እነ ውብሸት ታዬ ላይ ዘግናኝ ድብድባ ተካሄደባቸው

ኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዘደንት የሆኑት አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር “እጅና እግራቸው ታስሮ ለሁለት ቀን ተሰቅለው ሲደበደቡ እንደነበር ለፍ/ቤትና ለቤተሰብ መግለጻቸውን” ልጃቸው ወ/ሪት ሊዲያ ዘሪሁን ለዝግጅት ክፍላችን ገለፀች።

ወ/ሪት ሊዲያ አያይዛ «በአባቴ ላይ ሰብአዊነት የጐደለውና ኢ-ህገመንግሥታዊ የሆነ የጭካኔ ተግባር መፈፀሙ በአጅጉ አሳዝኖኛል፡፡» በማለት ሐዘኗን ገልፃለች፡፡ «ለህግ ቆመናል፣ ህግ አስከባሪዎች ነን ከሚል ተቋም የሚጠበቅ ተግባር አይደለም» ካለች በኋላ «ለሁለት ቀን ታስረው ሲቀመጡ የሕግ አማካሪ እንዳያገኛቸው ተከልክለው በህገወጥና በጭካኔ በተፈፀመ ምርመራ መዝገቡ ወደ ዐቃቢ ህግ መላኩ ቅሬታ ተሰምቶኛል። ጉዳዩን የሰማው ፍ/ቤት ድብደባው እንዲቆምና ህክመና አንደሰጠው ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ህክምና አላገኘም፡፡” ስትል ሥጋቷን ገልጻለች።

በተያያዘ ዜና በተመሳሳይ ሁኔታ ታስሮ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በእስር ቤት በመርማሪዎች ድብደዳ እንደተፈጸመበት ለፍ/ቤት እና ለቤተሰቦቹ መግለጹን ባለቤቱ ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለዝግጅት ክፍላችን ገለፀች፡፡ ወ/ሮ ብርሃኔ እንደገለፀችው “ባለቤቴ ተጠርጠሮ መታሰሩ ቅሬታ ባይሰማኝም ለህግ ቆመናል በሚሉ ፖሊሶች ድብደባ መፈጸሙ በዚህ አገር ያለው የህግ የበላይነትን ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡ ለህግ ቆመናል ለፍትህ እንሠራለን ከሚል አካል የህግ አማካሪ እንኳን እንደያገኘው መከልከሉ አሳዝኖኛል፡፡ የሕግ አማካሪ እንዲያገኘው ለፍትሕ ሚኒስቴር ለፍ/ቤትም አመልክተንም መፍትሔ አላገኘንም” በማለት ቅሬታዋን ገለጻለች፡፡

በተመሳሳይ ክስ ታስራ የምትገኘው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርባ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ስለተጠየቀባት መስከረም 4 ቀን 2003 ዓ.ም. መቀጠሯን ለማወቅ ተችሏል፡፡