አርጤምሳውያን
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዛሬዋ ቱርክ ኢያዞሎክ፣ በጥንታዊቷ የኤፌሶን ከተማ ተገኝቶ ነበር፡፡ በዚህች ከተማ እጅግ የታወቀች፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች አማንያን የሚጎርፉላት፣ ምስሏን የሚሠሩ አንጥረኞች ብር በቁና የሚያተርፉባት አርጤምስ የምትባል ጣዖት ትመለክ ነበር፡፡ ጳውሎስ እዚህ ከተማ ገብቶ ወደ አርጤምስ ቤተ መቅደስ በመጓዝ ‹‹አርጤምስ አምላክ አይደለችም›› ብሎ አስተማረ፡፡
ይህን ሲሰሙ የአርጤምስ ወዳጆች፣ ምስሏን በመሥራት የሚያተርፉት አንጥረኞችና፣ አርጤምስን ለመሳለም ከሚመጡ አማኞች ጠቀም ያለ ትርፍ የሚያገኙ ነጋዴዎች በከተማዋ ሑከት አስነሡ፡፡ ከተማዋ ተደበላለቀች፡፡ ከየአቅጣጫው ሕዝቡ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ጎረፈ፡፡ የሐዋርያት ሥራ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ብዙዎች ወዲያና ወዲህ እያሉ ይጮኻሉ፡፡ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ፣ የሚበልጡት ስለምን እንደተሰበሰቡ እንኳን አያውቁም ነበር፡፡››
አርጤምሳዊነት ባልተረዱት፣ ምስክርነት በማይሰጡበት፣ በማያውቁት ጉዳይ ላይ ሌሎች ስላደረጉት ብቻ፣ ወይም ደግሞ ሕዝቡ ሁሉ ሲያከናውነው ስለታየ ብቻ መደገፍ ወይም መቃወም፣ ወይም ያንኑ መሥራት ማለት ነው፡፡ የሚሰበሰቡበትን ምክንያት ሳያውቁ መሰብሰብ፣ የሚደግፉበትን ምክንያት ሳያውቁ መደገፍ፣ የሚቃወሙበትን ምክንያት ሳያውቁት መደገፍ፣ የሚወዱበት ምክንያት ሳይኖር መውደድ፣ የሚጠሉበትንም ምክንያት ሳይረዱት መጥላት ነው፡፡
ለምን? ሲባል ‹‹እኔ ከሰው እለያለሁ እንዴ›፣ ሰው ሁሉ እንዲህ እያደረገኮ ነው፣ መቼም አንድ ምክንያት አይጠፋም ብዬ፣ እነ እገሌ ሲሄዱ ሄድኩ፣ ዝም ብሎ ያስጠላኛል፣ እንዲሁ ጥሎብኝ እወደዋለሁ፤ ከሰው ጋር ሲኖሩ ሞኝ ሆኖ፣ አህያ ሲጭኑ ሦስት ሆኖ ስለሚባል፣ እየተባለ ዝም ብሎ መደገፍና መቃወም ነው አርጤምሳዊነት፡፡
መመሪያ ስለሆነ፣ አድርጉ ስለተባልን፣ አሠራር ነው፣ የተለመደ ነው፣ በኛ ጊዜ አልተጀመረም፣ ድሮም የነበረ ነው፣ ምን ይደረግ ታዝዘን ነው፣ እኔ ከማን እበልጣለሁ፣ እኔ ከማን አንሣለሁ፣ ከበላይ የመጣ ነው፣ ውጡ ስለተባልን ነው፣ የሚሉ ነገሮችን የምትሰሙባቸው መሥሪያ ቤቶች ካሉ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች በአርጤምሳውያን የሚመሩ ወይም የተሞሉ ናቸው ማለት ነው፡፡ ይፈርማሉ፤ ለምን? ማብራራት አይችሉም፤ ይሰበሰባሉ፤ ለምን ተሰበሰባችሁ? ሳትሰበሰቡ ማድረግ አትችሉም ነበር ወይ? ሲባሉ ምክንያት ያለው መልስ የላቸውም፡፡ ይውደም ይላሉ፤ ማንን እንደሆነ አያውቁትም፡፡ ይቅደም ይላሉ ማን እንደሚቀድም ግን አልወሰኑም፡፡
አንዳንዶች ጓደኞቻቸው ያደረጉት፣ የተከተሉት፣ ያወሩት፣ የወደዱት፣ የጠሉት፣ የደገፉት፣ የተቃወሙት ሁሉ ትክክል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ አመክንዮ የላቸውም፡፡ የተደረገውን ከመድገም በቀር፡፡ ከዚህም አልፈው ከራሳቸው አእምሮ ይልቅ በሰው አእምሮ ያስባሉ፡፡ ሌላውን ሰው መከተል እንጂ የት ይወስደኛል፣ ለምን አከተለዋለሁ፣ ትክክል ነው ወይ? እኔ የተሻለ ሃሳብ የለኝም ወይ? ብለው አይጠይቁም፡፡ እንዲሁ ይከተላሉ፡፡
አርጤምሳውያን ሰውን እንጂ ሃሳብን አይከተሉም፡፡ ሰውን እንጂ ሃሳብን አይቃወሙም፡፡ ለእነርሱ ቁም ነገሩ እነማን አሉበት? የሚለው እንጂ ምን ነገር አለበት? የሚለው አይደለም፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ድልድይ ላይ ብዙ ሰዎች ተሰብስበዋል፡፡ ተሰብስበውም ወደ ድልድዩ ሥር ይመለከታሉ፡፡ እኔ ማዶ ቆሜያለሁ፡፡ ቀስ በቀስ ድልድዩ ላይ ቆመው የሚመለከቱት ሰዎች ቁጥራቸው እየበዛ መጣ፡፡ በኋላም በድልድዩ ላይ መኪና ማለፍ እስኪያቅተው ድረስ በሰው ተሞላ፡፡የምጠብቀው መኪና መጣልኝና በድልድዩ ላይ ለማለፍ ከሌሎች መኪኖች ኋላ ወረፋ ያዝን፡፡ መኪኖቹ በሕዝብ በተጣበበው ድልድይ ላይ እንደ ዔሊ እየተንፏቀቁ ነበር የሚጓዙት፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ነገሩ ሲጀመር አካባቢ ድልድዩ ላይ ያየሁትን ሰው አገኘሁትና የመስኮቱን መስተዋት አውርጄ ‹‹ምንድን ነው ጉዳዩ?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡
እጁን ኪሱ ውስጥ ከትቶ ትከሻውን እያራገፈ ‹‹የሆነ ነገር ሳይገባ አይቀርም›› አለኝ፡፡
‹‹አንተ አላየኸውም›› አልኩት፡፡
‹‹አላየሁትም፤ አንዳንዶች ከብት ነው ይላሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ሰው ነው ይላሉ›› አለኝ፡፡
‹‹አንተ ምን ትላለህ›› አልኩት
‹‹እኔ እንጃ›› አለ፡፡
‹‹ይህንን ካላጣራህ ታድያ ለምን መጣህ›› አልኩት
‹‹ሰው ሲሰበሰብ ጊዜ ዝም ብዬ ነው የመጣሁት›› አለኝ፡፡
ቢያንስ ከሠላሳ ደቂቃ በላይ ቆሟል፡፡ እንዲህ ሰው ሳይጨናነቅ ነበር የመጣው፡፡ የመጣበትን ምክንያት ግን አያውቀውም፡፡ ሰው ተሰበሰበ፣ እርሱም አብሮ ተሰበሰበ፡፡ ሰው ወደ ድልድዩ ሥር ያያል፤ እርሱም ያያል፡፡ ምን እንደሚያይ ግን አያውቅም፡፡ ብቻ ያያል፡፡ አርጤምሳዊ፡፡
አርጤምሳውያን ነገሩ ሳያስቃቸው ነው የሚስቁት፡፡ የተሰበሰበው ሰው ከሳቀ ይስቃሉ፡፡ ቀልዱ ግን ላይገባቸው ይችላል፡፡ ባይገባቸውም ያጨበጭባሉ፡፡ ከዐዋቂ መካከል ከተቀመጡም ራስ ሲነቀነቅ ሲያዩ ይነቀንቃሉ፡፡ የሆነ ወረቀት ሲታደል ካገኙ ይቀበላሉ፤ ግን አያነቡትም፡፡ ማስተዋሻ ሲሰጥ ካዩ ተስገብግበው ይወስዳሉ፤ ግን አይጽፉበትም፡፡ የሆነ ምዝገባ ነገር ከተመለከቱ ወደ ሲኦል ለመሄድ ቢሆን እንኳን አያጣሩም፤ ብቻ ይመዘገባሉ፡፡ የሆነ ኮሚቴ፣ ማኅበር፣ ቡድን ሲመሠረት ዘለው ይገባሉ፤ ዓላማው፣ አሠራሩ፣ ማንነቱ አይመለከታቸውም፡፡ ዓላማቸው መቀላቀል ብቻ ነው፡፡
ኢሜይል አላቸው፣ የሚገናኙት ሰው የለም፤ ፌስ ቡክ አላቸው የሚለጥፉት ነገር የለም፡፡ ትዊተር አላቸው፣ የሚያስተላልፉት ነገር የለም፡፡ በሞባይላቸው ይቀዳሉ፣ እነርሱስ ከማን ያንሳሉ፡፡ ግን የቀዱትን አያዳምጡትም፡፡ እንዲያውም በቀጣዩ ደምስሰው ሌላ ይቀዱበታል፡፡ በሞባይል ፎቶ ያነሣሉ፤ ደግመው ግን አያዩትም፡፡ አርጤምሳውያን፡፡
አርጤምሳውያን ቤት የሚገዙት፣ መኪና የሚገዙት፣ ድርጅት የሚከፍቱት፣ ልብስ የሚገዙት፣ ውጭ የሚሄዱት፣ ርዳታ የሚረዱት፣ ድግስ የሚደግሱት፣ ሞባይል የሚቀይሩት፣ ምክንያት ስላላቸው አይደለም፡፡ እገሌ ስላደረገው፣ የዘመኑ ፋሽን ስለሆነ፣ ሰው እጅ ላይ ስላዩት፣ የሆነ ሰው ሲያወራለት ስለሰሙ ብቻ ነው፡፡
አንድ ሰው መንገድ ዳር ቆሞ ይለምናል፡፡ ‹‹አግኝቼ ያጣሁ ነኝ›› ይላል ደጋግሞ፡፡ ከሚያልፉት መንገደኞች አንዱ ጠጋ አለውና ‹‹እውነት አንተ አግኝተህ ያጣህ ነህ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ይለምን የነበረው ሰውም ‹አዎ›› ሲል መለሰ፡፡ መንገደኛውም ‹‹ለመሆኑ ከዶሮ ብልቶች በጣም ጣፋጩ ምንድን ነው?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ሲለምን የነበረው ሰውም ‹‹ቆዳው›› ሲል መለሰለት፡፡ መንገደኛው ሰው ‹‹እውነትም አንተ አግኝተህ ያጣህ ነህ›› ብሎ ጠቀም ያለ ገንዘብ ሰጠው፡፡
ከጎኑ ቆሞ ሲያይ የነበረ አንድ ሰው ቀበል አደረገና ‹‹አግኝቼ ያጣሁ›› ማለት ጀመረ፡፡
ሌላ መንገደኛም ጠጋ ብሎ ‹‹አግኝተህ ያጣህ ከሆንክ ከበግ ሥጋ የሚጣፍጠው ምንድን ነው›› ሲል ጠየቀው
‹‹ቆዳ›› አለ አሉ፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው