የወያኔ ተለጣፊ ፓርቲ መሪዎች ኩብለላ ቀጥሉአል፣ ቶሎሳ ተስፋዬ አገር ጥሎ መጥፋቱ ተዘገበ

ወያኔ በምርጫ 97 ለሽንፈት የዳረጉትን ፖለቲካ ፓርቲዎች ለማፍረስ እንደመሳሪያ ከተጠቀመባቸው ሆድ አደሮች መካከል አንዱ የነበረው ቶሎሳ ተስፋየ፤ በዕውቀት ማነስ ምክንያት የተሰጠውን የአፍራሽነት ተልዕኮ በሚገባ ሊወጣ ባለመቻሉ ለመደለያ ተብሎ ተመቻችቶለት በነበረው የሙስና ቅሌት በመከሰሱ አገር ጥሎ ሊኮበልል እንደ ተገደደ ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ በላከልን ዜና ለማወቅ ተችሎል። የመቶአለቅነት ማዕረግ የነበረው ቶለሳ ተስፋዬ በዶክተር መረራ ጉዲና ይመራ የነበረውን የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ(ኦብኮ) ለማፍረስ ተሰጥቶት በነበረው ተልዕኮ በወያኔ ምርጫ ቦርድ እየታገዘ የኦብኮን ዋና መሥሪያቤት እና ህጋዊ የምዝገባ ፈቃድ ቀምቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን በኦብኮ አባልነታቸው ምርጫ 97 ላይ ተመርጠው በወያኔ ፓርላማ ገብተው የነበሩትን ሳይቀር ለርሱ ተለጣፊ ድርጅት እውቅና ካልሰጡ በቀር በዕጩነት አቅርቦ ላስመረጣቸው ኦብኮና ለመረጣቸው ህዝብ ውክልና አንዳይኖራቸው ለማስደረግ የቻለ ክህደተኛ ሰው እንደነበር ይታወቃል።

ወያኔ የህዝብ ድምጽ በማጭበርበር የእራሱን ሥልጣን ለማደላደል ከተጠቀመባቸው አንዱ የሆነው ቶሎሳ ተስፋዬ የቅንጅትን ውህደት ለማደናቀፍ መሳሪያ እንደነበረው ልዴቱ አያለው ቀደም ሲል ኦብኮ ይገለገልባቸው የነበረባቸውን ማህተሞችንና ሰነዶችን በመውሰድ የራሱን ተለጣፊ ድርጅት ለማቋቋም የፖሊሶች ከለላ ተሰጥቶትና ሽጉጥ ታጥቆ የኦብኮ ጽህፈት ቤት ሠራተኞችን ጭምር አግቶ እንደነበር ይታወቃል።

መቶ አለቃ ቶለሳ ተስፋዬ ኦብኮን በማፍረስ ረግድ ለወያኔ በዋለው ውለታ ምክንያት ዜጎችን በአደባባይ በሽጉጥ ሲያስፈራራና ግልጽ በሆነ የመንግሥት ሃብት ዘረፋ ውስጥ ሲዘፈቅ ዝም ተብሎ እንደነበረ በመጨረሻ ግን ለወያኔ የሚሰጠው አገልግሎት አለመኖሩ ሲረጋገጥ ለክስ እንደተፈለገ በዚህም ምክንያት እግሬ አውጪኝ ብሎ ከአገር እንደወጣ ውስጠ አዋቂዎች ይናገራሉ።

በተያያዘ ዜና ወያኔ ቅንጅትን ለማፍረስ ከተጠቀመባቸው አንዱ የሆነው አየለ ጫሚሶ፤ በቅርቡ አገር ጥሎ መኮብለሉ ተዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።