ይድረስ ብዙ ለኖሩ ፖለቲከኞቻችን (ሶሎሞን አብርሃም)

አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ የምታሳዝን ሃገር ሆናለች። በነፃነትና በሰላም ተጠብቆ የመኖር መብታችን ተከብሮ ባያውቅም አሁን ደግሞ ያለገደብ ተጥሷል። ሰዎች በአመለካከታቸው ብቻ ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ፣ ሴቶች የደፈራሉ፣ መኖር ይከለከላሉ፣ በህግ ፊት እኩል አይደሉም፣ ፍትህ ተጓድሏል። ገዢዎቻችን አንብበው የማያውቅትን ህገ መንግስት ማገላበጥ የሚጀምሩት የዜጎችን መብት ለመርገጥ ብቻ መሆኑ እንደተባለው ህገመንግስቱን ህገ አራዊት አስመስሎታል። የሰው ልጅ ሲወለድ ነፃና በክብር፣ በመብት እኩልነት ያለው ነው የሚለውን ድንጋጌ ረስተዋል። ነፃነት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ የሚባሉት መሰረታዊ ነገሮች በኢትዮጵያ ምድር ተሳክተው አያውቁም።

በመስከረም 4 1967 በሰባት ሰዎች እንደተመሰረተ የሚነገርለት ማህበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ ከ6 ወራት ቆይታ ቡሃላ በየካቲት ወር 1967 አሁን በኢትዮጵያውያን ላይ ተንደላቆ የተቀመጠውን ሕውሓትን ፈጠረ። ዛሬ ሃያል የሆነው ሕውሓት በ37 ዓመት ጎዞው የሚቀንሰውን ቀንሶ የሚጨምረውን ጨምሮ አሁን የምናያትን ኢትዮጵያን የመከራ ቁልቁለት ላይ እያንደረደራት ይገኛል። የት እንደምንቆም ባይታወቅም ወደ አዘቅቱ እየወረድን እንገኛለን ። ከሕውሓት መስራቾች ውስጥ እና ከዚያ ቡሃላ ድርጅቱን የተቀላቀሉት ግለሰቦች በተቃራኒው ጎራ ተሰልፈናል ከሚሉት በርከት ካሉ ውልደታቸው ከ50 አመታትና ከዚያ በላይ ከሆኑ የዚያ ትውልድ አካላት ጋር በመተባበር የአሁኒቱአን አሮጊት እናት ኢትዮጵያን ፈጥረውልናል።

ይህች አገር በነዚህ በሁለት ጎራ በተሰለፉ የአንድ ዘመን ትውልዶች እየተቀለደባት ይህው እስከዛሬ አለች። እነዚህ ሰዎች ዘርፈ ብዙ ችግረቻችን አያሳስባቸውም። አንዱ አንዱን ለመጣል ብቻ ሲተጉ እዚህ ደርሰዋል። መድህን የሚሆንላት አጥታ የምትንገላታው አገራችን የነዚህን ክፉ ትውልዶች ማለፍ መጠበቅ ግድ የሆነባት ይመስላል። እነሱ ካልሞቱ አገራችን ከገባችበት ችግር ከቶ የምትውጣ አይደለችም። ክፉ ሰው ደግሞ ቶሎ አይሞትም ስለዚህ የነዚያን ያረጁ ትውልዶችን ያረጅ አክያሄድና የጃጀ አስተሳሰብ ወይ እስኪሞቱ ወይ አንድ መድህን መጥቶ እስከሚያስወግድልን የTom and Jerry አይንነት ፖለቲካቸውን ይቀጥላሉ ማለት ነው።

ቶምና ጄሪ መቼም ለማይረባ ነገር ምን ያህል ቤት እንደሚያወድሙ ሳናይ የቀረን አይመስለኝም። የኛም ፖለቲከኞች እንደዚያ ናቸው። እነሱ የማይረባ ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም ስለሚያጠፉት፣ ስለሚያውድሙት ሃገር እይጨነቁም። ይልቁንም አንዱ አንዱን እበልጣለሁ፣ አንተ አታውቅም እኔ አውቃለሁ በሚል አጉል አስተሳሰብ ጊዜ የሰጠው ሌላውን የማዋረድ፣ የማሳቀል፣ የማሳፈር ፖለቲካ ማራመድ አገራችንን ማለቂያ ለሌለው ርሃብና ችግር ውስጥ ከተዋት ይገኛሉ።
የሚገርመው ደግሞ በነዚህ ትውልዶች ካለኔ አዋቂ የለም በሚል ትምክህት ለሁለት ያልሰነጠቁት የፖለቲካ ድርጅት ማግኘት መክበዱ። ሕውሓት ሲሰነጠቅ፣ ኦነግ ሲሰነጠቅ፣ ኦብኮ ሲሰነጠቅ፣ መአሕድ ሲሰነጣጠቅ፣ መኢአድ ሲሰነጠቅ፣ ኤዴፓ ሲሰነጠቅ፣ ቅንጅት ሲሰነጠቅ፣ አንድነት ሲሰነጠቅ…ሁሉንም ችግር ፈጣሪዎች እነሱ ሲሆኑ ምክንያታቸው የኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ችግሮች አይደሉም። አንዱ ቶም አንዱ ጄሪ ሆነው አንዱ አንዱን ለመብለጥ፣ ለማጥፋት የሚደረግ ፖለቲካ ፉክክር እንጂ።

እነዚህ ትውልዶች የሚያስደስታቸው ነገር ደግሞ ይገርማል። ሰሞኑን በፍትህ ጋዜጣ ላይ ወደ አደባባይ ብቅ ያሉት አንጋፋ የሚባሉ የጓዳ ፖለቲከኞቻችን አስቲ እንዴት እንደተንጫጩ ተመልካቱ። ስብሓት ነጋ በጨረፍታ ለአቦይ ስብሃት አዲስ አይደለም ተስፋዬ ገብረአብ መደበሪያ አድርጉአቸው ነበር ከጋዜጠኛ ከተመስገን በፊት። ታዲይ አቦይ ተስፋዬን ትተው ተመስገንን ለመቆጣት መፍጨርጨራቸው ምን ለማለት ይሆን። በስራ ዘመናቸው የፈጠሩአትን ኢትዮጵያን እንደሆነ እያየናት ነው ታዲያ ከስራ ከተገለሉ ወዲያ ምነው ባይጨቀጭቁን። አገሪቱን እኮ እንዴት እንዳስትዳደርዋት አሳይተውናል፣ የእውቀታቸውን ልክ አይተናል፣ ታዲያ ዛሬም የኔ ሃሳብ ለምን ተነካ፣ ዛሬም ተነካሁ፣ ዛሬም ስድብ ዛሬም ሁሉን አውቃለሁ? ሲጀመር አንደ ስብሓት ነጋ አይነት ሰው ጡረታ ሲወጣ የበጎ አድራጊ ድርጅት አቋቁሞ ወይ ቢጤዎቹን አረጋውያንን ይጦራል ወይ ወላጅ አልባ ሕፃናትን ይረዳል ወይ ደግሞ የካበተ እውቀቱን ለሌሎች ለማካፈል ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በማስተማርና በምርምር በመስራት ጊዜውን ለበጎ አድራጎት ያውለዋል።

አንድ ጡረታ የወጣ ሰው ይህን ማድረግ ካልቻለ በቂ ግዜ ስላለው ወደ አእምሮው ተመልሶ እኛ እያልን ያለነውን ቁምነገር በጥሞና ማድመጥ ይገባዋል። አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን በርጋታ መመልከት ያስፈልገዋል። ስህተቱ ከገባው ንስሃ መግባት ወይም ስህተቱን መገንዘብ ካልተቻለ ደግሞ የወደደውን እየበላ እና እየጠጣ ጥጉን የዞ እለተ ሞቱን መጠበቅ ይገባዋል እንጂ አሁንም የሃገሪቱን ጉዳዮች አቦካለሁ ማለት አግባብ አይደለም። ጡረታ ላልወጡትም ቢሆን 50 አመት እና ከዚያ በላይ መኖር ቀላል አይደለም ያለቁምነገር መሆኑ ቢያበሳጭም ዛሬም አልረፈደም እስቲ ትምክህታችሁን ተውና ገበሬውን አስቡ ትውልዱ የሚለውን አድምጡ።

እኛ እያልን ያለነው እስከዛሬ በሃገሪቱ ላይ የልባችሁን ሰራችሁ። እየተቡአደናችሁ ስትደባደቡ ኢትዮጵያችን ፈራረሰች። የስራችሁም ውጤት እንዲህ ሆነ።

ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ኢንሸስትመንትን ለመሳብ ካልቻሉ ጥቂት አገሮች ተርታ ተመደበች። አቶ መለስና ተሿሚዎቻቸው ኢንሸስትመንትን ለመሳብ በሚል ሰበብ ወደተለያዩ አገሮች የሚያዝናና እና ውድ የሆነ ጉብኝት አድርገዋል። የተሳካላቸው ነገር ባይኖርም ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝንና በብዙ ህገሮች ተሞክሮ ያልተሳካ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ይዘው ተመልሰዋል፣ እንደ አበባ፣ ለም መሬትን ለውጭ ባለሃብት መርካሽ ዋጋ መሸጥን እና ጥቂት ኮስማና የኢንቨስትማንት ዘርፎችን።

መንግስት መጭው ትውልድ ከፍሎ የማይጨርሰው ብድር በየጊዜው ይበደራል። በተጨማሪም ከለጋሽ አገሮች በርከት ያለ ገንዘብ ለልማት በሚል ሰበብ ይቀበላል። ይህ ሁሉ ገንዘብ ግን ለአገራዊ ልማት መዋሉ ቀርቶ ለመንግስት በለስልጣናት ኑሮ ማደላደያ እና ለስልጣናቸው እድሜ ማራዘሚያ ጉልበት አድርገው መጠቀማቸውን ቀጥለዋል።
አገሪቱ ውስጥ በሰፈነው መልካም ያልሆን አስተዳደር እና ሙስና ምክንያት ኢኮኖሚው ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር አቃተው። አገሪቱ ላይ በተንሰራፋው አስተዳደራዊ ብልሹነት ምክንያት ዜጎች የራሳቸውን የስራ እድል በነፃነት መፍጠር አልቻሉም። ስለሆነም ኢትዮጵያውያን አገራቸው ላይ መኖርን ናቁ እንደ ውርደት መቁጠር ጀመሩ። ለዚህም ይመስላል ያገኟትን ቀዳዳ እየተጠቀሙ መሰደድ የመጀመሪያው ምርጫቸው ሆነ። ስደት መከራ ነውና ብዙዎች በመከራ ውስጥ ተዘፈቁ፣ ከፊሎቹ ያሰቡት ሳይሳካ መራራዋን ሞት ቀመሱ፣ ብዙዎች ታሰሩ፣ ተደበደቡ፣ ተደፈሩ፣ ደማቸውን አፈሰሱ፣ አገር አንደሌላቸውም ተቆጠሩ። የሚገርመው ነገር መንግስት ተሰደው የሚኖሩ ዜጎችን እንደስኬታማ በመቁጠር ብሔራዊ ጀግና እያለ በሕዝቡ ውስጥ ስደትን ያበረታታል። ሕዝቡም ስደትን የመጀመሪያው አላማው አድርጎ አገሪቱን ጥሎ የሚሄድበትን መንገድ መፈለጉን የቀጥላል።

የተማረውም፣ ያልተማረውም፣ ገበሬውም፣ ነጋዴውም ለምን አልሰደድ ይላል። ጥቂቶች ተባብረው ከማሕበረሰባችን ሁለንተናዊ ማንነት ጋር የሚጣረስ የንግድ ስርአት ዘርግተዋል። ይህ ስርዓት አብዛኛውን የንግዱን ማሕበረሰብ ክፍል የበይ ተመልካች ሲያደርገው ይህ ሂደትም በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል። የዋጋ ግሽበቱ በሁሉም ዘርፍ ጨምሯል፣ ባሳለፍነው ወር እንኳን በትራንስፖርትና በመገናኛ ዘርፍ 45% ሲደርስ፣ በምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ፍጆታዎች ላይ ደግሞ በአማካኝ 50% በአንድ አመት ውስጥ ደርሱአል። በምግብ ዘርፍ ከተከሰተው ግሽበት ውስጥ በተለይ ነዘይትና በቡና ላይ የተመዘገበው ግሽበት መጣም የከፋ ነው፣ ባሳለፍናት አንድ አመት ዎስጥ ብቻ ከ 1፩0% በላይ ጭማሪ አሳይቱአል።

ይህን ግሽበት ለማቆጣጠር የአገሪቱ የምርት አቅም በጣም መጨመር ነበረበት። ይህ ግን አሁን ባለው ስርዓት ሊሆን አልቻለም። በዚህ ስርዓት ሰርቶ ማደር ቀርቱአል፣ በአቓራጭ መክበር ያሸልማል። አገራዊ ጀግና ያስብላል። መንግስትን ከፓርቲ፣ የሕዝብን ንብረት ከፓርቲ ንብረት መለየት እስኪያቅተን ተደናግረናል፣ ገንዘብ በማባከን ከአፍሪካ ቀዳሚዎች ሆነናል፣ የሕዝብን ሃብት ለግል ጥቅም የሚያውሉ የመንግስት ሹማምንት ጥቂት አይደሉም። አንድ የቆየ አባባል አል “Steal a little and they throw you in jail, Steal a lot and they make you a king” የሚል። በርግጥ በሙስና የተዘፈቁት ተጠቃሚዎች ሲሾሙ እንጂ ሲከሰሱ አልታየም። ነገር ግን እጃችሁ ይቆረጣል የሚባሉት ሰርቶ ለማደት የሚፍጨረጨሩት ናቸው።

እኛ እያልን ያለነው የሰራችሁ ውጤት ዘርፈ ብዙ ችግር በሃገሪቱ ላይ ስለፈጠረ ኢትይጵያውያን ስፍር ቁጥር የሌለው ችግር ውስጥ ነን ያለነው ነው። ይህ ሁሉ ችግር እያለ አንዳንዱ ስለ ዲግሪው ጥራት ሊነግረን ይፈልጋል፣ ሊላው የራሱን ወጋግራ የሚያክል ስህተት ትቶ የሰዎችን ጥቃቅን ስህተት ሊነቅስ ይሞክራል። ባጠቃላይ የዚያ ትውልድ አባላት የሰውን ሃሳብ የሚያደምጡት/ካደመጡ ማለቴ ነው/ ለመማር እና ለመታረም ሳይሆን ለመቃወም ብቻ ነው። አቦይ ስብሓት እንደነገሩን ከፕሮፌሰር መስፍን የተገኘ እውቀት ልጅ ማሳደግ መሆኑ አይገርምም? ይህንን ስብሓት ነጋ ሲነግሩን አይደንቅም። በርግጥ የፕሮፌሰር ልጆች እንደ ስብሃት ልጆች በሰው አሻንጉሊት ሲጫወቱ አላደጉም ይሆናል።
ታዲያ ይህ ሁሉ አገራዊ ችግር እንዴት ተፈጠረ ብንል ብዙ መልስ ሊኖረው ይችላል። የፖለቲከኞቻችንም አጃቢዎቻቸውም/ተቃዋሚዎችን ማለቲ ነው/ መልስ አያጡም፣ ማጣፊያ አያጥራቸውም መልሱ ግን ለገበሬው፣ ለድሃው ሕዝብ አይጠቅመውም። መልሱ ምንም ቢሆን፣ ማንም በየትኛውም ጎራ ቢሰለፍ ዞሮ ዞሮ ግን ችግሩ እናንተን ከተጠያቂነት አያድንም። ስለዚህ አሁን የሚጠቅመው ያሳለፋችሁት ከንቱ እድሜ ጎስቋላ ኢትዮጵያን ፈጥሯል፣ ብዙ የሚያግባቡን ነገሮች እያሉ በጣት የሚቆጠሩ ልዩነቶቻችን ላይ ስትሟገቱ እዚህ ደርሰናል ያሳለፍነው ዘመን አሁን ከሚቀረን ስለሚያንስ እስቲ ወደልባችን እንመለስ።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ሶሎሞን አብርሃም
[email protected]