የማይናደፈውን መንደፍና ጦሱ፦ በእንተ ዓይናማው ኃያሲ ዳንኤል ክብረት

(በዶክተር ጌታቸው አሰፋ):- ዳንኤል ክብረት ለበርካታ ዓመታት በሐመርና ስምዐጽድቅ ጋዜጣ፤ በአዲስ ነገር ጋዜጣ፤ በሸገር ራዲዮ፤ በሮዝ መጽሔትና፤ በጻፋቸው መጻሕፍትና በቅርቡ ደግሞ የራሱ በሆነው መጦመሪያ (ብሎግ) www.danielkibret.com የሚያውቀው ሰው ብዙ ነው።  ይህ ሁሉ ጽሑፎቹን እየተቀባበሉ የሚያወጡትን የሀገር ውስጥና ውጪ ጋዜጦች መጽሔቶችና ብዙኃን መገናኛዎችን ሳይጨምር ማለት ነው። ዳንኤል ሲያስተምር ተሰሚ፤ ሲጽፍ ተነባቢ ለመሆኑ በኢትዮጵያም ከኢትዮጵያም ውጪ በተመላለሰባቸው አገሮች ያለነው ተማሪዎቹና አንባቢዎቹ ምስክሮች ነን። ሰፊ ተሰሚነትና ሰፊ ተነባቢነት ብዙዎች የሚታደሉት ነገር አይደለም – በተለይ በመስማትና በማንበብ ራሷን ችላለች ብለን አፋችንን ሞልተን በማንናገርላት አገራችን።

ብርሃኑ ደቦጭ ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻፪ ዓ.ም. (July 17/2010) በተነበበው አውራምባ ታይምስ ፫ኛ ዓመት ቁጥር ፻፳፬ እትም ላይ “ሀገራቸውን ለማቆርቆዝ የሚታትሩ ምስኪኖች የሞሉባት ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ  በዳንኤል ክብረት “የሁለቱ ሐወልቶች ወግ እና ሌሎች” መጽሐፍ ላይ ያተኮረ ዳሰሳ ሲያስነብበን  የዳንኤል  ክብረት ወጎች የብዙና የሁሉንም ዓይነት አንባቢዎች ትኩረት ለማግኘት እንዴት እንደቻሉ ሲገልጽ “ወጎቹ ተናዳፊ፤ ተሳዳቢና ሸንቋጭ አለመሆናቸው”ን እንደ ምክንያት አስቀምጧል።  ብርሃኑ ደቦጭ ልክ ብሏል። ዳንኤል ክብረት እገሌ የሚባል ቡድን ወይም ግለሰብን ለመናደፍ አይጽፍም

ከ፭ ወራት በፊት የተጀመረው www.danielkibret.com  መጦመሪያውን ብቻ ስንወስድ ወደ ፸ (70) የሚጠጉ ጽሐፎችን (ወጎችና ጥናቶችን) ጽፎ አስነብቦናል። እንደ ዜጋ፤ እንደ ካህን፤ እንደ እድር መሪ፤ እንደ ባል፤ እንደ ሚስት፤ እንደ ፓለቲከኛ፤ እንደ ምሁር፤ እንደ ሰባኪ፤ እንደ መንግሥት ኃላፊ፤ ወዘተ “ለካ እንደዛ ነን” እንድንል አድርጎናል። ባለፉት ፭ ወራት በመጦሞሪያው ላይ ያነበብናቸው ከታች የተመለከቱትን ርዕሶች ስንወስድ እንደ ግለሰብ፤ እንደ ቡድን፤ እንደ ቤተ ክርስቲያንና እንደ ሀገር ማድረግ ያልነበረብንን፤ የነበረብንን፤ የሌለብንና ያለብንን አሳይቶናል- በመንፈሳዊ፤ በማኅበራዊ፤በኢኮኖሚያዊና በፓለቲካዊ መስኮች።

1)    ችግር ነን መፍትሔ ?
2)    ባርባራ እና ስቴፈን
3)    የሆስፒታል ቫይረስ
4)    ኳሱን አትንኩብን
5)    የመፍትሔ ሃሳቦች
6)    ኑ እንፍጠር
7)    መታረቅ ወይስ መታረቅ
8)    የብርጭቆው ወይስ የምንጩ ውኃ
9)    ቅኝ አልተገዛንም?
10)    ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው
11)    የአንድ አባት ምክር
12)    ሰው በቁሙ ሐውልት ለምን ያሠራል?
13)    ስላላደረግክልኝ ነገር አመሰግንሃለሁ
14)    ማረፊያ
15)    በአንድ ሱቅ ታዛ ሥር
16)    በሰይጣን እጅ የወደቀ ቅርስ
17)    ጤፍ እና እንጀራ
18)    አለቃ ገብረ ሐና በፎቶ
19)    ኤልዛቤል ከታሪክ አንድ ገጽ
20)    171ኛው ሆስፒታል
21)    ሦስተኛው ወር
22)    ወንበሩ ነው እንዴ?
23)    የዓለም ዋንጫ በኢትዮጵያ
24)    ዝምታ ወርቅ አይደለም
25)    ተሳቢ
26)    ሰበር ዜና
27)    አለቃ ገብረ ሐና ተረት ናቸው እውነት
28)     ፕሮፌሰር ሳቤክ
29)     ሀገር እንወዳለን
30)    100%
31)    ልዩ መርሐ ግብር ከግንቦት 10 እስከ 12
32)    ፊደል እያለው የማያነብ ማነው?
33)    ገንዳ
34)    የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎች ታሪካዊ ፋይዳ
35)    ባልን ማን ፈጠረው?
36)    የመቅደላው ጌታ
37)    መንፈሳዊ ወይስ መንፈሳይ?
38)    ለዘብተኛነት/ሊበራሊዝም/፡የክርስትና ዘመናዊው ጠላት
39)     ባሕር ዛፍ
40)     አሜሪካን ያገኛት ማነው?
41)    የኔ ጀግና
42)    ጲላጦስ
43)    ገድለ ዜና ማርቆስ የያዛቸው መረጃዎችና ሁነቶች
44)    መመረሽ፣መፈረሽ፣መደንበሽ
45)    ቶም እና ጄሪ
46)     ለምጣዱ ሲባል
47)    ይምርሃነ ክርስቶስ- የተሠወረ ሥልጣኔያችን  
   

ጥናቶቹ እንድናውቅ፣ ወጎቹ እንድንቆጭ፤ እንድንሰተካከል፤ እንድንበረታ፤ እንድንለወጥ የሚያደርጉ ለመሆናቸው በየወጉ ሥር ወዲያውና በገፍ የሚጻፉትን የአንባቢያን አስተያየቶች የማያመልጠን ሁሉ የምናውቀው ነው። ይህን ጽሑፍ በምጽፍበት ሰዓት በዳንኤል ክብረት መጦመሪያ ገበታ ከመጋቢት መጨረሻ እስካሁን ወደ ፪ ሺህ ፮ መቶ ፳ አካባቢ አድናቂና አመስጋኝ አስተያየቶች ተጽፈዋል።  በአጭሩ ዳንኤል ክብረት ኢንተርኔት ውድና ቀሰሰተኛ ከሆነባት አዲስ አበባ ሆኖ በመደበኛነት በሳምንት ሁለት ጊዜ ከሚያወጣልን ወግና ጥናታዊ ጽሑፍ አንጻር ባለውለታችን ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

እኔ በግሌ ዳንኤል ክብረት “የኢትዮጵያ ማኅበራዊ የጽሑፍና የነቢብ ተግባቦት ዓይናማ ኃያሲ” (Master Thinker of Ethiopian Social Discourse) እንደሆነ አፌን ሞልቼ እመሰክርለታለሁ። በዛም እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ። በደጀ ሰላም ያነበብኩትን ወ/ሮ እጅጋየሁ በተባሉ ግለሰብ ዳንኤል ክብረት ላይ ያነጣጠረው የ“ወኅኒ” ትወርዳለህ” ማስፈራሪያ የማየውም ከላይ በአጭሩ ካቀረብኩት የዳንኤል ክብረት በጎ ማንነት አንጻር ነው። የማይናደፈውን ለመንደፍ መነሳት ምን ሊባል እንደሚችል አይገባኝም።

የወሮ እጅጋየሁና መሰል ግለሰቦችና ቡድኖች አካሄዶችና ማስፈራሪያዎች (የሚፈራ ቢገኝ)  የዳንኤል ዓይነት ብዕሮችን ለማሸማቀቅና አፍ ለማዘጋት ታስቦ ሊሆን ይችላል። የዳንኤል ብዕር ሀገረ ጽሕፈት ደግሞ የ፹፪ ሚሊዮን ሕዝብ ዕጣ ፈንታና አቅጣጫ እንጂ ወይዘሮ ወይም አቶ እገሌ እንዳልሆነ መግለጽ ከላይ ያልኩትን መድገም ይሆንብኛል።

የዳንኤል ክብረት አይነት ዓይናማ ብዕርን አሸማቅቆ ሸውራራ ወይም ማየት የተሳነው ለማድረግ  ያለመ የማስፈራራት ሙከራ በአጭሩ ሳይቀጭ ቀርቶ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም ከተበረታታ ተጠቃሚ የሚሆኑ አናሳዎች፤ ተጎጂ የምንሆነው ደግሞ በሦስት ቤቶች የምንገኝ ብዙኃን ነን። ከሚከተሉት ሦስት ቤቶች ያለን ሁሉ ይህ እንዳይሆንና ጦሱም ለኛ እንዳይተርፍ የድርሻችንን መወጣት አለብን።

፩) ቤተ ክህነት
የአስተዳደር ጥበብ፤ ሕግ የማውጣትና ለሕግ የመገዛትን አስተምህሮ ብቻ ሳይሆን በሕይወት ማሳየት ብዙ የሚጠበቀው ከቤተ ክህነት ነው –  ቤተ ክህነት የሞራል የበላይነቱና መሣሪያዎቹ አለውና። የአስተዳደር ብልሹነት፤ ሕግን አለመከተልና ለሕግ አለመገዛት ከዛው አካባቢ እንደአሁኑ ግራ በሚያጋባ መልክና መጠን ጎልቶ ሲታይ ግን እጅግ አስቸጋሪ፤የክርስቶስን ስም የሚያሰድብ፤የአርአያ ያለህ የሚያሰኝ ነው። የቤተ ክህነት የተጻፈና ያልተጻፈ አሠራር የማያውቃቸው ግለሰቦች ወሳኝ አዛዥና ናዛዥ መሆናቸው በቤተ ክህነት በኩል ቅቡል ተደርጎ ከተወሰደ ብሎም መነሻውና መድረሻው እዛው አከባቢ ከሆነ ለራሱ ለቤተ ክህነት ብቻ ሳይሆን ቀጥለው ለተጠቀሱት ሁለት ቤቶችም አደገኛ ነው። ስለዚህ ከላይ እስከታች ያሉት የቤተ ክህነት አስተዳዳሪዎች፤ ቅዱስ ሲኖዶስንና ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ አስፋልት ላይ እንደተበተነ ድንች ቅጥ ያጣውን አሠራር ሳይውል ሳያድር ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።

፪) ቤተ መንግሥት
ከመንግሥት የሁሉንም ዜጎች (የተፈረደባቸው ወንጀለኞችም ጭምር) መብትና ደኅንነት ማክበርና ማስከበር ይጠበቃል። በተለይ ለሀገር ለወገንና ለትውልድ ግድ የሚላቸው ሰዎች – እንደ ዳንኤል ክብረት ያሉትን ደኅንነት መጠበቅ ደግሞ መጠነ ሰፊና ተሻጋሪ ጠቀሜታ አለው። የተለየ ሀሳብ የማስተናገድ ባህል የቆረቆዘበት ህብረተሰብ መሐል የነዳንኤል ክብረት ብዕሮች ልዩነትን የማስተዳደር ባልትና ላይ የተካኑ ባለሞያዎችን ለማፍራት እጅግ ወሳኞች ናቸው። ከእንደዚህ ዓይነት ዕድገት ደግሞ የሀገርና የሕብረተሰብ  ደኅንነትና ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ተጠቃሚ ነው። በተቃራኒው ደግሞ የነዚህ ዓይነት ዜጎች በ”ይመስላል”ና በ”ይሆናል” ለማስፈራሪያና ከዛም ሊዘል በሚችል አደጋ መጋለጥ ሌላውን ዜጋ የበለጠ ያሸማቅቃል። በነጻ እንዳያስብ ይገድባል። ግለሰቦች ሁሉን ሰው አቃፊ ፤ በጎ ሥራን-ደጋፊ፤ መጥፎ ሥራን-ነቃፊ የሆነውን ዳንኤል ክብረትን በማን አለብኝነት ለማስፈራራት የማይመለሱ ከሆነማ እኛስ ምን ዋስትና አለን ያሰኛል። ይሄ ደግሞ ለመንግሥት ምቹ ሊሆን አይችልም። በተለይ ደግሞ መንግሥት ሕግ ለመተርጎም (ለምሳሌ ወኅኒ የሚወርደውንና የማይወርደውን በሕግ ለመለየት) የሚጠቀምባቸውን አካላት ግለሰቦች ሌሎችን ለማሸማቀቅ (በንድፈ ሀሳብም ደረጃ እንኳን ቢሆን) ማሰባቸና መድፈራቸው የመንግሥትን አሠራር የሚፈታተን ነው። ስለዚህ መንግሥት ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶት እንደነዚህ ዓይነት ግሰለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን “ሃይ” ሊል ይገባል።

፫) ቤተ ሕዝብ
ዳንኤል ክብረት እንደ ባለቤትም እንደ ጸሐፊም የሱ ባልሆነው ገጸ ድር ላይ በወጡ የሱ ባልሆኑ ጽሑፎች መነሻነት ነው “ስሜን የሚያጠፋ ነገር ጻፍክ” የሚል ማስፈራሪያ የደረሰው። ብርቱውና ዓይናማው ጸሐፊ ላይ እንዲህ ሲደርስ በአዲስ ነገር እናነበው ለነበርነው፤ ሮዝ መጽሄት ላይ ለሚያነቡት፤ መጻሕፍቱን ለምናነብ፤ በሸገር ራዲዮ ለምንሰማው አሁን ደግሞ በስሙና ከነፎቶግራፉ በሚጽፍበት ገጸ ድር ላይ በሳምንት ሁለት ቀን በሚያቀርብልን የቁም ነገር ድግስ ለምንታደመው ቤተ ሕዝብ ይህ ማስፈራሪያ ችላ ልንለው የማንችለው ነገር ነው። ለምን? የምንወደውንና ዋጋ የምንሰጠውን ነገር የሚነሳንን ግለሰብም ሆነ ቡድን ብቅ ማለት ደስ አይልማ። የዳንኤልን ጽሑፎች በማንበብ ሩሃችንን ስናረካ የነበርነውናን እያረካን ያለነውን ሰዎች ሁሉ ከእርካታችን ምንጭ የሚያቋራርጠን ነገር መፍቀድ አይቻለንም። ስለዚህ በያለንበት ዳንኤላዊ ብዕሮችን ለማድረቅ የሚደረግ ማንኛውም አይነት ሙከራን በመቃወም ማክሸፍ ይጠበቅብናል። ቤተ መንግሥቱም ቤተ ክህነቱም በሥጋም በነፍስም ለቤተ ሕዝብ ጥቅም መቆማቸውን በተግባር ማሳየት ይጠብቅባችኋል የሚል መልእክት ልናስተላልፍላቸው ይገባል። 

ከደጀ ሰላም፦
 
ዶ/ር ጌታቸውን ስለ ፍጡነ-አፖሎጄቴክነታቸው ከልብ እናመሰግናቸዋለን። ዶ/ር ጌታቸው ካናዳ በሚገኘው በዩኒቨርስቲ ኦፍ ካልጋሪ ተባባሪ ፕሮፌሰርና ቼይር ናቸው
http://www.ucalgary.ca/evds/people/faculty/assefa። እርሳቸውን ለማግኘት እነሆ በዚህ መጠቀም ይቻላል።
[email protected]