ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ‹‹ተጽዕኖ አልባ መሪ›› ተባሉ: አዲስ ጉዳይ መጽሔት
ዛሬ፣ መስከረም ፲፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ለንባብ የበቃው አዲስ ጉዳይ ሳምንታዊ መጽሔት የ፳፻፭ ዓ.ም የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የዓመቱ ምርጦች እየተባለ በሌሎች ኅትመቶች ከወጡት ተቋማትና ግለሰቦች በተለየ አኳኋን በ፳፻፭ ዓ.ም ‹‹ተጽዕኖ አልባ መሪዎች ነበሩ›› ያላቸውን አምስት ግለሰቦችና አንድ ተቋም ለይቷል፡፡
መጽሔቱ ለልየታው የተጠቀመው÷ ግለሰቦቹና ተቋሙ ካለባቸው ሰፊ ሓላፊነት፣ ከተቀመጡበት ወሳኝ ቦታና ከሚጠበቅባቸው ውጤት በተቃራኒ በተገመገሙ ጥቅልና ቀጥተኛ መመዘኛዎችን እንደኾነ በመግቢያው አመልክቷል፡፡ እንደ መጽሔቱ መመዘኛ ተጽዕኖ አልባ ነበሩ የተባሉት መሪዎች፣ በተለይ የሃይማኖት አባቶቹ፣ ባሳለፍነው ፳፻፭ ዓ.ም ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሂደቶች ውስጥ ጉልሕ ሚና ሊኖራቸው ይገባ ነበር፡፡
ነገር ግን፣ ተጽዕኗቸው ጎልቶ አለመውጣት ብቻ ሳይኾን ጭራሹን ከሚጠበቀው በጣም በአነስተኛ ደረጃ እንኳ ያልነበረ መኾኑን በግምገማው አትቷል፡፡ በጥቅልና ቀጥተኛ መመዘኛና በመመዘኛው ላይ ተመሥርቶ በተደረገው ግምገማ በዓመቱ ‹‹ተጽዕኖ አልባ መሪ›› ነበሩ ከተባሉት ውስጥ ፮ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይገኙበታል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በወቅቱ ከሚያስፈልጋት አስተዳደራዊ አንድነት፣ ተቋማዊ ለውጥ እና የዕቅበተ ሃይማኖት ተግባራት አንጻር ምዘናው ለሐራውያን ማንጸርያና መወያያ ሊኾን ይችላል በሚል በመጽሔቱ በቀረበበት መልኩ አስተናግደነዋል – ይመልከቱት፤ ይወያዩበት፡፡
* * *
የሃይማኖት አባቶች በአገራችን ውስጥ ለሚከሠቱ ችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ለማስገኘት የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፤ ነገር ግን የሃይማኖት አባቶች በሚፈለግባቸው መጠን ቀርቶ በተወሰነ ደረጃ እንኳ ይህን የሞራል፣ የዜግነት ይኹን የሃይማኖት ድርሻቸውን ሲወጡ አይታይም፡፡ ይህ በመኾኑም ዘንድሮም በተለይ የሁሉም ሃይማኖት አባቶች ከሚመሩት ምእመን ብዛት አንጻር ተጽዕኖ አልባ ኾነው ከርመዋል፡፡
በተለይ በርካታ ምእመናንን በሥራቸው በማቀፍ የሚታወቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ኾነ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች ሊኖራቸውን የሚገባውን ሚና በአግባቡ መወጣት አልቻሉም፡፡ ይልቁንም ባለፈው ዓመት ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፮ኛ ፓትርያርክ ኾነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በእርግጥ የሥራ ዘመናቸው ለምዘናው አነስተኛ ቢኾንም፣ አቡኑ የቤተ ክርስቲያኗን የውስጥ ችግር ኾነ በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩትን በርካታ ችግሮች ለማስወገድ የሚያስችልና የሚገባ ርምጃ ወስደዋል ለማለት ይቸግራል፡፡
በርግጥ በ፳፻፭ ዓ.ም ፓትርያርኩ ለማከናወን የሚጠበቅባቸው ሥራም ከፍተኛ የኾነበት ምክንያት፣ ቤተ ክህነቱ በእጅጉ መስተካከል የሚገባቸው በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመኾኑ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ለሁለት የተከፈለው ሲኖዶስና በዚህ ምክንያት በየሀገሩ በጎጥና በፖሊቲካ አመለካከት ተከፋፍሎ የሚያመልከው ምእመን ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ሥር የሰደደ ችግር በአጭር ጊዜ አክሞ ማዳን ባይቻልም ፓትርያርኩ ግን ቢያንስ አንድ ፈጣን የሰላምና ዕርቅ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ የሚል ግምት ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር የእምነት መከባበርን በመስበክ ሀገሪቱ በተሻለ ደረጃ መግባባት የሰፈነባት እንድትኾን ለማድረግ ይጥራሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደሚወሳው፣ ቤተ ክህነቷ ከመንግሥትና ከፖሊቲካው ጋራ በእጅጉ ተጣብቃ በአብዛኛው አካሄዷ የመንግሥትን የፖሊቲካ ዓላማ ማስፈጸም የኾነበት ጊዜ እንዲያበቃ የብዙ ምእመናንም ፍላጎት ነበር፡፡ ነገር ግን አቡነ ማትያስ የቀየሩትም ኾነ ሊቀይሩት ያቀዱት ነገር ለጊዜው ያለ አይመስልም፡፡ ፓትርያርኩ እንኳን የፖሊቲካው ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን የሃይማኖት[አስተምህሮ] ሽኩቻ ለመፍታት የአባትነታቸውን ድርሻ በሚገባ አልተወጡም፡፡ እነ እገሌ ተሐድሶ[መናፍቅ] ናቸው እየተባለ የተፈጠረውን የመከፋፈል ችግር ለመፍታት እንዲሁም በእምነቱ ተከታዮች መካከል ያለውን የመፈራረጅ ክፉ ልማድ ለማስቀረት በፍጥነት አልሠሩም የሚል ወቀሳ ከወዲሁ እየቀረበባቸው ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ፓትርያርኩ በሀገር ጉዳይ ላይ እንደ ሃይማኖት መሪ ጣልቃ ሊገቡበት የሚገባ በርካታ ዐቢይ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በመንግሥትና በሙስሊም ማኅበረሰቡ መካከል የተከሠተው ችግር በሰላም እንዲፈታ ለማድረግ የሃይማኖት አባቶች በቀዳሚነት ሓላፊነቱን መውሰድ ይችሉ ነበር፡፡ በዚህ ባለንበት ዘመን የሕዝቦች መብት ሲነካና አለመግባባት ተፈጥሮ የአገሪቱ ሰላም ስጋት ላይ ሲወድቅ በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ያለ አባት ጣልቃ ገብቶ ችግሩን ማርገብ ከሓላፊነቶቹ አንዱ ይኾናል፡፡ አቡነ ማትያስም ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ባላት ሥፍራና ሌሎች የሃይማኖት አባቶችን የማስተባበር ድርሻ ተጠቅመው ከመንግሥት ጋራ መደራደርና ችግሩን በአስታራቂነት ለመፍታት ሰፊ ጥረት ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ ጉዳዩ የእምነት መመሳሰልን የሚሻ ሳይኾን ሰላምን ለማስፈን የሚደረግ መንፈሳዊ ሓላፊነት ብቻ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ ፓትርያርኩ ወደ ማረሚያ ቤት ጎራ ብለው የታሰረ ሲጠይቁና ሲያጽናኑም አላየንም፡፡ በማረሚያ ቤቶች ኾነው መጽናናትን የሚሹ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ከአንድ የሃይማኖት አባት የሚጠበቅ መንፈሳዊ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግሥትን ምሕረት ጠይቀው የተከለከሉ አልያም መንግሥት እልህ የተጋባባቸው ዜጎችም አሉ፡፡ ቢያንስ የነዚህን ዜጎች ጉዳይ እንደ ሃይማኖት አባት መጠን አቤት ማለት ይችሉ ነበር፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ግን ከቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ተልእኮ ውጭ በኾኑ የመንግሥት የፖሊቲካ ስብሰባዎች ላይ ቀዳሚ ተሳታፊ እንድትኾን እየተደረገች፣ ምእመኑም እያዘነ ነው፤ ጸሎተ ቅዳሴን እስከ ማስተጓጎል የደረሰ የፖሊቲካ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ አቡኑ ከ፳፻፮ ዓ.ም የዘመን መለወጫ ቡራኬያቸው ከንግግራቸው አብዛኛው የመንግሥት የዕለት ተዕለት ንግግሮች የታከሉበት ነበር፡፡ እንደ ሃይማኖት አባት ስለ ሰላም፣ ስለ መፈቃቀር፣ ጠብን ስለማስወገድ፣ ስለ መከባበር. . .ወዘተ መስበክ ሲገባ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የኾኑ ይመስል ስለ መልካም አስተዳደር መስበክ ከእርሳቸው የማይጠበቅ እንደኾነ ብዙዎች ይነቅፋሉ፡፡
በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሣ ባለፈው ዓመት ፓትርያርኩ የወራት የሥራ ላይ ቆይታ የነበራቸው ቢኾንም ከ፳፻፭ ዓ.ም ተጽዕኖ አልባ መሪዎች መካከል አንዱ ኾነው መካተታቸው ግድ ኾኗል፡፡
