በሃገር ጉዳይ እኔ ማን ነኘ (በሎሚ ተራ)
ማሳስቢያ ፦ ይህ ጽሁፍ ለፍትህ የመቆም ጥያቄ እንጂ በምንምና በማንም መልኩ ወያኔ እንደሚያራምደው የሃይማኖት ነቀፌታ እንዳልሆነ በግልጽ እንዲታወቅና አንባቢያን በአንክሮ እንዲመለከቱት በጥብቅ አደራ እላለሁ አመስግናለሁ ።
ዛሬ በእዝች አጭር መጻጽፌ ላተኩረበት የፈለኩት ሥለሀይማኖት ድረጅቶች ማለትም፤ የኦርቶዶክሱ፤ የሙስሊሙ፤ የፕሮቲስታንቱም ሆነ የሌሎቸ ሃይማኖት ተከታዮች በተለይ ከሀገር ውጪም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉት ድርሻቸው ምንድነው? በሀገር ውስጥ ፍትህ ሲዛባ ሕዝብ በርሃብ ሲያልቅ ከማንም በፊት ፍትሕ ለምን ይዛባል? ሕዝብ ለምን ይበደላል? ፤ፍትህ በማጣት ሴቱም ወንዱም አዛውንቱም ህጻናቱም ከሀገር ለምን ይስደዳል? ያለፍርድ ህዝብ ለምን የታሰራል? ለምን የታፈናል? ወዘተ.. ፤ የዚሀ አይነት ኢ-ስበአዊ ስርአተ- መንግሥት መታቀብ አለበት። ብሎ መንግሥትን መጠየቅና አቤቱታ ማቅረብ ያልተቻለበት ምክነያት ምንድነው ትላላችሁ ? አይናችን ይገለጥ። ጆሮችን ይከፈት። ከተጠያቂነት በምድርም በስማይም አናመልጥምና አንድ በሉ። አንድ እንበል።
በማለት ሃይማኖት አለኝ :: የሀይማኖት መሪ ነኝ:: የሚሉትን ሁሉ ይሀንን አገራዊ ጥያቄ በትህትና በሀገሬ ጉዳይ እኔ ማነኝ ? በሚል አቀርባለሁ። መልስም እንደምትሰጡ አምናለሁ።
“እምነት” በሚል ሃሳብ በእምነት አቋማቸው የግድ አንድ ባይሆኑም ፍትኽን ለማስከበር ግን አንድ አቋም ሊኖራቸው የማይችሉበት መንገድ ምንም የለም:: ምነው ድምጻቸው አልስማ አለ? በ ኦርቶዶክስ በኩል በ አባ ጳውሎስ በኩል ያለወን ኢ- ስበአዊ የሆነ የሀይማኖትን በጎ ስነምግባር የሚያበላሽ አስተዳደር በጉሉህ መንጻብረቁ ግልጽ ቢሆንም ቅሉ፤ ሌሎች የሃይማኖት አባቷችና መረዎች ግን አንድነታቸውን አጠናቅረው የፍትሕ ያለ ብለው መጮህ ምነው አቃታቸው? እረ የፈጣሪ ያለህ፤ የምናመልከው አምላክስ ይህንን አይነት ድርጊት እንደሃይማኖት መሪነታችሁ ድምጽ አለማሰማታችሁን እስየው … የሚል ይመስላችኃል? እረ ጎበዝ አንድ እንበል፤ አንድ በሉ፤ በሀገር ጉዳይ የኔ ድርሻ ምንድነው? እኔ ማነኝ ? ብለን መጠየቅ ምነው አቃተን ? እያልኩ የሀይማኖት መሪዎችንም ተከታዮችንም ጆሮቻቸውን ይከፍቱ ዘንድ አይኖቻቸወንም ይገልጡ ዘንድ አሳስባለሁ።
እንደምናውቀወና እንደምናየው በተለይ በውጭ ያሉ የየትኛውም ሃይማኖት መሪዎች በተንጣለለ ሞርጌጁ ተከፍሎ ባለቀ ቪላና፤ በውድ በተገዙ የሚያማምሩ መኪኖቸ እየተንፈላሰሱ “እየሱስ ያድናል! እያሉ መስበካቸው ባልከፋ።
አሳዛኙ ግን ይሄ የሚስብኩት እየሱስ ለአልም ሁሉ ቤዛ የሆነና በምድርም አገልግሎቱን የፈጸመው ድሃን አብልቶ: በሽተኛን ፈውሦ፤ በ እምነት ስም የሚሸቅጡትን : በግልጽ ተቃውሞ፤ ለድሆቸ አዝኖ አልፎ ትርፎ እንባወን አፍሦ ለፍትህ ሁሉም ተከታይ በአንድ ልብ መቆም እንዳለበት አስተመሮ መሆኑን መዘንጋታቸው ነው።
በጣም የሚደንቀውና የሚገርመው ደግሞ የሚኖሩበትንም ቪላና የሚነዱትንም መኪና በስመ “የፍቅር ስጦታ” በሚባል ፈሊጥ እየገዛ የሚሰጠው ይሄው አገለግለዋለሁ የሚሉት የኔ ቢጤው ምስኪኑ መእምን መሆኑ ነው። እኔን በጅጉ የሚደንቀኝ ለምን የፍቅር ስጦታ ተሰጣቸው አይደለም፤ መሪዎቹም ሆኑ ተከታዮቹ ምነው አይናቸው ተገልጦ የሃገራቸው መከራና የህዝብ ስቆቃ አልታያቸው አለ? የሚለው ነው። የሚበደለው እኮ የወደዳቸውና የፍቅር ስጦታ በመስጠት ኪሱንና ኑሮወን አራቁቶ እናንተ ይመቻችሁ ። ይድላችሁ ። ብሎ ያከበራቸው ሕዝብ ነው።
ታዲያ ይህ ምስኪን ሕዝብ ሲበደልና ፍትሕ ሲጓደልበት አይንን ጨፍኖ ጆሮን ደፍኖ መቀመጥ ይቻላል? ነው ጥያቄውና መልስ ሥጡ።
ለመሆኑ በየትኛውም ሃይማኖት ጥላ ሥር ያሉት መሪዎችም ሆኑ ተከታዮች በሃገር ጉዳይ ለፍትሕ ከሕዝብ ጎን ለመቆም የሚያግድ ( በስመ ፖሎቲካ) መጽሃፍ ቅዱሳዊ መረጃ አለ? ካለ አዋቂዎች ቢያስተምሩን። ከሌለም ጥግ፤መያዙ አስፈላጊነቱና ጠቃሚነቱ ቢገለጽ መልካም ነው እላለሁ።
ደግሞስ ፤በአበሻው እምነት ተከታዩ አካባቢ በተለይ በፕሮቲስታንቱ አማኝ አካባቢ ፖሎቲካ ሲባል እንደ ጦር የሚፈራበት ምክነያቱ ምን ይሆን? በርግጥ ፖሎቲካ የሚያስፈራ ነው? እኔ እንደሚገባኝ አባገነኖች ለራሳቸው የስልጣን መራዘም ግብታዊ አላማ ሕዝብን በሃይል እረግጠው በመግዛት፡ ስለፍትሕ ጉዳይ የሚናገረውን እያሰሩ፤ የህዝብ ኑሮ ይሻሻል፤ የአገር ኢኮኖሚ ሃብት በአግባቡ ለህዝብ ይዳረስ፤ ሁሉም ዜጋ በመከባበርና በመተሳስብ በእውቀቱ ሰርቶ አገሩን የሚያለማበትና የሚያሳድግበት ደስ ብሎት ለአገሩ ልአላዊነት በአንድነት የሚቆምበት ሥረአት ለማምጣት የሚደርገውን ትግል እያስሩና እያፈኑ አልፎ ተርፎም እየገደሉ አስፈሪ እንዲሆን አደረጉት እንጂ፤ ፖሎቲካ በአንድ አገር ላይ ሕዝብ መብቱ እንዲጠበቅና የአገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከላይ የተዘረዘሩትን የህግ የበላይነትን መስረት በማድረግ ተፈጻሚ እንዲደረጉ የሚያደርግ ሥረአት ነው ብዬ አምናለሁ።
በበኩሌ ፤ እንዲያስፈራ የደረጉት አምባገነኖችና ጨካኞች ለሕግ የበላይነት ግድ የሌላቸው ጥቂት የግል ጥቅምና ሥልጣን ያሰከራቸው ግለስቦች ናቸው ብዬ አምናለሁ።
ዋናው ጥያቄ እነዚሀን አንባገነኖቸ ለማስወገድ ማንኛውም ዜጋ ሃይሉን እና አንድነቱን አስተባብሮ በሀገሩ ላይ ፍትህ እንዲስፈን ሃይሉን አስተባብሮ ለመታገል እምነት ምክነያት ለምን ይሆናል ነው። እነማርቲን ሉተር ኪንግና እነ ጋንዲ እኮ ያለምንም ጦርነት ሕዝብን አስተባብረው ነው መብት እንዲከበር ለአለም ሕዝብ ምሳሌ ሆነው ያለፉት።
ምነው ታዲያ አንድ እንኳን የሃይማኖት መሪ የዚህን ጥቂቱን ለማድረግ አቃተው? እስቲ ይሀንን መልስ ለመስጠት ሞከሩ። እኛ እኮ እየጸለይን ነው ። እንደማትሉኛ እርገጠኛ ነኝ። ዜጎች በሙሉ በታሪካቸን በጸሎት ነውና የኖርነው። እር አይናችን ይገለጥ ጆሮችን ይከፈት፤ ማን ታግሎ ማን መስዋትነት ከፍሎ በሰለምና በትድላ መኖር እንፈልጋላን ? ዛሬ ድርሻችንን ካላባረከትን ነገ በምድርም በስማይም ጥያቄ አለና ከዚሀ ታሪካዊና ስማያዊ እዳ ለመዳን ዛሬ የበኩላችንን እናበርክት እላለሁ።
በግልም ሆነ ባጋራ ምንም ሳያግዳቸው ድርሻቸውን እያብረከቱ ላሉት ምስጋናዬ የላቀ መሆኑንም ሳላወሣ አላልፍም። በርቱ ብድራቱን በምድርም በስማይም ትቀበላላችሁና ለሌሎች ታላቅ ምሣሌ መሆናችሁ ይቀጥል።
እግዚአብሄር ሆይ እባክህ የሃይማኖት መሪዎቸንም ሆነ የአንተን ተከታይ አማኞችን ልቦና ክፈት።
ስሞኑን ከአንድ ወዳጄ ጋራ በሀገር እውስጥ ሰላለው “እርሃብ ጉዳይ” ስንወያይ እንባ እየተናነቀው በሚያመልክበት ቤተክርስቲያን ከ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ የፈጀ አዲስ የቤተክርስቲያን ሕንጻ ተሰርቶ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አበሰረኘ። እርሱም ምንያህል ገንዘብ ለህንጻው እንዳበረከተ ነግሮኘ፤ አይመለስልኝም እንጂ በስጦታ ካበረከትኩት ገንዘብ ግማሹን ለወገኖቼ በላኩኝና፤ የአንድ ቤተስብ ነብስ እንኳን ባተርፍኩ ብዬ ተቆጨሁ። ያለወን ሣስበው እኔም መቆጨቴ አልቀርምና ስለሚሰራው ህንጻና የዜጎችን ተሳትፎ አድንቄ የሚከተለውን ግን ለራሴ ጠየቅኩ፤ እንዲኽ
ብዬ፡ እንዲኽ፤– አገር ስላም ቢሆን የህዝብ ነጻነትና እኩልነት ቢከበር ይህንን ያሕል ወጪ ፈጅቶ የተስራው ሕንጻ በሃገራችን ቢሆን አምስትና ስድስት የሚሆን እኔነኝ ያሉ ሕንጻዎች በሰራ፤ አገረንም ባስዋበ ነበር። ሆኖም በስደት በምኖንኖርበት አገር ይሀንን አይነት ትልቅ ህንጻ ስርተን ንብረትነቱ በስደት ለምንኖርበት ሃገር መዋሉን ሣስበው ተቆጨሁና፡ መፍትሄው ግን በአንድነት ተባብረን በሃገራችን ፍትሕ እንዲስፍን መታገል መሆኑንን በማስተዋል እንድመለከት አደርገኝ። ሌላውም ጉዳይ በርሃብ የሚያልቀውን ሕዝባችንን ሣስብ እያንዳንዳችንስ ለሕንጻው ካበርከትነው ሥጦታ ባሻገር በርሃብ ለሚያልቀው ሕዝባቸን ያደርግነው አስተዋጾ አለወይ ? ብዬም እንድጠይቅ አደርገኝ እንጂ ለምን ተስራ የሚለው እንዳልሆነ ተርዱልኝ አደራ።
ምክነያቱም ለማንኛውም የሃገር የለውጥ ትግል ሕዝቡ አንደነቱን እንዲገልጽና ግንባር ቀደም ተሣታፊ እንዲሆን የምንፈልገወን አክል በሚደርስበትም የግፍ ሥረአት መከራና ችግር ግንባር ቀደም ፈጥኖ ደራሽ በመሆን አጋርነታችንን በትግባር መግለጹ አለ የማይባል የዜግነት ድርሻችንና ግዴታችን እንደሆነም ማወቁ አስፈላጊ ነው እላልሁ።
ስሞኑን በዚሁ በፓል ቶክ ጎራ እትዮጵያዊው ሁሉ ስለሃገር ጉዳይ በየጎራው ለሃገር የሚበጀው የሄ ነው። የለም የሄን አይነቱ ትግል የሚያዛልቅ አይደለም። ኦነግና ኦበነግ ግንቦት 7 አብረው የሚያደርጉት የምክክር የዞታ ለሃገር የሚበጅ አይደለም ። መነጋገሩን ይነጋገሩ። መመካከሩን ይመካከሩ። አትነጋገሩ ያለ የለም። ሆኖም አካሄዳቸው ግን ለ85 ሚሊዎኑ የ ኢትዮጲያ ሕዝብ የሚበጅ አይደለም። ወቅታዊ የሆነወን የህዝብ ችግር ያማከለና የዜጎችን የልብ ትረታ ያዳመጠ ጉዞ አይደለም። በሚል የሚደረገወን የዜጎችን አገራዊ ወይይቶች በአንክሮ አዳመጥኩና እኔ ማነኝ ? የሚለወን ጥያቄ ለማንሳት ተገደድኩ እላችኃለሁ።
እንደ እኔ መረዳት እንዲኽ ያለው አለመግባባትና የፖሎቲካ ፍጭት በዜጎቸ መካከል ሲነሳ የሚያስማማና የሚያስታርቅ ሃሳብ ይዘው መምጣት ያለባችው ይነስም ይባዛ የሀይማኖት መሪዎች፤ ያገር ሽማግሌዎች ነበሩ። ሆኖም ከፉ ጊዜ ሆነና “ቄሱም ዝም መጽሃፉም ዝም” በመሆኑ እንደው ነገሩ ምን ይሆን ? በሚል ሃሳብ እኔ ማነኝ? በሚል የሃይማኖት መሪዎችንም ሆኑ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚለወን በተለይም የፕሮቲስታንት ተከታዩን ሁል ምን መልስ እንደሚስጡ እንደ እኔ ጉጉት ያላቸው ብዙዎች ናቸው በሚል ጽኑ እምነት ለመጠየቅ ተገደድኩ። ስለዚህ እባካችሁ ይኽቺን አጭር መጻጽፍ ያነበባችኹ የሃይማኖት መሪዎች ሁል የምትሉትን ለመስማት ብዙዎች ይጓጓሉና አደራ አንድ በሉን እያልኩ በትህትናና በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ለ እምነታቸን ብለን የምንቆረቆረውን ያከል፤ ለሃገራችን ፍትኽና አንድነት የሕግ፤ የበላይነት በአንድነት ብንቆም የሕገወጥ አባገነንነትን ሥረአትን በተባበር ክንዳችን አስወግደን የምንናፈቀውን የሕግ የበላይነትና ሁሉም በመተሳስብና በመከባበር አብሮ የሚኖሩበትን አዲሲቱን ኢትዮጲያ መገንባት እንችላለንና ሁሉም ዜጋ በማስተዋል በሃገሬ ጉዳይ እኔ ማነኝ ብሎ እንደገና ይጠይቅ ዘንድ በትኽትና እጠይቃለሁ።
እንደምናየወና እንደምንስማው በተለያዩ የጎረቤት አፍሪካ አገሮቸ በሚደርገው የነጻነት ትግል ዜጎች በስደት ከሚኖሩበት የሞቀ ኑሮአቸው ተነቃንቀው ኑሮቸውንና ቤታቸውን ቆልፈው ፤ እምነታቸው ሣያግዳቸው የነጻነት ትግሉን በመቀላቀል በአንድነት ሲታገሉና ሲሞቱ ስንመለከት፤ እኛማ የርጅም አመት የመቻቻልና የሃይማኖት መከባበርና መተሣሰር ጀግነነትም ጭምር ታላቅ ታሪክ ያለን ዜጎች በመከባበርና በመቻቻል ሃይላችንን አስተባብረን ላንዴና ለመጨረሻ እትዮጵያዊያን ማንነታችንን ከልዩነታችን ባሻገር በፍቅርና በመተባበር ማሣየት የማንችልበት ምንም ምክነያት የለም።
እትዮጵያ ታሪኳን፤ ሃይማኖቷን ዳር ድንበሮን በጀግኖች ልጆቿ አስከብራ እንደቆየች ሁሉ ዛሬም በዚሀ በ21 ክፍለዘመን መስተካከል ያለበትን የታሪክ ሥህተቶችን አስተካክላ በተባበርው የዜጎች አንድነትና የሃይማኖት ሕብረት አዲሲቱን ዲሞክራቲክ እትዮጵያን የስላም፤ የፍትሕና የ እኩልነት ሥረአት ለመመስረት እንድንቸል እግዛብሔር ጸጋውን ያብዛልን እላለሁ።
በመሆኑም የሃይማኖት መሪዎችም ሆናችሁ የ እምነቱ ተከታዮች እኔ ማነኝ ? ድርሻዬስ ምንድነው ? የሚለውን ጥያቄ በንጹሕ ኢትዮጲያዊ መንፈስ መልሥ ለመስጠት እንዘጋጅ፤ መልሣችሁንም አስሙን እያልኩ የዛሬውን መጻጽፌን እዚሁ ላይ አበቃለሁ። እግዚአብሄር ሁላችንንም ማስተዋልና ጥበቡን ያብዛልን እያልኩ የመስናበታችሁ ሎሚ ተራተራ አገሬን አደራ ነኝ። ጤና ይሥጥልኘ።
አንደነት ሃይለ ነው። አንደነትን ለማምጣት እኔ ማነኝ በአገረ ጉዳይ ብሎ መጠየቅም ለአንድነት ሃይል ነው ! ።
ተፈጸመ።
አስተያየት ወይም ጥያቄ ቢኖራችሁ የጸሃፊው አድራሻ ይኽ ነው። [email protected]
Friday, August-19-11