚያደርገን ይህ እውነታ ነው፡፡ በቃላችንና በተግባራችን የነጻነት ሃዋርያት ሆነን በመገኘት በቅድሚያ እራሳችንን ነጻ አውጥተን ሌላው ወገናችን ለነጻነቱ የሚያደርገውን ትግል በመደገፍ ከጎኑ መቆም እንችላለን፡፡