የጢስ አባይ ፏፏቴ እየደረቀ መምጣቱ ታወቀ
በኢትዮጵያ የሰሜን ምእራብ ክፍል ከባህር ዳር ከተማ 37 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ጢስ አባይ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውና በቱሪዝም መስብህነቱ የሚታወቀው የአባይ ፏፏቴ እየደረቀ መምጣቱን ነዋሪዎችና ባለሙያዎች መናገራቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ገለጸ።
እንደውስጥ ምንጮቻችን ዘገባ ለጢስ አባይ ፏፏቴዎቹ መድረቅ ዋነኞቹ ምክንያቶች በአባይ ወንዝና በጣና ሀይቅ መገናኛ ላይ የተሰራው የጨረጨራ ግድብና የጣና በለስ የሀይል ማመንጫ ግድቦች መሆናቸውን ባለሙያተኞች የሚናገሩ ሲሆን ቀደም ብሎ ግንባታዎቹ በተከናወኑበት ወቅት ባለሙያዎች ሊከተል የሚችለውን አደጋ በማስታወቅ አስተንቅቀው እንደነበርም ታውቋል።
የጢስ አባይ ፏፏቴን ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ በሚል በጢስ አባይ ላይ ለተጠናቀቀው ፕሮጀክት የፏፏቲው ውሃ መጠለፉ ችግሩን ማባባሱን፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ በብዝሃ ህይወት ላይ ሊከተል የሚችለው ጥፋት ጥናት አልተደረገበትም በሚል በወቅቱ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የጮሁ ባለሙያዎች በወቅቱ ዛቻና ዘለፋ እንደተፈጸመባቸው ሪፖርተራችን ያናገራቸው ታዛቢዎች ገልጸዋል።
በባህርዳር ከተማ የሚኖር አንድ የውሀ ጥናት ባለሙያ ” በአባይ ወንዝ ዙሪያ የሚኖረው ህዝብ በግድቦቹ ግንባታ ምክንያት ህይወቱ ታውኮ እያለ የአለማቀፉ ማህበረሰብና የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች ለምን ትኩረት እንዳልሰጡት አስገርሞኛል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቶአል።