ፍኖተ ነጻነት-በኢትዮጵያ ሰዎች በርሃብ እየሞቱ ነው
በአገራችን የተከሰተውን የድርቅ አደጋ የሚዳስስ ጥናት ተደረገ::
– “የተመጣጣኝ የምግብ እጥረት እየተከሰተ ነው”
– “በሴፍቲኔት የታቀፉት በረሃብ ተጋልጠዋል”
– “ለረሃብ የተጋላጮች ቁጥር ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው”
– “የከብቶች ዋጋ እያሽቆለቆለ ነው”
በአገራችን የተከሰተውን የድርቅ አደጋ የሚዳስስ የክትትል ጥናት መከናወኑን የዜና ምንጮቻችን ገለጹ፡፡ የዜና ምንጮቻችን ባደረሱን ማስረጃ መሠረት ባለፈው ዐርብ ዕለት በአሜሪካን ኢንባሲ ጥናቱ ቀርቧል፡፡ ጥናቱ በቀረበበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት የተራድኦ ድርጅቶች ተወካዮችና መሠረቱን አሜሪካን አገር ያደረገ የቅድመ ድርቅ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው የዳሰሳ ጥናቱ የተደረገው በደቡብ የአገራችን ክልል በምስራቅ ሐረርጌና በምዕራብ ሐረርጌ ውስጥ ነው፡፡
በደቡብ ክልል በኮንሶ፣ በአርባምንጭ ዙሪያ፣ በቁጫ፣ በቡርጂ ወረዳዎችና በአማሮ የክትትል ዳሰሳ መከናወኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡ በጥናቱ መሠረት በተገኘው ውጤት ችግሩ ከወረዳ ወረዳ ይለያያል። “በኮንሶ፣ በሐሌና በሐመር 100 ፐርሰንት የሰብል መክሰም ተከስቷል፡፡ በአንዳንድ አካባቢ ከ60-80 ፐርሰንት፣ በአንዳንድ ወረዳዎች ደግሞ ከ50-60 ፐርሰንት የሰብል መክሰም ተከስቷል” ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ነገር ግን በሐመር ወይጦ ወንዝን በመጥለፍ ከ150-200 ሄክታር መሬት በቆሎና ዘንጋዳን መዝራት ቢቻልም የደቡብ አካባቢ ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑን ተገልፃል፡፡ “በሴፍቲ ኔት የታቀፉትም ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል” ይላል ሪፖርቱ፡፡ ምክንያቱንም ሲዘረዝር “ከዚህ በፊት በሴፍቲኔት የታቀፉት የሚሰጣቸው ስንዴ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስንዴው ቀርቶ የሚሰጣቸው በገንዘብ ብቻ ሆኗል፡፡ ለአንድ ሰው በቀን 10 ብር ይሰጠዋል፡፡ የገንዘብ ዋጋ በመውረዱ በ10 ብር የሚገዛው በቆሎ የእለት ወጪውን መሸፈን አይችልም፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ እርዳታው የሚሰጠው በየሦስት ወሩ ነው፡፡ ለአንድ ሰው በቀን 21 ኪሎ ካሎሪ ያስፈልገዋል፡፡ “ይህ ሊሟላ ባለመቻሉ ከፍተኛ የሆነ ያልተመጣጠነ የምግብ እጥረት እየተፈጠረ ነው” ይላል የጥናቱ ሰነድ፡፡
ሰነዱ በማያያዝም «በአንዳንድ ወረዳዎች በምግብ እጥረት ሰዎች እየሞቱ ነው፡፡ ለምሳሌ በኮንሶ ወረዳ ኩቻላ ቀበሌ ስድስት ሰዎች በረሃብ ሞተዋል፡፡ ከሞቱት መካከል አራቱ ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፡ በ17 ሰዎች ላይ ደግሞ ባልተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት በበሽታ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡ በየወረዳውም የወባና ያልተመጣጠነ የምግብ እጥረት እየተፈጠረ ነው፡፡ የሴፍቲኔት ፕሮግራም እንዲሆን የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ በዓለም ባንክ ለአደጋ ጊዜ ከተመደበው ወደ 120 ሚሊዮን ዶላር እንዲጠይቁ በመታዘዛቸው ወረዳዎች እየጠየቁ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል» ሲል ጥናቱ ያብራራል፡፡
የዳሰሳ ጥናቱ በመቀጠልም «የረሃብ ተጋላጮች ቁጥር ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን ከዚህ በፊት በደቡብ 250,000 ሰዎች ብቻ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል ቢባልም የአደጋ ዝግጁነትና ባስተባባሪያ ኃላፊው አቶ ማቲዎስ የሚመራ ቡድን ወደ ደቡብ ተጉዞ እንዳስተዋለው ቀደም ሲል የተራደኦ ድርጅቶች እንደወተወቱት የተረጂዎች ቁጥር ከ750,000 በላይ እንደሆነ ታውቋል» ይላል፡፡
የጥናቱ ሪፖርት በዝርዝር ሲገልጸውም «ለምሳሌ በአንዳንድ ወረዳዎች በሴፍቲኔት ከታቀፉትና እርዳታ ከተጠየቀበት ቁጥር ከ30-35 ፐርሰንት ተጨማሪ ሰዎች ለርሃብ መጋለጣቸው ታውቋል፡፡ በኮንሶ ተጨማሪ 67ሺ ሰዎች ርዳታ እየጠየቁ ሲሆን በአጠቃላይ በኮንሶ 163ሺ ሰዎች ወይም ከነዋሪዎች 73 ፐርሰንት ርዳታ እንደሚያስፈልገው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ከፍተኛ የተረጂዎች ቁጥር በሌሎች ወረዳዎችም በስፋት እንደሚከሰት የተገኘው ማስረጃ ያሳያል፡፡ በምስራቅና በምዕራብ ሐረርጌዎችም የተደረገው የዳሰሳ ጥናት በአብዛኛው ተመሳሳይነት እንዳለው ጥነቱ ያረጋግጣል» ካሉ በኃላ በማያያዝም «በአሁኑ ወቅት በየወረዳውና ድርቅ በተከሰተባቸው ቀበሌዎች አካባቢ ተገኝቶ በርሃብ የተጐዳን ሰው ማነጋገርና ፎቶ ግራፍ ማንሳት ክልክል ነው፡» ይላል።
በተያያዘም ቀደም ሲል ቢ.ቢ.ሲ የተባለው የዜና አውታር በኢትዮጵያ ተከሰተ የተባለውን የርሃብ አደጋ የዘገበውን ዘገባ ለማስተባበል ሲባል ዶክመንተሪ ፊልም ለመስራት በመንግስት አካላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ መጀመሩንና በዶክመንተሪ ፊልሙ ፈረንጆችም እንዲካተቱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ከመሆኑም በላይ፣ ኪዚህ በፊት ለቢቢሲ ዜና ሰጥታችኃል የተባሉ አንዳንድ ግለሰቦች እየታሠሩ እየተፈቱ መሆናቸውን አንዳንድ የመድረክ አመራር አባላት በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡