የሊቢያው አምባገነን መሪ የሙአመር ጋዳፊ ውድቀት ለኢትዮጵያዊያን ትግል ተስፋ ሰጪ ነው ተባለ
እንደዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ ቁንጮ መለስ ዜናዊ በሊቢያዊያን ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ ላለፉት አርባ ሁለት አመታት የሊቢያዊያንን ደም ሲመጠምጥ የነበረው የሙአመር ጋዳፊ አገዛዝ መንኮታኮት መጀመሩንና ከጋዳፊ ሶስት ልጆች ሁለቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሊቢያ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስትና የአለማቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ማረጋገጣቸውን በርካታ የዜና አውታሮች ገልጸዋል።
እንደ ዜና አውታሮች ዘገባ የጋዳፊ ታማኝና ደጋፊ ተደርጎ ይቆጠር የነበረው ሰይፍ አል ኢስላም፣ የሊቢያ አብዮት በተነሳ ማግስት ንቀት የተሞላባቸውን ቃለምልልሶች በመገናኛ ብዙሀን ተገኝቶ ይሰጥ የነበር ሲሆን በርካታ የጦር ሰራዊት እንዳለውም ሲዘገብ ቆይቱአል፣ ፣ ይሁን እንጂ፣ አማጽያኑ ባለፈው ዕሁድ የትሪፖሊን ከተማ አብዛኛውን ክፍል ሲቆጣጠሩ እጁን ለተቃዋሚዎች ሰጥቶ እንደነበረ ሆኖም እስከዛሬ ባልታወቀ ሁኔታ ከነበረበት ቁጥጥር ሥር ወጥቶ በአደባባይ የታየ መሆኑንና የሙአመር ጋዳፊ አገዛዝ ያላከተመለት መሆኑን ሲደነፋ በአልጀዚራ ተሌቪዥን ታይቶአል። ሰይፍ አልእስላም በሊቢያ የተነሳውን ህዝባዊ አብዮት ለመደፍጠጥ በወሰደው የሃይል እርምጃ ከአባቱ ሙአመር ጋዳፊ ጋር በአለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከሚፈለጉት የሊቢያው አምባገነን ተባባሪዎች አንዱና ዋነኛው ነው ተብሎአል።
ቀደም ብሎ በሊቢያ መንግስት የመገናኛ ብዙሃን የጋዳፊ የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆነው ሙሳ ኢብራሂም በጋዳፊ እዝ ሥር 65 ሺ ዘመናዊ ስልጠናን የወሰዱ አስተማማኝ ወታደሮች አሉ በማለት ሲደነፋ የቆየ ቢሆንም አለ የተባለው ሠራዊት ህዝባዊ አመጽ የወለዳቸውንና ምንም አይነት ወታደራዊ ሥልጠና ያልወሰዱትን አማጽያን መቋቋም ተስኖት እየተፈረካከሰ መሆኑ ካለፈው ዕሁድ ጀምሮ አብይ የአለም ዜና ሆናኦል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት በአገር ውስጥ ካሉ ወጣቶች ጋር በሊቢያ ወጣቶች የተሰራውን ታሪክ አስመልክቶ ባደረገው ቃለምልልስ ወጣቶቹ ሊቢያዊያን ባከናወኑት ታሪክ መማረካቸውንና ኢትዮጵያም ውስጥ ተመሳሳይ ታሪክ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ተዘግቦአል።
ኢሳት በዘገባው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው አርብ ሞት የማይፈሩ ወጣቶች በሚል ርእስ በጻፈው ጽሁፍ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለለውጥ እንዲነሱ ጥሪ ማቅረቡን ገልጾ ተመስገን በጽሁፉ ” ወጣትነት ሆይ! ብትቀበለውም ባትቀበለውም ሀገር ማለት ወጣትነት ማለት ነው። ወጣትነት ደግሞ አብዮት ነው። አብዮትስ? ለውጥ ማለት መሰለኝ። ነውጥ አላልኩኝም። የዛሬ አዛውንቶች የትላንት ወጣቶች ” ተራራን አንቀጥቅጠው ነጻ እንዳወጡ መቼም ቢሆን ከልብህ እንዳታወጣው። ሞት አይፈሬ እንደነበሩም እንዳትረሳ። ሆኖም ግን ለዛሬ ስራቸው ያንን ድል ማካካሻ አታድርግላቸው። አርአያ አታድርጋቸው። ደርግን ስለጣሉልህ ሳይሆን ለምን ያህል ሰው ስራ ፈጠሩ፣ ምን ያክል ፋብሪካ ገነቡ ብለህ መዝናቸው። ተራሮችን ስላንቀጠቀጡ ሳይሆን የሰሩትን መንገድ ፣ የአስፋፉትን የቴሌ አገልግሎት እና የመሳሰሉትን የልማት ስራዎች መለኪያህ አድርጋቸው። ሀገርን ምን ያህል ለኑሮ እንድትመች እንዳደረጉልህ ገምግም። ምክንያቱም ይሄ ሲሆን ነውና ነው በስልጣን መቆየታቸው ተገቢ የሚሆነው። ይሄ ከብሄራዊ ውትድርና ታደግንህ፣ ከመታፈስ ገላገልንህ፣ ከቀይ ሽብር አተረፍንህ የሚሉትን እርሳው ፣ እሱ ታሪክ እንጅ ዳቦ በሻሂ አይደለምና። ” ማለቱን ገልጹአል። ተመስገን በጽሁፉ ማጠቃለያ ደግሞ ” በዚህ በኛ ዘመን የየትኛውም ሀገር ወጣት በረሀብ ሞቶ አያውቅም። ህግ እስካልጣስክ ድረስ ሞትን አትፍራ። ግፍና ጭቆና የወጣቶች ሸክም አይደለም። ጭቆናና ወጣትነት ከተገጣጠሙ ሰኔና ሰኞ እንደማለት ነው። ወጣትነት አብዮት ነው። ቦአዚዝም ልክ እንዳንተ ወጣት ነበር። ያውም ወጣት የነብር ጣት።” ሲል የኢትዮጵያ ወጣቶች ህግን አክበረው ለለውጥ እንዲነሱ መምከሩ ታውቁአል።