ሰሞኑን በጋዜጠኞች ላይ የጭካኔ በትሩን ያነሳው አፋኙ የወያኔ አገዛዝ ይህን እኩይ ተግባሩን በኢንተርኔት ካፌዎችና ተጠቃሚዎች ላይ መቀጠሉ ተዘገበ

አዲስ ነገር ኦን ላይን በመባል የሚታወቀው ድረገጽ እንደዘገበው ሰሞኑን ክፉኛ ይቃወሙና ይተቹት በነበሩ ጋዜጠኞች ላይ የጭካኔ በትሩን ያነሳው አፋኙ የወያኔ አገዛዝ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የኢንተርኔት ካፌዎች ላይ ፊቱን ማዞሩ ታውቁአል። እንደ አዲስ ነገር ዘገባ፣ የዘረኛው ወያኔ አገዛዝ ከቅርብ ወራት ወዲህ የስለላ ሃይሎቹ በሙሉ አቅም ተሰማርተው በኢንተር ኔት ካፌዎች ላይ ጥብቅ ክትትል ሲያደርጉ እንደቆዩ የታወቀ ሲሆን፣ የአዲስ ነገር ሪፖርተር ከአዲስ አበባ እንደገለጸው ባለፈው ሳምንት ኢንተርኔት ካፌ ውስጥ ሆኖ አገዛዙን የሚቃወሙ ድረገጾችን ይመለከት የነበረን ተጠቃሚ ድረገጾቹን እንዳያነብና እንዲዘጋቸዉም ሲያስጠነቅቁት፣ በትዝብት መመልክቱን ገልጹአል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሌላ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ግለሰብ በዘረኛው አገዛዝ ሶስት ታጣቂ ሃይሎች ከኢንተርኔት ካፌ እንዲወጣ መደረጉና ፕሮክሲ ሰረቨርን በመጠቀም ጸረ ሰላም የሆኑ መረጃ ድረ ገጾችን ማንበብ ወንጀል እንደሆነና በሃገሪቱ ህግም እንደሚያስቀጣ ገልጸው ከከባድ ማስጠንቀቂያ ጋር እንደለቀቁትም ታውቁአል። እንዲህ አይነት ተግባራት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም ተስፋፍተው ያሉና እየተተገበሩ መሆናቸውንም አዲስ ነገር አክሎ ዘግቡአል።

ባለፈው ማክሰኞ አራት ኪሎ የሚገኙ ሁለት የኢንተርኔት ካፌዎች መዘጋታቸውንና ባለቤቶቹም ወደ እስር ቤት መወሰዳቸውን የዘገበው አዲስ ነገር፤ እነኝህን የካፌ ባለቤቶች ወደ እስር ቤት የወሰዱ ማንነታቸውን ቀይረውና የሲቪል ልብስም ለብሰው ሲሰልሉ የነበሩ የደህንነት ሰራተኞች መሆናቸውን ገልጹአል። በኢንተርኔቱ ውስጥ የነበሩት ኮምፒዩተሮችም በፖሊሶች መወሰዳቸውን፣ የኢንተርኔት ካፌ ባለቤቶቹም የተያዙት ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ወንጀል ሰርታችኋል በሚል እንደሆነም ፖሊሶች መናገራቸውም ተያይዞ ተገልጹአል።

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ አሁን እየፈጸመ ያለው ድርጊት ጭራሹኑ ዘግናኝና ህዝብን ዝቅ አድርጎ ከማየትም ያለፈ እንደሆነ አስተያየታቸውን ለአዲስ ነገር ዘጋቢ የገለጹ ግለሰቦች ቀደም ብለው በፖሊስ የተወሰዱት የኢንተርኔት ካፌ ተጠቃሚዎችና ባለቤቶች የት እንደደረሱ እንደማያውቁም መናገራቸው ታውቁአል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባሁኑ ሰአት የዘረኛው ወያኔ አገዛዝ የወቅቱ የጥቃት ኢላማዎች ኢንተርኔት ካፌዎች መሆናቸው በስፋት እንደሚታወቅ ተገልጹአል።

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ ሞልቶ ከፈሰሰ ጊዚያቶች የተቆጠሩ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያዊያን የአገዛዙ የፕሮፓጋንዳ ማሺኖች ከሆኑት የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ስርጪቶች ውጪ ምንም አይነት አማራጭ መረጃ እንዳያገኙ ለማድረግ ሌት ከቀን እየሰራ እንደሆነ በተደጋጋሚ ስንዘግብ መቆየታቸን ይታወሳል።