አደራው ቀጠለ! በተፈሪ መንግስቴ

ተውለብልቦ እንዲቆይ ከፍብሎ በድምቀት
ሰንደቅአላማችን ሁሌም ባራት አመት
አቤ ደከም ሲል የማራቶኑ አባት
ማሞን አስቀደመው አደራ ሆኖበት
ሜክሲኰ እንዲቀጥል ሮም የጀመሩት።

ምሩጽ ተቀብሎ በድል ያቆየውን
የረጅም ሩጫ አኩሪ ታሪካችን
በነኅይሌ ጥረት የቆየው ክብራችን
ለወጣቱ ትውልድ ቀጥሎ ማለፉን
አደራ እንዳይበላ የተረከበውን
የኦለምፒኩ ዛር ወርቅ የለመደውን
በጀማሪዎቹ በማራቶን አገር
አደራውን ሰጠው ቀነኒሳ እንዳይቀር።

ሆኖበት ቃልኪዳን የባንዲራ ነገር
እዳው ከበድ ያለ ተጠብቆ ሚኖር
የተወረሰ ነው በወርቅ አሽብርቆ
በአበቦች ታጅቦ በባንዲራ ደምቆ።
ቀኔም እንዳባቱ አርጎት የራሱ ሃብት
ከአቤ የወረደ የመጣውን ከጥንት
አቆየው ጠብቆ ድፍን አስር ዓመት።
አደረገው የኛ ክብረ ሞገሳችን
አንገት ስንደፋ አንገት ማቃኛችን
አደባባይ መውጫ ቋሚ ተምሳሊያችን።

ቀኔም እንደኅይሌ ታሪክን ደገመው
የተረከበውን ጀባ ብሎ ሰጠው
ይዞት የቆየውን በማተቡ ጽናት
ዓለም እንዲረዳው የኢትዮጵያን ማንነት
ዓሜን ብሎ አማትቦ በፊት ከወሰደው
መርሀባ ብሎ ጄለን ተቀበለው
ዓላህ ዋክብር ብሎም ተራውን አዞረው።

በዓላህ ይዠሀለሁ ኢብራሂም ከእንግዲህ
እንድትቀጥልበት እንዳጀማመርህ
የተሸለምከው ወርቅ አደራ ሁኖብህ።
አንተም አውለብልበው የምየን ባንዲራ
ተለይቶ እማያውቅ ከኦሎምፒክ ጎራ።
አቤ ያመጣውን ከጣሊያኖች መንደር
ችቦውን አቀጣጥል በንግሊዞች ምድር።

ዳላስ ነኅሴ 19 2001
ዴጉ ደቡብ ኮሪያ ቀነኒሳ ውድድሩን ሲያቋርጥ ኢብራህም በሚገርም ሁኔታ
አሸንፎ ወርቅ ሲወስድ ታሪክም ራሱን ሦስት ጊዜ ደገመ__ሜክሲኮ፡ አቴንስ፡ ዴጉ፡፡