ጥምረት ለነጻነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት በሎንዶን ከተማ ባዘጋጀው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ተወካይ ያደረጉት ንግግር ግርድፍ ትርጉም

ክቡራትና ክቡራን፣

በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ንግግር አድርግ ዘንድ ዕድሉን ለፈጠራችሁልኝ የመድረኩ አዘጋጆች በኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባርና በኦጋዴን ህዝብ ሥም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። የወያኔ አገዛዝ በአሁኑ ወቅቱ በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን ጭቆናና በደል አስመልክቶ ሃሳብ ለመለዋወጥና የጋራ ግንዛቤ በማዳበር ይህንን አስከፊ ሥርዓት በጋራ ለመታገል የሚያስችል መፍትሄ በማፈላለግ የኢትዮጵያን የመከራ ቀናት ለማሳጠር ወደሚያስችል የተቀናጀ ትግል ለማምራት እንዲህ አይነት መድረክ ሊኖረው የሚችለው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የተከበራችሁ ተሰብሳቢዎችና ውድ ወገኖቼ፤

ዛሬ ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው የወያኔ አገዛዝ እያካሄደ ባለው አስከፊ ጭቆናና አፈና ከቀደምቶቹ አገዛዞች ሁሉ የከፋ መሆኑን በተገባር አስመስክሮአል። አናሳነቱ በፈጠረበት የስነልቦና ችግር ምክንያትም ከስጋትና ጥርጣሬ በመነጨ ስሜት ጭካኔያዊ እርምጃንና ሽብርን ዋንኛ የሃይል ዜደ አድርጎታል። ወያኔ በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለው አርሜኔያዊ ጭፍጨፋ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት አዶልፍ ሂትለር አደረሰ ከሚባለው የሚስተካከል ነው።

አገዛዙ በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል እየወሰደ ካለው ከዚህ የሸብር ተግባሩ በተጓዳኝ የሐገሪቱን ኢኮኖሚ በማዳሸቅ፤ በደሃው ወገናችን ስም የሚሰበስበውን እርዳታ እህል ለተረጂው እንዳይደርስ በመከልከልና ዜጎችን ከመሬታቸው በማፈናቀል በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ ጦርነት ከፍቶአል። በእንዲህ አይነት የጅምላ ሰቆቃ በኦጋዴን ብቻ እየተፈጸመ ያለው ወንጀል በየትኛውም መመዘኛ የዘር ማጥፋት መስፈርት የሚያሟላ ሆኖአል።

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ 2010 እና 2011 ብቻ ከ20ሺህ በላይ ህዝብ ተጨፍጭፏል፤ ቢያንስ በየቀኑ ከ30 ያላነሱ ሰዎች ይገደላሉ፤ በሺዎች የሚቆጠሩት በእስር ቤት ይማቅቃሉ፤ እንስቶችን አስገድዶ በመድፈር እየተወሰዱ ያሉት የበቀል እርምጃዎች በቃላት መግለጽ ከሚቻለው በላይ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ወገኖቻችን ለከፋ ረሐብ አደጋ በተጋለጡበት በዚህ ባሁኑ ሰዓት ከአለም አቀፍ ህብረተሰብ የሚሰጠው የምግብ እርዳታ እንኳ ለተጎጂው እንዳይደርስ ታግዶአል።ይህ የሚደረገው በዚያ ክልል የሚኖረው ህዝባችን በሙሉ በረሃቡ ምክንያት ህይወቱ እንዲቀጠፍ ነው።

በህዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው መከራና ስቃይ በዚህ ብቻ ሳያበቃ፤ እየደረሰበት ያለውን ዘግናኝ ሰቆቃ ተቋቁሞ እራሱን ለመከላከል እየተፍጨረጨረ ያለውን ማንኛውንም ሰው ለመደፍጠጥ ሲባል መለስ ዜናዊ በክልሉ ያሰማራው ሰራዊት ለወሬ ነጋሪ እንኳ የሚሆን ሰው እንዳይተርፍ ያገኘውን ሁሉ እንዲገድል እና መንደሮችን በሙሉ እንዲያወድም መመሪያ ሰጥቶ እያስተገበረ ነው።

እነኚህ በክልሉ የተሰማሩ የመለስ ዜናዊ ገዳዮች የሚይዙትን ሰው ሁሉ ከሚታወቅበት መኖሪያ ሰፈር 40 እና 50 ኪ.ሜ በላይ ወስደው ስለሚገድሉ የሟች ማንነት የማይታወቅ ብቻ ሳይሆን አስከሬኑም የጅብ ዕራት እንዲሆን እያደረጉ ነው።

እንዳለመታደል ሆኖ! ይህ ጭካኔ የተሞበት ግፍ በዚህ መልኩ እየተፈጸመ መሆኑ በሚታወቅበት በአሁኑ ሁኔታ እንኳ የተባበሩት መንግስታትና ም ዕራባዊያን ለጋሽ ሀገራት ከወያኔ ጋር ያላቸው መልካም የኢኮኖሚ ትብብር ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊያላሉ ቀርቶ አጠናክረው ለመቀጠል የወሰኑ ይመስላል። በዚህም የተነሳ በህዝባችን ላይ እየፈጸመ ባለው ወንጀል እጠየቃለሁ የሚል ስጋት ወይም ፖለቲካዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንደማይኖርበት ስላወቀ በእኩይ ተግባሩ ገፍቶበታል።

በተመሰሳይ ሁኔታ የመለስ አገዛዝ ከቻይና በሚያገኘው የቴክኖሎጂ ድጋፍ ነጻ የሆኑና የተቃዋሚዎች ሃሳብ የሚገለጽባቸውን መገናኛ ብዙሃኖችን በማፈን ህዝቡ የነጻ ፕሬስ ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረገ ነው። ቻይና ለምትሰጠው ለዚህ ውለታዋ የኦጋዴን ዘይትና ነዳጅ በገጸበረከትነት ተሰጥቶአታል።

መለስ የኢትዮጵያን ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ብቻ ሳይሆን ለውጪ ባለሐብቶች እየቸበቸበ ያለው ፤ ኦጋዴንን በሃያ አንድ ቦታ ሸንሽኖ ለቻይናና ለሌሎችም እያጫረተ ይገኛል።

በመሆኑም ህዝባችንን ከወያኔ መንጋጋ ለማውጣት የውጭ ጣልቃ ገብነትን የምንጠብቅበት ምንም ምክንያት ስለሌለ ያለን ብቸኛ አማራጭ እየሆነ የመጣው እራሳችንን በራሳችን ነጻ ለማውጣት ያለንን ሃብት፤ እውቀትና ጉልበት በማቀናጀት ወያኔንን በተባበረ የጋራ ትግል ለአንዴና ለመጨረሻ ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን ለማስወገዱ መነሳት ይኖርብናል።

የወያኔ አስተዳደር ላለፉት 20 ዓመታት ስልጣን ላይ የቆየው በአስከፊ የጭቆና አገዛዙ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የሆነው ታዲያ በህዝቡ መካከል የነገሰውን ያለመተማመን ስሜትና ፍርሃት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ነው። ምናልባትም በአገራችን የሰፈነውን ፍረሃትና አንዳንድ ቅራኔዎችን ወያኔ ያልፈጠራቸው ሊሆን ይችላል። ከጥንት ጀምሮ በሂደት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ዛሬም ድረስ በአግባቡ ያልተፈታ ችግሮች ስላለን፤ ሁላችንም የእነዚህን ችግሮች መኖር በቅንነት ተቀብለን፤ በልዩነታቶቻችን ውስጥ እንድ የሚያደርጉን የጋራ ጉዳዮች ስላሉ አንድ ላይ ሆነን ዘላቂ መፍተሄ ካልፈለግን በቀር እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የጎሳና የነገድ ክፍፍል እየረገጠ በሽብር እየገዛን ላለው ጨቋኝና አሸባሪ ሥርአት የምንመቻች መሆናችንን ልንዘነጋው አይገባም።

ወያኔ ልዩነታችንን መሠረት በማድረግ ከፋፍሎ ለመግዛት የተጠቀመበትን ስልት መናድ ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ በመካከላችን የተፈጠረው ፍርሃትና ጥርጣሬ መወገድ አለበት፤ ቅራኔያችን በውይይት መፈታት ይኖርበታል። ይህ እርምጃ ነው አምባገነኑን የወያኔ ጨቋኝ አስተዳደር ከስሩ መንግሎ ለመጣል የሚያስችለን።

ያለበለዚያ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ወያኔ በትረ-ስልጣኑን አሳልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ አይኖርም፤እንደ መስፍናዊና መካከለኛው ዘመን ባላባት ሁሉ ስልጣኑን እስከወዲያኛው ተቆጣጥሮ ይዘልቅ ዘንድ ሁኔታዎች ይመቻቹለታል። በሰዎች መካከል ልዩነት መኖሩ ያለና የነበረ የሰውልጅ ተፈጥራዊ ባህርይ ነው።ያም ሆኖ ልዩነትን በልዩነት ተቀብሎ በጋራ ጉዳዮች ላይ በሰለጠነ መንገድ ተባብሮ መስራት መቻል ለችግሮቻችን ምክንያት የሆኑትን በደሎች አስወግዶ በምትኩ ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበትን እድል ለመፍጠር ከሚያስችል የትግላችን ግብ ሊያደርሰን እንደሚል ታሪክ ያስተምረናል። የየግል ፍላጎትን ወደሁዋላ ትቶ ተቻችሎ በጋራ መስራት በሂደት ለድል እንደሚያበቃ ይታመናል።

የኦጋዴን ህብረተሰብና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር የወያኔን ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል። የህብረተሰቡ መብት በአግባቡ እስኪከበር ድረስ በትግላችን እንቀጥላለን።እናም የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር የወያኔን ጥቃት ለመመከት ያላሰለሰ ጥረት ሲያካሂድ መቆየቱን ስገልጽ ከሌሎች ጸረ-ወያኔ አጋር ድርጅቶች ጋር ተባብሮ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ በጽኑ እንደሚያምን ሳልጠቁም አላልፍም። በያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል መሰረታዊ ልዩነት እንዳለ የኛ ግንባር ይገነዘባል።ያም ሆኖ ልዩነትን ተቀብሎ በመግባባትና በመፈቃቀር መስራት ይቻላል ባይ ነው። የጋራ ዓላማችን ይህንን ጨቋኝ ስርዓት ገርስሶ መጣል ነው። ለዚህ ግብም እንደተቃረብን ይሰማኛል።

ድርጅታችን ኦብነግ ያሉንን ልዩነቶች ወደጎን ተወት አድርጎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የወያኔን አገዛዝ መታገል ይቻላል የሚል ጽኑዕ እምነት አለው። ያ ካልሆነ ግን ወያኔ ስልጣኑን ለሌላ ተጨማሪ አመታት ይዞ በላያችን ላይ ሲጨፍር እንደሚኖር አይጠረጠርም። ሁላችንም በሂደት እየፈታናቸው የምንሄድ ችግሮች እንዳሉ እንረዳለን። የአሁኑ ቀዳሚ እርምጃችን መሆን ያለበት በህዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሰቆቃ ማስቆም መሆን አለበት የሚል እምነት አለን። እጅ ለእጅ ተያይዘን ወያኔን በአስቸኳይ ካስልጣልን ማውረድ ካልቻልን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በርህራሄ የለሹ የመለስ አገዛዝ ጭፍጨፋ ህይወታቸውን ማጣታቸው የማይቀር ነው ። ስለዚህ ወያኔን ከዚህ እኩይ ተግባሩ ማስቆሙ ጊዜ የማይሰጠው አስቸኳይ ጉዳይ መሆን ይኖርበታል።

ለማጠቃለል ያህል ወያኔ እጅግ ደካማ ሃይል እንደሆነ ለማስገንዘብ እወዳለሁ። የአገዛዝ ቀንበሩን አስከዛሬ ለማርዘም የቻለውም በኛ መለያየትና መከፋፈል ብቻ ነው። ስለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በዘረ፤ በሃይማኖት፣ በክልል ወይም ፣ በፖለቲካ መስመር ሳይከፋፈል ይህንን አስከፊ የወያኔ አገዛዝ ለመጣል በጋራ እዲነሳ ድርጅታችን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል። በኛ በኩል ህዝብ ለራሱ ነጻነት የሚያደርገውን ትግል ከሚደግፍ የትኛውም ቡድን፣ ድርጅት ወይም ስብሰብ ጋር በጋራ ለመታገልና ህብረት ለመፍጠር ዝግጁ መሆናችንን ላረጋግጥ እወዳለሁ።

አመሰግናለሁ።