ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝቦቿ በአስቸኳይ የአለም አቀፍ ምግብ እርዳታ ስር የምትገኝ አገራችንን የሚመሩ የወያኔ ባለሥልጣናት “በአገራችን ረሃብ የለም” ማለት እንደጀመሩ ተዘገበ

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በሚከተለው የተሳሳተ የኢኮኖሞ ፖሊሲ ምክንያት ረሃብ አገራችንን ላለፉት 20 አመታት በተከታታይ ማጥቃቱ በድፍን አለም እየታወቀና፤ በየአመቱ ቁጥራቸው ከ4 ነጥብ 5 እስከ 15 ሚሊዮን የሚደርሱ ህዝቦቿ በአለም አቀፍ የምግብ እርዳታ የዕለት ህይወታቸውን እያቆዩ ባሉበት አገር የወያኔ መሪዎች አንድም ረሃብተኛ የለም ሲሉ መናገር መጀመራቸውን የወያኔ ዜና ማሰራጫዎች ዘግበዋል።

የአገዛዙ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ከሁለት ሳምንት በፊት በአገሪቱ ውስጥ በረሃብ የሚሞት ሰው የለም ብሎ በአደባባይ ከተናገረ ወዲህ እያንዳንዱ የወያኔ ባለሥልጣን እንደገደል ማሚቶ እያስተጋባ ያለው ይህ አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ አይነት የጅል ቅጥፈት፤ ዕድገትና ልማት በአገሪቱ ውስጥ አስፍነናል የሚለው የወያኔ ፕሮፖጋንዳ በየአመቱ በረሃብ እንደቅጠል የሚረግፈውን ህዝብ ቁጥር ሊደብቅ ባለመቻሉ ለማደናገሪያ የተፈጠረ ሌላ ዘመቻ መሆኑ ታውቆአል።

ሰሞኑን ኢትዮጵያን ጎብኝተው የተመለሱ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ባለስልጣናት አስቸኳ መፍትሄ ካልተገኘ በስተቀር በርሃብ የተነሳ በኢትዮጵያ ብዙዎች ሊያልቁ ይችላሉ በማለት ስጋታቸውን በሚገልጹበት ባሁኑ ሰዓት፤ ዘረኛው መለስ ዜናዊ ራሱ በፈጠረው የረሃብ አደጋ የፖለቲካ ምስሉ እንዳይበላሽበት ከሹመት በሚገኝ የስልጣን ትርፍራፊ በዙሪያው ያሰባሰባቸውን ሆድ አደሮች በውሸት ዘመቻው ተሳታፊ አድርጎአቸዋል። ባለፈው ሃሙስ (ነሀሴ 12 2003 ዓ/ም) ምሽት ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል በአገራችን ድርቅ እንጂ ረሃብ የለም በማለት በግብርና ምንስቴር የአደጋ መከላከል ዝግጁነትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ምንስትር ዴታ ተብዬው ምትኩ ካሳ ያደረገዉ ንግግር ባለፉት 20 የወያኔ አገዛዝ አመታት በደረሰው የረሃብ አደጋ ህይወታቸው የተቀጠፉ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውን ለማቆየት ሲሉ ከአለም አቀፍ የምግብ እርዳታ መስጫ ጣቢያዎች የእለት ጉርሳቸውን ለመቀበል እየጎረፉ ያሉትን ዜጎች ኢትዮጵያዊነት የሚክድ ነው።

በ1966 በአገራችን ደርሶ በነበረው ተመሳሳይ የረሃብ አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደቅጠል ሲረግፉ ንጉሱና በዙሪያቸው የተሰበሰቡት መኳንንቶች ልክ እንደዛሬው የወያኔ ባለሥልጣናት በአገራችን ምንም አይነት ረሃብ የለም በማለት ይክዱ እንደነበረ ታሪክ መዝግቦታል።

ይህ በዚህ እንዳለ በደቡብ ኢትዮጵያ ያለዉ የረሀብ አደጋ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ:: በደቡብ ሶማሊያ ለተከሰተዉ የረሃብ አደጋ ከፍተኛ ትኩረት ስለተሰጠዉ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚታየዉ የምግብ እጥረት እጅግ የከፋ መሆኑን በዉል እንዳይታወቅ አድርጎታል ሲል አሶስየትድ ፕሬስ የዜና አገልግሎት ገለፀ።

በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናት በየእለቱ ወደ እርዳታ መስጫ ጣቢያዎች በመጉረፍ ላይ እንደሚገኙም ታውቆአል።ሸበዲኖ በተባለዉ የምግብ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች እንደገለፁት ከአመት በፊት በምግብ እጥረት የተጎዳ ሰዉነት በአማካይ የነበራቸዉ ህፃናት ቁጥር አነስተኛ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥሩ ከ9 እጥፍ በላይ ጨምሮአል ተብሎአል። ደቡብ ክልል በቁጥር ብዙ የሆኑ የብሄረሰብ አባላት ያሉበት ክልል ሲሆን በእያንዳንዱ ቤተሰብም ከስድስት ሰዉ በላይ ከመገኘታቸዉ ሌላ በመንግሰት የተያዙ አነስተኛ የእርሻ መሬቶችን በማረስ የሚተዳደሩ መሆናቸዉ ተገልጿል።

እንደዜና ምንጩ ዘገባ የመጪዉ የዝናብ ወቅት ሁኔታ በትክክል ስለማይታወቅ በመጪው አመት ባካባቢዉ ምን ያህል ሰዉ ለምግብ ርዳታ ይጋለጣል የሚለዉን መገመት አልተቻለም። ሆኖም በአገራችን ምንም ረሃብ የለም በማለት በረሃብተኛው ችግር መቀለድ የጀመረው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በአሁኑ ጊዜ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ሰዎች ቁጥር 250 ሺህ ብቻ እንደሆነ ይገልፃል።

በሌላ በኩል የአካባቢዉ የግብርና ቢሮ የስራ ሃላፊዎች ለ385 ሺህ ተረጂዎች የርዳታ እህል እንዲላክ ሲጠይቁ የአለም የምግብ ፕሮግራም 700 ሺህ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉ ይናገራል።