አንድ ሰሞን ሲጨፈርለት የነበረው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አደጋ ላይ መውደቁ ተገለጸ፣ ጃፓን የረጅም ጊዜ ብድር እንድትሰጥ ተጠየቀች
የአባይ ግድብ ግንባታ ወሬ ከመናፈሱ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያዊያንን ሲያደነቁር የነበረው የአምስት አመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በሃገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን መሰማቱ ከተቋረጠ በርካታ ወራቶች የተቆጠሩ ሲሆን እቅዱም በዕርዳታ ብቻ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ማሳካት ስለማይቻል፣ የጃፓን መንግሥት አነስተኛ ወለድ ያለው በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር እንዲሰጠው ዘረኛው አገዛዝ መጠየቁን ለአገዛዙ ቅርበት ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገበ፡፡
እንደ ሪፖርተር ዘገባ የወያኔው አገዛዝ በአምስት ዓመቱ ለማሳካት ያቀዳቸውን የመንገድ፣ የባቡር ሐዲድና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታዎችን ለማስፈጸም ይችል ዘንድ፣ የጃፓን መንግሥት ከዚህ ቀደም ሲሰጠው ከነበረው ዕርዳታ በተጨማሪ አነስተኛ ወለድ ያለው የረጅም ጊዜ ብድር እንዲሰጥ መጠየቁ ታውቁአል፡፡
የዘረኛው አገዛዝን የትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በውጪ ሃገር የሚገኙ የኢኮኖሚክስ ምሁር በሰጡን አስተያየት ፣ የወያኔ እቅድ ድሮዉንም ቢሆን የምእራባዊያንን ቀልብ ለመግዛት በሚል ያናፈሰው ወሬ እንጂ ፍጹም ተግባራዊ ሊሆን የማይችል እቅድ እንደነበር ይታወቃል ብለዋል፡፡ ወያኔ መጉረስ የማይችለውን ጭብጦ ወደ አፉ ለማስገባት እንደሚሞክር አይነት ሰው ይመሰላል ያሉን እኒሁ ባለሙያ፣ እኔ የታሰበው እቅድ አለመሳካት ምንም አያስገርመኝም፣ ነገር ግን የእቅዱን አለመሳካት አስመልክቶ የወያኔው አገዛዝ የሚሰጠውን ምክንያት ለመስማት በጉጉት እየተጠባበቅሁ ነው በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡
የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ቀደም ብሎ አከናውነዋለሁ በማለት ይፋ አድርጎት የነበረውን የትራንስፎርሜሽን እቅድ የአለም ባንክን ጨምሮ በበርካታ ታዋቂ ምሁራን ሲተች እንደነበረና ተግባራዊነቱ ገና ከጅምሩ ጥርጣሬ አስነስቶ እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም፡፡