ትግሉ ወደ ሰላማዊ ተግባር ይሸጋገር በእስክንድር ነጋ

ነሐሴ 29ቀን 2003ዓ.ም. በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በተደረገ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ወቅታዊ የሀገሪቷን ጉዳይ አስመልክቼ ያቀረብኹትን ፅሁፍ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡ – መለካም ንባብ፡፡ ሐሳባችሁን አካፍሉኝ፡፡

የተከበሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የተከበራችሁ የአንድነት አባላትና እንግዶች

የነሃሴን ወር አገባደን ወደ ጳጉሜ ወር እየገባን ነው፡፡ ጳጉሜ ከየትኛውም ወር በተለይ ኢትዮጵያዊነት የሚገለፅበት ነው፡፡ በዓለም ብቸኛው 13ኛው ወር መሆኑ ከሌሎች ወራቶች ሁሉ የተለየ ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ 13 ወራቶች ያሏት ብቸኛዋ ሀገር መሆኗ ከሌሎች ሀገሮች ሁሉ የተለየ ያደርጋታል፡፡ ስለዚህም ጳጉሜ የኢትዮጵያ የተለየና ልዩ ማንነት መገለጫ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልዩና የተለየ ማንነት ከ13ኛ ወሯ ሌላ በፊደሏ ይገለፃል፡፡ ለፅሁፍና ለንባብ ምቹ የሆነ ፊደሏ ከዓለም ታላላቅ ውርሶች መካከል በቀላሉ የሚመደብ ነው፡፡ ዓመተ ምህረቷና የሰዓት አቆጣጠሯም ከሌላው ዓለም የተለየ ነው፡፡ ጤፍ የብቻዋ ነው፡፡ የራሷ የሆነ ዜማም አላት፡፡

ስለኢትዮጵያ ብርቅዬ ማንነት ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ቁምነገሩ ግን ኢትዮጵያዊነት የዜግነት መገለጫ ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ራሱን የቻለና ልዩ የሆነ ስልጣኔ መገለጫም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ስልጣኔ የአውሮፓ፣ የአረብ፣ የኢራን፣ የቻይና፣ የህንድና የጃፓን ስልጣኔዎች የሚያሟሉትን መስፈርቶች የሚያሟላ ነው፡፡ በ8ኛው ክፍለ ዘመን የግብፅ ስልጣኔ በአረቦች ወረራ ከጠፋበት ጊዜ አንስቶ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪቃ የብቸኛው የተሟላ ስልጣኔ ማዕከል ሆና ኖራለች፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ልዩ ቦታ የሚሰጣት ሀገር ነች ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ በዓለም ዙሪያ ካሉት 200 ሀገራት መካከል እንደ ኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የተሟላ ስልጣኔ ያላቸው ከ10 አይበልጡም፡፡

የኢትዮጵያ ስልጣኔ የብሄር/ብሄረሰቦቿ የጋራ ውጤት ነው፡፡ የተለያዩ ሃይማኖቶቿ የጋራ ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድም ጊዜ አንድ ቋንቋ የሚነገርባት፣ አንድ ሃይማኖት የሚመለክባት ሀገር ሆና አታውቅም፡፡ ህብረብሄራዊነትና ህብረሃይማኖታዊነት፣ በሂደት የመጡ የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች ሳይሆኑ ራሱ አፈጣጠሯ ናቸው፡፡

የስልጣኔ አንዱ አበይት መገለጫ መንግስት ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩት ዶ/ር ሄንሪ ኪስንጀር፣ የኢትዮጵያ ያልተቋረጠ የመንግስታትነት ታሪክ በዓለም ተወዳዳሪ የለውም ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያን በአንደኛነት፣ የቻይናን በሁለተኛነት ነው የሚያስቀምጡት፡፡ ዶ/ሩ አሜሪካ ካፈራቻቸው ታላላቅ ምሁራን መካከል የሚመደቡ ስልሆነ ምስክርነታቸው ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ ታሪካችን እኛ ከምንገምተው 3000 ዓመታትም በላይ ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡

የዶ/ሩን አባባል የሚቀበሉም የማይቀበሉም ምሁራን አሉ፡፡ ከቻይና የሚቀድም የለም ብለው የሚከራከሩ ብዙ ናቸው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ማስረጃ ሊሆን የሚችል ሰነድ ማቅረብ ስለማይችሉ ክርክሩ የሚጠበቅና መኖርም ያለበት ነው፡፡
የክርክራቸውን ያህል ደግሞ ሁለቱም ወገኖች የማይጠራጠሩትና የማይክዱት ሃቅም አለ፡፡ ላለፉት 100 ዓመታት፣ በአዲስ አበባ ማዕከሉን ተክሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ቢያንስ ቢያንስ ከ2000 እስከ 2500 ዓመታት የሚዘልቅ ቀጥተኛና ያልተበጣጠሰ ታሪክ እንዳለው ይተማመናሉ፡፡ በዚህ የረዥም ዘመን ታሪኩ ግዛቱ አንዳንድ ጊዜ ሲሰፋ ሌላ ጊዜ ሲጠብ ኖሯል፡፡ ጥንካሬው አንዳንድ ጊዜ ሲያይል ሌላ ጊዜ ሲላላም ኖሯል፡፡ ጥሩም መጥፎም መሪዎችን አብቅሏል፡፡ ኢትዮጵያን ከባዕዳን ወረራ ሲጠብቅ ኖሯል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ በግምት ከ7ኛው እስከ 17ኛ ክፍለ ዘመን በነበሩት 1000 ዓመታት በተለያዩ ሀገራት የነበሩ መንግስታት፣ ህዝቦቻቸው አንድ ሃይማኖት እንዲከተሉ ሲያስገድዱ፣ ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖቶች ሀገር መሆኗን አክብሮ ኖሯል፡፡

ይህ የረዥም ዘመን ያልተቋረጠ የመንግስትነት ታሪክ የሚያረጋግጠው ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያ የስልጣኔ ሀገር መሆኗን ብቻ ሳይሆን ህዝብ የእኔ ነው የሚለው መንግስት እንደነበራትም ነው፡፡ ህዝብ ያልተቀበለው መንግስት በቅብብሎሽ ለሺህ ዓመታት መዝለቅ አይችልም፡፡ የኢትዮጵያም ሆነ እንደ ቻይና የመሳሰሉ ጥንታዊ መንግስታት ለረዥም ዘመን ሊኖሩ የቻሉት በአብዛኛው እድሜያቸው በሚያስተዳድሯቸው ህዝቦች ፈቃድ ስለኖሩ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የጭቆና ታሪክ የላትም፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም እስከ 18ኛውና እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዘውድ ስርዓቶች በህዝብ ፍቃድ የቆሙ ነበሩ፡፡ የሚፎካከራቸውና አማራጭ የሆነ ስርዓት አልነበረም፡፡ ከክርስቶስ ውልደት በፊት በአቴንስ ብልጭ ብሎ ድርግም ያለው የዴሞክራሲ ተሞክሮ፣ እንኳን ዓለምን ሊያጥለቀልቅ ቀርቶ፤ በመሳፍንት አገዛዝ ተበጣጥሰው ይኖሩ የነበሩትን ግሪኮች ማዳረስ አልቻለም ነበር፡፡ አቴንስ ስትወድቅ በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ እንኳን በአውሮፓ ከ1000 ዓመታት በላይ ጠፍቶ ነበር፡፡ አውሮፓውያን እንደ አዲስ የተዋወቁትና ያዳበሩት «ሬናስንስና ኢንላይትንመንት» ወይም «የትንሳዔና የብርሃን ዘመናት» በሚሏቸው የ16ኛው የ17ኛው ክፍለ ዘመናት ነው፡፡ እስከዚህኛው ዘመን አውሮፓዊያንም ዘውዳዊ ስርዓትን በፈቃዳቸው ተቀብለውና አቁመው ነው የኖሩት፡፡ ዴሞክራሲን በህዝብ ደረጃ መቀበል የጀመሩት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ስርዓት እስከመጨረሻው 100 ዓመታቱ ድረስ በህዝብ ነፃ ፍላጐት የቆመ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ባሉት 100 ዓመታት ግን አውሮፓውያን «ሬናስንስ፣ ኢንላይትንመንትና ሪፎርሜሽን» ወይም የትንሳዔ፣ የብርሃንና የለውጥ ዘመናት» የሚሏቸው ወደ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃለው ገብተው ተቀባይነቱ በመሸርሸሩ፣ ዘውዳዊው ስርዓት በህዝብ ፈቃድ ከቆመ መንግስትነት በህዝብ ትከሻ ላይ በጉልበቱ ወደ ተፈናጠጠ አምባገነናዊ ስርዓት ተቀይሯል፡፡ የ1966ቱ አብዮት የዚህ ለውጥ ውጤት ነው፡፡

የ1983 ለውጥ ደግሞ የ1966ቱ አብዮት መጨናገፍ ውጤት ነው፡፡ ሁለቱም የህዝብ ፈቃድ የመንግስት ምንጭ እንዲሆን የተደረጉ ትግሎች ውጤቶች ናቸው፡፡ ምንጫቸው ዘውዳዊ ስርዓት የህዝቡን አመኔታ ካጣበት ጊዜ አንስቶ የተቀጣጠለው ትግል ነው፡፡

የ1983ቱ ለውጥም ልክ እንደ 1966ቱ በመጨናገፉ ሀገሪቱ ይኸው ሌላ ለውጥ አርግዛ ትገኛለች፡፡ ይህ ማለት 50 ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ለ3ኛ ጊዜ በለውጥ ሂደት የምትናወጥበት ቅድመ ሁኔታዎች ተሟተዋል ማለት ነው፡፡

እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ገፅታዎች አሏቸው፡፡ ከፖለቲካው አኳያ ከ2003 አጋማሽ ጀምሮ ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ትልቋ አምባገነናዊ ሀገር ሆናለች፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ክብሩ የናይጄሪያ ነበር፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ግን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ በቅታ የዴሞክራሲ ሀገራትን ተርታ ተቀላቅላለች፡፡ በታሪኳ አዲስና ተስፋ የተሞላበት ምዕራፍ ከፍታለች፡፡

ናይጄሪያን በመከተል በአፍሪካ 2ኛዋ ትልቅ አምባገነናዊ ሀገር ግብፅ ነበረች፡፡ ከየካቲት ወር አንስቶ ግን ነፃነት የሞላበት ሀገር ሆናለች፡፡ ዛሬ በእስር ቤቶቿ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም፡፡ ወደስደት የሄዱ ምሁሮቿ ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው፡፡ የሙያ ማህበራት ያለምንም ተፅእኖ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ መንግስትን በጦር መሳሪያ ይፋለሙ የነበሩ ዜጎች ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ተመልሰዋል፡፡

ግብፅን በመከተል የሶስተኝነት ደረጃ በነበራት ኢትዮጵያ ግን በ2003 ለውጥ አልተከሰተም፡፡ ስለዚህም ናይጄሪያንና ግብፅን በመተካት የአንደኝነት ቦታ ተጐናፅፋለች፡፡ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አሁንም እንደታፈኑባት ነው፡፡ በ2001ዓ.ም በፓርላማ ውስጥ ከነበራቸው 178 መቀመጫዎች በ2002 ወደ 1 መቀመጫ ዝቅ ብለዋል፡፡
ከ1977 እስከ 2002 ባሉት 5 ዓመታት ግን ተቃሚዎች የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስክበር ደፋ ቀና ሲሉ ከመንገላታት፣ ከመታሰር፣ ከመደብደብ፣ ከመሰደድና ከመሞት ሌላ ከህዝብ የሚያጣላቸው አንድም ተግባር አልፈፀሙም፡፡ በተገላቢጦሹ አሳሪ፣ ደበዳቢ፣ አሳዳጅና ተኳሽ የሆነው ኢህአዴግ ከህዝብ ልብ ውስጥ ንቅል ብሎ የወጣበት ወቅት ነበር፡፡

ናይጄሪያዊያንና ግብፃዊያን የነፃነት አየር በተነፈሱበት 2003ዓ.ም በኢትዮጵያ ያሉ ነፃ የሙያ ማህበራትና ሲቪክ ተቋማት ድቅድቅ ወዳለ ጨለማ ተገፍተው ገብተዋል፡፡ በዶ/ር ታየ ወልደሰማያት ይመራ የነበረው ኢመማ ሙሉ ለሙሉ ተዘግቷል፡፡ አመራሮቹ አዲስ ማህበር እንዳያቋቁሙ ከህግ ወጭ እግድ ተጥሎባቸዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ዋነኛ ሰለባ የሆኑትን ሰራተኞች ይወክላሉ በሚባሉት ማህበራት ላይ ያለው ቁጥጥርና ክትትል ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠበቋል፡፡ ከሩሲያው ጠ/ሚኒስትር ፑቲን እሳቤ ተቀድቶ የፀደቀው አ ዲሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህግ፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱትንና እያቆጠቆጡ የነበሩትን የሲቪክ ድርጅቶች አጥፍቷል፡፡ ታዋቂው ኢሰመጐ እንኳን አልተረፈም፡፡ ዛሬ በሞትና በሽረት መካከል ይገኛል፡፡ በክልል የነበሩት ቢሮዎቹን ሙሉ በሙሉ ዘግቷል፡፡ አዲስ አበባ የነበሩት ሰራተኞቹንም ከሞላ ጎደል ሙሉ ለሙሉ አሰናብቷል፡፡

ሀሳብን በመግለፅ ረገድ ያለው አፈናም ተባብሷል፡፡ ጋዜጠኛ ውብእሸት ታዬ እና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ በሽብር ክስ ሽፋን በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ፡፡ ጋዜጦች በከፍተኛ የፍርሃትና የመሸማቀቅ ድባብ ውስጥ ሆነው ነው የሚሰሩት፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ነፃ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከሌለባቸው ጥቂት የአፍሪቃ አገራት አንዷ ናት፡፡

እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በፖለቲካ እስረኞች ብዛት ኢትዮጵያ በአፍሪቃ የአንደኝነት ቦታ እንድትይዝ አድርጓታል፡፡ በሰሜንም፣ በደቡብም፣ በምስራቅም፣ በምዕራብም ያሉ ወህኒ ቤቶቿ በፖለቲካ እስረኞች ተጣበዋል፡፡ ከመካከላቸው በሞት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው በርካታ ናቸው፡፡

በአንፃሩ፣ ኢትዮጵያ ለነፃነት ካበቃቻቸው ጥቁር አፍሪቃ ሀገራት መካከል ከግማሽ በላይ የሆኑት ዴሞክራሲያዊ ሆነዋል፡፡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እየተደረገባቸው ነው፡፡ የሙያ ማህበራት በነፃነት እየተንቀሳቀሱባቸው ነው፡፡ ሀሳብ በነፃነት እየተገለፀባቸው ነው፡፡ ኢህአዴግ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት ስልጣን ሲይዝ ግን ከቦትስዋና በቀር ሁሉም በአምባገነኖች ቀንበር ስር ነበሩ፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ነው ምንም አይነት የሽግግር ጊዜ ሳያስፈለጋቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶችን የገነቡት፡፡ የእነዚህ ሀገራት ዝርዝር በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው፡፡ አንዷ ማሊ ናት፡፡ ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ የምትገኝ በረሃማ ሀገር ናት፡፡ ድህነቷ ከኢትዮጵያ ባይብስም የሚሻል አይደለም፡፡ አብዛኛው ህዝቧ በገጠር ነው የሚኖረው፡፡ ህብረብሄራዊ ናት፡፡ ኢኮኖሚ አላት ማለት አይቻልም፡፡ በምሁራን ብዛት ኢትዮጵያ ትበልጣታለች፡፡ ለዴሞክራሲ ስርዓት ጠቃሚ ግብአቶች ናቸው በሚባሉት ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ኢትዮጵያ የሰማይ ያህል ትርቃታለች፡፡ ልብ በሚሰብር ሁኔታ ግን ለዴሞክራሲ የታደለችው ማሊ፤ በአምባገነኖች እየማቀቀች ያለችው ኢትዮጵያ ሆነዋል፡፡

ከኢኮኖሚው አኳያም የተሻለ ነገር የለም፡፡ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ባለፉት 20 አመታት ኢትዮጵያ ከብድርና ከእርዳታ ከ30 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ ወደውጭ ከላከቻቸው ምርቶቿ ተጨማሪ 30ቢሊዮን ዶላር ገደማ አግኝታለች፡፡ ከዚህ ውስጥ ግን 8.4 ቢሊዮን ዶላሩ በመንግስት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች ተመዝብረው ምዕራባውያን ባንኮች ውስጥ ገብቷል፡፡ 24 ቢሊዮን ይቀራል ማለት ነው፡፡ ከእርዳታውና ከብድሩ ጋር ሲደማመር ከ30 እስከ 75ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ ብዙ ገንዘብ ነው፡፡ በገሃድ የምናየው ልማት ይሄን ያህል ገንዘብ የሚያወጣ ነው ብሎ ማመን ይቸግራል፡፡ ገንዘቡ የት ገባ?

ባለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ የሚገባውን ያህል አላደገም፡፡ እዚህም ያለው ምክንያት ፖለቲካው ጋር ያለው ነው፡፡ ኢህአዴግ የገበያውን ነፃነት ለማክበር ዝግጁ አይደለም፡፡ በገቢያው ገለልተኛ ብይን ምትክ እሱ ጣልቃ ገብቶ ማዘዝ ነው የሚፈልገው፡፡በቁጥጥር ያምናል፤ የምንም ነገር ነፃነት ያስፈራዋል፡፡ ውጤቱ ኢትዮጵያን የላኪዎች ወይም Exporters ሀገር ሳይሆን የአስመጪዎች ወይም Importers ሀገር አድርጓታል፡፡ ይህ ደግሞ ለደሃ ሀገር የማያዛልቅ ቅንጦት ነው፡፡ ጊዜውን ጠበቆ ሀገሪቱን ከባድ ችግር ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡

ከ30 እስከ 50 ከመቶ እየዋዠቀ የሚገኘ የዋጋ ግሽበት ደግሞ፣ የስርዓቱ ብልሹነት መገለጫ ሆኗል፡፡ የግሽበቱ ምንጭ መንግስት ነው፡፡ የዓለም ባንክ እንዳረጋገጠው ገንዘብ እያተመ ይረጫል፡፡ ምርት ግን አይጨምርም፡፡ ስለዚህም ብዙ ገንዘብ ትንሽ ምርት ያሳድዳሉ፤ ፉክክሩም ለመሸጥ ሳይሆን ለመግዛት ሆኗል፡፡

በመሰረቱ የዋጋ ግሽበት ለማንኛውም ኢኮኖሚ ቀሳፊ በሽታ ነው፡፡ ትንሽ ህሊና ያለው መንግስት የሚፈራውም የሚከላከለውም ነው፡፡ የህዝብን ኑሮ በማቃወስ ረገድ የሚብሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የኢህአዴግ መሪዎች የዋጋ ግሽበቱን አቃሎ የማየት አባዜ ለህዝብ ያላቸው ንቀት መገለጫ የሚሆነው፡፡ ያስከተለው ችግር እነሱ ጓዳ ባይገባም፣ በአማካኝ ያለውን ኢትዮጵያዊ ህልውና ግን እየተፈታተነ መሆኑ ህሊናቸውን ሊከሰኩሰው ይገባ ነበር፡፡ የኑሮው ውድነት ረሃብን ከገጠር ወደ ከተማ እያስገባ ነው፡፡ የአንድ ኪሎ ሽሮ ዋጋ 25 ብር ገብቶ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ደሃና ሽሮ ተራርቀዋል፡፡ የደሃው ማዝገሚያ ከሽሮ ወደ ጎመን ተለውጧል፡፡ ድሮ ደሃው ስጋ ሲያምረው ከእሱ ወደተሻለው ጎረቤቱ ጎራ ይል ነበር፡፡ ዘንድሮ ሽሮ እያማረው ጎራ ማለት ጀምሯል፡፡ በዋጋ ግሽበቱ ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ወለሉ በታች እየተገፉ ናቸው፡፡

በአንፃሩ፣ ጥቂቶች ደግሞ ከጮማ በዶላር ብቻ ወደ ሚገዛው ካቪያር ተሸጋግረዋል፡፡ የኢህአዴግ ልማት ብዙሃኑን እያደኽየ ለጥቂቶች ደግሞ ሀብት እየጨመረላቸው ነው፡፡ ይሄ ለሀገር የሚበጅ አካሄድ አይደለም፡፡

በማህበራዊው መስክም ያለው አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ ገጠር የሚታረስ መሬት እየጠፋ ወደከተማ የሚፈልሰው ወጣት ቁጥር የሚያስደነግጥ ነው፡፡ የሴቶቹ መሰደጃ የአረብ ሀገራት ሆነዋል፡፡ የትምህርት ጥራት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሸቆልቁሏል፡፡ የከተማውን ወጣት የጫት ጥገኛ የማድረግ ያልተፃፈ ህግ አለ ማለት ይቻላል፤ ከፖለቲካ ለማራቅ ሲባል፡፡
ይህ ሁሉ ተደማምሮ ኢትዮጵያን ለውጥ አፋፍ አድርሷታል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ለውጥ ትሻለች፡፡ ኢትዮጵያ ለውጥ ያስፈልጋታል፡፡ የኢህአዴግ አመራሮች ይህንን ተገንዝበው የለውጡን ጥያቄ በሰላም ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በ3 ምክንያቶች፡-

1. ኢህአዴግ በስልጣን ላይ 20 ዓመታት ቆይቷል

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በአሜሪካ 4 ፕሬዘዳንቶች ስልጣን ተቀባብለዋል፡፡ በእንግሊዝ እንዲሁ 4 ጠ/ሚኒስትሮች ተለዋውጠዋል፡፡ ቻይና እንኳን የኮሚኒስት ፓርቲው ስልጣን አይልቀቅባት እንጂ 3 መሪዎች አይታለች፡፡ በኬኒያ ነባሩ ካኑ ፓርቲ ለተቃዋሚዎች ስልጣን ለቋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ 3 መሪዎች ለዋውጣለች፡፡ በዛምቢያም 3 መሪዎች ስልጣን ተረካክበዋል፡፡ በአጠቃላይ በአፍሪቃም ሆነ በሌላው አለም ባለፉት 20 ዓመታት ቢያንስ ሶስቴ እና አራቴ፤አንዳንዴም ከዚያም በላይ፣ የመሪዎችና የፓርቲ ለውጥ ተስተናግደዋል፡፡ የቀሩት ኢትዮጵያ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኩባን የመሳሰሉ ጥቂት ሀገራት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀገራት አንድ ፓርቲ ስልጣን ላይ ለረዥም ጊዜ መቆየቱ ያተረፈላቸው ሙስናን፣ ኋላቀርነትንና ድህነትን ብቻ ነው፡፡ እነዚህ በሽታዎች የሚፈወሱት የስልጣን ቅብብሎሽ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደክሞታል፡፡ ሌላው ቢቀር ቢያንስ ቢያንስ ከ20 አመታት በኃላ እረፍት ያስፈልገዋል፡፡ ህዝቡ ህጋዊና ሰላማዊ ለውጥ ይፈልጋል፡፡
የኢህአዴግ አመራሮች ፍላጐቱንና መብቱን ሊያስከብሩለት ይገባል፡፡ ጊዜው የዓለም አቀፉ ሁኔታም መብቱን እንዲያከብሩ የሚያስገድድ ነው፡፡

2. የዴሞክራሲ ተስፋ ተቀጣጥሏል

በአረብ ሀገሮች የተቀጣጠሉት ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢታዎች በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻለ ለታፈኑ ህዝቦች ማስረጃ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ህዝቦች መካከል ኢትዮጵያዊያን ይገኙበታል፡፡ በሰላማዊው እና ህጋዊ የፖለቲካ ሂደት ላይ ታላቅ ተስፋ ጥለዋል፡፡ ለእነዚህ ዜጐች ሰላማዊ ጥያቄ ምላሹ ጭቆና መሆን የለበትም፡፡ ጥፋት መሆን የለበትም፡፡ እስር መሆን የለበትም፡፡ ለሰላም ምላሹ ሰላም መሆን አለበት፡፡ የዴሞክራሲ ተስፋ አንድ ጊዜ ከተቀጣጠለ በፖሊሲና ወታደር ፈፅሞ ሊዳፈን አይችልም፡፡በግብፅ ታይቷል፣ በሊቢያ ታይቷል፣ በቱኒዚያ ታይቷል፡፡ በሶሪያና በየመን እየታየ ነው፡፡ ጭቆና እንደ ትላንት አይሰራም፡፡ ከቤን አሊ፣ ከሙባረክ፣ ከጋዳፊና ከአሳድ ተሞክሮዎች መማር የግድ ይላል፡፡

3. ኢትዮጵያ ከጥቁር አፍሪቃ ሀገራት አታንስም

የጥቁር አፍሪቃ ሀገራት ከኃላ ተነስተው ኢትዮጵያን መቅደማቸው በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሀገራዊ ቁጭት ፈጥሯል፡፡ ጋና ዴሞክራሲ ሀገር መሆን እንደቻለች እየታየ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መሆን የማትችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ትላንት የተፈጠሩት ማላዊና ዛምቢያ ዴሞክራሲያዊ ሀገራት ለመሆን በቅተው የፖለቲካ ድርጅቶች ስልጣን መቀባበል ከቻሉ፣ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የተሻለች ዴሞክራሲያዊ ሀገር መሆን ትችላለች፡፡

አፍሪቃዊያን ያለምንም የሽግግር ዘመን በቀጥታ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ከቻሉ ኢትዮጵያዊያን የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋችኋል ሊባሉ አይችሉም፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪቃ መሪ እንጂ ጭራ ሆና አታውቅም፡፡ ታሪኳ ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለሌሎች አፍሪቃዊያን ሞዴል የሚሆን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ፍላጐቱም አቅሙም አላቸው፡፡ ሩጫው አውሮፓና አሜሪካ ላይ ለመድረስ ሳይሆን ከጥቁር አፍሪ ካዊያንን ጋር ለመስተካከል ሆኗል፡፡ ከዚህ በላይ ሀገራዊ ቁጭት ሊፈጥር የሚችል ነገር ፈፅሞ ሊኖር አይችልም፡፡ የኢህአዴግ መሪዎች ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው መጠን የህዝቡን ቁጭት ሊረዱና ሊጋሩት ይገባል፡፡
የተከበራችሁ ወገኖቼ!

አዲሱን አመት ለመቀበል እየተዘጋጀን ነውና ለ2004 የሚሆን ሰላማዊና ህጋዊ ጥሪ በማቅረብ ላጠቃል፡፡
በ2004 ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሀገር እንድትሆን ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ከቃላት ወደ ተግባር የሚሸጋገርበት ይሁን፡፡ ከዚህ በኋላ ቃላት ትርጉም የላቸውም፡፡ የሚባለው ሁሉ አልቋል፡፡ የቀረው ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ነው፡፡ ተግባር ነው

በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ታሪክ ይሰራ፡፡
ፀሐፊውን ለማግኘት [email protected]