ወያኔ ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሚስጥራዊ መረጃዎች ተጋለጡበት

«የሚስጥራዊ መረጃዎች ተራራ» በሚል የአልጃዚራ የዜና አውታር የገለጸውና የአሜሪካ ዲፕሎማቲክ ሚስዮኖች በሚስጥር የሚለዋወጡአቸውን መልእክቶች ማጋለጥ የጀመረው ዊኪሊክስ ባለፈው ሳምንት እጅግ በርካታ የሆኑ መረጃዎችን በመረጃ ድረ ገጹ ላይ የለቀቀ ሲሆን፣ የዘረኛው የወያኔ አምባገነን አገዛዝ ከዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜርካ ጋር የተለዋወጣቸውን ሚስጥራዊ መልእክቶችና፣ አንዳንድ በዘረኛው አገዛዝ የስልጣን ወምበር ላይ የተቀመጡ ባለስልጣናት አገዛዙን ያጋለጡባቸው ከአራት ሺህ አምስት መቶ በላይ አስገራሚ ሚስጥራዊ መረጃዎች ይፋ ሆነዋል።

ዊኪሊክስ ለአለም ህዝብ ይፋ ያደረገው ግዙፍ የመረጃ ተራራ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር እስከ 2010 በነበሩ ጊዜያቶች በአለም ዙሪያ የተሰማሩ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች የየተሰማሩባቸውን አገሮች ጉዳይ አስመልክቶ ለአገራቸው መንግሥት ያስተላለፉት እንደሆነ ሲታወቅ መረጃው ሊወጣ የቻለው፣ ከአሜሪካኖች ቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ አፈትልኮ በዊኪልክስ ቡድን እጅ በመግባቱ እንደሆነ ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል።

ዊኪሊክስ ይፍ ባደረጋቸው በዚህ መረጃ ውስጥ ኢትዮጵያን አስመልክቶ የወያኔ አገዛዝ የሚያከናውናቸው አበይት ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ክንዉኖች ምን እንደሚመስሉና በዚህም ላይ የአሜሪካ መንግሥት እይታ ምን እንደሆነ የሚገለጹ ከአራት ሺህ በላይ ሰነዶች ተዘርዝረዋል። በዚህም መሠረት አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ. ወያኔ አገራችንን በምን አይነት ሁኔታ እየገዛ እንዳለ፤ በወያኔ ሹመኞች መካከል የአገዛዝ ቀንበራቸውን በፈረጠመ ጡንቻ ለማራዘም እየባዘኑ እንዳለ፤ የምዕራቡን የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት እነመለስ ዜናዊ ለውጪው አለም በሚለፍፉት ዲሞክራሲያዊነትና በተግባር መካከል ስላለው ክፍተትና በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ስላለው አፈናና ወዘተ በሠፊው የሚያትቱ መረጃዎች ለህዝብ ዕይታ ቀርበዋል።

ዊኪሊክስ የለቀቃቸው መረጃዎች በኢትዮጵያዊያን የነጻነት ትግል ላይ ሊኖረው የሚችለው አንድምታ ምን ሊሆን እንደሚችል እንዲያብራሩልን የግንቦት ሰባት ንቅናቄን ከፍተኛ አመራር አካል በስልክ አነጋግረን በሰጡን ምላሽ ሰነዶቹን በትኩረት የማጥናት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ከገለጹልን በሁአላ መረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ማንበብ፤ አንብቦም መረዳት እና ለትግላችን ያላቸውን እንድምታ ለመመዘን ጊዜ የሚፈጅ ጉዳይ ነው። በመሆኑም በሰነዶቹ ላይ የሚኖረንን አስተያየትም ሆነ ለትግላችን የሚሰጠውን ጠቀሜታ ወደፊት የምንገልጸው ይሆናልይሁን እንጂ የተለቀቁትን መረጃዎች በጥሬው ስንመለከት የዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ አገዛዝ አምባገነንነቱ እየጨመረ የመጣ መሆኑን፣ በእስረኞች ላይ አስቃቂ ሰቆቃዎችን (ቶርቸር) የሚፈጽም መሆኑን፣ የመለስ አገዛዝ የሚደሰኩረው የኢኮኖሚ እድገት ውሸት መሆኑን፤ ከመለስ ዜናዊ የቅርብ ባለሟሎች እንኳን ሳይቀር በሥርዓቱ የተማረሩ እና ተስፋ የቆረጡ መኖራቸውን አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በደንብ ያውቃል፤ ይህንኑም ዋሽንግተን ለሚገኘው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሳውቋል ብለዋል።

በተያያዜ ዜና በህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣናት ምርጫ ወቅት መለስ ዜናዊ በአርከበ እቁባይ ተሸንፎ እንደነበር ዊኪሊክስ ይፋ ካደረገው ምስጥራዊ መረጃ ለማወቅ ተችሎአል።

በዊክሊኪስ ይፋ በሆነው የአሜሪካ ኢምባሲ ሚስጢራዊ መልእክት ዉስጥ እንዳተመለከተው፤ የህወሀት የአመራር አባላት በሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ ወቅት፣ አርከበ እቁባይን በአንደኝነት፣ ዘረኛውን መለስ ዜናዊን በሁለተኛነትና ስዩም መስፍንን በሶስተኛነት እንደተመረጡ የነበር ሲሆን። ይሁን እንጅ አርከበ እቁባይ የፓርቲው ሊቀመንበር ወይም ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆን በፓርቲው አባላት ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርትዋል። እርከበ ስልጣን ለመረከብ ፈቃደኛ ያልሆነው በመለስ ዙሪያ የተሰባሰቡትን ሰዎች በመፍራት ነውም ተብሎአል።

የወያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ እቅድ አማካሪ የሆኑትን እንግሊዛዊውን ጸሀፊና ጋዜጠኛ ፓትሪክ ጊልክስን በመረጃነት የሚጠቅሰው የኢምባሲው መረጃ እንዳመለከተው መለስ የህወሀት አባላትን ድምጽ ያጣበት ዋና ምክንያት በባድሜ ጦርነት ምክንያትና በአገሪቱ የሚታየው የኢኮኖሚ ቀውስ የትግራይን ህዝብ እየጎዳ መሆኑ ስለታመነበት ነው ።”

በብአዴን፣ በኦህዴድ፣ በደህዴን እና በሶህዴፓ ውስጥም ተመሳሳይ ክፍፍል ተፈጥሮ እንደነበር ይፋ ያደረገው ምስጥራዊዉ መረጃ በመቀጠልም ተፈራ ዋልዋ የህወሀትን የበላይነትና ለረጅም ጊዜ በስልጣን መቆየትን ከሚቃወሙት ውስጥ የተፈረጀ ሲሆን፣ በረከት ስምኦንና አዲሱ ለገሰ ደግሞ የህወሀት የበላይነት እንደተጠበቀ እንዲቆይ ፍላጎት ነበራቸውም ተብሎአል።

እነ በረከትና አዲሱ ፤ ተፈራ ዋልዋን ከብአዴን ምክትል ሊቀመንበርነት ቦታ ያነሱበት ምክንያትም ተፈራ የህወሀትን ፍጹም የበላይነት እየተቃወመ በመምጣቱ መሆኑ ተመልክቶአል።

በተመሳሳይም አቶ ስዬ አብረሀን በዋቢነት የጠቀሰው የአሜሪካ መረጃ እንደሚያመለክተው ለሱዳን የተሰጠው ሰፊ የአማራ ክልል መሬት በብአዴኖች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር አድርጓል ። አምባሳደር ዶናል ያማማቶ በላኩት መልክት ህወሃት ውስጥ ከ10 አመት በፊት ተከስቶ በነበረው ክፍፍል ምክንያት መለስ ዜናዊ ስልጣኑን ሊያጣ ተቃርቦ እንደነበርና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት ትችቶችንና አስተያየቶችን በቀናነት እንደማያይ ገልጸዋል።