የጭቆና ሰንበሮች በአንዱዓለም አራጌ
ከመጀመሪያዋ የብርሃን ብልጭታ ጀምሮ ጊዜ እንደ ጅረት ይተማል፡፡ የጊዜ ጅረት መጠኑ አይሞላም፣ አይጎድልም፣ ሁልጊዜም አንድ ነው፡፡ የማይደርቅ ጅረት ነው፡፡ ትውልድም ከሰው ልጅ የህላዌ ጅማሮ አንስቶ በጊዜ ስጋጃ ላይ ይነጉዳል፡፡ የትውልድ ጅረት ግን አቀበትና ቁልቁለት፣ የበጋ እና የፀሐይ ወራት አሉት፡፡ የትውልዱ ዘመን ትርጉም፣ ማጠሩም መርዘሙም ከዚህ አንፃር ሊቃኝ ይገባዋል፡፡ የአንድ ትውልድ ዘመን የበልግ ወራቶች ካልበረከቱበት የሰኮንድ፣ የደቂቃ፣ የሰዓታት፣ የቀናትና የዓመታት እብቅ ክምር ከመሆን አይዘልም፡፡ ፍሬ አልባ ገለባና ዱካአልባ ጉዞ ይሆናል፡፡
ረጅሙን የሀገራችንን የህላዌ ዘመን ላፍታ ቁጭ ብለው ሲያንሰላስሉት በዚህ ረጅም የዘመን ምህዋር ትውልዶች እንደ ሰንሰለት ተቀጣጥለው ሲያልፉ ባይነ ልቦናዎ ይታዩዎታል፡፡ አብዛኛው የትውልድ ሰንሰለት በሀሩር ወራት እየተጠበሰ ሲያልፍ በምናበዎ አተኩረው ያዩታል፡፡ የትውልዶች ሰንሰለት የተርመጠመጡባቸውንም የሀሩር ወራት እየጨረሱ የሰንሰለቱ ጫፍ ላይ ሲደርሱ እየራቋቸው የመጡት የሀሩር ወራት እንደበልግ እየሆኑ በአይነ ልቦናዎ ውልብ እያሉ ይታዩወታል፡፡ ከእዚያ የትውልድ የቅጥልጥል ጉዞ በራቁ መጠን ያሉበት ትውልድ ዙሪያ ገባው በዕቶን እንደጋመ ያስተውላሉ፡፡ የቆሙበት የሀሩር ወቅት እንደ እሳተ ገሞራ ሲንተከተክ አለቶችም እቶኑን መቋቋም አቅቷቸው ዋይ ዋይ እያሉ ሲቀልጡ እርስዎ ግን ድምጽ እንኳን ሳያሰሙ እቶኑን ችለው ላፍታ በርተው፣ ጠልሸተው ሲያልፉ ያስተውላሉ፡፡ ጠልሸተው በሚያልፉባት ቅጽበት ምላሽ ያላገኙለት እንቆቅልሽ ያለማቋረጥ ይሞግተዎታል፡፡ አንደበት አልባ አለቶች ዋይ ዋይ እያሉ ሲቀልጡ የእርስዎን ልሳን ምን እንደዘጋው ይመሰጣሉ፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በአንክሮ ለመረዳት የሚሞክር ሁሉ ባአብዛኛው ይኸን በመሠለው ምናባዊ ስቃይ ውስጥ ማለፉ አይቀርም፡፡ ይኸንን መሰሉ የምናብ ፍጭት ማባሪያ ከሌለው የመከራ ዝናብ ጋር ይደመርና ጨርቅ ሊያስጥልም ይችላል፡፡ እንደ አቦይ ስብሀት አይነቶቹ ደግሞ ይህን አይነት የሕዝብ ሰቆቃ እንደትልቅ የምርምር ግኝት ይቆጥሩታል፡፡ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ 1993ዓ.ም ላይ ከህወሀት ክፍፍል በኋላ “ተሀድሶና የወደፊት አቅጣጫችን” በሚል በተካሄደው የኢሕአዴግ የግምገማ ጉባኤ ላይ አቦይ ስብአት የአገዛዙ የአፈና ስልት ምን መምሰል እንዳለበት ለታዳሚው ለማስገንዘብ ያቀረቡት ሀሣብ ላነሳነው ውይይት ጥሩ ማሣያ በመሆኑ ነው፡፡ “ቢስማርክ ጀርመንን ጀርመን ያደረገው ሃይልን ያለርህራሄ በመጠቀም እና አልፎ አልፎም ማባበያ በመስጠት ነው፡፡ እንግሊዞችም በኢንዱስትሪያል ሪቮሉዩሽን ጊዜ ለፋብሪካ የሚሆናቸውን የበግ ፀጉር ያገኙ የነበረው የገበሬውን መብት በማክበር አልነበረም ገበሬውን በማፈናቀል እንጂ፡፡ እንዲሁም ሰራተኛውን ከገጠር ወደ ከተማ በሃይል በማምጣት ጀርባው ላይ ማህተም እየታተመበት እንደቁስ ያሰሩት ነበር፡፡” ካሉ በኋላ አክለውም በኢትዮጵያም ይህኑ መሰል ተግባር መከተል እንደሚገባ ገልጸው ነበር፡፡ ያሉት አልቀረም በሚገባ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በረጅም የመከራ ሌሊት እያለፈ ቢገኝም ለአገዛዙ ግን እንደ በልግና እንደ ፀደይ ወራት የሚቆጠር የቀደመ ስሌት ውጤት ነው፡፡
በታሪካችን አያሌ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡ ብዙም ጊዜ ታግለን ጥለናቸዋል፡፡ በተለይም ዛሬ በደረስንበት ሁሉ አንገታችን ከክብር ጋር ቀና አድርገን መሬት ለመርገጥ ድፍረትን የሚሰጡን ገናና ታሪኮች አሉን፡፡ ሁል ጊዜም እንደሚባለው ኩራታችን ናቸውና ብጠቅሳቸው አንባቢዎቼን ቅር አላሰኝም፡፡ ከአክሱም፣ ከላሊበላ፣ ከጎንደር ስልጣኔዎችና የገዳ ዴሞክራሲና ከሌሎች አያሌ የታሪካችን አምዶች ተርታ ልጠቅሰው የሚገባኝ ሌላው ሁነኛ የታሪካችን አምድ ለጥርኝ አፈራችን እንኳን የመሰሰት የአይበገሬነት ታሪካችን ነው፡፡ እኛ ባናወሳው ጣሊያኖች፣ ግብጾች፣ ቱርኮችና ሌሎቹም የተፋለሙአቸውን አጫጭር፣ ቀጫጭንና ጠያይም እሳት የሚተፉ አይኖች ያሏቸው ጀግኖች አባቶቻችንን ሳይወዱ በግድ ይዘክሯቸዋል፡፡ እንዳው ለነገሩ ያክል እንጂ በአጥንታቸው አጥረው፣ በየተራራው ሸብተው የሚናፍቋቸውን ሕፃናት ልጆቻቸውን ተመልሰው ሳይሰሙ በሀገራቸው ማህፀን ውስጥ በየፊናው ያንቀላፉትን ጀግኖች አባቶቻችን እንደማንዘነጋቸው አጥቸው አይደለም፡፡
የታሪክን ነፀብራቅ ወደ ኋላ ዞረን ለማየት ስንሞክር እንደ ጣሊያንና ቱርክ በተግባር አባቶቻችን ለሚያውቅ እነዚያን ሞትን የናቁ ጀግኖች አገራቸው ምን አደረገችላቸው? ወይንም ምን ብታደርግላቸው ነው እንዲህ የሚወዷት? ብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡ መሪዎቻቸውስ ምን አይነት የክብር ኒሻን ሸለሟቸው?የሚለው ጥያቄም መነሳቱ አይቀርም፡፡ ራሱን የቻለ ምርምር የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ከድል መልስ በየቀያቸው የጭቆና ሰለባዎች እንደነበሩ የዋቢ መጽሐፍት ችግር አይገጥመንም፡፡
ታዲያ አባቶቻችን የሀገር ፍቅራቸው መሠረት ምን እንደሆነ ሊጠየቁ ቢችሉና ቢመልሱልንም መታደል ነበር፡፡ አባቶቻቸው ያስረከቧቸውን አገር ከነክብሩ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የመኖራቸው አንዱ ትርጉም አድርገው ይወስዱት ነበር፡፡ ከእነሱ በፊት ለነበረው ትውልድ ያላቸውን ውለታና በእቅፋቸው ለሚገኘው ትውልድ ያላቸውን ፍቅርና ርዕይ የሚገልፁት ለራሳቸው እንኳን ባለመሳሳትና ለሀገር ክብርና ነፃነት ተሰውተው ዘመናቸውን ማሳረግ እንደትልቅ የተሳካ ፍፃሜ ይቆጠሩት ነበር፡፡ የታሪክና የትውልድ ትርጓሜንም በሚገባ ይረዱት ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን እትብታቸው ለተቀበረበት በኋላም እነርሱ ላሸለቡበት ምድር፣ ለተነፈሱት አየር፣ ለተጠለሉበት ሰማይ፣ ለሚጠሩበት የሀገር ስም፣ ለሚወከሉበት ባንዴራ፣ አገራቸውን ለመጠበቅ ተገን ለሆኗቸው ጋራና ሸንተረሮች እና ሌሎች አያሌ አገራዊ እሴቶች ትልቅ ፍቅርና አክብሮት ነበራቸው፡፡ መስዋእትነቱንም በሚፈለገው ደረጃ የተወጡት ከዚህ አንፃር ይመስለኛል፡፡ ይህ ባይሆን የትኛው የውስጥ ነፃነታቸውና የሰውነት ክብራቸው ተጠብቆ? ከጥቂቶች በስተቀር የትኞቹ የሜዳልያ ጣዕም ገብቷቸው? ቢያውቁትስ ስንቶቹ ተሸለሙ? እንዲያውም አንዳንዶች ለገዢዎች ከጎረበጡ የገዢዎች በኒሻን ፋንታ አረር እራት ይሆኑ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የአባቶቻችን ህልም ግን ኒሻምኑ አረሩም አልነበረም፡፡ የዳርድንበር ነፃነት እንጂ፡፡ እነርሱ በየቀያቸው ነፃነታቸውን የተነፈጉ የግፍ ቋቶች ሳሉ የዳር ድንበር ነፃነት የሰርክ ስስታቸው ነበር ፡፡
እንዲሁ ወደ ኋላ በምናይበት ወቅት የሌሎችንም አገሮች ሁኔታም ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ እንደ አሁኑ የመገናኛ አውታሮች መልክ ባለው ሁኔታ ባልነበሩበትና ባልተትረፈረፉበት በዚያም ወቅት ጭቆና የስብዕና ፀያፍ ጉድፍ እንደሆነ እንስማማለን፡፡ ይሁን እንጅ እንደ ሀገራችን ሁሉ በሌሎች አገሮችም ገዢዎች ሕዝባቸውን ደጋግመው ይረግጡ ከስብእናም በታች አውርደው ይገዙ እንደነበር ብዙ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ነገር ግን በእነዚህ አያሌ አገሮች የሰው ልጅ ሉዓላዊነት በጊዜ ዑደት እንደ ፀደይ ወራት አበባ ፈክቶ ይታያል፡፡ በሰው ልጅ ልዕልና ላይ በተመሰረተው የኢኮኖሚ ሥርዓታቸውም ዜጎች ቁራሽ አይለምኑም፡፡ እንዳውም ታዛቸውን ለሌሎች መጠለያ ሲያደርጉ ሲሳያቸውንም ለተራቡ እና ለተመናተሉ ወገኖች ብዙሽህ ኪሎሜትሮችን አቋርጠው ይልካሉ፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ኢትዮጵያ ትናትም ሆነ ዛሬ የሀሩር ወራቶች ዋነኛ የታሪኳ መገለጫ የሆኑባት አገር ነች፡፡ ትናንት የአደዋን ተአምራዊ ገድል በደሙ የፃፈ ትውልድ፣ የራሱ የውስጥ ነፃነት፣ የማንነቱ ባለቤትም አልነበረም፡፡ እንቆቅልሹን ግን የባሰ የሚያደርገው ግን ያሁኑ ዘመን ጭቆና በብዙ እጅ የከፋ መሆኑ ነው፡፡
በተለይ የአሁኑን ዘመን ኢትዮጵያዊ ትውልድ አንገት የሚያስደፋው፣ አምባገነኖች የአባቶቻችን የመስዋእትነት ውሎዎች የሚያረክስ፣ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ስሜት የተለየውና ታሪካችንን የሚያንቋሽሽ የክህደት ተግባር መፈፀማቸው ነው፡፡ ለዚህም ውለታቸው ራሳቸውን ስልጣን ሸለመው ያቆሸሹት ታሪክ ተጠሪዎች ነን ብለው፣ አይናቸውን በጨው ታጥበው በጫንቃችን ላይ ተፈናጠዋል፡፡ ያፈረሱትንም ድንበር ‹‹አስከባሪዎች›› ሆነው ለሃጢያታቸው ስርዬት ሕይወትን በቅጡ ያልጠገቡ 7ዐ,ዐዐዐ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ፈንጂ ማምከኛ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በህይወት እያሉም የህይወታቸውና የመብቶቻቸው ባለቤቶች አልነበሩም፡፡ በሕይወት ለቤታቸው ቢበቁም ከዚህ የከፋ እንጂ የተሻለ ሕይወት አልነበራቸውም፡፡ የእነርሱ የህይወት እሽክርክሪት ‹‹ዓላማው›› የአምባገነኖችን ትኩሳት ማብረድ የመሆን እድሉ ከፍ ያለ ነበር፡፡ የሀገርንም ሆነ የራሳቸው ነፃነት ገዢዎች ለክተው የሚሰጧቸው እንጂ በሰውነታቸውና በዜግነታቸው የሚጎናፀፉት የማይገሰስ ፀጋ ባለቤት አልነበሩም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩን የዳር-ድንበር ነፃነት ለማስጠበቅ ወደኋላ የሚል ባይሆንም አብዛኛው የዓለም ህዝብ የፃነትን ጮራ በሚሞቅበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማያችንን ከወትሮው የከፋ የጭቆና ጥቁር ደመና ጋርዶታል፡፡ ክቡር በሆነው መብቱ ተጠቅሞ መሪዎቹን መምረጥ አይችልም፡፡ ድምፁን የማስጠበቅ መብትም የለውም፡፡ ከጠየቀ ይወነጀላል፡፡ መብት ይገባኛል ካለ ይገደላል፡፡ የእሱ መብት መሞት ነው፡፡ የአምባገነን ገዢዎቹ መብት ደግሞ መግደል ነው፡፡ ጦር ሜዳ ሄዶ ይሞታል፡፡ በየቀየው መብቱን መጠየቅ ስርዬት የሌለው ወንጀል በመሆኑ ይገደላል፡፡ እጣው ይኸ ሆኖአል፡፡ ከደመናው በሚዘንበው የአምባገነኖች ጥይት እየተበላ በየማጀቱ ድምጽ አውጥቶ ለማልቀስ እንኳን ነፃነት የለውም፡፡ እየሞተም ስለሞቱ የመናገር ነፃነት የለውም፡፡ ይልቅስ እየሞተ ስለሕይወቱ፣ ስለልማቱና ከልማቱም ስለተገኘው ፈንጠዝያ በባዶ አንጀቱ እንዲጨፍር ይገደዳል፡፡ የቲያትሩ ፈቃድ አልባ ገፀ-ባህሪ ነው፡፡ እንደተጠየቀውም ይፈጽማል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ላይ ጐልቶ የሚታይ የጭቆና ሰንበር ነው፡፡ የሳት ልጅ አመድ? ወይንስ?
አሁን ያለው ሥርዓት በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ ከፈፀማቸው አያሌ በደሎች ውስጥ ምንአልባት ከፍተኛው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመለያየት ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ የተከተለው እጅግ ዘረኛና ከፋፋይ የሆነው ስሌቱ ነው፡፡ ለዘመናት በደምና በስጋ የተገመደው የኢትዮጵያውያን አንድነት ሆኖ እንጂ በሌሎች አንዳንድ አገሮች ዘንድ የተፈፀመ ጉዳይ ቢሆን ኑሮ ተበታትነን በቀረን ነበር፡፡ ያም ሆኖ አገዛዙ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ ያደረሰው በደል ሰንበር አሁንም ጉልህ ሆኖ ይታያል፡፡ በታሪካችን ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ በውጭ ሀገር ያሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ቤተ-አምልኮአቸውንም እስከ መለያየት ድረስ ሄደዋል፡፡ ከ2ዐ ዓመታት የከፋፍለህ ግዛው ሥርዓት በኋላ ይኸ ሁኔታ አሁንም ይታያል፡፡ በ2ዐ ዓመታት ውስጥ ከ34 ጊዜ በላይ ኢትዮጵያውያን ዘር ተቋጥረው ሰይፈው ተማዘዋል፡፡ ደም ተፋሰዋል፡፡ ሕይዋት ጠፍቷል፡፡ የዚህም ሁሉ ስሌትና የደም ግብር ማጠንጠኛው አጤዎቻችንን ሥልጣን ላይ አውሎ ማሳደር እንደሆነ ክፉ ተግባራቸው ሁነኛ ምስክር ነው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በኢህአዴግ ዘመን የተፈጠረው ወጣት አንዱ ከሌላው ጋር እንዳይግባባ ብሎም አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ደባ ተሰርቷል፡፡ እየተሰራም ነው፡፡ ቃሊቲ በተለይም ‹‹ቦዘኔ ክልል›› ወይንም ዞን 6 ወደሚባለው ክልል ለቅጣት በተወሰድኩበት ወቅት ከአንድ በኦነግነት ተጠርጥሮ ከታሰረ ወንድሜ ጋር ተዋወኩ፡፡ የትውልድ ፀር ስለሆነው የገዢዎቻችን የቋንቋ ፖሊሲ አንስተን ስንወያይ የራሱን ተሞክሮ አጫወተኝ፡፡ ላውጋችሁ፡፡ ለበርካታ ዓመታት የታሰረ ዜጋ ነው፡፡ ለታናናሽ ወንድሞቹና እህቶቹ ደብዳቤ መፃፍ ነበረበት፡፡ የፃፈላቸው በቁቤ አልነበረም፡፡ በአማርኛ ነው፡፡ ሕፃናቱ ማንበብም ሆነ መፃፍ የሚያውቁት ቁቤ ነው፡፡ አማረኛ ማንበብ የሚችል ዘመድ ደብዳቤው ከደረሳቸው ከ15 ቀናት በኋላ በድንገት ለመጠየቅ እስኪመጣ ድረስ ከሚናፍቁት ወንድማቸው የመጣውን ደብዳቤ ምን እንደሚል ለመረዳት አልቻሉም፡፡ ተጣጥፎ ተቀምጧል፡፡ ይህ ትንሽ የሚመስል ነገር ግን አገዛዙ ሆንብሎ የፈጠረው ትልቅ ችግር ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚናገሩት ቋንቋ ሁሉ ክብራችን፤ ኩራታችንና ባህላችን ነው፡፡ ቢቻል ኑሮ የአገራችንን ቋንቋዎች ሁሉ ልናውቅ በተገባን ነበር፡፡ ካልተቻለ ደግሞ ኦሮምኛን ብንማረው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ እንቆቅልሾቻችንን ብንፈታበት ምኑ ጋ ነው ችግሩ? አማረኛንስ ብንማረው ብንሰራበት ብንግባበት እንዴት ይሆን የምንጎዳው? ሁለቱንም ቋንቋዎች እንዲሁም ሌሎችንም በሂደት እድገታቸው እየታየ ብሔራዊ ቋንቋዎች ብናደርጋቸው የታላቅ አገርና ሕዝብ መገለጫ እንጂ የውድቀታችን ምክንያት እንደማይሆኑ ገዢዎቻችን ሳያውቁት ቀርተው አይደለም፡፡ ዳሩ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲግባባ የገዢዎች ፀሐይ እንደምትጠልቅ፤ ሕዝብ በነቃ፣ በተግባባ እና በአወቀ ቁጥር ለገዢዎች የሚስማር ኮርቻ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ የሕወሓት/ኢህአዴግ የሕዝብን ቋንቋ የመደበላለቅ ቅዥትም የሚመነጨው ከዚሁ ሰጋት አንፃር መሆኑን ፈጽሞ ልንዘነጋው ይገባም፡፡
ሌላውን የጭቆና ሰንበር እንይ፡- አንድ ቀን አመሻሽ ላይ እግሬን ለማፍታት ወጥቻለሁ፡፡ በሃምሳ ሜትር ርቀት ላይ አጠር ያለች ወጣት የላስቲክ ወተት መሬት ላይ ለተዘረጋ ሌላ ወጣት ለማጠጣት ብቻዋን ትታገላለች፡፡ በፍጥነት ተጠግቼ የሆነውን ሁሉ ለመረዳት ሞከርኩ፡፡ ዘሪሁን ይባላል፡፡ የአስረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዶ ከደብረ-ብርሃን ወደ አደስ አበባ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ በረባሶው በኢትዮጵያ ባንዴራ ተለብጧል፡፡ ከርሃብ የተነሳ አይኑን ለመግለጥ የቻለው 4ዐ% ጉሉኮስ ከወሰደ በኋላ ነበር፡፡ ብርታት ያገኝ ዘንድ ሌሎችም ሰዎች ተጨምረው እገዛ እየተደረገለት ነው፡፡ በድንገት ከዘሪሁን በእድሜ በዓምስት ዓመት የሚበልጥ ሌላ ወጣት በመካከላችን ገፈታትሮ ገባና ‹‹አርፈህ አትበላም›› ብሎ ቀልዶበት ከመቅጽበት ብቻውን እያወራ አልፎ ሄደ፡፡ የተወሰኑ ሜትሮች ከተጓዘ በኋላ የዚህኛው ችግር ደግሞ ምን እንደሆነ ለመረዳት ቻልን፡፡ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ለሚያማትር ሰው ይኸን መሰል ዘግናኝ ትይንት ደጋግሞ የሚያጋጥም አጥንት ሰብሮ የሚገባ፣ ሀፍረት የሚያከናንብና አቅመቢስ ብሎ አፍ አውጥቶ የሚዘልፍ ክስተት ነው፡፡ የፓርቲ ካምፓኒዎች የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ባያምሱት አገርን ሊያለማ የሚችል አፍላ ጉልበት እንደዚህ በየ መንገዱ መክኖ ባልቀረ ነበር፡፡ ነገር ግን ይኸን መሰል ዋጋ ካልተከፈለ እንዴት 8.5 ቢሊዬን ዶላር በውጭ አገር የማኖር ግባችን እውን ይሆናል? የገዢዎቻችንስ ካምፓኒዎች እንዴት ሊደልቡ ይችላሉ? ፖለቲካውንም ሆነ ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር ታሪካዊው የእነአቦይ ተልኮስ እንዴት ግቡን ሊመታ ይችላል?
ይኸ የዘመናችን የኢትዮጵያ ወጣቶች ከመኖርና ካለመኖር ጋር የሚገጥሙት ግብግብ በጣም ቲኒሽ ማሳያ ነው፡፡ የዘሪሁን አይነቱ እድለኛ በወገኖቹ እርዳታ ይተርፋል፡፡ አያሌዎች በድርቅ የተመቱት እና በእድሜ የገፉት ይቅርና በወጣትነት እድሜም እንደዚህ ከጠኔ ጋር ግብግብ ገጥመው ይሸነፋሉ፡፡ የወጣትነት ህልማቸውና ለሀገራቸው እድገትና ሥልጣኔ ሊያበረክቱት የሚችሉት ምትክ አልባ አስተዋፆ የፈሰሰ ውሃ ሆኖ ይቀራል፡፡ ይሄም ሌላው እንደሸንተረር ጐልቶ የሚታይ የዘረፋና የአፈና ሰንበር ነው፡፡
ጥቂቶች ደግሞ ከኑሮ ጋር በሚገጥሙት ግብግብ የኢህአዴግ አባል በመሆን የእለት ጉርሳቸውን ማሸነፍ ይፈልጋሉ፡፡ አባል ይሆናሉ፡፡ ኢህአዴግአዊ ተልኮ ይቀበላሉ፡፡ ይፈጽማሉ፡፡ ለውለታቸው ኮብራ ይገዛላቸዋል፡፡ አክለው ሕዝብ እንዲረግጡ ይታዘዛሉ፡፡ እንደታዘዙት ያደርጋሉ፡፡ ከገዛ ሕሊናቸው ጋር ጥዋትና ማታ ፍልሚያ ይገጥማሉ፡፡ ነገሩ ውስብስብ ነው፡፡ ያለ ትምህርት ደረጃቸውና ያለአቅማቸው ሥልጣን ይደራረብባቸዋል፡፡ ከህዝብ እና ከህሊናቸው ጋር ተቃቅረዋል፡፡ ለሕሊናቸው ቢሸነፉ እሰየው በተባሉበት ወንጀል ሙሰኛ ተብለው ይከሰሳሉ፡፡ ወደ ሕዝብ ቢወርዱ ከህዝብ ጋር ደም ተቃብተዋል፡፡ በሠላም መኖር ቢችሉ እንኳን የኢህአዴግ አባል በመሆን የደፈኑት ጉረሮ እንደገና ጦም ሊያድር ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚሰጣቸውን የጭቆና ተልኮ እየፈፀሙ ከሕሊና ጋር ጠዋትና ማታ እየተሟገቱ መኖር የመኖር ተልኳቸው ሆኖአል፡፡ ይኸ የብዙ ኢህአዴግ ፊታውራሪዎች የሚመስሉ ወጣቶች ሕይዎት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው አገዛዙ በሕዝብ ላይ ጭቆናን አንግሶ የቀጠለው፡፡ እነርሱም ከህሊናቸው ሙግት መዳን ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱም ነፃነት ይናፍቃቸዋል፡፡ አገዛዙን መገላገል የሁልጊዜም ሕልማቸው ነው፡፡ ግን እንዴት የሚለው ጥያቄ ያስጨንቃቸዋል፡፡ እውነት የማይመስል ግን ሌላ የጭቆና ሰምበር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በደረሰውና እየደረሰ ባለው የከፋ ጭቆና ምክንያት የሚታዩትን ሰንበሮች የትየለሌ ናቸው፡፡ ከፍትህ አንፃርም ብዙ ሊባል ይችላል፡፡ በዚህ ዘመን የፍትሕ ሚዛን እዴት እንደተጣለ የማይረዳ፣ በየወቅቱ ‹‹ፍትህ›› የገዢዎች አገልጋይ ሲሆን ያላየ ወይንም ያልሰማ ማን ይኖራል? የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ባለፉት 2ዐ ዓመታት የተፈጠሩ የዚህ ትውልድ አባላት ስለ ፍትህ ምንነት ምን እየተማሩ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በፍትሕ ላይ ከሚሰራ ግፍ በኋላ ፍትህን ማስከበር እንዴት አስቸጋሪ ዳገት እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ፀረ-ሙስና›› ኮሚሽን እያለ ሙስና የባሰበት፡፡ የዚች ሀገር የሙስና ዶሴ በእውነተኛ ዳኞች የተገለጠ እለት ስንት ጉድ ይወጣ ይሆን?
የፍትሕ ሥርዓቱ መቀለጃ ከመሆኑ የተነሳ ሕዝቡ ከፈጣሪ ውጭ የሚተማመንበት አንዳች ነገር እንደሌለ ሲናገር መስማት የተለመደ ነው፡፡ እጅግ የሚያስቆዝመው ግን አንዳንድ ሰዎች ነፃነት አልባ ሕይወት እየኖሩ የሚደርስባቸውንና የሚሰማቸውን እንኳን በድፍረት አለመናገርን እንደብልህነት ወስደውታል፡፡ ከሞት ወዲያ ላለው ሕይወት ወይንስ አሁን ለምንኖረው? ሰው ከወገኑና አብሮት ከሚታረዘው ጋር ካልተግባባ ከራሱም ጋር አይግባባም፡፡ ሰው ቢያንስ ከፈጣሪ ውጭ በወገኑ ሊተማመን ይገባል፡፡ አንዱ ሁሉንም የማያመን ከሆነ ትልቅ የሥነ-ልቦና ስብራት ውስጥ እንደሚገኝ መገመት ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነት ሰው በራሱ ፈጣሪ በለገሰው ችሎታና የሰውነት ክብርም ማመኑ ያጠራጥራል፡፡
የጭቆናውንም የአሳሳቢነት ደረጃ ያሳያል፡፡ መተማመንና መቀራረብ የትግሉ የመጀመሪያውና ወሳኙም ምዕራፍ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሥነ-ልቦና ይዞ አገር መገንባት አይቻልም፡፡ በአርምሞ መግባባት፣ መተማመን ብሎም መወያየት አይቻልም፡፡ ባለመነጋገራችን በራሳችን ላይ ትልቅ በደል እየፈፀምን ነው፡፡ በየፊናችን ለጨቋኞች አርጩሜ ጀርባችንን በግላጭ እየሰጠን ነው፡፡ ጀርባችን ላይ ማህተም እየመቱ እንዲያግዙን እየተስማማንም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በእቅፋችን ውስጥ ያሉ ህፃናትን ወይንም ቀጣዩን ትውልድ እኛ እያለፍንበት በአለው ጭቆና እንዲያልፉ ሁኔታዎችን እያመቻቸን እንደሆነ በጽሞና መገንዘብ ያሻናል፡፡ ኃላፊነትም ልንወስድ ይገባል፡፡
በሌሎች አገሮች ያለ ሕዝብ መተማመን መቀራረብ ብሎም በትግሉ የጭቆና ሥርዓቶችን መገርሰስ ከቻለ እኛ የማንችልበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም፡፡ አገዛዙ በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ የፈፀማቸው በደሎች ሰምበር ሁልጊዜም የሚያመን ቁስል ነው፡፡ ፈውሱም መታገል ነው፡፡ እየመሸ ያለው የአገዛዙ የእውር ድንብር ጉዞ የታሪክ ፀኃፊዎች ድርሻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድርሻ ደግሞ ከእንግዲህ በግልጽ በሰንበሮቹ ላይ መወያየት፣ ከችግሮቹም እንዴት ሊወጣ ነፃነቱንም እንዴት እንደሚጎናፀፍ ዘዴ መዘየድ ‹‹ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ›› ሊሆን ይገባል፡፡ ሕዝቡ ከሁሉም አስቀድሞ በራሱ ወርቃማ የለውጥ ኃዋርያነት ብሎም የታሪክ ፈርጥነት ሊያምን ይገባዋል፡፡ በመጨረሻው ሰዓት በታሪካችን እንደሆነው ሁሉ የለውጥ አልፋና ኦሜጋ ሕዝብ እንጂ ጥቂት ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡ አይደለንም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይችላል፡፡ በተደጋጋሚ ወራሪዎችን ተፋልሞ አስደማሚ ታሪክ ሰርቷል፡፡ ከገዢዎቹም ጋር ግብግብ ገጥሞ ጥሏቸው ያውቃል፡፡ መዘውሩን ግን በእጁ ጨብጦ እስከወዲያኛው የነፃነቱ ባለቤት ለመሆን እስካሁን አልቻለም፡፡ ከዚህ ሁሉ የጭቆናና የአፈና ዶፍ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማቁን ጥሎ ትቢያውን አራግፎ እንደሚነሳ ለአፍታም አንጠራጠር፡፡
ከትውልድ ሰንሰለት ጋር ተገምዶ የመጣውን የጭቆና ገመድ ከሰንሰለቱ ላይ ነጥሎ መበጠስ ይገባል፡፡ ሕዝብ ከገዢዎቹ መዳፍ ራሱን ነፃ ለማውጣት መታገል አለበት፡፡ አዳዋ ተሳክቷል፡፡ ለውስጥ ነፃነታችን የምናካሂደው ሚያዚያ 3ዐ ግን ገና ነው፡፡
በትውልድ የሠንሠለት ጫፍ ላይ ሌላ ትውልድ እንደዘለበት ሆኖ ብቅ እያለ ነው፡፡ የሰንሰለቱ ጫፍ እሳት ውስጥ በመቆየቱ ምክንያት የእሳቱን መልከ እየያዘ ነው፡፡ ሁለንተናችን ጭቆናን እየተወዳጀ ነው፡፡ አልችልም ባይነት ቤቱን እየሰራብን ነው፡፡ ድምጽ አልባ አለቶች ድምጽ አውጥተው እንዲጮሁ በሚያደርግ የጨቆናና የችጋር እቶን እየተበላን አርምሞን መፍትሔ አድርገን ወስደናል፡፡ በሚንተከተከው የችጋርና የጭቆና እሳተ-ገሞራ ውስጥ ሆነን እቶኑን ለማስቀጠል የሚወጡ የወዮልህ ድምፆች ያስበረግጉናል፡፡ በአንድ የመከራ ሸለቆ ውስጥ እየፈሰሰን አለመነጋገርንና አለመቀራረብን የብልህነት ቁንጮ አድርገን ወስደነዋል፡፡ ከጭቆና ጋር በመተባበር መፍትሔ እንደማይገኝ እየተረዳን አገዛዙን የነፃነት ደጃፍ ነው እያልን ራሳችንን እንሸነግላለን፡፡ እኛ ምን አይነት ኢትዮጵያውያን እየሆንን ነው? ለጭቆናና ለችጋር መፈልፈል ምክንያት የሆኑ ተግባራትን እየከወንን በየቤታችን እናለቅሳለን፡፡ ከተስፋ መቁረጥ ጋር የተጋባን እንመስላለን፡፡ ጥቂቶች ለመታገል ሲከጅሉ እንደኛው ተስፋ ቆርጠው እንዲቀመጡ እንመክራለን፡፡ የውስጥ ነፃነታችን ቁጥር አንድ ጠላቶች እኛው ራሳችን ነን፡፡ እኛ ችግሮቻችን ፈተን ለነፃነት ትግል ስንነሳ የሚንተከተከው የችጋርና የጭቆና እሳተ ገሞራ መቀዝቀዝ ይጀምራል፡፡ ብርቱ የነፃነት ትግል ማድረግ ስንችል ደግሞ ከእሳትነት ወደ ክሰልነት ከዚያም አለፎ ወደ አመድነት ይለወጣል፡፡ የዛን ጊዜ የትውልድ የፀደይ ቀናት ተግተልትለው ይመጣሉ፡፡የጭቆና ሰንበሮቻችን ይከስማሉ፡፡ እስካሁን ያላቆምነውን ከቅርሶቻችንን ሁሉ የላቀውን ታላቅ ሀውልት በአንድነት እናቆማለን፡፡ የነፃነት፣የእኩልነትና የወንድማማችነት ሀውልት ሰማያችንን ስር ተደርሮ ይቆማል፡፡