አያ ጅቦ ሳታመኻኝ ብላኝ ሀገር ወዳዶችን አንገት ለማስደፋት የሚደረገው የጮሌዎች ዘመቻ ዋቆ ዘጅማ

ዘመኑ ላፈራው የመረጃ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ሰዎች ሀሳባቸውን ስፋት ላለው አድማጭ ወይም አንባቢ ለማድረስ አንድ ኮምፒዩተርና በደቂቃዎች ብቻ የሚቆጠር ጊዜ በቂ መሆኑ አለማችን በኛ ዕድሜ ያሳየችው ታላቅ እምርታ ውጤት ሲሆን የሰው ልጅ ህይዎትም ፈጣን መሻሻልን በማሳየት ይገኛል። ይህ የእድገት ርምጃ በአብዛኛው ዕሰየው የሚያሰኝ ግኝት መሆኑ ባያጠራጥርም አላግባብ ከተጠቀሙበት ጉዳቱ በቀላሉ የማይገመት ይሆናል።

በመሰረቱ እኔ ያለኝን የሥነጽሁፍ ድክመት ሰበብ እያደረግሁ ከአናባቢዎች ጎራ ራሴን መድቤ ብኖርም አቶ በቀለ ንጋቱ የተባሉ ጸሃፊ “ዛቻና ስድብ፤ የኢሕአፓ ፖለቲካ” በሚል ርዕስ በኢትዮሚዲያ ለንባብ ያበቁትን ጽሁፍ ካነበብኩ በኋላ የተሰማኝን ለመግለጽ ፈራ ተባ እያልኩ ብዕሬን አነሳሁ።

እንደ ጸሐፊው አባባል አንድ ስሙ ያልተገለጸ የኢሕአፓ አባል ለዶር ጌታቸው ዛቻ ስለላከ ኢሕአፓ ሀላፊነቱን ይወስዳል የሚል ማጠየቂያ (logic) ይዘው የቀረቡ ይመስላል።

1ኛ፦ ለብዙዎች ኢትዮጵያውያን ወቅታዊው አሳሳቢ ጉዳይ ሀገር እንጅ አንድ ግለሰብ (ለዚያውም መብቱን በህግ ለማስጠበቅ አቅሙ ያለው) አይደለም። እንደዚህ ዓይነት ዝባዝንኬዎች ከሀገራዊ አጄንዳ ፊታችንን አዙረን ለርስ በርስ ሽኩቻ እንድንጠመድ ይጋብዙናል።

2ኛ፦ ጸሐፊው የጥብቅና ሙያ ካላቸው በፍርድ ቤት ጉዳዩን ማስተናገድ እንጅ በስማ በለው ዶር ጌታቸውን ተክተው የመናገራቸው አግባብነቱ አልታየኝም።

3ኛ፦ ዛቻውን ጻፈው ያሉን አንድ ስሙ ያልተገለጠ ግለሰብ እንጅ እንደ ድርጅት ኢሕአፓ አለመሆኑን ከጽሁፋቸው መረዳት ይቻላል። ታዲያ የግለሰብን ጉዳይ ከድርጅት ጋር ማያያዛቸው “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” አይሆንባቸውም እንዴ።

4ኛ፦ ወደድንም ጠላንም አንድ ግለሰብ (ዴሞክራሲ በሰፈነበት ሀገር) ለአመራር የሚበቃው ከሌላው አባል የተሻለ የአመራር ክኅሎት፡ የዳበረ ልምድ፡ የጠለቀ ዕውቀትና ተሰሚነት ሲያገኝ ብቻ ነው። ይሁንና ጸሐፊው የኢሕአፓ መሪ ያሏቸውን ሲያጣጥሉና ሲዘልፉ ይስተዋላል። ታዲያ እርሳቸው “ዛቻ ጻፈ” ብለው ቡራ ከረዩ ከሚሉበት ግለሰብ በምን ተሻሉ? ካልተሳሳትኩ ኢሕአፓን የመሰለ አንጋፋ ድርጅት ብዛት ያላቸው አባላትና ደጋፊዎች ይኖሩታል ብዬ እገምታለሁ። ታዲያ እነኝህ አባላት ከርሳቸው የተሻለ የማስተዋል ችሎታ እንደሌላቸው ዝቅ አድርጎ መመልከት አይሆንባቸውም? ትልቅ ድፍረት ይመስለኛል። ለመሆኑ አቶ በቀለ ንጋቱ ስንት ሰው ያውቃቸዋል? ምንስ ሀገራዊ ሃላፊነት እየተወጡ ነው? ለምሳሌ እኔ ከዛሬ በስተቀር ስማቸውን ሰምቼ አላውቅም። አንድ ሰው ከአይኑ ሥር ያለውን እርፍ የሚያህል ጉድፍ ሳያይ እንዴት መርፌ የሚያክለውን የሌላውን ጉድፍ ሊያይ ይቻለዋል ነው ያለው መጽሐፉ?

5ኛ፦ እኔ የኢሕአፓ አባል ስላልሆንኩ ዓላማዬ ኢሕአፓን ወክዬ ለመሟገት አይደለም። በተለይ ቅር የተሰኜሁባቼውና ሃላፊነት የጎደለው አነጋገር ነው ብዬ የወሰድኩት ነገር ቢኖር፤ ለሕዝባቸው ነፃነት፡ ዴሞክራሲ፡ ፍትሕና አንድነት ብለው ከወሮበላ ፋሽስት አገዛዝ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ውድ ሕይዎታቸውን ለኢትዮጵያ ሀገራቸው ቤዛ ያደረጉ እልፍ አዕላፋት ብርቅዬ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ላይ “ሲመች ግድያ” በማለት የፃፉት ስላቅ የስንት የሃዘን ማቅ የለበሱ ኢትዮጵያውያንን አንጄት እንደሚያሳርር አልገባቸውም ወይስ በቁስላችን ላይ ጋሬጣ ለመሰንቀር ነው? ሁለት ሸበላ ወንድሞቹን ካጡት አንዱ ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ነኝ እኮ። ለርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ እስከ መቼ ድረስ በሰማዕታት በድን ላይ ቁማር እንጫዎታለን? ግፍ አይሆንም?

በኔ እይታ ጸሐፊው ለዶር ጌታቸው ተላከ በተባለው ዛቻ አስታክከው ሊያስቆጥሩት የፈለጉት በቀል እንዳለ መገመት አያዳግትም። እውነት ነው በኢሕአፓ ተሰልፈው እምብይ ለአምባገነን አገዛዝ ብለው ታላላቆቼ ከሌሎች ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ጋር ለሀገራቸው ውድ ህይዎታቸውን ከፍለዋል። ከዚያም አልፎ ለአቅመ አዳም ደርሼ የሀገሬን ፖለቲካ እንደተከታተልኩት በኢትዮጵያዊነት ራዕይ ላይ የማያዎላውል አቋም ያለውና የተትረፈረፈ ንዋየ ፖለቲካ ያከማቼ የፖለቲካ ድርጅት ኢሕአፓ ነው ቢባል ስህተት አይደለም። በኔ እይታ ወያኔ፡ ሻዕቢያና ሌሎች የብሄር አቀንቃኞችን በተመለከተ የጠራ ግንዛቤና በቂ ዕውቀት ያለው ድርጅት ነው። ወያኔ ወደ በትረ መንግሥቱን መቆናጠጡና መዘዙ፡ ሊያካሄድ ያቀዳቸውን የይስሙላ ምርጫዎች አስመልክቶ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ትክክለኛውን ግምገማ ያቀረበ ኢሕአፓ ብቻ ነበር ለማለት ያስደፍራል።

ለኔ ዘወትር የሚገርመኝ የሀገራችን ድርጅቶች በተቋቋሙ ምሽትም ሆነ 3 አባላት ብቻ ይዘው የተቃውሞ ምሳራቸውን የሚያነሱት በኢሕአፓ ላይ መሆኑ ነው። እስካሁን በሀገራችን ፖለቲካ ብቅ ጥልቅ ያሉ ድርጅቶች ኢሕአፓን በሆነ ባልሆነው ከመኰነን ይልቅ ጠጋ ብለው ለሢሦ ክፍለ ዘመን ካዳበረው ልምዱ ለመካፈልና ተደጋግፈው ለመስራት ቢጥሩ ኖሮ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን የዘረኛ ቡድን መፈንጫ ባልሆነች ነበር። በጣም የሚያሳዝነው የሀገራችን ፖለቲከኞች ተሞክሮ ካላቸው ድርጅቶች ከመማር ይልቅ እነሱን በማጣጣልና ከኛ በላይ ላሳር በሚል ትምክህት የራሳቸውን ዕድሜ ከማሳጠራቸው በላይ የሀገራችንንም ፍዳ አራዝመዋል።

ትክክል ነው ኢሕአፓ ለዘመናት የቆመለትን የሀገር ሉዓላዊነት፡ እኩልነትና ፍትሕ ዓላማ የሚያፋልስ ካለ በቃላት ልውውጥ ብቻ ሳይሆን አሁን በዘመን አመጣሹ ቋንቋ “ሁለገብ ትግል” ሲፋለም ቆይቷል። ከደርግና ከወያኔ ጋር ያደረገው ትግል የዚህ መርህ ነጸብራቅ ነው። ከብሔርተኞች ጋር ያለውም ልዩነት የሚቀዳው ከዚሁ ተመሳሳይ የመርህ ምንጭ ነው። ቅን ለሆነ ኢትዮጵያዊ ይህ አቋሙ ደግሞ ሊያስወድሰው እንጅ ሊያስወቅሰው የሚገባ አይደለም። ኢሕአፓ ወያኔን ዘረኛ ነህ ለኢትዮጵያ አታስፈልግም ብለን በመዘንነው ሚዛን ለምን የወያኔን ዓላማ ፎቶ ኮፒ ይዘው የሚንቀሳቀሱትን ጭምር አንመዝናቸውም? Double standard (አቋም የለሽ) አትሁኑ ማለቱ የት ላይ ነው ስህተቱ?
በተለይ የግንቦት 7፡ ኦነግና ኦብነግ ፍቅር ከደራ ወዲህ በተለያዩ ክፍሎች በሀገር ወዳዶች ላይ ዘመቻ መከፈቱ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በመቶ አለቃ አያልሰው ደሴ፡ አምባሳደር እምሩ እና በፈረደበት ኢሕአፓ ላይ የስም ማጉደፍና ቅስም መስበር ዘመቻ ተጧጡፏል። ይህ ዘመቻ በተለያዩ የውስጥና የውጭ ተቀጥላዎቻቸው በፕሮጄክት ደረጃ ተይዞ እየተገፋ መሆኑን መገመት አያዳግትም። በፖለቲካ ቁማርተኞች ተቀፍድዳ በተያዘች ሀገር ያደግን ስለሆነ ይህ ተራ ማጨብጨብ ሳይገባን ቀርቶ አይደለም። ከህዝብ ከቶም ሊሰዎር የሚችል ነገር የለምና! ሀገራችን የሰው ያለህ በምትልበት ወቅት ይህንን እኩይ ተግባር የሚቀፈቅፉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች መጨረሻቸው አሳዛኝ እንደሚሆን ለመተንበይ ነቢይነትን አይጠይቅም።

በአሁኑ ወቅት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሀገር ወዳዶች ላይ የተነጣጠረው የስነ ልቦና ዘመቻ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቃጣ የጥፋት ጎዳና ነው። ይህ ደግሞ ለሀገር ወዳድ ድርጅቶች ብቻ የሚተው የመከላከል እርምጃ ሳይሆን ሀገሩን የሚወድ ዜጋን ሁሉ የሚመለከት አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ። ዝምታን እንደ አለማዎቅ የሚገምቱ ካለ ተሳስተዋል። የሀገራችን ጉዳይ የያንዳንዳችንን ጎጆ የሚያንኳኳ እስከሆነ ድረስ በሀገራችን ላይ የምትነግዱና የምታስነግዱ አይበጅም ቢባሉ መታቀብ እንጅ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ብዙም የሚያወላዳ አይመስለኝም። ለነገሩማ ኢሣያስ አፈዎርቂና መለስ ዜናዊ ገና በእንጭጩ “ሳይቃጠል በቅጠል” ቢባሉ ኖሮ ከ80 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለባርነት ባልተዳረገ ነበር። ስለዚህ የሀገርን ጉዳይ እንደተራ ዛቻ የሚመለከቱ ካሉ ከእንቅልፋቸው መንቃት አለባቸው።
ሀገርና ግለሰብ እኩል አይደሉም። አሜሪካውያን ውቅያኖስ አቋርጠው አፍጋኒስታንና ኢራቅ ውድ ዜጎቻቸውን የሚገብሩት የሀገራቸውን ደህንነትና ጥቅም ለማስከበር ነው። ሣይንቲስትም ቢሆን ከሀገርና ከሕዝብ በላይ መሆን አይቻለውም (ለዶር ጌታቸው አክብሮቴ እንደተጠበቀ ሆኖ)። የእርሳቸውን የቴሌቪዢን ዲስኩርም ሆነ መጣጥፎች ተመልክቻለሁ። በድጋሜ ከአክብሮት ጋር ከእርሳቸው ሃሳብ ጋር በፍጹም አልስማማም። ለምን ቢባል አቀራረባቸው ሀገር ለሚባለው ክብደት ያልሰጠ መዘዘ ብዙ ነው። በየትኛውም የፖለቲካ ሀሁ በትጥቅ ጡንቻውን ያፈረጠመና ለአያሌ ዘመናት መገንጠልን ሃይማኖቱ አድርጎ ደም የገበረ ብሄርተኛ ጋር ተመጣጣኝ የኃይል ሚዛን ሳይያዝ በመቶ ሰማንያ ዲግሪ ዞሮ እንዲያይ አደርገዋለሁ ማለት ከምኞት አያልፍም። በታሪክም አልተመዘገበም። በሺሪላንካ መንግሥትና እና በታሚል ታይገር አማጺያን ልዩነት የተደመደመው የአንድነቱ ሀይል የሀይል ሚዛኑን ወደራሱ እንጊያጋድል በማድረግ ነው። በሀገራችን የኤርትራ ጉዳይ የተበላሸው የአንድነት ሀይሉ ቦታ ስላልተሰጠው ነው። ስለዚህ ግንቦት 7ም ሆነ ዶር ጌታቸው ያላዩት ነገር ቢኖር አሁን የተያዘው እርምጃ የአንድነት ኀይሉን ማዳከም ነው። እውነተኛ ሀገር ወዳድ ከሆነ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የሚጠበቀው መጀመሪያ የራሱን ቤት ማጽዳት ነው። የመጀመሪያው የቤት ሥራ በኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነት፡ የሕዝቧን አንድነትና የዴሞክራሲ የበላይነት የሚያምኑትን በተለይም እነኝህ ብሐርተኞች እንወክለዋለን ከሚሉት ክልሎች በቋንቋ ቢደራጁም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እስካመኑ ድረስ እነሱን ማጠናከሩ ለጽንፈኞቹ መለሳለስ መንገድ ጠራጊ ነበር።
የግንቦት ሰባት ሆነ የዶር ጌታቸው አካሄድ ጋሪውን ከገረሱ ያስቀደመ ነው። በተለይ የወያኔንና በሻዕቢያ ጉያ የተኰለኰሉ ጽንፈኞችን ቅድመ ታሪክና ተጨባጭ ሁኔታ ያልመረመረና ያላገናዘበ ነው። ይህን ህፀፅ ተመልክተው ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች አግባብ አይደለም ብለው ድምጻቸውን ቢያሰሙ ስማቸውን በማጉደፍና በጠላትነት በመፈረጅ መንቀሳቀሱ የሚያተርፍ ቢኖር ወያኔና ዘረኝነት ናቸው። በተለይም እኔን የመሰለውን ተራ ዜጋ የሚያስቆጣና ለወያኔም ዱላ እንደማቀበል ይቆጠራል። አንድ የግንቦት 7 ደጋፊ ይህንን አቁዋሜን በመቃዎም ብርሃኑም ሆነ ጌታቸው ዶክተሮች ናቸውና ፖለቲካ ያውቃሉ አንተ መሃይም ስለሆንክ እነሱን መስማት አለብህ ብሎ ፃፈልኝ። የኔም መልስ የቢዝነስ ወይም ኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ ሁሉ ሚልዮነር አይደለም። መረጃ፦ Rich Dad Poor Dad; Robert T. Kiyosaki ነበር።

ከአክብሮት ጋር
ዋቆ ዘጅማ