በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ነዋሪዎች “በክልላችን ረሀብ ገብቷል ብላችሁ አትናገሩ” ተብለው መታዘዛቸው ተዘገበ
“በክልላችን ረሀብ ገብቷል ብላችሁ አትናገሩ” ተብለው መታዘዛቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ነዋሪዎች ለኢሳት የምርመራ ቡድን መናገራቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ዘገበ:: ኢሳት በዚሁ ዘገባው ላይ እንደገለጸው ወኪሎቹ ሰሞኑን በደቡብና በኦሮሚያ ክልል የገጠር አካባቢዎች በመጓዝ የአካባቢውን ህዝብ ያነጋገሩ ሲሆን፣ ከህዝቡ በተገኘው መረጃ መሰረት ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ እርዳታ እንደሚከለክል፣ የህዝቡን መብት እንደሚያፍንና፣ ለኢንቨስትመንት በሚል ህዝቡን እንደሚያፈናቅል ከነዋሪው ለማረጋገጥ መቻላቸው ታውቋል።
ኢሳት በተጨማሪም አያይዞ እንደዘገበው በኦሮሞያ ክልል የሚገኙ አንዳንድ ነዋሪዎች፡ በፖለቲካ አቋማቸው የተነሳ የእርዳታ እህል እንዳያገኙ መከልከላቸውንም ኢሳት ዘጋቢዎቹ ያነጋገሯቸውን ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ አጋልጧል። በደቡብ ክልል ደግሞ ዘረኛው አገዛዝ በአካባቢው ረሀብ መግባቱን ለማንም እንዳትናገሩ ብሎ ለህዝቡ ትእዛዝ መስጠቱን በጋሞጎፋ ዞን የሚገኙ ነዋሪዎች ከኢሳት ዘጋቢ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ተናግረዋል።
ቀደም ብሎ በዚሁ የደቡብ ክልል ሰፋፊ ለም መሬቶች ለኢንቨስተሮች በርካሽ ዋጋ ሲቸበቸብ እነደቆየ በስፋት የተዘገበ ሲሆን ለዘመናት ከኖሩበት ቀየ እየተፈናቀሉ መሬታቸው ለኢንቨስተሮች እየተሰጠ መሆኑ እንዳሳዘናቸውም ለነዚሁ የኢሳት ዘጋቢዎች የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በሌላም በኩል የኢሳት ዘጋቢዎች የብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ቢቢሲ የእርዳታ እህል ለተገቢው አላማ እንዳይውል ተደርጓል፣ ከምእራባዊያን ለወያኔ አገዛዝ የሚጎርፈው በቢሊየን የሚቆጠር የዶላር ርዳታም ህዝብን ለማፈንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ለመጨፍለቅ ውሏል በማለት በቅርቡ የሰራው የምርመራ ዘገባ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻላቸውን የኢሳት ዘጋቢዎች የላኩት ሪፖርት ማመልከቱ ታውቋል።
የዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛ ቁንጮዎች ቢቢሲ ያወጣው ዘገባ እጅግ በጣም ያበሳጫቸው መሆኑንና የቢቢሲንም ዘገባ የማዳፈን እንዲሁም በቢቢሲ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።