የአንዲት ሀገር ሁለት ዜጎች በይነጋል በላቸው
ሰሞኑን በይልማ በቀለ በእንግሊዝኛ ተጽፎ ከድረ ገፆች ያነበብኩት መጣጥፍ በጣም ነው የሳበኝ፡፡ ግሩም ቅንብር ነው፡፡ መልእክቱ በአፄ መለስ ዜናዊ የሚመራው የወያኔ ዘረኛ መንግሥትና በባሽር አላሳድ ፈላጭ ቆራጭ ይዞታ ሥር የሚገኘው የሶሪያው ባዝ ፓርቲ የመመሳሰላቸው ያንንም ተከትሎ በብዙኃን ዜጎች ከቃላት የመግለጽ አቅም በላይ የሆነ ግፍና በደል የማድረሳቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ በቀጥታ ወዳማርኛ ልተረጉመው ወደድኩና ዛር ከፈረስ የሚሆንብኝ ግላዊ ስሜቴ አላግባብ ጣልቃ እዬገባ ጸሐፊው ሊያስተላልፍ ከተነሳበት ጭብጥና ድምፀት ያፈነግጥብኝና አስቀይመው ይሆናል በሚል ሥጋት ተውኩት፡፡ በራሴው መንገድ ግን ጥቂት ነገር ላክል ፈለግሁ፡፡
ዘውጋዊ ልዩነቶችና ሃይማኖታዊ ክፍፍሎች (ethnicity and religious sects) በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸው ተፅዕኖ በጣም ከባድ መሆኑን በእሳት አለንጋ እየተገረፍን በተግባራዊ ተሞክሮ እያረጋገጥነው ያለነው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የመከራ ሕይወት ከሕዝባዊ የአኀዝ መበላለጥ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት እንዳለውም በሚገባ የተረዳነው እውነት ነው፤ በዚህ አጋጣሚ ጥቂቶች በብዙዎች ላይ ሲሰለጥኑ የሚደርሰውንም ጥፋት እየታዘብን ነው፡፡ ኢትዮጵያና ሶርያ የቅርብ ጊዜ የነዚህ መርገምት ሕዝባዊ የልዩነት መንስኤዎች ሰለባ መሆናቸውንም ይልማ በቀለን ጨምሮ ሌሎችም ጸሐፍትና ምሁራን እያስገነዘቡን ናቸው፤ እኛ ተራ ዜጎችም በሚገባ እያጤንነው ያለነው ነገር ነው፡፡
እንደሚባለው የበርካታ የዓለም ሀገራት ችግር በአብዛኛው ከነዚህ ከፍ ሲል ከተጠቀሱት የችግር ምንጮች አይዘልም፡፡ እርግጥ ነው አደጉ ከሚባሉት ሀገሮች አንጻር ሲታይ ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የቅርብና የሩቅ ጊዜያት ትልሞች በግጭት መንስኤነት ሊካተቱ እንደሚችሉ እንገነዘባለን፡፡ አሜሪካና አውሮጳ ለሊቢያ ሕዝብ ‹ነጻነት› ያን ያህል የተረባረቡት ለሕዝቡ አዝነው እንዳልሆነ የኢትዮጵያ፣ የኬንያ፣የዚምባብዌ፣ የየመን፣ የሱዳን፣ የባሕሬን፣ የሳዑዲ አረቢያ ወዘተ. ሕዝቦች በጨቋኝ መንግሥቶቻቸው በጭካኔ ሲጨፈጨፉ ኔቶን ሊያዘምቱ ቀርቶ ጠንከር ያለ የቃል ማስጠንቀቂያና የገዢዎችን እልህ ሊያበርድ የሚችል ማዕቀብ እንኳን አልጣሉም፡፡ ነገሩ ‹ከሌለህ የለህም› ነው፡፡ የእነዚህ ሀገሮች አምባገነን ባለሥልጣናት፣ አንድም በዴሞክራሲ ስምና ሽፋን ለሰው ዘር ጥብቅና እንደቆሙ በማስመሰል ለሚመጻደቁቱ ‹ውስጡን ለቄስ› ሀገራት መሪዎች ሸሪኮች ናቸው፤ አንድም ሀገሮቹ የታላላቅ ‹ወንድሞችን› ወስፋት የሚያስጮህ ነዳጅን የመሰለ የመሬት ውስጥ ሀብትም ይሁን ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ አያገኙም፣ አንድም ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ዱሮውን ሥልጣን ላይ ከሚገኘው የሀገሩንና የሕዝቡን ጥቅም ለባዕዳን አሳልፎ ከሸጠ የመለስ ዜናዊን የመሰለ ከሃዲ መንግሥት እያገኙ ነው፡፡
ወደመመሳሰሉ ልግባ፡፡ ይልማ እንዳለው የሶርያ የሀፌዝ አል አሳድ መንግሥት እ.ኤ.አ በ1970 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ያዘና ባመቱ ነባር የሀገሪቱን ህግጋት በመለዋወጥ በፕሬዝደንትነት ‹ተመረጠ›፡፡ ለተጨማሪ ግንዛቤ ቀጣይዋን ጥቅስ ይመልከቷት፡፡
In November 1970 General Hafez al-Assad seized power. Assad became president in March 1971; he formed a new cabinet in December 1972, giving the Baathists more than half the posts and dividing the rest among the other parties. Like Assad, many of the new members of the government belonged to the Alawite sect of Islam, which comprises about 11 percent of Syria’s population. (Source: Microsoft Encarta, 2009 edition)
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሥልጣንን እንደአፅመ ርስት ለልጅ አውርሶ አባቱም ቢሞት ሕዝቡ በልጁ እየተሰቃዬ ይገኛል፡፡ እኛም ቢስ አይይብንና መለስ ቢሞት ሰምሃል መለስ ዜናዊ በሀገረ እንግልጣር (እንግሊዝ) የጀመረችውን የማስተርስ ዲግሪ የሌሊት ጭፈራዋን ለኛ ስትል አቋርጣ ወደሀገሯ በመምጣት ልትነግሥልን ትችል ይሆናል፡፡ በተዓምረኛ ሀገር ውስጥ የማይታይ ምን ተዓምር አለ?
ወደ ሃያ ሚሊዮን አካባቢ ከሚገመተው የሶርያ ሕዝብ 11 በመቶውን ቁጥር የሚይዘው የአላዋይት እስላማዊ ጨንፈር(sect) 89 በመቶ የሚሆነውን ሌላውን ሕዝብ በጉልበት ደፍቆ መግዛት ከጀመረ እንግዲህ የጋዳፊን የሥልጣን ዘመን ሊያክል አንድ ዓመት ብቻ ነው የሚቀረው፤ አባት 30 ልጅ 11 በድምሩ 41 ዓመታት – እሚገርም መመሳሰል፡፡ እኛም ገና 20 ዓመት ሊቀረን ይሆን እንዴ? እዚህ ላይ ስደርስ ምነው ሆዴን ባር ባር አለው ጎበዝ? ኧረ የሠይጣን ጆሮ ይደፈን!
አንድ ነገር ጣልቃ ላስገባ፡፡ አህያ በመሠረቱ ጅብን አያሸንፍም ተብሎ ነው የሚታሰበው፤ ትምክህታዊ አስተሳሰብ ሊሆን ይችል ይሆናል እንደአካሄድ፡፡ የሆነ ሆኖ አሸንፎ የማያውቅ ማሸነፉ ያለ ነው – ጠንቁ ግን ከባድ ነው፡፡ አህያ ጅብን ማንቁርቱን ይዞ ገደለው እንበል – ትናንትና ማታ፡፡ ዛሬ ጧት ላይ ሰዎች ደርሰው አህያውን ከጅቡ ሬሣ እናላቅቃለን ቢሉ በጭራሽ አይሆንም፡፡ ልዩ ዘዴን መጠቀም አለባቸው፡፡ አህያው መግደሉን አያምንም፤ ‹ብለቀው ተነስቶ ይቆረጣጥመኛል› ብሎ ነው እሚያምን፡፡ ስለዚህ ብልህ ሰዎች በዘዴ አህያውን በገመድ ያሥራሉ – በቀላል ከማይነቀል ግንድ ወይም ወደመሬት በተቀበቀበ እንጨት ላይ፡፡ ከዚያ በጋለ ብረት አፉን ይለመጥጡታል ወይም እንደምንም መንጋጭላውን በእንጨት ይፈለቅቁታል፡፡ ያኔ ሩጫውን ያቀልጠዋል፤ ካልታሠረ መቆም የለም – ገደል ገብቶ ነው እሚሞት፡፡ ለዚህም ነው ታዲያን በገመድ ወይ በጠፍር ከግንዲላ መታሠር ያለበት፡፡ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ማሸነፉን ከማያውቅ ገገማ አሸናፊ ይሠውራችሁ፡፡ ጥሩ አሸናፊ ያሸነፈውን ሰው በወዳጅነት ቀረቤታ ይይዝና ግጭትን አስወግዶ ለመልካም ነገር ይበረታል፤ ተሸናፊውም እንደተሸነፈ ባለመቁጠር በይቅርታና በሰላማዊ መወቃቀስም ቂሙን ከልቡ አውጥቶ ጥሎ ከአሸናፊው ጋር ለጋራ ብልፅግና በጋራ ይሠለፋሉ፡፡ ይሄ ዓይነቱ ጤናማ መሸናነፍ ውብ ነው፡፡ ሁለቱም አግኝተውበታልና፡፡
አሳድና መለስ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ አሳድ ሕዝባዊው እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ ከራሱ የሃይማኖት ጎራ በተገነባው ሠራዊቱ ሕዝቡን ያለመታከት እንደዐይጥ እየጨፈጨፈ ይገኛል፡፡ እኛ ግን የናቡከደነፆርን ልዩ ጭካኔ በተለይ በ97ቱ ምርጫ አማካይነት አሳምረን ስለምናውቅ እህህኣችንን በሆዳችን አምቀን ይዘን የፈጣሪን የመጨረሻ ፍርድ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቅን ነው ያለነው፡፡ ግን ማንም እንዲህ እንዳይል፡- ‹ሕዝቡ ፈሪ ነው›፡፡ በጭራሽ ሕዝቡ ፈሪ አይደለም፡፡ ብዛት ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ሁነኛና ቀን ዐይቶ የማይከዳ፣ በሞቀበት የማይዘፍን፣ ወዳለውም የማያዘነብል አስተባባሪ ያስፈልጋል፡፡ ጠንካራ የአንድነት መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝባዊ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ጭቆና ስላለ ብቻ ነጻ መውጣትም ትንሽ ቆይቶ ወይም ወዲያኑ ይከተላል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህ ምሳሌ ሊቢያንና ሶርያን ማየት ነው፤ እነሱም እንደኛው በጻዛባቻቻ ‹ሰነፍ፣ ፈሪ፣ ቦቅቧቃ…› እየተባሉ ነበር – ለብዙ አሠርት ዓመታት፡፡ ዛሬና አሁን የግፍ ቋቱ ሲሞላ ግን አሁን እያየን ያለነውን እያየን ነው፡፡ እኛም እንደነሱ ለ30 እና 40 ዓመታት ተኝተን እንክረም ለማለት ፈልጌ እንዳልሆነ ግን ከብዕረ ውሃየ መገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የእስካሁኑም ዕጅ ዕጅ ከማለት አልፎ እግር እግር ብሎኛል በበኩሌ፡፡ አውሬው – አፎምያን ሊሰለቅጥ የነበረው ደራጎን ግን ብዙ የደም ግብር ካላስከፈለ በቀላል የማይተወን መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ከልባዊ ጸሎት ጀምሮ ብዙ ሁለንተናዊ ሥልቶች ካልተነደፉ ነጻነትን እንዲሁ በነጻ እንደኀብስተ መና መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ ሊቢያንና ሶርያን ማየት ነው፡፡ ደራጎኖችን ለማሸነፍ ብልሃትን ይሻል፡፡ እነዚህ ጭራቆች ለማስወገድ የተፈለገውን ያህል ብልሃትን ይሻ እንጂ ጎራ እየለዩ በነገር ወንጭፍ መተጋተግን ግን አይጨምርም፡፡ ያ ለነሱ ሠርግና ምላሽ ነው፤ ይወዱታል፤ የሠለጠነ የሰው ኃይልና ሥራ ማስኬጃ በጀትም ይመድቡለታል፡፡
አሳድን እንተወውና ወደነመለስ እንምጣ ደግሞ፡፡ መለስ ለምን ሥልጣን አይለቅም? እንዳይለቅስ ምን ምን ቅድመ ሁኔታዎችን አከናውኗል? አሳድና መሰሎቹ ዓለም አቀፍ የዘውገኛነት ወይም የሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ልክፍተኞች በሙሉ ያደረጉትንና እያደረጉ ያሉትን መለስም ልቅም አድርጎ አንድም ሳትቀር አድርጓል፤ እያደረገም ነው፡፡
እዚህ ላይ በተለይ በሁለት አፋ ሠይፍ መካከል የሚገኙ የትግራይና የኤርትራ ኢትዮጵያውያን እህቶቼንና ወንድሞቼን እንዳይከፋብኝ አንድ እውነት ልናገር፡፡ በዚህ ጽሑፌ ‹ትግሬ› ስል ኀሊናቸውን በዘረኛነት መርዝ ሳይበክሉ፣ ለንዋይና ለኃላፊ ጠፊ ምድራዊ ሥልጣን ሳይንበረከኩ፣ ሀገራዊ ግዴታቸውን በተገቢው መንገድ እየተወጡ የሚገኙ ወገኖቼን አይደለም፡፡ መደባበቅ መጥፎ ነው፡፡ በስመ ትግሬ እንደዓይናችን ብሌን ልንጠብቃቸው የሚገባንን የግፈኛውን የወያኔ ሥርዓት በቻሉት መንገድ ሁሉ እየታገሉት የሚገኙ ትግርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችንን ሊያልፍ ቀን በ‹ከኑግ ጋር የተገኘሽ ሰሊጥ አብረሽ ተወቀጭ› የሰነፎች መመሪያ ልናስቀይማቸው፣ በሌላም በኩል የዘረኝነት አብሾኣቸውን ለመተው በቋፍ ላይ የሚገኙትንም ደግሞ ሃሳባቸውን ደግመው እንዲያጤኑ ልናደርግ አይገባንም፡፡ እዚህ ላይ ወያኔ ሳይሆኑ እንደኛው በተለያዩ ሥጋዊና መንፈሳዊ ችግሮች ውስጥ እያለፉ ያሉት ትግራዉያን ወገኖቻችን እኛ ትግሬ ባለመሆናችንና ኢትዮጵያዊነት ይሻለናል በማለታችን ምክንያት በገዛ ሀገራችን የምንሳደደውን ወገኖቻቸውን በመንፈስም ይሁን በተጨባጭ የትግል አጋርነት መቀላቀላቸው የግዴታ ግዴታቸው እንጂ የውዴታ ግዴታቸው እንዳልሆነ በበኩሌ ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ትግርኛ ተናጋሪ ለምሳሌ እንደ ጌታቸው ረዳ ዓይነቱ ለኢትዮጵያዊነቱ ፍጹም ሟችና የድርሻውን እየተወጣ ያለ ዜጋ ለኔ ለይነጋል በላቸው ብሎ ሳይሆን ለገዛ የጋራ እናቱ ብሎ የሚታገል መሆኑን በሙሉ ልቤ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በደስታ ጊዜ የሚይዙት በመከራ ጊዜ ደግሞ የሚለቁት የትርፍ ሰዓት መዘናጊያ እንዳልሆነና ለኢትዮጵያዊነት የመታገልን ተፈጥሮኣዊ ግን በኩራት የማያንጠባርር ዕጣ ፋንታ ሰጪና ተቀባይ የለም እያልኩ ነው ባጭሩ፡፡ የአሁኑን ብኑን ዘመን አያድርገውና ትግራይ እኮ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊት ነበረች፡፡ እስከማስታውሰው ድረስ ከማንም ሌላ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ በተለዬ፣ አስከሬን በኢትዮጵያ ባንዴራ ተሸፍኖና መጽሐፍ ቅዱስ ራስጌው ላይ ተቀምጦ ወደ ወደመቃብር የሚሄድባት ክፍለ ሀገር ትግራይ ነበረች፤ የአሁኑን አታስዋሹኝ አላውቅም፡፡
ዛሬ ታዲያ ምን ገባብንና ልዩነት ተፈጠረ? አሁንማ የዲያቢሎስ ምሣር የሆነው ወያኔ ተሰነቀረብንና እንዲህ ሆንን፡- አዲስ አበባ ላይ ባይኔ በብረቱ እያየሁት ያለሁትን ስለሆነ የምናገረው አይዘግንናችሁ -በተለይ ትግርኛ ተናጋሪ የሆናችሁ በውጪ ሀገራት የምትኖሩ ወገኖቼ ትግስታችሁን ተንበርክኬ እለምናለሁ፡፡
ወደ መከላከያ ሚኒስቴር የትኛውም ሥፍር ሂዱና ውስጠኛው ክፍል ድረስ ዝለቁ፤፡ ካለ ትግሬ አታዩም፡፡ የትኛውም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሂዱ እዚያም ያው ነው፤ መሽቆጥቆጣቸው አንጀታችሁን የሚበላው የሌሎች ዘውጎች ሰዎች ቅስማቸው ስብር ብሎ እዚያና እዚህ ተጨብጠው ከምታገኗቸው ሌላ በአንደና ዜጋነት ትልቅ የመኮፈስ ስሜት ሲንጎራደዱና ሲፈልጡ ሲቆርጡ የምታዩዋቸው ወያኔ ትግሬዎች ናቸው፡፡ ሌላ ወንበር ያለውም ቢሆን እንኳ በራሱ አይወስንም- ትግሬ አለቃውን ማማከር አለበት፡፡ በነገራችን ላይ ቀደም ሲል በአንድ የጨዋታ ማዕድ ላይ የተቋደስኩትን ዝነኛ ወያኔያዊ ጀብድ ልንገራችሁ፡፡ ሲግናል ውስጥ አንዲት የአንድ መኮንን ሚስት አለች፡፡ ሌሎች ሴቶች በትግርኛ ያናግሯታል፡፡ ትግርኛ እንደማታውቅ ትገልጻለች፡፡ ትግርኛ ባለመቻሏ በሳቅ ያስካኩባታል፤ በጣምም ይገረማሉ፡፡ እንዴት በዚያ ግቢ ልትገኝ እንደቻለችም በመደነቅ ይጠይቋታል፡፡ በባሏ ምክንያት እንደሆነ ነገረቻቸው፡፡ ይህን ስል ከሌላው ዘውግ የጦር መኮንን የሆነ አይኖርም ከሚል አይደለም፡፡ ይኖራል፡፡ ነገር ግን መኖር አትበሉት፡፡ በየጊዜው በሚደረግበት ስለላና ቁጥጥር ሰውነቱ እያለቀና ሙዳ ሙዳ ሥጋ እየቀነሰ ነው እሚኖር – መኖር ተብሎ፤ ሌላ ሥራ የለማ! በሌላም መሥሪያ ቤቶች ሁኔታው ከዚህ ቢብስ እንጂ ያው ነው፡፡ ለይስሙላ ከሌሎች ዘውጎች ሆዳቸውን ብቻ የሚወዱ ሰዎች በአነስተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ይቀመጣሉ – በትልቅም ሊሆን ይችላል፤ አይሠሩበትም እንጂ፡፡ ለታይታዊው የጎሣ ተዋፅዖ ፍጆታ ነው – ለድራማ ብቻ፡፡ ከላዩ ወይም ከጎኑ ግን ትግሬ በግድ መኖር አለበት፡፡ ትግሬ ስል ወያኔም ማለቴ ነው፡፡ ወያኔ ስል ደግሞ የተጋቦትም ስላለ ስሜቴን በተሟላ ሁኔታ አይገልጽልኝም፡፡ እንጂ የጎንደርን፣ የጎጃምን፣ የወሎንና የሸዋን ሜዳና ተራራዎች አቋርጠው አዲስ አበባ የገቡት በትግሬው(የኤርትራ ትግሬ) በረከት የሚመራው በጀንፈሉ ኢህዲንና በየዋሁ ሕዝብ አጋዥነት አይደለምን? ኢትዮጵያ እኮ ትንግርተኛ ሀገር ናት፡፡ በሬ ካራጁ እንዲሉ ወያኔን ከትግራይ አዝሎ ወደመሃል ሸዋ ያመጣት በስድብና በሥውር የዘር ማጥፊያ ዘዴ ዕልቂቱ በወያኔ የተቀነባበረለት አማራው ራሱ መቼስ ቢሆን ለዘነጋ ይችላልን? ቢያንስ ቢያንስ ከመጥፋት ራሱን እዬተከላከለ ግን ለራሱ ጥፋትና ውድመት ከሼረኞች ጋር መተባበሩን ቢተው ኖሮ እኮ አማራውም ሆነ ሌላው ኢትዮጵያዊ አሁን ተያይዞ ከማለቅ ይድን ነበር፡፡ ግን ዕውቀት እሚገኝ በሃምሳ ገንዘብ እሚገኝ በሠላሣ እንደሚባለው ሆነና ሁሉም ፀፀቱን ብቻ ታቅፎ ቀረ፡፡ ለበጎ ነው ይሁን ግዴለም፡፡ ለወደፊቱ ብዙ እንማርበታለን – ለዚያውም ‹ወደፊት› የሚባል ነገር ካለን፡፡
ለይምሰል በሚኒስትርነት ቦታ ላይ የምታገኙትን ትግሬ ያልሆነ ሰው ‹ሂድና ሌላህን ብላ› በሉት፤ ውሸት ነው፡፡ ዘበኛና ጽዳት የሆኑት ትግሬ ወያኔዎች ጎይታይ እምበይተይ ብሎ አስኪሰግድ ያስደገድጉታል – በግልጽ፡፡ ‹አማሮችን እንዳያንሠራሩ አድርገን አርቀን ቀብረናቸዋል› የሚል የ‹ኢትዮጵያ› ኤታማዦር በሚገኝባት ጉደኛ ሀገር ውስጥ ትግሬ ዘበኛ አማራ ሚኒስትርን ቢያንቆራጥጥ ከላይ ከአናት ጀምሮ አይዞህ ባይ እስካለው ድረስ ይሾም ይሸለማል እንጂ ሌሎችን ማሽቆጥቆጡን እንዲተው ሃይ የሚለው የለም፡፡ ትግሬ ወታደር ትግሬ ያልሆነ ዜጋ ቢገድል ቦታ ይቀየርለታል እንጂ ዝምቡን እሽ የሚለው እንደማይኖር ከውስጥ አዋቂዎች ስትሰማ ሰው ሆነህ መፈጠርህ ራሱ ያስጠላሃል፤ ቋንቋን ጨምሮ በብዙ ነገር በሚመሳሰሉ ነገደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይህን መሳይ ዘግናኝ ክስተት መፈጸሙን ስታውቅ ምነው ዜግነቴ የሌላ ሀገር በሆነ ብለህ ትመኛለህ፡፡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እሚያስገኙ የሀገሪቱ ዋና ዋና መሥሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በትግራዉያን ቁጥጥር ሥር ናቸው፤ ከሁለተኛ ዜጎች ውስጥ የመንግሥታዊ መ/ቤቶች የቦርድ ሊቃነ መናብርትና አባላት ሆነው የምታገኘው በቁጥር ነው – በዚህኛው ወይም በዚያኛው መንገድ ንክኪ የሆኑ፡፡ ፀረ ሙስና የተባለውን ጨምሮ ብዙ መ/ቤቶች ቁጭ በሉ ናቸው፡፡ የፈለጉትን ለመጥቀምና ያልፈለጉትን ለመጉዳት በአንድ አዳር ሳይቀር የሚኒስቴር መ/ቤት ፈጥረው ሊያድሩ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ልብ አድርጉ – የምድር ጦሩ፣ የሰማይ ጦሩ፣ የአየር ጦሩ፣ ፖሊሱ፣ ደኅንነቱ፣ ታጣቂ ሲቪሉ፣ ቤተ መንግሥት ዘቡ፣ የአየር መንገድ ጠባቂው፣… ሁሉም በአንድ የትግራይ ዘውግ ተጠፍንጎ በተያዘበት ሁኔታ መለስ ማንን ሊፈራ ይችላል? እውነት ነው ማንንም! ግን የሁሉም ትብታብ መፍረሻ ስላለው ያንን ነው መፍራት፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ደግሞ ያ ጊዜ ሳይመጣና እንደነሊቢያ ጉድ ሳይሠራን ከአሁኑ በተባበር ክንድ የደም ጎርፉን ወደ ልማት ጎርፍነት እንለውተው ነው፡፡ አይነጋምን ትተሸ ይነጋልን ባሰብሽ ነው፡፡ ይህንን ሀገራዊ አሳዛኝ እውነት እያወቁ አለመናገር ጥፋት ይመስለኛል፡፡ ቁስላችን ይፍረጥረጥና መድሐኒቱ ይፈለግለት፡፡ ብዙ የሚገማ ቁስል በመካከላችን ይገኛል፤ አሁን አሁን ሽታውና ግማቱ አላስቆም አላስቀምጥ ብሎን እምንሠራውን አሳጥቶናል፡፡
ከዚህ ሥርዓት ታዲያ አንድም ቢሆን የአማራ ከፍተኛ መኮንን እንዲገኝ ትጠብቃላችሁ? እንዴት ብሎ? ይሙት በቃ ተፈርዶበት? በየጊዜው የወያኔ መቀለጃና ማሽሟጠጫ ሊሆን? በነጄኔራል ተፈራና በሌሎቹ አማሮች የደረሰውን እኔን ያየህ ተቀጣ ዓይነት ኢሰብኣዊ የሥቃይ ውርጅብኝና የሚዘገንን ውርደት እያዬ? የሚሠራውን ቲያትር እየተመለከተ በተለይ በወታደርነት ከወያኔ ጋር የተሠለፈ ሰው ተራው እስኪደርስ ይቆይ እንደሆነ እንጂ ተዋርዶ ነው የሚቀር፡፡ ሆዳም ከሆነ እርግጥ ነው የተቻለውን ቦጭቆ ዘወር ሊል ይችላል፤ ሊያውም በክትትል ሥር ሆኖ፡፡ ካለ ትግሬ የማይገባባቸው መሥሪያ ቤቶች መኖራቸውንስ ስንቶቻችን እንሆን እምናውቅ? ኢንሳ አንዱ ነው – ነጻ ሚዲያን እሚያፍነው፡፡ (INSA)
ንግዱንና ፖለቲካውን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያሰደፍር ሁኔታ የተቆጣጠሩት ትግሬዎች ናቸው – የሥርዓቱ ተጠቃሚ ትግሬዎች፡፡ ተጠቃሚ ያልሆናችሁ ትግሬዎች እንደኔው ኩሩ፤ ዋጋችሁ በነገይቷ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡ ነገን ልናያት ባይቻለን እንኳን ከቆሸሸ ኀሊና ይልቅ ንጹሕ ኅሊናን ይዞ ወደማይቀርበቱ መሄድ የገዛ ትውልድን ከማሳፈር ይታደጋል፡፡ የነአፄ ኃይለ ሥላሤና የነመንግሥቱ ኃጢያትና ወንጀል ከነመለስ ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ የሰማይንና የምድርን ያህላል፡፡ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ በመንግሥት ሠራተኝነት ከዱሮ ሥርዓቶች ባንደኛው ስቀጠር አለቃየ ባጋጣሚ ትግሬ ነበር፤ ወደሌላ ቦታ ስዛወርም አለቃየ እንዲሁ ባጋጣሚ ትግሬ ሆነ፡፡ የሚገርመው ነገር እኔ ምን እንደሆንኩ አላውቅም፤ የአለቆቼ ትግሬነትም አላስኮራኝም ወይም አላሳፈረኝም፤ የዘውግ ዕውቀቱም ሆነ ግንዛቤው እንዳሁኑ ስላልነበር፡፡ አሁን ግን አለቆች ትግሬዎች መሆናቸው ፀሓይ የሞቀው ሃቅ ከመሆኑም በተጨማሪ አንተ ትግሬ ካልሆንክ በሥነ ልቦናህ ተጨማድደህና ተኮማትረህ አንገትህን ደፍተህ ዕጆችህን የኋሊት አጣምረህ ነው አለቃህን እምታነጋግር፡፡ የትግሬው ወያኔ ኩራትና ትዕቢት ደግሞ ቅስምህን ይሰብራል፡፡ ከዚህም ታዲያ ስደትን ሲያንስም ለምኖ መብላትን ልትመኝ ትችላለህ፡፡ እውነት ነው! ፍርድ ቤቶች የተሞሉት፣ ሀኪም ቤቶች የተሞሉት፣ በከተሞች የሚታዩ ትላልቅ ሕንጻዎች የተያዙት፣ ምን አለፋችሁ ሁሉም በትግሬዎች ለትግሬዎች ነው፡፡ ቁርጥህን ዕወቅ ወዳጄ በአሁኑ ወቅት ሀገር የለህም፡፡ ሆድህን ከሞላህ በሌላው እንደእኩዮችህ ሌሎች እንስሳት በድብቅ እንደአህያ እያናፋህ ወይ እንደአንበሣ እያገሣህ ወይ ውሻ እየጮህክ መኖር ነው፡፡
አዲስ አበባም ሆነ ሌላ ቦታ የትም ሂድ፡፡ ቡና ቤትም ግባ፡፡ ትላልቅ ሆቴሎችም በድንገት ዘው በል፡፡ ብሔራዊ ቋንቋ ትግርኛ እስኪመስልህ ልትደነግጥ ትችላለህ፤ የምለው ግልጽ ይሁንልኝ፤ የመደንገጥህ መንስኤ ትግርኛ ብሔራዊ ቋንቋ መሆኑ አይደለም – ያ አያስከፋም፤ አያስደነግጥምም፡፡ ችግሩ ሌላውን ሕዝብ ምን ዋጠው? ነው ጥያቄው፡፡ ሌላውና ብዙውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚወክል የሚነገርለት ወገንስ አይዝናናም? አይበላም? አይጠጣም? በትምህርት ቤቶች ግቡና የነማን ልጆች በጥሩ ትምህርት ቤቶች እንደሚማሩ እዩ፡፡ በዩኒቨርስቲዎችም ግቡ፡፡ ያለማጋነን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የውድ ክፍያ ት/ቤቶች ተማሪዎች የትግሬ ልጆች ናቸው፡፡ ጥያቄው ለምን ተማሩ አይደለም፡፡ ይማሩ ወገኖቼ ናቸው፡፡ ግን ሌላውስ? ሌሎች ደንቁረው እንዲቀሩና በረንዳ እንዲያሞቁ ሤራ የሚሸረበው ለምንድነው? የንግድ ተቋማትን ስናይ ሌላው ወገን በግብርና በቀረጥ፣ በጉልበትና በዘዴ ወደውጪ እየተገፋ ሳለ፣ ትግሬነቱን እስከጥግ ሊጠቀምበት የሚፈልግ ትግሬ ዜጋ በህግ ሽፋን እዬተደገፈ ካለግብርና ቀረጥ አዬር ባየር እየነገደ በአንድ ሌሊት ይከብራል – ይሄ ጭንቅላት ብሎ ነገር ጭራሽ ያልፈጠረበት የወያኔ ጀሌ፡፡ ይሄ የደም ዋጋ በ20 ዓመት እንኳን ተከፍሎ አያልቅም እንዴ? ለትውልድ እየተላለፈስ ሕዝብን ማሰቃየት አለበት እንዴ? ትግሬ አለመሆን በወንጀል የሚያስቀጣ ያህል ሆንዋል እኮ በሀገራችን፡፡ ምን ይብቃን እንግዲህ? ‹እናቴ ስትወልደኝ መቼ አማከረችኝ…› የሚለው ዘፈን የማን ነበር? አዎ፣ እናቶቻችን ሲወልዱን ቀድመው አማክረውን ቢሆኑ ኖሮ ማን ጎንደርና ጎጃም ወይም ወለጋና ኢሉባቦር ይወለድ ነበር — እዚያችው አድዋና ሽሬ እንተፋፈጋት ነበር እንጂ! ብቻ … ብዙ ችግር፣ በጣም ብዙ ችግር፤ እጅግ በጣም ብዙ ችግር አለብን ወገኖቼ፡፡ በምን ታጥበን ከዚህ ሀገራችንን ካጨቀያት ወረርሽኝ እንደምንጸዳ እንጃልን፡፡ ቀበሌ ብትሄዱ ከመዝናኛው አቅም ከሞላ ጎደል በትግሬዎች ነው የተያዘው፡፡ በየትኛውም የመስተዳድር ቢሮ ስማቸው የኦሮሞ ወይም የአማራ ሊሆን ይችላል እንጂ የሚያዙት የሚናዙት እነሱው ናቸው፡፡ ሠራተኞች ለመሥሪያ ቤታቸው ጥያቄ ለማቅረብ ቢፈልጉ ተጠሪ አድርገው የሚመርጡት ትግሬዎችን ነው – ጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ፡፡ አለበለዚያ በነፍጠኝነት ወይም በኦነግነት አስጠርጥሮ ዘብጥያ ሊያስወርድ ይችላል፡፡ ቡና ቤቶች ባቅማቸው ቤታቸው እንዲከበር የትግርኛ ዘፈን ነው የሚከፍቱት፡፡ በትግሬዎች ተፅዕኖ ምክንያት ትግሬ ሳይሆን ትግሬ የሆነ አስመሳይ ወይም ፈርጅድ ‹ትግሬ› ከተሞቻችንን አጥለቅልቆታል – ያሳፍራል፡፡ ሰው ከመሬት ተነስቶ ‹ትግሬ ነኝ› ሲል ትሰማለህ – የምታውቀው አማራ ወይም ኦሮሞ፡፡ ነገሩ ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ ዓይነት መሆኑ ነው፡፡
በሃይማቱም ይሄው ነው፡፡ አማራ ከሆንክ የሚያስቀርብህ የለም፤ ብትቀርብም በከፍተኛ የስለላ መረብ ውስጥ ትገባና እስትንፋስህ ሁሉ በየቀኑ ትለካለች፡፡ የደብር አለቃ ለመሆን ከአድዋ መምጣት ወይም የብፁዕ አባታችንን እግር መላስ ሳይኖርብህ አይቀርም፤ ብዙ መማርህ አይጠቅምህም ብቻ ሳይሆን ይጎዳሃል፡፡ እግዚአብሔር ተረስቶ ሥጋዊ ፍላጎትና ምኞት እውን የሚደረግባት ሆናለች ቤተ ክርስቲያን፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ይዞታዎች ስትሄድ እዚያም ብሔራዊ ቋንቋችን ትግርኛ የሆነ ያህል ይሰማሃል፡፡ እንዲህ እያልኩ ያለሁት ስለእውነት ብዬ እንጂ ማንንም ለመጉዳት ወይም ለመጥቀም አይደለም፡፡ ይልቁንም ራሴን እያሰቃየሁ ነው – መናገር የማይገባኝንና በሽፍን መያዝ የነበረብኝን የወንድምና የእህቶቼን ነውር እኔም በበኩሌ ለማውጣት በመድፈሬ፤ ግን በሌላ አቅጣጫ ሳየው የሚያደርጉትን ያሳጣቸው ራሳቸው ልበ-ዕውራኑ ያላፈሩ እኔን ምን ያሳፍረኛል? ብዬ እጽናናለሁ፡፡ እዚህ አካባቢ አንድ ጥያቄ በአእምሮህ ሊያጭር ይችላል፤ ‹ለመሆኑ ይሄን ሁሉ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታ በትግሬ ወያኔ ለመሙላት ዝግጅቱ መቼ ይሆን የጀመረው›? መልሱን ደግሞ በቀላሉ ታገኘዋለህ፡፡ ‹የሥልጣን ቦታዎቹ በታማኝ ትግሬዎች ይሞሉ እንጂ የባለሥልጣኖቹ የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ በጭራሽ አስፈላጊ አይደለም› የሚለው የዝግጅቱን አላስፈላጊነት ያሳይሃል፡፡ አንድ የሥራ ሂደት ባለቤት ደረቱን ነፍቶ ለሚናገረው ነገር አስቀያሚነት ወይም ትክክለኝነት ሳይጨነቅ እንደ ልቡ ካነጋገረህ ያ ሰው የትግሬ ወያኔ መሆኑን ለመረዳት ተጨማሪ ማረጋገጫ አያስፈልግህም፡፡ በኢትዮጵያዊነቴ እንደዚህ ዘመን አፍሬ የማላውቅ መሆኔን የምገልጽላችሁ የሀፍረቴን ሸማ አንድዬ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አውልቆ እንዲጥልልኝና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገኔ በሀገሩ የጋራ ባለቤትነት ኮርቶ በእኩልነት የሚኖርባት ሀገር እንዲኖረው በጽኑ በመመኘትና በመጸለይም ጭምር ነው፡፡ ይህችን ኢትዮጵያ ሳላይ በእናቴ ማሕፀን ውስጥ ያኔ ወላጅ እናቴ ቅሪት እንዳለች ውኃ ሆኜ ብቀር ኖሮ ምንኛ በታደልኩ ነበር? የማወቅ መጥፎነት እዚህ ላይ ነው፡፡ አንዳንዴ አለማወቅን የመሰለ ፀጋ የለም፡፡ በውጪ ያላችሁ ታድላችሁ! ቢያንስ እንደዚህ ዓይነት አድልኦዎችንና ሸውራራ የትግሬው መንግሥት አሠራሮችን እየተመለከታችሁ በየዕለቱ ህሊናችሁ አያለቅስም፡፡ እኛስ ዕንባም ባቅሙ እዬተጓደደብን በደረቁ ለማልቀስ ተገድደናል፡፡
እንደማጠቃለያ – በዚህ አያያዝ በወያኔ ትግሬ በወለድ አገድነት የተጠረነፈች ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ምን ማድረግ ያስፈልጋል? የሚለው ትልቅ ጥያቄ ሁላችንንም ከዳር እዳር ሊያነጋግረን ይገባል – ይሄን እዚያ ማዶና እዚህ ማዶ ሆኖ በከንቱና ለትዝብት ዓምድ የሚዲያ ፍጆታ በሚውል መልኩ መነታረኩን ትተን፡፡ ለዚህ ጥያቄ በተለይ ከትግርኛ ተናጋሪ ጤነኛ ኢትዮጵያውያን ሁነኛ ምላሸ ብንጠብቅ ሞኝነት አይመስለኝም፡፡ ሌላው ሕዝብ በሀፍረትና በኑሮ ውድነት አንገቱን ደፍቶ እየኖረ ነው – መኖር ተብሎ፤ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብም እንደዚሁ በተወሰነ ደረጃ አንዳንዶች ባልተገባ መንገድ ሊጠቀሙበት ከሚፈልጉት የሥነ ልቦና እርካታ ውጪ ይህ ነው የሚባል የረባ ጠቀሜታ ያገኙ አይመስለኝምና ብዙዎቻችን በአንድ የሥቃይ ቅርጫት ውስጥ የምንገኝ መሆናችንን አምናለሁ፡፡ መላው የኢትዮጵያ የተረገጠ ሕዝብ አንገቱን ቀና የሚያደርግበት ጊዜ መምጣቱ ግን በፍጹም የማይቀር ነው፡፡ እሾህን በእሾህ መንቀል የነበረና ያለ በመሆኑ የትግራይ ሕዝብ ከአንጀቱ ካለቀሰ የወያኔ ዕድሜ አጭር ነው፡፡ ወያኔ ከትግራዉያን ያለው ድጋፍ ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ዓሣውን ለመያዝ ባሕሩም የበኩልን አስተዋፅዖ ሊያደርግ ይጠበቅበታል፡፡ ያኔ የትግሉ ዘመንና የመስዋዕትነቱ መጠንም ይቀንሳል፡፡ ለፀረ-ዳግማይ ወያኔ የነጻነት ትግል የትግራይ ሕዝብ ያለው ድርሻ በመጥፎና ማፈሪያ የጋራ ልጆቻችን የጠየመውን የዚህችን የኢትዮጵያዊነት እምብርት ታላቅ ክፍለ ሀገር የቅርብ ጊዜ ታሪክ እስከማደስ የሚደርስ በጎ ጎን አለው፡፡ ብዙ ማለት እችል ነበር ግን ለጊዜው ይብቃኝ፡፡ እየሆነ ከሚታየው አንጻር ምንም አልተናገርኩም ማለት እችላለሁ፡፡ ሌሎችም አግዙኝና እውነቱን ዐውቀን ለወደፊቱ የሚበጀንን መምረጥ እንዲያስችሉን በግልጥ የሚታዩና በሥውር የሚካሄዱ ወያኔያዊ የግፍ አሠራሮችን እያጋለጥን በታሪክ ስንክሳር እናስመዝግባቸው፡፡ ዛሬ ያልፋል፤ ነገም ሌላ ቀን ነው – እንደሚባለውና እንደውነቱም፡፡
በመጨረሻየ መጨረሻ ጥሩዎቹን የትግራይ ተወላጆች ደግሜ ይቅርታ እንድል ይፈቀድልኝ፡፡ ከላይ የጠቀስኩት አበሳና በኢትዮጵያ ላይ እየወረደ ያለው መቅሰፍት በሁሉም የትግራይ ሕዝብ ምክንያት ሳይሆን አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ሕዝባዊውን ድል ወደቤተሰባዊና ቡድናዊ የዘውግ አደረጃጀት በለወጡ የእርግማን ፍሬዎች አማካይነት ነው፡፡ ስለዚህ የእነሱን ገመና ለመናገር ያደረግሁት በጣም ኢምንት ጥረት ደጋጎቹን እንዳያስቀይምብኝ አደራ እላለሁ፡፡ በበኩሌ በሁለት አጣብቂኞች መካከል ላላችሁ ወገኖቼ ያለኝ አዘኔታ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ነገረ ሥራችን ላም እሳት ወለደች ዓይነት ነው፡፡ ፈጣሪ የሚያፈቃቅር ደግ ዘመን ያምጣልን፡፡