አርአያነታቸው የሚያኮራ ፍጡራን በይነጋል በላቸው
እንደምን ሰነበታችሁ ውድ አንባቢያን፡፡ የሰሞኑ የሀገራችን የፖለቲካ ንፋስ እንዴት ይዟችኋል? እኔማ አንዱን ስሰማው እያደነገዘኝ ሌላውን ስሰማው ደግሞ እያደነዘዘኝ ፈዝዤላችኋለሁ፡፡ ለደግ ያድርግልህ በሉኝ፡፡ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ ይመስለኛል፡፡ አንዱ ከአንዱ መማርና ካለፈ ታሪክ ዕውቀትን ገብይቶ የወደፊቱን ለማስተካከል መሞከር ዕርም የተባለበት ጊዜ ላይ ሳንደርስ የቀረን አይመስለኝም፡፡ ትርምስምስ ያለ አኳኋን ላይ የመገኘታችን ምሥጢር ግልጽ ሊሆንልኝ አልቻለም፡፡ ኧረ አንድዬ አስተዋይ ልቦና ሰጥቶን በቃችሁ ይበለን እናንተዬ! ነገራችን ሁሉ እኮ የእምቧይ ካብ እየሆነ በጣሙን ተቸገርነ፡፡
ከምሽቱ የአልጄዚራ ዜና የተደሰትኩባቸው ጥቂት ነገሮችን አገኘሁ፡፡ ሁሉም ያስደሰቱኝ ነገሮች ስለሀገሬ አንዳች ነገርን የሚያጭሩ ናቸው፡፡ እናንተስ – ያልተከታተላችሁ ማለቴ ነው – የደስታየ ተካፋይ ብትሆኑ ምን ይላችኋል?
ከየትኛው ልጀምርላችሁ? ጥሩ – ከቅርቡ ከሊቢያ ልጀምር፡፡ ሊቢያውያን ተቃዋሚ ኃይላት በለስ እየቀናቻቸው ናቸው፡፡ ዛሬ ዝልታን የተባለችውን ከትሪፖሊ 150ኪ.ሜ ርቃ የምትገኘዋን ቁልፍ ከተማ ያዙ፡፡ ደስታቸውን በጭፈራና ሆታ እየገለጡ ናቸው፡፡ ጋዳፊን በየአቅጣጫው ወጥረው ይዘውታል፡፡ በሌላ በኩልም አል ዛውያ በሚባለው ግምባር የተሠለፈው የአማጽያን ኃይል ጋዳፊ ከመሸገበት ጎሬ 60ኪ.ሜ ገደማ ርቃ የምትገኘውን ሌላ ቁልፍ ከተማ(አል ዛውያን) አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጥሮ የማጥራት ዘመቻውን እያካሄደ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የሊቢያ ሁኔታ የኛን የ1980ዎቹን የወያኔ የፀሐይ ግባት፣ የ‘ዋለልኝ’፣ ‘የቴዎድሮስ’ … ዘመቻዎችን ያስታውሰኛል፡፡ “ጀግናው የኢሕአዲግ ሠራዊት በወሰደው መብረቃዊ ድንገተኛ የማጥቃት ዘመቻ 602ኛ ኮር የደርግን ሠራዊት ከጥቅም ውጪ አደረገ፡፡ በዚህ ዘመቻ ጀግናው የኢሕአዲግ ሠራዊት ሺዎችን ገድሎ፣ ሺዎችን አቁስሎና ሺዎችን ማርኮ …” እያሉ በበረሃ ሬዲዮናቸው ሲያቅራሩ እንደነበር ትዝ ይለኛል – የውስጥና የውጪውን ሻጥርና ደባ ለጊዜው እንርሳውና ቀረርቷቸው በርግጥም ፍሬ አፍርቶ ይሄውና ሃያኛውን ዓመት ዘልቋል፡፡ እናም የማይቀጣጠቡት ቀረርቶ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የኛ ቀረርቶ ነው እስካሁን ያልያዘልን፡፡ በተያያዘ የዚያን ጊዜው ወያኔያዊ ዜናም “ደርግ በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ባዘነበው የአየር የቦምብ ጥቃት ሦስት አህዮች ሲሞቱ ሁለት ዶሮዎች ቆስለው ‘በህክምና ላይ እንደሚገኙ’ በአካባቢው ከተሠማራወው የኢሕአዴግ የጦር ሜዳ ውሎ ዜና ዘጋቢ መረዳት ተችሏል፡፡” የመሳሰሉ ‘ቁም ነገር አዘል ዜናዎች’ አልፎ አልፎ ይደመጡ እንደነበር በጭል ጭል አስታውሳለሁ፡፡
የሆኖ ሆኖ ከ42 ዓመታት በላይ በተናጋሪ እንስሳነት ተፈርጀው ከምግብ በስተቀር ሌላው ሁሉ ሰብኣዊና ብሄራዊ መብታቸው ታፍኖ የነበሩት ሊቢያውያን ወደማይቀረው የነጻነት ዐውድ እየገሠገሡ መሆናቸው ታላቅ የዕለቱ የምሥራች ነው በማለት ወደቀጣዩ ሀተታዬ ልለፍ፡፡
የመጀመሪያው ስንኝ ጠፋኝ፡፡ ባወጣ ባወርድ ትዝ አልልህ አለኝ – አሁን፡፡ ሁለተኛው ግን “ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል፡፡” የሚለው ነው፡፡ እባካችሁን እናንተው አሟሉና አንብቡልኝ – ለወደፊት ትዝ ሲለኝ ወይም ሰው ጠይቄ በሌላ ጉዳይ ማንሳቴ አይቀርም፡፡
መናገር የፈለግሁት በጀርመን ሀገር በሰዎች አጥር ተጨቁኖ መኖሩ አጉራው ጠንቷትና አንገሽግሽዋት በረት ጥሳ ጫካ ስለገባችውና አሁን ወደአውሬነት እዬተለወጠች መጥታ ሰው አላስቀርብ ስላለችው ላም ነው፡፡ በጣም የሚገርም ምናልባትም የክፍለ ዘመኑ አስደናቂ ነገር ሊሆን የሚችል ክስተት ይመስለኛል ይሄ ጉዳይ፡፡ 700ኪሎ ግራም እንደምትመዝን የተነገረላት ይህች የፈረንጅ ላም (ዱሮውንስ የሀበሻ ላም ወደ ጀርመን ምን ይወስዳታል እንዳትሉኝ እንጂ) ከቤት ጠፍታ በሰማይም በምድርም በእግር በፈረስ ስትፈለግ ቆይታ ጫካ ውስጥ ተገኘች፡፡ የሰውን ክፉ ባሕርይ አሳምራ ያወቀች የምትመስለዋ ይህችው ላም ማንንም አላስጠጋም ብላ ‹እውልኝ! በኋላ ውርድ ከራስ፤ ካጠገቤ ዞር በሉ› እያለቻቸው ናት – በልሣነ ከብታዊ ሰውኛ ዘይቤ፡፡ አንዳንዶች አደጋ ሳታደርስ ትገደል ሲሉ የእንስሳት መብት ተከራካሪዎች ደግሞ “እኛ ሰዎች የእንስሳት አያያዝን ዘዴ ሳናውቅበት ቀርተን መብታቸውን ለማስከበር ሲሸፍቱ ለምን ወደግድያ እናመራለን? ለምንስ የፍጡራንን መብት እንደፈጥጣለን? በጭራሽ ልትገደል አይገባም” ብለው እዬተከራከሩላት ናቸው፡፡ ስታስቀና! እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ85 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከመጤፍ ተቆጥሮ የቁም ስቅሉን ይበላል – በጀርመን ደግሞ ለአንዲት ሰው አስጠላኝ ብላ በራሷ ጊዜ ነጻነትዋን ላወጀች ላም የመብት ተከራካሪዎች ደጀን ሆነው ቆመውላታል፡፡ ለነገሩ ወግ አይቀርም አሁን የት እንዳለ እንጃ እንጂ በደብረ ዘይት ከተማ አንድ የአህዮችን መብት አስጠጠብቃለሁ የሚል ድርጅት ተቋቁሞ እንደነበር ቀደም ባለ አንድ ወቅት መስማቴ ትዝ ይለኛል፡፡ በኛ ሀገር መጀመር እንጂ መጨረስ ባህላችን ባለመሆኑ አሁን ይኑር አይኑር አላውቅም፡፡ ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማለቀስ! እኛ በወያኔ እንደአይጥ እየታየን ደግሞ ለአህያ መብት ድርጅት ይቋቋም?
እንዴ? የሀገራችን መንግሥታት እኮ አንዳንዴ እንደጠጦ ያደርጋቸዋል፤ ጦጣ በመኮረጅ አንደኛ ናት አይደል? የኞቹስ ከውጮቹ የማይኮርጁት ምን ነገር አለ? በሀገራችን የፍትህ ሚኒስቴር አለ አይደል? በሀገራችን የዕንባ ጠባቂ ኮሚሽን የሚባል አለ አይደል? በሀገራችን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚባል አለ አይደል? በሀገራችን የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የሚባል ነገር አለ አይደል? በሀገራችን የትምህርት ሚኒስቴር የሚባል አለ አይደል? በሀገራችን ፀረ ሙስና የሚባል ኮሚሽን አለ አይደል? የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሚባልስ አለ አይደል?… ምን የሌለ ቀፎ መሥሪያ ቤት አለ፤ ወግ ወጉማ ተይዟል፡፡ አብዛኛው ማት በሚቻል ሁኔታ ውስጡን ለቄስና ለታይታ ያህል ነው፡፡ ሂዱና እዩ፡፡ እዩና መሥክሩ፡፡ በቀጭን ሽቦ ቀጭን ትዕዛዝ እየተላለፈላቸው ለጥቂት የገዢው ኃይልና ለአደግዳጊዎቻቸው በሎሌነት የሚያገለግሉ የግብር ይውጣ ሥራ የሚሠራባቸው መሥሪያ ቤቶች ቁጥር የትዬለሌ ነው፡፡ ለማንኛውም የእኛስ አንዴ ለምደነዋል ላሚቷን ይቅናትና ከጀርመን ጥይት የሚያድናት ዕድል ይግጠማት፡፡ መብቷንም እንዳወጀች የፈጠራት ነይ እስኪላት በነጻነት ትኑርበት፡፡
ሦስተኛው የመረጥኩላችሁ ዜና የሕንዱ የዜጎች መብት ተሟጋች ነው፡፡ አና ሃዛሬ በመባል የሚታውቀውና ዳግማዊ ማህተመ ጋንዲ እየተባለ ገና ከአሁኑ መቆላመጥ የጀመረው ጀግና ሰውዬ ሕንድ ተዘፍቃበታለች የሚባለውን ሙስና ለመዋጋት ቆርጦ ተነስቷል፡፡ የኛ ወያኔዎች እሥር ቤት የገባ ባለወኔን አኮላሽተው በስንትና ስንት ማስፈራሪያና ዛቻ ወኔውን ሰልበው ሲፈቱ ይህ ቆራጥ “እባክህን እንፍታህ” ሲሉት “በጭራሽ አልፈታም፤ የምፈታው ተቃውሞየን በአደባባይ የርሀብ አድማ መትቼ ዓላማየን ሰው ዐውቆልኝ፣ መንግሥቴም ችግሬን ተረድቶልኝ በዕቅዴ መሠረት እንድጓዝ ሲፈቀድልኝ ብቻ ነው” በማለቱ ይሄውና ተፈቅዶለት ከስንትና ስንት ደጋፊዎቹ ጋር በግላጭ የመንግሥቱን ገመና ለዓለም ሕዝብ እያሳጣ ይገኛል – ከዛሬ ዓርብ ነሐሴ 13/03ዓ.ም ጀምሮ፡፡ የኛ ሰው እንዲህ ሊል አይችልም – ልድፈር ቢል እንኳን “የማነህ ዓለመኛ” ተብሎ በሽሙጥ የሥላቅ ሳቅ ተስካክቶበት አንድ ሁለት ጥይት በግንባሩ ይሰጠውና የቤተሰቡ አባላት ደግሞ በሠፈር ውስጥ ልመና ይገቡ ነበር – የጥይቱን ዋጋ ለመክፈል ትንሽ ሣንቲሞችን ለማግኘት፡፡ በኛ ሀገር ላይ የወረደ መቅሰፍት መቼም የጉድ ነው፡፡ መሞቱ ሳያንሰን ከደርግ ጀምሮ የምንሞትበትን ጥይት ዋጋ እንድንከፍል መገደዳችን የግፍ ግፍ ሆኖ ያለ በሮመዳውያኑ አነጋገር አጃኢብ የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ለመሆኑስ የአንዲት ጥይት ዋጋ ሁለት ሺህ ብር ይደርሳል እንዴ? እባካችሁ ለመሞት ስንዘጋጅ በራሳችን ጥይት እንዲገድሉን ቀድመን እናዘጋጅና እኛው እንስጣቸው፡፡ ትንግርተኛ ሀገር ከትንግርተኛ መሪዎች ጋር – የጥይት ዋጋ ክፈሉ? አይ ስይጥና!
የመጨረሻው የዚያች ሞገደኛ በርማዊት የሳን ሱ ቺ ጉዳይ ነው፡፡ “የቆዬ ሰው ከሚስቱ ይወልዳል” ይባል ነበር ዱሮ – ዛሬ ከማን እንደሚወልድ ወላጁ ራሱ ይወቀውና፡፡ ይህ ዜና በውነቱ በእጅጉ ነው ያስደነቀኝ፡፡ በለውጥ ኅለውናም አመንኩ፡፡ የወታደራዊው ጁንታ መሪ ከዚህች ለዓመታት እሥረኛ አድርገዋት ካቆዩዋት የበርማ ብርቱካን ሚዴቅሳ ጋር ጎን ለጎን ተቀምጦ ይነጋገራል የሚል ግምት በእውኔም በህልሜም አልነበረም፡፡ ግን ዛሬ ሆነ – ‘ቀድመው ሳያስጠነቅቁኝ’ ድንገት በቲቪ በማየቴ የምሬን ነው የምላችሁ ደነገጥሁ፡፡ ስለዚህ፣ ሰው ካለመሆን ወደ ሰው መሆን መሸጋገር ይቻላል ማለት ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ይህን ያልጠበቅሁትን ክስተትም በምናቤ ወዳገሬ አመጣሁትና መለስ ዜናዊ ነገ ጧት ወይም ከነገ በኋላ ባሉት ማናቸውም ቀናት ከዶክተር ብርሃኑ ነጋ ወይም ከአቶ ስዬ አብርሃ ወይም ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ወይም ከአቶ ሌንጮ ለታ ወይም ከአቶ መርሻ ዮሴፍ ወይም ከዶክተር ነገደ ጎበዜ ወይም ከ’ብርሃነ መስቀል ረዳ’ ወይም ከ’ኃይሌ ፊዳ’ ወይም ከ’ኃይሉ ሻውል’ ወይም ከ’ልደቱ አያሌው’(ለምን እሱስ አምሮት ይቅር?) ወይም ከ’እኔ ከይነጋል በላቸው’ ኡፍፍ…ስም መጥራቱ ደከመኝ… ምናለ በጥቂቱ ብትደራጁ ጃል የሁሉንም ስም ብጠራ እኮ አሥር ገጽም ላይበቃኝ ነው ማለት ነው እናንተ ሆዬ … ብቻ ከነዚህ እስካሁን መግባባት ካልቻሉ የአንዲት እናት ልጆች ጋር እየተሳሳቁና በሚያቅባት ቀልድ እዬተተራረቡ ያለፈ የሞኝነት ዘመናቸውን በማስተወስ አቶ መለስ “አይ ብሬ ያንን ጅል ጊዜ እንኳን አናንሳው የሆነ ጄኒ ገብቶብን እንጂ እንዲያው በጤናችን ይመስልሃል?…” እየተባባሉ ሲወቃቀሱ ታየኝ – የማይታይን ማየት ደግሞ መብት ነው፡፡ አቤት በዚች ሰዓት – ስንቶቻችሁ ‹እንዳፍህ ባደረገልን› ትሉ ይሆን? ከሰይጣን በስተቀር መቼም ይህን የሚጠላ የለም ባይ ነኝ፡፡ እንዴ? ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከ300 ዓመታት በላይ ተንሠራፍቶ የነበረው አፓርታይድም እኮ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ነው ሥልጣኑን በምርጫ ለብዙኃኑ አስረክቦ በይቅር ለእግዜር ሰላም የወረደው፡፡ ነገር ግን – በመሠረቱ ደግሞ እንደማለቴም ነው – ሰላምና ነጻነት የገና ዳቦ አይደሉም – እየተቆረሱ በደጅ ላለፈና እባካችሁ ሙጥናን ብሎ ለለመነ ሁሉ የሚሰጡ፡፡ ዴሞክራሲ የምትሉትን ነገር እርሱት – ውሸት ነው፤ እስኪበቃን አዬነው፤ የቁጩ ነው፤ በነአሜሪካም ስለመኖሩ አሁን አሁን እተጠራተርኩ መጥቻለሁ፡፡ በኛዋ ሀገርማ ማን ደምቶ ለማን ለምርመራ ታህል እንኳን ደም ከእጣቱ ፍልቅ ሳያደርግ ቤተ መንግሥት ሊገባ? ሊያውም በኢትዮጵያውያን የሥልጣን ፍቅር? መታሰቡስ? እንኳንስ ስንትና ስንት ገመና በፀጉሩ ልክ ተሸክሞ ከሚኖር ኢሕአዲግን ከመሰለ የመሽቁቆች ስብስብ ይቅርና ከሌላም አካል ሥልጣንን ካለፉክቻ በውዴታ መውሰድ አስቸጋሪና ከባድም ይመስለኛል – አሁንም በኢትዮጵያ የሥልጣን ፉክክርና የእርስ በርስ ጦርነት ታሪክ፡፡ ሳን ሱ ቺ የከፈለችው መስዋዕትነት እንኳንስ ከሚያናማር(በርማ) መሪ፣ አምላክን ተዳፈርክ አትበሉኝና ከፈጣሪም ጎን ብትቀመጥ አያንሳትም፡፡ ለዓመታት የከፈለችው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ ነው እንዴ? የኛ ችግር፣ ብዛት ብቻውን ነጻነትን ያቀዳጅ ይመስል “የኛ ቁጥር ይህን ያህል ሆነን ሳለ፣ እነሱ ይህን ያህል ሆነው ሳለ” እያልን ከኛ የሚጠበቀውን ምንም ሣንሠራ ወይም የሚሠሩትንም ቢሆን ለመደገፍ ሳንጥር ሰላምንና ነጻነትን እንደኅብስተ መና ከሰማይ መጠበቃችን ነው፡፡ አይደለም ጎበዝ? አዲስ ነገር እኮ አይደለም እያልኩ ያለሁት፡፡ ብለነው ብለነው መስማቱ ራሱ የደከመን ነገር ነው፡፡ ጥሎብን ግን ከስህተታችን አንማርም፡፡ ምን ይሆን ግን ችግራችን? ኢትዮጵያውያን ስንባል ሁላችንም ለማለት ባልደፍርም ብዙዎቻችን በሥልጣን ሱስ የመለከፍ ተፈጥሮኣዊ አባዜ ስላለብን ይሆን እንዲህ ያንዳችን ነገር ላንዳችን አልጥም እያለ በመቶዎች ፖለቲካዊና ጎጣዊ ኩይሳዎች የምንኮየሰው? እስኪ ጥናት ይካሄድብንና ሥሪታችን ይታወቅ – እኔ በበኩሌ ለጥናቱ የመጀመሪያው በጎ ፈቃደኛ እሆናለሁ፡፡ ይህን ስል መቼስ የሚያንጓጥጠኝ እንደማይኖር ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ የተጨነቀ ብዙ እንደሚል እናንተስ መቼ ታጡትና፡፡ ከላይ ለተጠቀሱት የወረደው በረከት ለኛም ይድረሰን አቦ ፡፡ ከጎንደር ባንዴ ወደሀረር፡፡ እየተኛችሁ እንደሆን ቅዠት የሌለው መልካም እንቅልፍ፤ እየተነሳችሁ እንደሆን እንከን የሌለው መልካም የሥራ ወይም የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ፡፡