ፓትርያርኩ÷ አቡነ ጢሞቴዎስን በመደገፍ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ሻሩ

  • ቋሚ ሲኖዶሱ የሚያጤነውን የአካዳሚክና አስተዳደር ዲኖች ሹመት አጽድቀዋል
  • የመምህራኑ የመብራትና ውኃ አገልግሎት ከተቋረጠ አንድ ወር ሊሞላው ነው
  • ደመወዛቸው እንደታገደ ነው

ከሥልጣናቸው ተገልለው እንዲቆዩ በተወሰነባቸው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ እየተመራ ያለው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር÷ በሕንጻ እድሳት አመካኝቶ በኮሌጁ ቅጽር የሚኖሩ መምህራን ቤቶቻቸውን ለቀው እንዲወጡ ያስተላለፈው ትእዛዝና ቤቶቹን ካለቀቃችኹ በሚል በመምህራኑ ደመወዝ ላይ የጣለው እገዳ ውድቅ ተደርጎ፣ መምህራኑ÷ በመኖርያ ቤቶቹ መገልገላቸውን እንዲቀጥሉ፣ የታገደው ደመወዛቸው እንዲለቀቅና በቀጣይም በአግባቡ እንዲከፍል በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ የታዘዘበት ውሳኔ በፓትርያርኩ ተሻረ፡፡

ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የጻፉት ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ስለ ኮሌጁ በተላለፉ ውሳኔዎች ላይ ‹‹አስተዳደራዊ እርምት መውሰድ›› ማስፈለጉን ይገልጻል፡፡

ፓትርያርኩ ራሳቸው በሰብሳቢነት በመሩት የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ ውሳኔ የተላለፈባቸው ኮሌጁን የተመለከቱ አጀንዳዎች፣ ‹‹ሐቀኝነት የጎደላቸው›› እና ‹‹በቃል ብቻ የቀረቡ›› እንደነበሩ ደብዳቤው ተችቷል፤ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ መሠረት በማድረግም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ለኮሌጁ የተጻፈውና የኮሌጁ አስተዳደር ያስተላለፋቸው ውሳኔዎችና የወሰዳቸው አስተዳደራዊ ርምጃዎች ውድቅ የተደረገበት ደብዳቤ በፓትርያርኩ ደብዳቤ የተሻረ መኾኑን አስታውቋል፡፡

‹‹የተጠናከረ ማስረጃ እስኪቀርብ›› በሚል በፓትርያርኩ በተወሰደ ‹‹አስተዳደራዊ እርምት›› የተሻሩት የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔዎች በደብዳቤው ላይ በግልጽ ተዘርዝረው ባይጠቀሱም÷ በዋናነት በቋሚ ሲኖዶሱ አባላት የእምነት ርቱዕነት ጥያቄ የተነሣባቸው አዲሶቹ የአስተዳደርና አካዳሚክ ዲኖች ሹመት እንዲጤን የተደረሰበትን ስምምነት እንደሚመለከት ተገልጧል፡፡ ከዚህም ጋራ መምህራኑ የኮሌጁን መኖርያ ቤት ለመልቀቅ እንዳይገደዱና በምትኩ በአስተዳደሩ የተቆረጠባቸው የመብራትና ውኃ አገልግሎት እንዲሟላላቸውና የታገደባቸው የነሐሴ ወር ደመወዝ ተለቆላቸው በቀጣይም በአግባቡ እንዲከፈላቸው የተላለፈውን ውሳኔ እንደሚያካትት ተዘግቧል፡፡Teachers of the Holy Trinity Theological College

የኮሌጁ አስተዳደር÷ ፓትርያርኩ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመሻር በጽ/ቤታቸው በኩል የጻፉትንና በዋና ሥራ አስኪያጁ የተመራለትን ደብዳቤ በመጠቀም መምህራኑና ሠራተኞቹ እስከ ኻያ ዓመት ያህል የቆዩበትን የኮሌጁን መኖርያ ቤቶች ያለአንዳች የኪራይ አበል ለቀው እንዲወጡ፣ ለቀው የማይወጡ ከኾነ በደመወዛቸው ላይ የተጣለው እገዳ እንደሚቀጥል መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም በድጋሚ በቅጽር ግቢው በለጠፈው ማስታወቂያ ማሳሰቡ ታውቋል፡፡

ማሳሰቢያው÷ ከቅ/ሲኖዶስ ተጠያቂነት ውጭ የኾነውና ከፓትርያርኩ ጋራ ባላቸው ግላዊ ግንኙነት መደገፉን የቀጠለው የአቡነ ጢሞቴዎስ የጉልበት አስተዳደር አስከፊ መገለጫ ነው ያሉት መምህራኑ እንደ ማሳሰቢያው ቃል ከቤታቸው አልወጡም፤ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ጀምሮ በአስተዳደሩ የተቆረጠባቸው የመብራትና የውኃ አገልግሎት እንደተስተጓጎለ አንደኛ ወሩን ሊያስቆጥር ተቃርቧል፡፡

በአካላዊ የመስማትና ማየት ችሎታ ውስንነትና በአስተዳደራቸው አስከፊ ብልሹነት ምክንያት ለ14 ዓመታት በኮሌጁ ከነበራቸው የበላይ ሓላፊነት ሥልጣን በቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ የተገለሉት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ÷ ፓትርያርኩ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በቀጥታ በመፃረር የጻፉትን የመሻርያ ደብዳቤ፣ ከሥልጣናቸው ከተገለሉ በኋላ አላግባብ ለወሰዷቸው የቅጥር፣ ዝውውርና ስንብት ርምጃዎች ሕጋዊ ልባስ ለመስጠትም ጭምር እየተጠቀሙበት እንደኾነ ተመልክቷል፡፡

ኹኔታው እንደ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ አባባል፣ ሙስናን መዋጋት በተግባራዊ ርምጃ ወይስ በቃላዊ ዕወጃ!?