ፍኖት ጋዜጣ – ኢትዮጵያዊነትኔን ማንም ሊነግረኝ አይችልም !
በህይወቴ የማንነት ጥያቄ ችግር ኖሮብኝ አያውቅም፡፡ነገር ግን ክፉዎች፣ የሀገር መምራት ሥልጣነ-መንበሩን ከተቆናጠጡት በኋላ (እግዚአብሔር የሥራቸውን ይስጣቸው) በሚመቻቸውና ሥልጣናቸውን ለማርዘም ሲሉ ብቻ ከፋፈሉን፡፡ ለያዩን፡፡ እኛ ግን እግዚአብሔር ይመስገን እስካሁን አለን፡፡ ወደፊትም ሳንከፋፈል እንኖራለን፡፡
ይህን ያለምክንያት አላነሳሁም፡፡ በአንድ ወቅት በ”ኢህአዴግ” የወረደ አስተሳሰብ እና ብልሹ አመራር ተበሳጭቼ ኑሮዬ የኋሊት ሲጐትተኝ ስደት ተመኘሁ፡፡ ለዚህም ይረዳኝ ዘንድ ፓስፖርት ማዉጣት ስላለብኝ በቅድሚያ መሟላት ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ የቀበሌ መታወቂያ ነው፡፡ ነዋሪነቴም፣ ተወልጄ ያደኩትም አዲስ አበባ ሲሆን፣ ወደምኖርበት ቀበሌ መሄድ ነበረብኝና በዕለተ ሰኞ ሄድኩኝ፤ ከዚያም መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አሟልቼ ለማክሰኞ እንድመጣ ተነገረኝ፡፡
በነጋታው የተነገረኝን አሟልቼ ስመጣ አንድ አስደንጋጭ ነገር ገጠመኝ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችሁ የቀበሌ መታወቂያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማውጣት ስትሄዱ እንደኔ ገጥሟችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምን መሰላችሁ? ጉዳዩ የመታወቂያ ካርድ ቅጹ ላይ፣ ስም ከእነ አያት፣ የእናት ስም፣ የትውልድ ቦታ እና ቀን፣ በአደጋ ጊዜ ተጠሪ፣ አድራሻ ይላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለየት ያለብኝ ነገር ደግሞ «ብሔር» የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ ግራ ገባኝና ዜግነት ማለትህ ነው? አልኩ፡፡ ‹አይ ብሔር› አለኝ፡፡ እኔም ‹አልገባኝም ምን ማለት ነው?› ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ምክንያቱም ድሮ ዜግነት ነበር የሚጠየቀው፡፡ በተለይ እኛ ሰፈር የውጭ የሶማሊ፣ የቻይና፣ የህንድ ዜጐች ስለሚበዙ ግልፅ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኔ በወላጆቼ፣ በዘመዶቼና በዜጐቼ የምኮራ ቀብራራ ሀበሻ ነኝ፡፡ አዎ ነኝ! ያውም ኩሩ ኢትዮጵያዊ፡፡ የዛን ቀን ግን መልስ ለመስጠት ተደነባበርኩ፡፡
እስካሁን በተለያዩ ሁለት የሀገራችን ዩኒቨርስቲዎች የተለያየ ሙያ ተምሬያለሁ፡፡ በኃይማኖት ተቋማትም እንዲሁ፡፡ ግን እንደዚህ ጥያቄ ከብዶኝ አያውቅም፡፡ የማላውቀውን መልስ መስጠት አልወድም፤ ከቻልኩ እመልሳለሁ፡፡ ካልቻልኩ እንዲነግሩኝና እንዲያሳውቁኝ ጠይቄ ለማወቅ እሞክራለሁ፡፡
የዛን ቀን ግን አያምጣው፡፡ ለምን መሰላችሁ? ስም ከነአያት፣ የልደት ቀንና ቦታ ከመሳሰሉት ውጭ ያሉ ቅፆች ደስ ካለዎት ይሞላሉ፤ አሊያም በስረዝ ይታለፋል፡፡ ብሔር የሚለው ግን የግድ ነው ስለተባልኩ፤ የቃሉን ትርጉም ፍቺ ጠየቅሁ፡፡
እነሱም የተወለድክበት ቦታና የምትናገረውን ቋንቋ ነው የሚገልፀው አሉኝ፡፡ እኔም መልስ ሰጠሁ፡፡ የተወለድኩት አዲስ አበባ፣ ያደግኩት ምስራቅ ሸዋ፤ በትምህርት ምክንያት አዋሳ፣ ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ከዚያም እስከ አሁን አዲስ አበባ ነው አልኩት፡፡ የምችለው ቋንቋ ደግሞ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሀድይኛ፣ ትግርኛ፣ ሲዳምኛ (በትንሹ) እና ከውጭ በትምህርት ያገኘሁት እንግሊዘኛ፣ፈረንሳይኛና አረብኛ (በትንሹ) አልኩት፡፡
ወላጆችህስ? አለኝ፡፡ አባቴ ደግሞ ከሲዳምኛ ውጭ እኔ የምችለውን ሁሉ ይችላል፣ ከውጭ ግን ሩስኪ (የራሺያ)፣ ጀርመንኛ እና እንግሊዘኛ ይናገራል፡፡ እናቴ ግን የሀገር ውስጥ እኔ የምችለውን ከሲዳምኛ በስተቀር መናገር ትችላለች ስል በጣም ይደነቅና ሊፈትነኝ ሞከረ፡፡
በነገራችን ላይ የሚያስተናግደኝ ሰው በትግርኛ አናገረኝ መለስኩለት፤ ከአማርኛ እና ከትግርኛ ውጭ አልቻለም መሰለኝ የቋንቋው ፈተና አበቃ፡፡ ከዚያም የትኛውን ብሔር ልሙላልህ? አለኝ፡፡ እኔም ኢትዮጵያ ስል ተናደደና አትቀልድብኝ አለኝ፡፡ እኔም የምሬን እንደሆነ ነገርኩት፡፡ ከዚያም ግራ ገባው፤ ተጨነቀ፡፡ ግን የግድ መሞላት አለበት የሚል መመሪያ እንዳለ እሱም ይህን እንደማያምንበት ነገረኝ፡፡
የሚገርመው እኔ ከእናትና ከአባቴ ብቻ ሳይሆን በአያቶቼም እጅ አድጌአለሁ፡፡ የእናቴ የትውልድ ሀረግ ሲዘረዘር የጐንደር፣ የአምቦ፣ የደብረማርቆስ፣ የተንቤንና የመራቤቴ ቤተሰብ ግንድ አለባት፡፡ አባቴ ደግሞ የሀድያ፣ የጉራጌ፣ የቤተእስራኤል፣ የጅማ እና የጐንደር አካባቢ ግንድ አለባቸው፡፡ የተለያየ ቋንቋም ይናገራሉ፡፡ ፍረዱኝ እንግዲህ … እኔ የየትኛው ብሔር አባል ነኝ ልል ነው? ወይንስ እንደ ዶሮ ብልት አካሌን ልበልት? ለመሆኑ ማነው የኔን ኢትዮጵያዊነት የሚነግረኝ? ምንስ አገባው? እሱ ማነውና? 2ዐ ዓመት ተጉዘን እንኳን አይበቃንም? እኔ ግን ትናትም፣ ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም፣ ብሞትም በአጽሜ ሳይቀር ኢትዮጵያዊ ነኝ።
የፍኖት ጋዜጣ እትይም 5 ሙሉዉን ለማነበብ ወደ አንድነት ፓርቲ ድህረ ገጽ ይሂዱ።