ጉራማይሌ ሕዝብና መንግሥት በኢትዮጵያ በነጻነት ዘገዬ
ታርጋ በቀላሉ የሚወጣባት ብቸኛዋ ሀገር
በተለይ በሀገርኛ ባህል ያገባችሁ ይሄ የባህል የሠርግ ዘፈን ትዝ አይላችሁም? ‹እሸት ፣ እሸት፣ የወረት፤ እሸት ቢሉህ…የሽምብራ እንዳይመስልህ፤ እሸት ቢሉሽ… የማሽላ እንዳይመስልሽ…› ይህ ነገር በጽሑፍ ሳይሆን በዜማ ነበር የሚያምረው፤ ታዲያ ምን ዋጋ አለው – የምንገኝበት ሥፍራ ተራራቀ፡፡
ታርጋ ስልህ ታዲያ የመኪና እንዳይመስልህ፤ ታርጋ ቢሉህ የሮቢላም እንዳይመስልህ፤ ታርጋ የምልህ ከምትናገረው መካከል የሚፈልገውን ያህል ቦጨቅ ያደርግና ‹ አሃ! ለካንስ እገሌ እንዲህ ዓይነት ሰው ነው፤ ለካንስ እገሊት እንዲህ ዓይነት ሰው ኖራለች፤ ለኬ እገሌ አበሉ የዚህ ዓይነቱ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊና አባልም ነው…› የሚልህን የወጪ ቬርባል ያልፈረምክበትን ታርጋ ከሜዳ አንስቶ የሚለጥፍብህን ሰው ማለቴ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን ሥራ ፈት ሰው በቀላሉ የምታገኘው በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ታርጋ ካለአንዳች ተወራራጅ የወጪ ደረሰኝ ወይም ቫውቸር እንዲለጠፍልህ ከፈለግህ ተናግረህ ብቻ ሳይሆን ገና ከዐይነ ውኃህ በመነሣት ‹አሄሄ፣ ይሄ ሰውዬማ እንዲህ ዓይነት ሰው አይደለም እንዴ ጃል?› ብሎ አንድ ጭራሽ ያላሰብከውን ወይም ካንተ ጋርም ፈጽሞ ሊሄድ የማይችለውን የስም ታርጋ እንድትጀባ ከሻህ ወደሀገራችን ኢትዮጵያ ብቅ በልና ከብዙዎች ሰዎች ብዙ ታርጋዎችን ትከናነባለህ፤ እውነትን መናገር ገመናን እንደማውጣት ሊቆጠር አይገባም፡፡ ይልቁንስ ከዚህ አዘናጊና እጅግ ኋላቀር ባህል ተስፈንጥሮ በመውጣት ብዙው የዓለም ሕዝብ በሚተምበት የዘመናዊነት አውራ ጎዳናን መቀላለቀል ነው የሚበጀን፡፡ ወግ አጥባቂነትና በባዶ ሜዳ ተኮፋሽነት የትም አላደረሰንም፤ አያደርሰንምም፡፡ እነዚህ ታርዎች ተጠረቃቅመው ወደመገናኛ ሚኒስቴር ቦሎ ክፍል ቢገቡና ቢጣሩ በአንተ በአንዱ ሰውዬ ላይ የተለጠፉት ታርጋዎች ዓይነታቸው ለዬቅል ነው እሚሆን – የንግድ 3 ቁጥር ታርጋ ፣ የዲፕሎማት ታርጋ፣ የመንግሥት 4 ቁጥር ታርጋ ፣ የታክሲ 1 ቁጥር ታርጋ፣ የቀይ መስቀል 5 ቁጥር ታርጋ ወይም የመያዶች ታርጋ ሊሆን ይችላል የተሸከምከው የታርጋ ዝግንትል፡፡ እልፍ ሲልም የአማራነት ታርጋ፣ የነፍጠኝነትና የትምክህተኝነት ታርጋ፣ የጎበናነትና የአፍቃሬ ዱሮ ሥርዓት ታርጋ፣ የተቸካይነት ታርጋ፣ የተለጣፊነት ታርጋ፣ የአድርባይነት ታርጋ፣ የትግሬነት ታርጋ፣ የኦሮሞነት ታርጋ፣ የሀረሪነት ታርጋ፣ የደቡብነት ታርጋ፣ የሰሜንነት ታርጋ፣ የሰሜናዊ ምሥራቅ፣ የደቡባዊ ምሥራቅ፣ የምዕራባዊ ሰሜን፣ የምሥራቃዊ ምሥራቅ፣ … ባጭሩ ምን አለፋህ የማይሰጥህ የታርጋ ዓይነት የለም፤ በሀገራችን የታርጋ ችግር የለም፤ በሽበሽ ነው፡፡ ሰው ቆም ብሎ እያሰበና በመረጃና ማስረጃ ላይ እየተደገፈ አይደለም ታርጋ የሚያሽረው፡፡ ለወቅቱ የሚለጥፈው አንዳች ነገር አይጣ እንጂ ስለሚለጥፈው ታርጋ ጥራትና ውበት እንዲሁም እውነተኝነት በጭራሽ ሊጨነቅበት አይፈልግም፡፡ ከግልብ አስተሳሰብ የሚመረት ግልብ ታርጋ ተሸክመህ ስትንጋፈፍ ቀኑ እስከወዲያኛው ይመሽብሃል፤ ግልግል! የሚመጥንህን ታርጋ የምታገኘው አልፎ አልፎና ዕድልህ ከሰመረልህ ነው፡፡ አለዚያም ከሞትክ በኋላም ሊሆን ይችላል፡፡ ‹አሄሄ፤ አፈሩን ገለባ ያድርግለትና ያን ሰውዬ በከንቱ ነበርና ስናማው የነበረው!› ተብለህ የከንፈር መምጠጥ የመጀመሪያ ዕርዳታ ሊደረግልህ ይችል ይሆናል – ሁሉም ነገር ካለፈ በኋላ – ላይጠቅምህ፡፡መቼ ይሆን ከዚህ አስቀያሚ ባህል የምንገላገለውና በአስተዋይነት በመጓዝ ጠላትን በማፍራት ሳይሆን ወዳጅን በማብዛት መልካም ተግባር ላይ ወርቃማውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው?… በዚህ በጀመርኩት ጉዳይ ዙሪያ የሃሳብ ድርቀት ስለገጠመኝ ርዕስ ልቀይርባችሁ ነው፡፡
ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝትን ለማጎልበት
እንደድንገት ወደቀኜ ዘወር ስል ዐይኔ አንዲት ብጫቂ ወረቀት ላይ ዐረፈ፡፡ ሳነብባት አንድ ወቅት ከወረዳችን አመራር በስሜ የተላከችልኝ የጥሪ ወረቀት ናት፡፡ ያኔም እንደገረመኝና ጥሪውን ንቄም እንደቀረሁ አሁንም ገረመኝ፤ የጥሪውንም መልእክት አሁንና ወደፊትም እንደናቅሁት እኖራለሁ – በዚህ ብቻ ሳይሆን በዚያኛውም ዓለም፡፡
መልእክቱን ከነትየባና ከነቋንቋ ግድፈቱ ከዚህ በታች አስቀምጨዋለሁ፡፡
ቀን ______________
ለ ነጻነት ዘገዬ
አጭር የስብሰባ ጥሪን ይመለከታል
እንደሚታወቀው የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) በክልሉ ብሎም በአዲስ አበባ የክልሉን መሰረተ ልማት ለመፋጠን ባለፉት አመታት በርካታ ስራዎችን እየሰራን ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ የክልሉ ተወላጅን በጋራ ተዋውቆና ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ላይ አንዳንድ ጉድለቶች ይስተዋላል፡፡ እነዚህን በተደራጀ መልኩና በተወላጆች ዘንድ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ለማጎልበትና በሌሎች የክልላችን ጉዳዮች ላይ በ22/06/03ዓ.ም በ2፡30 ሰዓት በ________ ቦታ ላይ እንዲገኙና የውይይት ተሳታፊ እንዲሆኑ እናሳስባለን
የወረዳ 666 የአማራ ልማት ማህበር አስተባባሪ
ለይዘትም ሆነ ለቅርጽ በላቾች እንዲስማማ ከዚህ በላይ በተቀመጠው የስብሰባ ግብዣ የጥሪ ወረቀት የኮምፒውተር ግልባጭ ላይ ምንም አርትዖት አልተደረገም – ከስብሰባው ዕለትና ከወረዳችን ስያሜ መጠነኛ ለውጥ በስተቀር፡፡ ቢደረግ ኖሮ ከአንድ የ‹አማራ› ተቋም በዚህ ቁራጭ ወረቀት ላይ የሠፈረውን ያህል ስህተት ይኖራል ብሎ መገመት የሚከብድ መሆኑን ከመገንዘብ በተጓዳኝ በርካታ እንከኖችን በመንቀስ ማስተካከል በተቻለ ነበር፡፡ አማራ ነን ባዮቹ ይህን ያህል የአጻጻፍ ግድፈት በዚህች ሚጢጢዬ ጽሑፍ ላይ ካንጠባረቁ መጽሐፍ ቢጽፉ አማርኛውን ምን ያህል ሊከታትፉት ኖረዋል? ብሎ መጠየቅ ከብልህ አማራ ይጠበቃል፡፡ የምንመራበት ዋነኛ ፍልስፍናችን ‹ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን› ማጎልበት ነው ተብሏላ!
እስካሁን ያልገባኝና ወደስተፊትም ይገባኛል ብዬ ተስፋ የማላደርገው ጉዳይ ይሄ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት የሚሉት ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለተቀረው ዓለምም እንግዳ የሆነ ጥንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? በዘመናት የእርስ በርስ መጋባትና ማኀበራዊ ተራክቦ ከ80 በመቶ በላይ የተዋሃደንና የተባዘቀን ሕዝብ አሁን ድንገት ተነስቶ በደምና በአጥንትህ እዬተፈላለግህ ተደራጅና ብሔርህን ወይም ጎሣህን አጎልብት ማለት ከየት የመጣ ጉድ ነው? ሕይወት የሌላቸውን መኪናና ወንበር የመሳሰሉ ግዑዛን ነገሮችን ሳይቀር በዘርና በብሔረሰብ እየፈረጁ ዕቃዎችን በዘውጋዊ ስያሜ መጥራትስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? አማ 02 – 000፤ ትግ 03 – 000፤ ኦሮ 01 – 000 …እያሉ ለመኪና ታርጋ ማውጣት አግባብ ነው ወይ? እኔ በዘር ሐረጌ ከሦስት በላይ የተዛነቅሁት ሰውዬ ምን ዓይነት ታርጋ የተለጠፈባት መኪና መያዝ ሊኖርብኝ ይሆን – መኪና ሊኖረኝ ቢችል? መቼ ነው ይህ ዓይነቱ ዕብደት ይሉት ወፈፌነት በዐዋጅ የሚቀረውና ሰው በሰውነቱና ሰው በዜግነቱ ብቻ እንዲኮራ የሚደረገው? ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲያፍሩ በምትኩ ደግሞ ሆን ተብሎ ዘውጋዊ ማንነት ቅድሚያውን እንዲወስድና የጋራውን ማንነት እንዲጨቁን የሚደረገው ቀልብ ያጣ ሩጫ ማንን ለመጥቀምና ማንንስ ለመጉዳት ይሆን? ይህ አካሄድ አማራን የጎዳ መስሎን የጋራ መቀመጫችንን በ‹ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተገመሰ› ዓይነት የልጆች ጨዋታ የልጆቻችንን የወል ሀገር እንደማፍረስ አይሆንም ወይ? ባሏን ለመጉዳት ስትል አርቆ ባለማሰብ የሞኝነት ግርዶሽ ተነሳስታ የገዛ ሰውነቷን በጋሬጣ እንደጎዳችው ሴት በከንቱ የምንጃጃል ዜጎች አቅል ካልገዛን የጉዟችን ጫፍ እልም ያለ ገደል እንደሚሆን መጠራጠር አይኖርብንም፡፡ … አሁንም ይሄ ርዕስ አላማረኝም መለወጤ ነው ይቅርታ፡፡
የአምባገነኖች መመሳሰል
የመለስ ዜናዊን የንስሃ አባት የሙኣማር ቃዛፊን ሁኔታ የማይከታተል የለም መቼስ፡፡ ጉራውና ውሸቱ አላስገረማችሁም? አምባገነኖች እንዲህ ናቸው – ሁሉም! መለስ አንድ ወቅት ስለሀብቱ ሲጠየቅ ‹ ከነዚህ እዚህች ትንሽዬ መደርደሪያ ላይ ከምታዩዋቸው መጻሕፍት በስተቀር ቃል ለሰማይ ቃል ለምድር ምንም ሀብትና ንብረት የለኝም፡፡ እኔ ንብረት አለኝ የምለው ‘የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍቅር ብቻ’ ነው፡፡…› ብሎ ነበር፡፡ የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ ነውና የሥጋ አባቱ አባባ ዜናዊም ለአንድ መጽሔት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ‹ልጄ መለስ እንኳንስ ብዙ ገንዘብ ሊያከማች የአምስት ብርን ኖት ከአሥር ብር ለይቶ የማያውቅ ሙልጭ የወጣ ድሃ ነው፡፡እኔንም በገንዘብ አይረዳኝም፤ ከየት አምጥቶ ይሰጠኛል?› ብለው አስደምመውን ነበር – በ95 ይሁን 96ዓ.ም አካባቢ ይመስለኛል፡፡
ቀብራራው ጋዳፊ ደግሞ ሕዝባዊው አመጽ እንደተጀመረ በዚያን በወዲያኛው ሰሞን እንዴትና በምን ገቢ እንደሚተዳደር ሲጠየቅ ‹ መንግሥት በሚከፍለኝ 469 ዲናር ነው ሕይወቴን ‹እንደምንም የምገፋው›፡፡ እኔ ምን አለኝና? ሀብታም ነው የሚሏችሁ ምቀኞቼ ናቸው – ከሕዝቤ ጋር ሊያጣሉኝ፡፡› ነበር ያለው፡፡ ጋዳፊ እንዳሁኑ ለቃሉ ሳይሆን ለሕይወቱ ሳስቶ ያልታወቀ ጉድባ ውስጥ ሳይወተፍ ‹እነዚህን ሀሺሻሞችና አሸባሪዎች የአልቃኢዳ ሹምባሾች የአክራሪ ሙስሊሞች ሙንጣዦች ድምጥማጣቸውን ነው የማጠፋው፤ እስከመጨረሻው እስትንፋሴ እፋለማቸዋለሁ፤ አንድ ሰው አንድ ጥይት እስኪቀር…› ብሎ ነበር – በምዕራባውያን አንጀት ውስጥ ገብቶ የሚዘፈዘፍ መስሎት፡፡ ትንኝም እንኳን ለመግደል የጭካኔ መንፈስ የሌለው የኛው – እደግመዋለሁ – በርግጥም የኛውና ጨካኙ መንግሥቱ ኃ.ማርምም እንዲሁ ነበር ያለው፡፡ ነገር ግን አሁን ጋዳፊ እንደተሠወረው ሁሉ ኮሎኔል መንግሥቱም እኛን ግለቱ ለማይበርድ የእቶን እሳት አጋፍጦ እሱ አሁን በአንጻራዊ ሁኔታ በደህና ይኖራል፡፡ አምባገነኖች እንዲህ ናቸው፡፡ ሲወጡም ሲወርዱም ይመሳሰላሉ፡፡ ውልደትና ዕድገታቸውም እንደዚሁ ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም፡፡የሳዳም ሁሴን አፈ ቀላጤ ታሪክ አዚዝ የአሜሪካን ሠራዊት ባግዳድን እየከበበ ባለበት ወቅት ‹ ለእነዚህ ወራሪዎች ባግዳድ መቀበሪያቸው ትሆናለች፡፡ ይምጡና ወደከተማዋ ይግቡ ፤ግዴለም፡፡ የሚቀበሩበት ጉድጓድ ላይ አፈር በመመለስ እንተባበራቸዋለን፡፡…› እያለ ሲዝት ቆይቶ አባቱ ሳዳምም እሱም በመጨረሻው ደብዛቸው ጠፍቶ ለብዙ ጊዜ በድብቅ ቆዩ፡፡ የጋዳፊ ቃል አቀባይ ሙሳ ኢብራሂም የተባለው ቀላማጅም በተመሳሳይ ሁኔታ ከ80 በመቶ የሚበልጠው የትሪፖሊ ከተማ በአማጽያን ዕጅ ገብቶ ‹ብዙ ሺህ ገና ያልተሠማራ ጦር በተጠባባቂነት አለን፤ ያን ስናዘምት እነዚህ አይጠ መጎጦችና የ‹ሥልጣናችን ፀሮች› ድራሻቸው ይጠፋል፤ እንደጉም ይተናሉ፤ እንደጤዛም ይረግፋሉ፤ታያላችሁ!› አለ፡፡ ይህን ተናግሮ ሦስት ቀናት እንኳን በቅጡ ሳያልፉ ራሳቸው እንደጢስ በንነው እምጥ ይግቡ እስምጥ ባልታወቀበት ሁኔታ ያቺን ክፉኛ ይጠሏት የነበረችውን ቃል ድርድርን ባለቀ ሰዓት ያነሷት ጀምረዋል፡፡ አበው ‹ማን ሊስምሽ ታሞጠሙጭ› አሉ? ሲስሟት ቀርታ ሲስቧትም ቢባል ያው ነው፡፡ አሁን 12፡00 ሰዓት ካለፈ በኋላ ድርድር ግዝኣ ምዛዕ ቢሉ ማን ይሰማቸዋል? መጥኖ መደቆስ ዱሮ ነበር፡፡ አሁን ጊዜው አለፈ፡፡ አምባገነኖች በተፈጥሮኣቸው ደደቦች ስለሆኑ እንጂ ከዚህ ከጋዳፊ ሁኔታም ብዙ በተማሩ ነበር፡፡ ይሄም ርዕስ አስጠላኝ እባካችሁ፤ የመጨረሻ ዕድል ትሰጡኝ ልለውጠው?
ሕዝብ በርሀብ አለቀሰ፤ ንብረት ወደውጭ ተጋዘ!
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የማያለቅስ የለም፡፡ ካለም የነአያ እንደልቡ የወያኔዎች አዘጥዛጭና አጋፋሪ ብቻ ነው፤ በፖለቲካም ይሁን በንግዱ ዘርፍ፡፡ የማይራብና የማይቸገር ወያኔና የወያኔ ንክኪ ያለው ነው፡፡ ኑሮ ወደሰማይ ጓነ፤ ሽቅብ ተወነጨፈ፡፡ እንደሚባለውና ከሁኔታዎች ተነስተንም እውነትነቱን እንደምንቀበለው ከሆነ ገንዘብ የሚያስገኙ ሀገርኛ ሸቀጦች ሁሉ በወያኔው ልማታዊ ነጋዴዎች ሁሉም ነገር ወደውጪ እየተጋዘ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ለሀገር ዜጎች መሸጥ የነበረበት ሁሉ ለውጪ ገበያ ቀርቦ የውጪ ምንዛሬ እንዲያስገባ በሚደረገው ከፍተኛ ርብርቦሽ ተሸጦ ገንዘብ የሚያስገኝ ነገር በባትሪ እየተፈለገ ለውጪ ገበያ ሊያውም በርካሽ ዋጋ እየተቸበቸበ ነው፡፡ የሀገሬው ሕዝብ ግን ከቁጥጥር በወጣ ችግርና ችጋር እየተሸነቆጠ ይገኛል፡፡ መጥኔ ለኛ፡፡ በውጭ የምትኖሩስ ወላፈኑ እንጂ ዋናው እቶን አይነካችሁም፡፡
የምንነጋገረው በአማካዩ የመለኪያ አሃድ(ዩኒት) በአንድ ኪሎ ወይም ሊትር ወይም ሜትር ነው፡፡ የመብል ሥጋ ሉካንዳዎች እንዳፈተታቸው እንዲሸጡ ስለተፈቀደ ባማካይ 100 ብር ነው፡፡ ይህን ዋጋ ችሎ የሚበላ ደግሞ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ሲነጣጠር ኢምንት ነው፡፡ ደመወዙ ከወር እወር ቀርቶ ለዕለቱም የማይበቃውና በተዓምር የሚኖረው ሕዝብ ጥቂት ባልሆነበት ወቅት ኪሎ ሥጋ 120 ብር ገዝቶ ማን ሊበላ ይቻለዋል? የሚበሉ እርግጥ ነው ሞልተዋል፤ አለበለዚያ ሉካንዳ ቤቶች ይከስሩ ነበር ወይም ዋጋቸው ወደ አብዛኛው ሕዝብ የመግዛት አቅም ይወርድ ነበር፤ በነበር ባይቀር፡፡ የኛ ሕዝብ ደግሞ በትብብር አድማ በማድረግ ነጋዴንና መንግሥትን የመገሰጽ ባሕርይ የለውም፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ፤ ዱሮ በኪሎ 0.50 ሣንቲም የነበረ ቡና አሁን 120 ሊያውም እስትራፕ የተባለው ሳይበስል የተለቀመ ጥራት የሌለውና ለውጭ ገበያ የማይመጥን ውዳቂ ቡና! ጥራት ከተነሣ አይቀር ብዙ ነገሮች ጥራታቸው ሞቷል፡፡ ቡና ልትጠጣ ቡና ቤት ገብተህ የሽምብራና ገብስ ጥቁር ጭማቂ ልትጠጣ ትችላለህ፡፡ ለማንኛውም ባቄላና ሽምብራ እኳን 15ብር ደርሰዋል – በጥሩ ሚዛን ቢለኩ በተናጠል ምዘና አንድ ኪሎ አይሞሉም ብዙዎቹ የሚገዙ ነገሮች፡፡ ስንዴ 11 ብር፡፡ ፉርኖ ዱቄት 14 ብር፡፡ ጋዝ 15 ብር ገደማ፡፡ ቤንዚን ብር 20.94፡፡ ጠጅ በሡልልታው ሃኒሙን የሚባለው የሀብታሞች መዝናኛ መሥፈርት 60 ብር(ዱሮ አንድ ዋይት ሆርስ ዊስኪ ብር 8.00 ሲሸጥ አስታውሳለሁ፤ እሱ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ 630.00ብር ደርሷል – ሊያውም ተጠንቅቀህ፤ አለዚያ በስመ ዊስኪ ብዙ ነገር አለ ወዳጄ!)፡፡ እንደጎንደር ቄስ ነጭ ጥምጣሙ ያማረ አንድ ጃምቦ ድራፍት ባማካይ ብር 8.00(ጥቃቅን ቡና ቤቶች ነው ይህም ታዲያ!)፡፡ ቢራ ትንሹ ባማካይ 10.00፤ ትልቁ 12፡፡ ምግብ የፆም በያይነቱ ባማካይ 25.00፤የፍስግ ወጣ ወጥ 50.00ብር (ለዐይን የሚቀፍህ ነገር በማታይበት ሻል ያለ ቦታ)፡፡ ሙዝ 11.00 ብር፡፡ ብርቱካን 12.00 ብር፡፡ የኑግ ዘይት 60 ብር – ከምን እንደተሠራ የማይታወቀውና አንጀት ላይ ከተለጠፈ በዳቦ ቤት እሳትም የማይቀልጠው የጀሪካን ዘይት 24.00ብር፡፡ ምሥር ክክ 30.00 ብር፡፡ አንድ ለምለም እንጀራ 2.50፡፡ አንድ ዕንቁላል በችርቻሮ 2.50፡፡ የኔው አቡሻ ትከሻው ላይ አስቀምጦ የሚያንከበክባት ሙትቻ በግ ብር 800.00፡፡ ደህና በሬ 15,000.00 ብር(የተሳሳትኩ እንዳይመስልህ አሥራ አምስት ሺህ ብር! እስከ ሃያ አምስት ሺም አለልህ)፡፡ አንበሣ አውቶቡስ ለአጭር ጉዞ 2.00 ብር(አሥራ አምስት ሣንቲም የነበረው ዱሮ)፡፡ ለክፍለ ሀገር ጉዞ በኪሎ ሜትር 0.27 ገደማ – ሊያውም በወያኔው ስካይባስ ሳይሆን በደረጃ 3 የተራው ሕዝብ ትራንስፖርት (ለምሣሌ ደብረ ማርቆስ ለመሄድ 300ኪሜx0.27ሣንቲም= ብር 80 ከ0.25ሣንቲም ፣ በሰው በላው የደርግ ሥርዓት አምስት ብር አካባቢ እንደነበር ያስታውሷል):: ኤሌክትሪክ በኪሎዋት ለቤት ፍጆታ ከ0.50 ሣንቲም በላይ( በደርግ ዘመን ለቤት ከ0.09 ሣንቲም ይጀምር ነበር)፡፡ የወያኔ ድል ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ሁሉም ሰማይ፤ ገቢው ከሞላ ጎደል ዜሮ! የሸቀጦችና የአገልግሎት ዋጋ በኢምክንያታዊነት ይጨምራል እንጂ ደመወዙ እንደሆነ ‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው› ዓይነት ነው- በተለይ የግል ኢንተርፕራይዞችና የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ፡፡ ልብስ መልበስ አይታሰብም፤ዛሬ ዛሬ ሳልቫጅ መግዛትም የሀብታም ሆንዋል ወዳጄ! በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ካምሱሩ እየተቀጣጠለ ያለ ፈንጅና ቦምብ ነው አጠቃላይ ሁኔታው ሲጤን፡፡ እግዜር ይሁነን እንጂ፡፡…
መንጃ ፍቃድ ለማውጣት፣ማንኛውንም ዓይነት ግብር ለመገበር፣ ስም ለማዘዋወር፣ ለልጆች ትምህርት ቤት፣ ለግድብ መዋጮ፣ ለቤት ካርታ፣ ለንግድ ፍቃድ ዕድሳት፣ ለንግድ ቤት ዓመታዊ ግብር(ባመት ሁለት ሺህ ብር አጠቃላይ ገቢ ለማታገኝበት የንግድ ሱቅ አሥር ሺህ ብር ዓመታዊ ግብር ብትጠየቅ ትልቅ አስተያየት እንደተደረገልህ በመቁጠር ያለክርክር ንግድ ቤቱን ዘግተህ ወደልመና ማምራት ነው የሚያዋጣህ – ብትከራከር ይስቁብሃል እንጂ አዝነው አይቀንሱልህም፤ አንተ ዜጋ ነህ እንዴ መጀመሪያ ደረጃ?)፣ ለልማት መዋጮ፣ ለዕድር፣ ለሰንበቴ፣… በስመ አብ … ሕዝብ የሚገፈግፈውን ብታዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገቢው አኳያ እንዴት ነፍሱ ሳትወጣ ሊኖር ቻለ ብላችሁ ትገረማላችሁ፡፡ በዚህ ሳቢያ ይመስላል በአሁኑ ወቅት የሰካራሙ አበዛዝ፣ የዕብዱ አበዛዝ፣ ካበደው ይልቅ ለማበድ የተዘጋጀውና ከፍተኛ የመወፈፍ ዳርዳርታ እያሳየ ያለው ሕዝብ አበዛዝ፣ ተስፋ የቆረጠው ሕዝብ አበዛዝ፣ ነገር ለመቆስቆስና ለመጣላት ያቆበቆበው ሕዝብ አበዛዝ፣ የሚያገኛት ወርኃዊ ምንዳ ለምንም ዓይነት የረጂምም ይሁን የአጭር ጊዜ የቤት መሥራትም ሆነ የመኪና ግዢ ዕቅድ ስለማትበቃው በመጠጥ ቤቶች ከትሞ ኩላሊትና ጉበቱን በአልኮል እያንጨረጨረ የሚገኘውና በእግረ መንገዱም ወያኔን ለመርሳት በሞኝ አንግሷ ሲስተር ጤናዬ ራሱን የሚያታልለው ዜጋ አበዛዝ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ኢትዮጵያዊ ሕይወት ‹የሥራ ሂደት ባለቤት› የሆነው ወያኔ ነው እንግዲህ ‹ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ካላጎለበታችሁ አታድጉም› ብሎ ዘልዛላ ዕድሜውን በማጭበርበር እየገፋ የሚገኘው፡፡ እኛም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የርሱን ሥልታዊ አምልኮተ ዘውግ ደግፈን እያጨበጨብንና በቁማችን ሞተን እውናዊውን የማይቀር ሞት በፀጋ ለመቀበል በጉጉት እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡ ስንገርም! ማጭበርበር የበጀው ለወያኔ ብቻ ነው፡፡ አይፎርሹም እኮ እናንተዬ! … አይ፣ አሁንስ ርዕስም አለቀብኝ፤ እናንተንም ይደክምብኛል፡፡ ቻው፡፡