ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ለምና ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን መቸብቸቡን ቀጥሉአል፣ ለህንድ ኩባንያዎች 500 ሺህ ሄክታር ተጨማሪ መሬት ሊሰጥ ዝግጅቱ መጠናቀቁ ታወቀ
ኢትዮጵያን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ቀደም ብሎ በብዙ መቶ ሺህ ሄክታር ሸጦለት የነበረውን የካራቱሪ ኩባንያን ጨምሮ 500 ሺህ ሄክታር ለም መሬት ለበርካታ የህንድ ኩባንያዎች ለማስረከብ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ዘጋቢያችን የውስጥ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ፡፡
እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት ይህን የለም መሬት ሽያጭ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ የህንድ ኩባንያዎች ባለንብረቶች አዲስ አበባ መግባታቸውና የጠየቁትንም ያህል ሰፋፊ ለም መሬት ለመስጠት የዘረኛው አገዛዝ ባለስልጣናት ቃል መግባታቸው ታውቁአል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የደረሰን ዘገባ እንደሚያመለክተው ኩባንያዎቹ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳትን የሚያስከትለውን የአበባና ሌሎችም ሰብሎች የማምረት ተግባር የሚያከናዉኑ እንደሆኑ ታውቁአል፡፡
ቀደም ብሎ ካሩቱሪ በመባል የሚታወቀው የህንድ ኩባንያ ለሚያካሂደው ኢንቨስትመንት 300 ሺሕ ሔክታር መሬት መውሰዱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት በሃገሪቱ ምእራባዊ ክፍል በሚገኘው የጋምቤላ ክልል እንዲሁም በባኮ በመቶ ሺዎች በሚቆጠር ሔክታር መሬት ላይ እጅግ በርካታ የአካባቢዉን ነዋሪዎች በማፈናቀል በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሩዝና ሰሊጥ በማምረት ምርቶቹን ወደውጪ አገር በመላክ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
ከእነዚህ የህንድ ኩባንያዎች በተጨማሪ ትልቅ የእርሻ መሬት የጠየቀው የዘረኛው አገዛዝ ጋሻ ጃግሬ የሼክ አላሙዲ ኩባንያ የሆነው ሳውዲ ስታር ሲሆን ለዚህ ኩባንያ ብቻ 500 ሺሕ ሔክታር መሬት ለመስጠት ዝግጂቱ ተጠናቁአል፡፡ ስዉዲ ስታር በአሁኑ ጊዜ ጋምቤላ ውስጥ በ10 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ በሩዝ እርሻ መሰማራቱ ይታወቃል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይም በሊቢያ ከስድስት ወራት በፊት ጀምሮ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ ፍጻሜ እያገኘ ከመጣ በሁኋላና፣ ሊቢያዊያንም እንደቻይና ያሉ ከሙአመር ጋዳፊ ጋር ያበሩ ሃገራትን ኩባንያዎች ይወርሳሉ የሚል ወሬ መናፈስ ከጀመረ ቦኋላ በኢትዮጵያ ኢንቨስትሜንት ያላት ቻይናና ሌሎችም ኩባንያዎች ስጋት ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን በኩባንያዎቹ ውስጥ ተቀጥረው የሚያገለግሉ የውስጥ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ተመሳሳይ የሆነ ህዝባዊ አመጽ ከተነሳ አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ስጋት የገባቸው የነኝህ ሃገራት ኩባንያዎች በቀጣይ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው እያሰቡበት እንደሆነም ተያይዞ የደረሰን መረጃ አመልክቶአል፡፡