ኢትዮጵያ ሶማሊያን አትሆንም !!!
ከዝግጅት ክፍላችን
ከሰሞኑ በህወሃት መንደር ስንሰማው የኖርነው ሟርት እንደገና ታድሶ መወራት ጀምሯል።ሊቢያ፤ ግብጽ፤ ቱኒዚያና ሌሎችም አገሮች ውስጥ የሚታየው ዓይነት አብዮት በኢትዮጵያ ቢነሳ ኢትዮጵያ ትጠፋለች የሚል የተለመደ ሟርት በሰፊው መወራት ጀምሯል። ይህ ባዶ ማስፈራሪያ አይደለም። ህወሃቶች ህዝቡ በነጻነት ከሚኖር ይልቅ ዜጎች እርስ በርሳቸው ተጫርሰው አገሪቷ ብትጠፋ ቅር የሚላቸው ግለስቦች እንዳልሆኑ የ1997 ዓ.ም ምርጫና ውጤቱ በቂ ምስክር ነው።
ኢትዮጵያ በብዙ ብሄሮችና ሃይማኖቶች የተከፋፈለች ነች። ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳች ዓይነት የለውጥ ፍላጎት ቢነሳ እልቂትና መበታተን ይከተላል እያለ መለስ ዜናዊ ማላዘን ይዟል።
እንዲህ ዓይነቱን ሟርት የግብጹ ሆሲኒ ሙባረክ፤ የቱኒዚያው ቤኒ ዓሊ፤የሊቢያው ሙሃመድ ጋዳፊ እና ሌሎችም ዘራፊ አምባገነኖች አሟርተውታል።ህዝቦች በአንድነት ለነጻነታቸውና ለክብራቸው ፀንተው ቁመው ሟርተኞችን አሳፍረዋቸዋል። የእኩልነት፤ የነጻነትና የፍትህ ጥያቄ ሰው የመሆን ጥያቄ እንጂ የዚህና የዚያ ብሄረሰብ ወይም ደግሞ የዚህና የዚያ ሃይማኖት ጥያቄ ብቻ አይደለም። ምንም እንኳን መለስና ግብረአበሮቹ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ ዓይን እያላቸው የማያዩ ፍጡራን በመሆናቸው የሚነገራቸውን ሊያደምጡ ባይችሉም ደግመን ደጋግመን ኢትዮጵያችን እንደ ሶማሌ እንደማትሆን አበክረን መንገር እንፈልጋለን። የኦትዮጵያን ጥያዌ አንድ ነው።የነጻነት፤የፍትህና የእውነተኛ ዴሞክራሲ ጥያቄ ይበልጥ ያስተሳስረናል እንጂ አይበትነንም። እርስ በርሳችን ተደጋግፈን እንድቆም ምክንያት ይሆነናል እንጂ የሶማሊያ እጣ ፈንታ እንዲደርስብን አያደርግም። ኢትዮጵያችን እንደ ሶማሌ አትበታተንም። መለስ ሆይ ሟርትህና ተንኮልህ እንደማይሰምርልህ ተረድተህ ከህዝባችን ጫንቃ ላይ እንድትወርድ እንጠይቅሃለን።
ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም። ኢትዮጵያ አርቆ ማየት የሚችሉ አስተዋይ ዜጎች ያሏት አገር ነች።ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ እንዳትሆን ለመታደግ ቆርጠው ግዜውን የሚጠብቁ ምርጥና በክፉ ቀን የሚነሱ ልጆች አሏት። ምንም እንኳ የእነመለስ ዜናዊ የጥፋት ሰይፍ መመዘዙ ባይቀርም ያንን መክቶ አገሪቷን በሠላምና በህዝቦች ሙሉ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ለመዘርጋት የተዘጋጀ ኃይል እንዳላት ለማስገንዘብ እንወዳለን።አሁንም ኢትዮጵያን እንደ ሶማሌ ለማድረግ ቆርጣችሁ የቆማችሁ ግለሰቦች (በተለይም መለስ ዜናዊ) ቆማችሁ ራሳችሁን እንድትመረምሩ እናሳስባችኋለን። በታሪክ ተወቃሾች፤ በህግ ፊት ተጠያቂዎች መሆናችሁንም መዘንጋት አይገባችሁም።
የተከበራችሁ የአገራችን ዜጎች የሁላችንም ጠላት መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ የወለዱት የነጻነት እጦትና የፍትህ መጓደል ነው። ነጻነታችን ተረጋግጦና ፍትህ ነግሶ እስከምናይ ድረስ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል። የመለስ ዜናዊ ስሜት ህግ መሆኑ ሳያበቃ እንቅልፍ በዓይናችን ዝር አይበል። እኛ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ አባላት በአገራችን ዜጎች ላይ የሚቀልደውን መለስ ዜንዊን ከስልጣን ሳንወርድ አናርፍም። ረፍታችን የመለስ ከስልጣን መባረርና በአገራችን ውስጥ ነጻነት፤ ፍትህና እኩልነት መስፈኑ ነው።እስከዚያ የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም።
የመለስ ዜናዊ ስሜት ህግ በሆነበት አገር ዜጎች በሰላም አይኖሩም። የመለስ ዜናዊ ስሜት ህግ በሆነበት አገር ዜጎች ሠርተው ለመኖር የህግ ዋስትና የላቸውም። የመለስ ዜናዊ ስሜት ህግ በሆነበት አገር ዜጎች በእኩልነት እየኖሩ አይደለም። ጥቂቱ በፎቅ ላይ ፎቅ ሲሰራ፤ አይቶት የማያውቀውን ባለቀለም መጠጥ እንደውሃ ሲራጭና ሆዱ ከሚችለው በላይ ያገኘውን ሁሉ ሲያገበስብስ ሌላው በዝምታ የዚህ ሁሉ ተውኔት ተመልካች በሆነበት አገር ውስጥ ሠላም አለ ማለት ራስን ከማታለል የዘለለ ትርጉም ያለው ነገር አይደለም። ኢትዮጵያችን ውስጥ ያለው ዝምታ ሠላም ሳይሆን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ሮሮ መሆኑን ለመለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በሊቢያ ወጣቶች መኩራታችሁን መግለጻችሁን እያየንና እየሰማን ነው። ይሄ መልካም ነገር ነው።ከሊቢያ ወጣቶች ቀደም ብለው የኢትዮጵያ ወጣቶች እምቢ ለነጻነቴ እምቢ ለክብሬ ብለው አገራቸውን በነጻነት ጠብቀው አልፈዋል። አሁን ያሉት የኢትዮጵያ ወጣቶችም ከቀደሙት ዜጎች የወረሱት የነጻነት መንፈስ በውስጣችሁ እነደሚነድ እናውቃለን። ኢትዮጵያችን ለነጻነቱ ቀናዒና ለክብሩ ሟች ትውልድ ባለቤት ነች። በላይ ዘለቀ፤ አብዲሳ አጋና ሌሎችንም ያፈራች አገር ነች። በላይ ዘለቀና አብዲሳ አጋ የነበራቸው ሃሞት የዛሬውም ወጣት አለው። የበላይና የአብዲሳ የጀግንነት መንፈስ በዛሬው ትውልድ ላይም አለ። የዘመኑም ትውልድ ነጻነቱን የሚጠይቅበት ግዜ ሩቅ አይደለም።ብዝበዛ፤ዘረኝነት፤ ጭቆናና በስልጣን መባለግ ይብቃ የሚልበት ግዜ እየመጣ ነው።
ውድ የተከበራችሁ የአገራችን ዜጎች ለነጻነት የሚደረግ ትግል አርቆ አስተዋይነትን፤ ርህራሄንና ፍቅርን ይጠይቃል። እነመለስ ዜናዊ በብሄራችንና በሃይማኖታችን ከፋፍለው እርስ በርሳችን እንድንጫረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ማወቅ ይኖርብናል። ለነመለስ ዜናዊ የሰው ልጆች ህይወት የቁጥር ጨዋታ እንጂ ሌላ አይደለም። ስንት በመቶ የሚሆነውን ለእርድ እናቅርብ ብለው ያሰላሉ እንጂ የሰው ልጆች ደም መፍሰስ ቅንጣት ታክል የሚቆጫቸው ሰዎች አይደሉም። ለነጻነቱ የሚታገል ሰው በአንድ ብሄር ላይ ካነጣጠረ ጥላቻ ራሱን ማራቅ አለበት። ጠላታችን አንድ ብሄር ወይም የአንድ ወገን ህዝብ አይደለም። ችግራችን የነጻነት ማጣትና የፍትህ መጓደል ነው። የምናተኩረውም ነጻነታችንን ነጥቀው በሚያዋርዱን ሃይሎች ላይ ነው እንጂ ሌላ ማንም ላይ አይደለም።
በየትኛውም ዓለም ህዝብ የህዝብ ጠላት ሁኖ አያውቅም።እነመለስ ዜናዊ ግን አንድ ህዝብ የሌላው ህዝብ ጠላት እንደሆነ ሲሰብኩ ኖረዋል።የሰማቸው ግን አልተገኘም። ይህን ክፉ ምኞታቸውን በተግባር ለማሳየት ግን የሚችሉትን ሁሉ ሞክረዋል ወደፊትም እንደሚሞክሩ መጠበቅ አለብን።ስለሆነም የነመለስ ዜናዊን የተንኮል ወጥመድን ሰብሮ ለማለፍ ሁላችንም በፍቅር፤ በአንድነትና በጽናት እንድንታገል ግዜውና ሁኔታው ግድ ይለናል።ድምጻችንንም ከፍ አድርገን ኢትዮጵያ ሶማሊያንን እንደማትሆን ለመለስና ለግብረ አበሮቹ ማሳሰብ አለብን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!