ኢትዮጵያውያንን ስለከፋፈለው የኢሕአዴግ የቋንቋ ፖለቲካ

ፍኖት — ቋንቋ ምድን ነው? እንዴትስ ይበየናል? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች አንስተን መቃኘት አለብን፡፡ ቋንቋ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቋንቋ የሰው ልጆች የመግባቢያ መሣሪያ ነው፡፡ ባንደበት ተቀናብሮ ካንድ ግለሰብ ወደ
ሌላው ግለሰብ መልዕክት ይስተላለፍበታል፡፡ የግንኙነቱ ሁኔታም አንድ ዓይነት ልሣን (Linguistic) ተናጋሪዎች መሆን አለባቸው፡፡ መልዕክት ወይንም መረጃ ተለዋዋጮቹ አንድ ዓይነት ቋንቋ የማይናገሩ ከሆኑ ግን ልውውጡ በምልክት ወይንም ባስተርጓሚ ይሆናል፡፡

እንስሳት፣ አራዊትና አእዋፋትም ርስበርሳቸው የሚገናኙበት “የድምፅ” ምልክት አላቸው፡፡ ነገር ግን እንደ ሰው ልጅ ቋንቋ አያድግም፤ አይሰፋም፤ አይጠፋም፡፡ ድምፅ በመሆኑ የነበረ፣ ያለ፣ የሚኖር ነው፡፡ መልዕክታቸውም እንደ ሰው ልጅ ሰፊና ጥልቀት ያለው አይደለም፡፡ ውሱን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እንደ ሰው ልጅ ቋንቋ ጥበብ አይደለም፡፡ ስለዚህ የቋንቋ ተጠቃሚው ብቸኛው የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ ቋንቋ ምንድን ነው? ለሚለው መሠረተዊ ጥያቄ መልሱ ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ ከላይ የተጠቀሰውን ይመስላል፡፡ ቀጥለን ደግሞ እንዴትስ ይበየናል? የሚለውን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

በቋንቋ ፍላጎታችን፣ ምኞታችን፣ ተስፋችን ፣ ፍቅራችን፣ ጥላቻችንን፣ ባህላችን፣ ወጋችን፣ ፍልስፍናችንን.. ለሌሎች እንገልፅበታለን፡፡ ይህ በመሆኑም ቋንቋ የውስጥ ስሜትን ግልፅልፅ አድርጎ በማሣየቱ (sensational) በመሆኑ አንዳንድ ደካማ ፖለቲከኞች በደም፣ በስጋና ባጥንት እንደ ሚወረስ አድርገው ፈጣሪ ባለቤት በመሥጠት ከመግባቢያነት መሣሪያው ውጭ “የኔ” የሚሉትን ሕዝብ “ቋንቋህ ተረገጠ፣ ቋንቋህ ተጨቆነ፣ ተናቀ…” በማለት የፖለቲካ ጥላሽት ሲቀቡት ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህም ዘለል ባለመልኩ ቋንቋን ጨቋኝና ረጋጭ ሥርዓት እንደሆነ በማስመሰል እንወክለዋለን የሚሉትን ጎሳ ወይንም ሕዝብ በማነሳሳት ለድብቅ አላማቸው ማሣኪያ ይሆን ዘንድ በሌላው ብሔር ወይንም ነገድ ላይ ቀስት በማስፈንጠር በከንቱ ደም ሲያፋስሱ ይታያሉ፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በዚህ 20 ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የከፈለው ፍዳና እየከፈለ ያለው ሲቃይ ከበቂ በላይ ማረጋገጫ ነው፡፡ ሀቁ ግን ቋንቋ በፍፁም በዘር ወይንም በደምና በሥጋ አይወረስም፡፡ ማህበራዊ ግንኙነት የሚፈጥረው እሴት ነው፡፡ ምናልባት ሊሆን የሚችለው ያምባገነን ገዥዎች ፍልስፍና ማስፈፀሚያ መሣሪያ ሆኖ ሊያገለገግል ይችላል፡፡ ከዚህ በስተቀር ቋንቋ በማንኛውም መመዘኛ ፈጣሪ ባለቤት ሊኖረው አይችልም፡፡ በመሆኑም ቋንቋ አብሮ በመኖር የሚፈጠር የመግባቢያ መሣሪያ እንጂ ያንድ ስብስብ ቡድን ብቻ ሀብት ሊሆን አይችልም፡፡ሆኖም አያውቅም፡፡ ግብር አይከፈልበትም፤ቀረጥ አይቀረጥበትም፤ ወይንም “ይህ የኔ ቋንቋ ነው ማንም እንደፈለገ ሊናገርበት አይችልም!” ተብሎ አይከለከልም፡፡ በሌላ አባባል ከሳሽ፣ ወቃሽ ባለቤት የለውም፡፡

በመሆኑም አንድ ቋንቋ የተናጋሪው ሕዝብ የመገናኛ ሀብት ነው፡፡ ርግጥ ነው በደምና በሥጋ የተሳሰሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባንድ ላይ፤ባንድ አካባቢ አብረው በመኖራቸው አንድ ዓይነት ቋንቋ በመናገራቸውና በቀላሉ በመግባባታቸው ቋንቋን ፈጣሪ ባለቤት እንዳለው ሊመሰለን ይችላል፡፡ ግን በፍፁም ከደምና ከሥጋ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ከደምና ከሥጋ ጋር ግንኙነት ያለው ቢሆን ኖሮ በቅኝ ግዛት ሥር ወድቀው ሲማቅቁ የነበሩ ጥቁር አፍሪካውያን የቅኝ ገዥዎቻቸውን ቋንቋ መናገር ባልቻሉ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ “እንግሊዘኛ ተናጋሪ ያፍሪካ አገሮች…” እየተባሉ የሚጠሩት፡፡

ባገራችንም በተወሰነ መልኩ ከ85 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች አማርኛ ቋንቋ በሁለተኛ ቋንቋነት ይግባቡበታል፡፡ እንዲያውም በከተሞች አካባቢ ዜጎች ባፍ መፍቻነት ይናገሩበታል፡፡ በመሆኑም አማርኛ ቋንቋ የኢትዮጵያውያን ቋንቋ እንጂ ላማሮች ብቻ የተፈጠረ ልዩ ፀጋ አይደለም፡፡ እያወቅንም ሆነ ሳናውቅ ወይንም የክፋትን መንገድ በመከተል የባለቤትነትን መብት ፈቅዶ መልቀቅም ውጤቱ ዘግይቶም ቢሆን የሚያስቆጭ ነው የሚሆነው፡፡

ያገራችን ቋንቋዎች ሁሉንም መናገር አለመቻላችን እንጂ ብንችል ኖሮ እንዴት መታደል ነበር፡፡ በርግጥ በያካባቢያችን እንደ አኗኗራችንና እንደየ ጎሳችን ስብጥር ያፍ መፍቻ ቋንቋ መኖሩ ተገቢና አስፈላጊም ነው፡፡ ቋንቋ የማንነት መገለጫም ነውና ባህልና ወግ ይንፀባረቅበታል፡፡ በመሆኑምእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብና ጎሳ ቋንቋውን ጠብቆ የማቆየት ግዴታም ሀላፊነትም አለበት፡፡

ይሁን እንጂ ከምንኖርበት ቀዬና ክልል እየራቀን ስንሄድ ደግሞ ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ሊያገናኘን የሚችል የጋራ ቋንቋ ደግሞ ያስፈልገናል፡፡ አለበለዚያ በቆዳ ቀለማችን ወይንም በመልካችንና በቅርፃችን ሳንለያይ በቋንቋ ተፋጠን ባይታወርነት ሊሰማን ነው፡፡ እንዲህ መሆን ከቻልን ደግሞ ተከባብሮና ተፋቅሮ አብሮ በመኖር የምንፈልገውን እድገት ለማምጣት የሚታሰብ አይደለም፡፡ የተጠመደልን ወጥመድ ግን እንደ ባቢሎን ግንቦኞች በቋንቋ ሳንግባባ በጠላትነት የጎሪጥ እየተያየን እንድንኖር ነው፡፡ ከቋንቋ ብያኔ አንፃር እንዲህ ዓይነት ሂደት ትልቅ ስህተት ብቻ ሣይሆን ጥፋትም ነው፡፡

ስለ ቋንቋ ምንነት ወይንም ብየና አቶ ታከለ ታደሰ የተባሉ ምሁር በህዳር ወር 1995 ዓ.ም ባሳተሙት “ቋንቋ የማነው?” በተባለው ጽሐፋቸው በመጽሐፉ የፊት ገጽ “ቋንቋ የማነው?” በማለት ይጠይቁና ከ25 ያላነሱ ይችን ሀገር ቅንቅን እንደ በላው ደረቅ እንጨት አድርቀው ዱቄት እያደረጓት ያሉትን የክፋትና የጭካኔ እሳቤዎችን ተንትነዋቸዋል፡፡ እነሱም፡-

ጎሰኝነት፣ ዓላማ ቢሰነት፣ ብሔርተኝነት? (ጠባብነት) ራስወዳድነት፣ ፀረ አንድነት? ዘረኝነት፣ ኢሉዐላዊነት፣ ጭፍንነት፣ ወገናዊነት፣ ትምክህተኝነት፣ የበታችነት፣ ገንጣይነት፣ በታኝነት፣ ኢ-ሰብዓዊነት፣ ኢፍትሐዊነት፣ ስግብግብነት… ናቸው፡፡

እንግዲህ ምሁሩ ያስቀመጧቸውን የክፋትና የጨካኝነት ተግባራት በጥንቃቄ ካጤናቸው ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ያለማቋረጥ ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ሥራ ላይ ሲውሉም አንዱና ዋናው የመተግበሪያ መሣሪያው አማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ ገዢዎች የነሱን መርዝ ሲረጩበት ግን ተጠይፈው ወይንም ጠልተው አልተውትም፡፡ ዛሬ ባንዳንድ አካባቢዎች ባማርኛ ቋንቋ በቀላሉ ሐሳብን መግለጽ አይቻልም፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ በብርቱ የሚያሰነቅፍ ሆኗል፡፡ “በገማ ቋንቋ አትናገር!” እስከመባል ተደርሷል፡፡ ይህ አባባል ከባድና አሸማቃቂ የሆነ ክፉ የጥላቻ መግለጫ ነው፡፡ በዚህ ውጤት ወደ ፊት ማን ሊጠቀም ማን ሊጎዳ እንደሚችል ለታሪክ መተው ነው፡፡

ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርነው ከቀያችንና ካካባቢያችን እየራቅን በሄድን ቁጥር ከሌሎች የማህበረሰቦች አባላት ጋር ሊያግባባን የሚችል በታሪክ አጋጣሚ የዳበረ ወይንም በስፋት የሚነገር ቋንቋ ያስፈልጋናል፡፡ በዚህ በኩል የድንቁርናና የክፋትን ካባ ካላጠለቅን በስተቀር የምንከራከር አይመስለንም፡፡ ለማንኛውም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ያጋጠማቸውን ገጠመኝ ከዚህ ላይ መጥቀሱ አግባብነት ያለው ይመስለናል፡፡ እንዲህ ይሉናል፡፡

“…ባንድ ወቅት ወደ ምእራብ የሀገራችን ክፍል እየሄድኩ ሳለ አንዲት ልጅ ከመንገድ ቁማ መኪና ትጠብቅ ነበርና ሊፍት ስለጠየቀችኝ አሳፈርኳት፡፡ ልጅቷ 10ኛ ክፍል ጨርሳ ከቴክኒክ ት/ቤት በሴክሬታሪያል የሦስት ዓመት ኮርስ ጨርሳ ያንድ መንግሥታዊ መ/ቤት ጸሐፊ ነች፡፡ እንዳጫወተችኝ ከሆነ ልጅቷ አዲስ አበባ ገብታ ከፍተኛ ትምህርት መማር ትፈልጋለች፡፡ ችግሯ ግን ከራሷ ቋንቋ ውጭ አማርኛ ቋንቋን መናገርም ሆነ መጻፍ አትችልም፡፡ ደግነቱ እኔ ኦሮምኛ ቋንቋ መናገር በመቻሌ ከኔ ጋር ለመግባባት ግን አልተቸገርንም፡፡

ይች ልጅ ዕድሜዋ ቢያንስ 21 እና 22 ገደማ ይሆናታል፡፡ ይህ ማለትም ኢሕአዴግ አገሪቱን ከመቆጣጠሩ በፊት ያንድ ዓመት ወይንም የሁለት ዓመት ዕድሜ ቢኖራት ነው፡፡ ታዲያ በዘመነ ኢህአዴግ ጊዜ የተቀየሰው የቋንቋ ፖሊሲ ለዜጎች የሾህ አጥር አልሆነም ትላለችሁ ?” በማለት ምሁሩ ቁጭታቸውን በጥያቄ ይደመድማሉ፡፡

ወደ አቶ ታከለ ታደሰ ትንታኔ እንመለስ፡፡ ምሁሩ በመጽሐፋቸው የውስጥ ገጽ ገና ከመነሻው የዚህ መንግሥት የጉዞ አቅጣጫ ያላማራቸው ምሁራን በየመጽሄቱ ያስቀመጧቸውን ለማስረጃነት ጠቅሰዋቸዋል፡፡ እኛም አግባብነት ያላቸው ሆነው ስላገኘናቸው በድጋሚ ጠቅሰናቸዋል፡፡

“ሰውን በዘር ከመከለል የበለጠ ዘረኝነት የለም፡፡ በጎሳ ላይ የተመሠረተ ክልል የሰዎችን እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን አእምሯቸውንም ይከልለዋል!” ዶ/ር መሥፍን ገናናው “በዛሬው ዘመን የተቸገርንበትና እያነጋገረን ያለው ትልቁ ጉዳይ በሀገራችን የጎሰኝነት፣ የዘረኝነትና የፀረ-ኢትዮጵያ መንፈስ መስፋፋትና ለሀገር ስጋት መሆን ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? መልሱ ከታሪክ የሚሳብ ነው፡፡ “የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ባገራችን የባሕር ጠረፍ ላይ ከተቆናጠጡበት ጊዜ አንስቶ ለጠላት አድሮ የመሥራት (የባንዳነት) ባህል ማቆጥቆጥ ጀመረ፡፡ ይህ ተውሳክ ቀስበቀስ አካባቢውን ሲበክል ከቆየ በኋላ ወደታችና ወደ መሀል አገር በመዛመት ብዙ ተከታይ ለማፍራት ቻለ፡፡” ጎባቸው ሰንደቄ

“ገዥው ፓርቲ የጎሣን ፖለቲካ ማራመድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አገራችን ውስጥ ስላም የለም፣ዛሬም ሰላም አለ ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ግጭቶች በየቦታው ይከሰታሉ፡፡ በየቦታው የተፈጠረው ግጭትና ያስከተለው የሕዝብ እልቂት አንዱ ምሳሌ ነው” ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ

ምሁራኑ በዚያን ጊዜ የጠቀሷቸውን መሠረታዊ ነጥቦች ስንዳስስ መነሻቸውም ሆነ የመዳረሻ ግባቸው አማርኛ ቋንቋን እንደ መሠረታዊ ጠላትና እንደጨቋኝ ሥርዓት በመቁጠር ለዚህ ቋንቋ ባለቤት በመስጠት በጠላትነት በመፈረጅ ሰፊ የደም መፋሰስ ደርሷል፡፡ በውጤቱ ግን የኋሊዮሽ ጉዞ ሆኗል፡፡ በስሜት ፈረስ ይጋልቡ የነበሩትም ራሳቸው የጎሳ ሰለባ ሆነው እየተተራመሱ ይገኛሉ፡፡ ይህ የሚያመለክተንም የገዥው ፓርቲ የጉዞ አቅጣጫ ኢ-ሳይንሳዊ በመሆኑ ነው፡፡ በማንኛውም መሥፈርት ቋንቋ በጠላትነት ሊፈረጅ የሚችል አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ89 በላይ ብሔረ ብሔረሰቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ያንድን ቋንቋ ሌላው የሚንቅና የሚጠላ ከሆነ የመከራችን ቋት መሙሊያው ገና ነው፡፡ ይህ የተሳከረና የተወናበደ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች ወደ ትክክለኛ የሰው ልጆች ባህሪ እስካልተመለሱ ድረስም ችግሮቻችን እየተባባሱ መሄዳቸው አይቀሬ ነው፡፡

አቶ ታከለ ታደሰ በመጽሐፋቸው ገጽ 32 ላይ የከበዳቸውን ነገር እንዲህ በማለት ገልፀውታል፡- “የሰውን ልጅ የቋንቋ መለያየት ክፉኛ ከፋፍሎታል፡፡ የህም መከፋፈል አንድነቱን ለመለየት አስኪሳነው ድረስ ህሊናውን አውሮታል…” አያይዘውም በገጽ 4ዐ ላይ በደርግ ጊዜ የሆነውን “…በኢሕአፓ ስም በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ዘመቻ እየታደነ ተጨፈጨፈ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አማራ የተባለ የመደመም ኑሮ እንዲኖር ተደረገ፡፡ በተጨማሪም አማርኛ እንደ አድሃሪና ፊውዳል ቋንቋ መገመት ብቻ ሳይሆን እንደ ጨቋኝ ቋንቋና የገዥ መደብ ምልክት ሆኖ ይወሰድ ጀመር” በማለት ገልፀውታል፡፡

እንግዲህ ምሁሩ ከፍ ብሎ እንደ ገለፁት ላማርኛ ቋንቋ ምን ያህል የተዛባ ትርጓሜ እንደተሰጠውመረዳት ይቻላል፡፡ አቶ ታከለ አያይዘውም በገጽ 43 ላይ፡ “…ይህ ችግር ወዴት ነው እያመራ ያለው? …” በማለት ይጠይቁና “የሦስት ሺ ዓመታት ታሪክ አላት በተባለች ሀገር ከደቡብ አፍሪካ የተነቀለው የአፓርታይድ ሥርዓት ሊዘረጋባት ተዘጋጅቷል” ይሉናል፡፡

ምሁሩ ያንዬ ይህን ይበሉ እንጂ ዛሬማ አፓርቲይድ ጓዙን ጠቅልሎ ኢትዮጵያ ውስጥ በመግባት ተንሰራፍቶ ተቀምጧል፡፡ አቶ ታከለ አክለውም “በልሳነ ብዙ ሀገራት ጎሰኝነት የሚከሰተው በቋንቋ ዙሪያ በሚነሱ ጥያቄዎች ነው – “በማለትበስፋት ገልፀውታል፡፡ ይህ የምሁሩ አባባል አውነት ነው፡፡ ደካማና ያልበሰሉ ፖለቲከኞች ለድብቅ አላማቸው ማሳኪያ ሲሉ፡- “ቋንቋህ ተረገጠ፣ ተናቀ፣ ተንቋሸሸ” በማለት ጠላነው የሚሉትን ብሔር ውይንም ብሔረሰብ የሚናገረውን ቋንቋ አብረው በመጥላት የግንኙነቱን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ሰማይ ሲቧጥጡ ይስተዋላሉ፡፡

ታዲያ ያሁኑ አንገብጋቢ ጥያቄ እስካሁንስ እንደተባለው በከፋ መልኩእ የተናከስንም፣ እየተቧጨቅንም ከዚህ ደርሰናል፡፡ ወደፊትስ ምንድን ነው መፍትሄው? ከልዩነቱ ከገዥው ፓርቲና ደጋፊዎቹ በስተቀር የተጠቀመ ባይኖርም የተጎዱ ዜጎች ግን ሚሊዮኖች ናቸው፡፡ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ አገር ጥለው ተሰደዋል፤ ተገለዋል፤ ተገርፈዋል፤ ዐይኖቻቸው እያዩ በገመድ የፊጥኝ እየታሰሩ በገደል ሳይቀር የተጣሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ይኸ ሁሉ ሆኖ አልፏል፡፡ በቀጣዩ ምን ርምጃ ሕዝብ ይወስድ? የሚለው ጥያቄ እያንዳንዱን ዜጋ ሊከነክነውና ሊቆጨው ይገባል፡፡

በምንም ሁኔታ ገዥው ፓርቲ የቋንቋ አጥር ሊሠራልን አይችልም፡፡ ይህንን የቋንቋ አሸክላ ሕዝብ በጣጥሶ ርቃኑን ሊያስቀረው ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ሳንግባባና ሳንደማመጥ የባቢሎን ግንበኞች ሆነን መቅረታችን ነው፡፡

እንዲህ ከመሆናችን በፊት ግን እንመካከር፤ እንግባባ፤ ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት ልምድ ይኑረን፤ እንዲህ መሆን የምንችለው ደግሞ ሊያግባባን በሚችለው ቋንቋ መግባባት ስንችል ነውና የቋንቋ አጥርን አፈራርሰን መጣል አለብን፡፡ ቋንቋን እንደ ጨቋኝ መሣሪያ አድርገን መመልከት የለብንም፡፡

ቋንቋ ከሆነ የኛ ጠላታችን በምን ተግባብተን ነው የምትገነባው ድሃ አገራችን?