በሽብር ወንጀል ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

(ሪፖርተር) — ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብርና የአመፅ ድርጊት ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል፣ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው የነበሩ ሁለት ኢትዮጵያውያንና ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞችን ጨምሮ በዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ላይ ጳጉሜ 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው፣ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ መምህርትና በፍትሕ ጋዜጣና በሌሎች ጋዜጦች ላይ አምደኛ በሆነችው ርዕዮት ዓለሙ፣ የስዊድን ዜጋ በሆኑት ጋዜጠኞች፣ መርቲን ካርል ሽብዬና ጁሃን ከርል ፐርሰን፣ ቋሚ አድራሻ በሌላቸው አብዲ ወሊ መሐሙድ እስማኤልና ከሊፍ አሊ ዳሂር፤ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር፣ ሒሩት ክፍሌና ኤልያስ ክፍሌ (በሌሉበት) ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክስ ማመልከቻው እንደገለጸው፣ ጋዜጠኛ ውብሸት፣ ርዕዮት፣ ዘሪሁን፣ ሂሩትና ኤልያስ በዋና ወንጀል አድራጊነት ካልተያዙ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ አሸባሪዎች ጋር ተካፋይ በመሆን ራሳቸውን ግንቦት 7፣ አርበኞች ግንባር፣ ኦነግና ኦብነግ በሚል በሚጠሩትና በኤርትራ መንግሥትና በኤልያስ ክፍሌ አሰባሳቢነትና በቡድን አስተባባሪነት፣ በህቡዕ፣ ትጥቃዊና በሽብር የተደገፈ ትግል የማድረግ ጥምረት ፈጥረዋል፡፡ የትብብር ስምምነትም ፈርመዋል፡፡ ከሰኔ ወር 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሽብር ድርጊት ለማፈራረስ ሲዘጋጁ መቆየታቸው በክሱ ላይ ተመልክቷል፡፡

ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በኤልያስ ክፍሌ (የኢትዮጵያ ሪቪው አዘጋጅ) በአገር ውስጥ በህቡዕ ተደራጅተው ከውጭው ቡድን ጋር በመቀናጀትና የሥራ ክፍፍል በማድረግ፤ አዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ወልድያ፣ ሐረር፣ ሐዋሳ፣ አሶሳ፣ ወለጋ፣ ጅጅጋና ጐንደር ላይ የኤሌክትሪክ፣ የስልክና የፋይበር ኔትወርክ መስመሮችን ከጥቅም ውጭ ለማድረግ መስማማታቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው በኤልያስ በኩል በስውርና በረቀቀ መልኩ እንደነበር የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ የሽብር ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ በአዲስ አበባና በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ሕገወጥ ጽሑፎችንና በራሪ ወረቀቶችን በየአደባባዩ በመለጠፍ፣ የማነሳሳትና የቅስቀሳ ሥራ ለመሥራትና ለማሠራት ይንቀሳቀሱ እንደነበር ገልጿል፡፡

የሽብር ቡድኖቹ (የኤርትራን መንግሥት ጨምሮ) የጋራ የወንጀል አድማ ስምምነት ላይ በመድረስ የወንጀል ድርጊቱን ዓላማ፣ ግብና የውጤቱን ፍሬ ሙሉ በሙሉ በመቀበል፣ በአመራር ሰጭነት፣ ፈጻሚነትና አስፈጻሚነት መሳተፋቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጾ፣ እያንዳንዳቸው ተከሳሾች ፈጸሙ ያላቸውን ድርጊቶች በመዘርዘር አስረድቷል፡፡ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔርና ሒሩት ክፍሌ ጊዜውና ወሩ ባልታወቀበት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ከኤልያስ ክፍሌ ጋር በህቡዕ ይገናኙ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ሁሉም ተከሳሾች ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመገርሰስ መንቀሳቀስ ወንጀል፣ በሽብርተኛነት ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ሲከሰሱ፣ ኤልያስ ክፍሌ የሽብርተኛነት ድርጊቱ ፍፃሜ እንዲያገኝ የገንዘብ ወይም የፋይናንስ አገልግሎት መስጠቱ፤ ለሽብርተኝነት ድጋፍ በመስጠት ተጨማሪ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ዘጠኝ የሰዎች፣ 51 የሰነድ፣ አንድ የኦዲዮና ቪዲዮና አንድ የካሜራ ማስረጃዎችን ያቀረበባቸው አምስቱም ተጠርጣሪዎች፣ ክሳቸው ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሰማት እንደሚጀመርም ገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተመሳሳይ ቀን ማለትም ጳጉሜ 1 ቀን 2003 ዓ.ም. በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ የመሠረተባቸው የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች፣ ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች ጁሃን ካርል ፐርሰንና መርቲን ካርል ሽብዬ፤ ከሊፍ ወሊ ዳሂርና አብዲወሊ መሐሙድ እስማኤል ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሽብርና በአመፅ ድርጊት ለማፈራረስ፣ ራሱን የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ ከውጭ ግንባር (ኦብነግ) በማለት ከሚጠራው የሽብር ቡድን ጋር አባል በመሆን፣ የወንጀል ድርጊቱን ዓላማ፣ ግቡንና ውጤቱን ፍሬ ሙሉ በሙሉ በመቀበል የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን የዓቀቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

አብዲወሊ መሐሙድ እስማኤል የተባለው ተጠርጣሪ ወርና ቀኑ ባልታወቀ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ሙስጠፋ ኃይሌ በሚባል የኦብነግ አባል ተመልምሎ ጫካ ገብቶ ከመንግሥት ወታደሮች ጋር መዋጋቱን የፖለቲካ፣ የወታደራዊና የሽብር ሥልጠና መወሰዱን ክሱ ይገልጻል፡፡ ተጠርጣሪው ደገሃቡር፣ ዬአሌና አዋሬ በተባሉ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች በሽብርተኝነት የተንቀሳቀሰ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ከሊፍ አሊ ዳሂርም ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ የኦብነግ አባል በመሆን ጫካ ገብቶ ከመንግሥት ወታደሮች ጋር የተዋጋና የተለያዩ ሥልጠናዎችን መውሰዱን፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ መንቀሳቀሱንና የሽብር ተግባር ለመፈጸም ከሶማሊያ ክልል ልዩ ፖሊስ ኃይል ጋር በተደረገ ውጊያ ከግብረ አበሮቹ ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነት የተያዘ መሆኑን ክሱ ይተነትናል፡፡

ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ኦብነግ አመራሮች ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት እንደፈጠሩ የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

እ.ኤ.አ. በማርች 2011 እንግሊዝ አገር ድረስ በመሄድ አብዲ ከተባለ የሽብር ቡድኑ ቃል አቀባይ ጋር በመገናኘት በጋራ የሽብር ዓላማውን ለመደገፍ በመስማማት ከስዊድን ወደ ኬንያ፣ ከዚያም ወደ ሶማሊያ በመግባት ከኦብነግ ተዋጊዎች ጋር መገናኘታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ጋዜጠኞቹ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የጋዜጠኝነት ሙያቸውን ከለላ በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት ለማድረስ ራሳቸውን እንደ ታጣቂ በማዘጋጀት፣ የአገሪቱ የነዳጅ ሀብት ባለበት ቦታ ቁፋሮውን፣ የፕሮጀክት ሁኔታውን፣ የፕሮጀክቱንና የመከላከያ ኃይል የጥበቃ ሁኔታ ማጥናታቸውንና ለኦብነግ የሽብር ዓላማ ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ እንደነበር ክሱ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን የሶማሊያ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል ከአሸባሪው ኦብነግ ጋር ባደረገው ውጊያ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ለሽብርተኞች ድጋፍ በመስጠት ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ጋዜጠኞቹን በሦስት፣ ሌሎቹን አሸባሪ ያላቸውን በሁለት ክሶች ከሶ፣ አራት የሰው፣ ስድስት የጽሑፍ፣ አንድ የኦዲዮና ቪዲዮ፣ በኤግዚቢት ደግሞ 12 ማስረጃዎችን ያቀረበባቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ ጥቅምት 7 ቀን 2004 ዓ.ም. ክሳቸው መሰማት ይጀምራል፡፡