የዘረኛው ወያኔ አገዛዝ ግብርና ሚኒስቴር “ድርቅ እንጂ ረሃብ የለም“ ማለቱ የአገዛዙን ባለስልጣናት በቀቀንነት ያመለክታል ተባለ

የዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ የግብርና ሚንስቴር ሚንስትር ዴታ ተብዬዉ ምትኩ ካሣ አለቃው መለስ ዜናዊ የተናገረውን በመድገም በኢትዮጵያ አሁንም ሆነ ባለፉት ሃያ ዓመታት ድርቅ እንጂ ረሃብ የለም ሲል መናገሩ የአገዛዙ ባለስልጣናት በራሳቸው የማይመሩና ጌቶቻቸው ያዘዙአቸውን ብቻ የሚያደርጉ በቀቀኖች ናቸው ሲሉ አንድ የግብርና ሙያ ከፍተኛ ኤክስፐርት ለዘጋቢያችን ገለጹ፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉና በግብርና ሚንስቴር ውስጥ ለበርካታ አመታት በአግሮኖሚስትነት ያገለገሉት ከፍተኛ ባለሙያ ለዘጋቢያችን እንደገለጹት ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጋር ቃለምልልስ ያደረገው ይኼዉ የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ” በኢትዮጵያ ድርቅ እንጂ ረሃብ የለም”፣ በድርቁ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥርም የፊታችን ጥቅምትና ኅዳር በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል በማለት መናገሩ ባለስልጣናቱ ምን ያህል ህሊናቸውን ሸጠው ለሆዳቸው ያደሩና ለኢትዮጵያ ህዝብ ቅንጣት ታክል እንኩአን ክብር የሌላቸው መሆኑን ያሳያል ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለሙያው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አስራ አምስት ሚሊየን የሚጠጋና በ አገዛዙ በይፋ የተገለጸ ህዝብ በርሃብ ምክንያት የምግብ ርዳታ ጥገኛ ሆኖ በሚገኝበት፣ ከዚህም ውስጥ ወደ አምስት ሚሊየን የሚሆኑት በአስቸኩአይ የምግብ ርዳታ ውስጥ ተካተው በሚገኙበት በ አሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ እንጂ ረሃብ የለም በማለት በአደባባይ መናገር እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ ኤክስፐርቱ እንደገለጹት፣ በግላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በርሃብ አለንጋ እየተቀጣ ያለው ህዝብ ቁጥር አገዛዙ በይፋ ከገለጸው እጅጉን የሚበልጥ እንደሆነ፣ በተለይም ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነት ምክንያት በቀን አንዴ እንክዋን ለመመገብ አቅም ያጡ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመላው ሃገሪቱ ከተሞች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ለኢትዮጵያዊያን ባስተላለፉት መልእክት የወያኔ አገዛዝ እየፈጸመ ካለው ግፍና በደል መላቀቂያ መንገዱ አንድና አንድ ብቻ ነው ይሄውም፣ አገዛዙን ከስልጣን ማስወገድ ብቻ በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡