የፋሽስቱ መለስ ዜናዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ እየፈፀመ ስላለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ይፋ ላደረገው የቢቢሲ መርማሪ ጋዜጠኞች ቡድን አስተያዬታቸውን በሰጡት በሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ ላይ የውንጀላ ዘመቻ መክፈቱ ተዘገበ። የሰብዓዊ መብት ጥሰቱንም ” የደርግ ርዝራዦች የሚያናፍሱት የፈጠራ ወሬ ነው” ሲል ማጣጣል ጀምሮአል
የወያኔ አገዛዝ ከምዕራባዊያን ለጋሾች የሚቀበለውን የዕርዳታ ገንዘብ እንዴት አድርጎ የፖለቲካ ሥልጣኑን ዕድሜ ለማራዘም የሚያስችል ድጋፍ እንደሚገዛበትና ተቃዋሚዎችንም ለማፈን እንደሚጠቀምበት ሀምሌ 29 ቀን 2003 ዓ.ም በታዋቂው የቢቢሲ ቴለቪዝን ላጋለጡት የምርመራ ጋዜጠኞች ቢሮ ቃላቸውን የሰጡትን ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን፤ዶክተር መረራ ጉዲናንና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን “የአገርን መልካም ስም” ማጉደፍ“ በሚል ወንጀል፤ ዘመቻ የከፈተባቸው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ፤ በመረጃ ይፋ የሆነውን የቢቢሲን ዘገባ እራሱ በሚቆጣጠራቸው ሬዲዮና ቴሌቪዝን ማብጠልጠል መጀመሩን የግንቦት 7 ዘጋቢ ከላከልን ሪፖርት ለመረዳት ተችሎአል።
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ፤ በረሀብ፣ በድህነት፣በዲሞክራሲ እጦትና፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የምትታወቀውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስኬታማ ባልሆኑ መንግስታት(ፌይልድ ስቴትስ) ተርታ እየተመደበች ስላለችው አገራችን የሚያውቁትን በአደባባይ የሚናገሩ ተቃዋሚዎችን “የአገርን መልካም ስም በማጉደፍ ተግባር ተሰማርተዋል” በማለት የሚከሳቸው የመለስ በረከት አገዛዝ “ጎደፈ ስለሚባለው መልካም ስም” የሰጠው ዝርዝር ግን የለም። ቢቢሲን የመሰሉ አለም አቀፍ ከበሬታና ታማኝነት ያላቸው ሚዲያዎች የሚያወጡዋቸው ዜናዎችና ዘገባዎች ከዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን በቀላሉ የሚደርስ በመሆኑ የተደናገጠው የወያኔ ቡድን የሚይዘውንና የሚጨብጠውን በማጣቱ ምስክርነታቸዉን ለቢቢሲ የሰጡትን ዜጎች “የደርግን ስርዓት ለመመለስ የሚሰሩ” ብሎ እስከ መወንጀል መድረሱ ብዙዎችን አስገርሞአል።
የደርግ ሥርዓት ከወደቀ ከሃያ አመት ቦኋላ ወያኔ አሁንም ለውጥ ፈላጊዎችን በደርግ ሥርዓት ናፋቂነት መክሰሱ ምናልባት ሰሞኑን ከወደ ዚምባብዌ በህይወት መኖራቸውን ከመግለጽ ላላለፈ ጉዳይ ድምጻቸውን በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ያሰሙት የቀድሞው አምባገነን መንግሥቱ ሃይለማሪያም መልዕክት ሌላ ተጨማሪ ሽብር ፈጥሮበት ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ አሳድሮአል።
በኢትዮጵያ ደሃ ህዝብ ገንዘብ የሚተዳደረው ሚዲያ ሰሞኑን በቢቢሲ ላይ ስለተከፈተው ዘመቻ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሮፈሰር በየነ ጰጥሮስ “ይህ ሰሞኑን በወያኔ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የምንሰማው ማስተባበያ ‹‹ችግሮችን ለመሸፈን የሚደረግ ከንቱ ፕሮፖጋንዳ ነው›› በማለት አጣጥለውታል፡፡
‹‹የምንለው በሬ ወለደ አይደለም በምርጫ ስለተሸነፍንም አይደለም፡፡ ሕዝባችን በረሃብ እያለቀ መሆኑን ስላረጋገጥን ነው፤›› ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ ዕርዳታ- በመንግሥት መዋቅር ቁጥጥር ሥር በመሆኑ ለፖለቲካ መሣርያነት እየዋለ እንደሆነ በደቡብ የሚገኙ በርካታ ቦታዎችን በመጥቀስ እርግጠኛነታቸውን በድጋሚ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም በአገራችን እየተፈጸመ ስላለው ሰቆቃ ያጋለጠው ዶክመንተሪ ከመሰራቱ በፊት ፤ ጋዜጠኞቹ ሲያነጋግሩዋቸው በእርዳታ እየተቀጡ ካሉ ደጋፊዎቻቸው ያገኙትን መረጃ ተመርኩዘው ለቢቢሲ ጋዜጠኞች መንገራቸውንና ወደስፍራዎቹ ሄደው በራሳቸው መንገድ እንዲያጣሩ ጥቆማ መስጠታቸውንም ፕሮፌሰር በየነ አልሸሸጉም።
ፕሮፌሰር መስፍን በበኩላቸው፣ ‹‹መንግሥት በእኛ ላይ የሚያቀርበው ወቀሳ ምንም አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ግን ትችት ተቀብሎ ችግሩን ከማስተካከል ይልቅ፤ማን ምን አለ? ወደሚል ጨዋታ መግባቱ ነው››ብለዋል።
በአገሪቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክተው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታ እያቀረቡ መሆናቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ለፍትህ ሲሉ የሚሠሩትን ሥራ በማጣመም ባለሥልጣናቱ “መንግስቱ ሀይለማርያምን ለማስመለስ ነው የሚሰራው” ማለታቸው እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል።
ፕሮፌሰሩ አክለውም፦‹‹ሌላ አገር ቢሆን፣ እንዲህ ዓይነት ትችት ሲቀርብ ችግሩን ተቀብሎ አጣራለሁ፣ አስተካክላለሁ ነበር የሚባለው፤ በእኛ ላይ የሚያደርጉት ውርጅብኝ መቼም የሚቀር አይሆንም፡፡ አገሪቷን ግን እየገደሏት ነው፡፡ የያዙት ነገር ስለማያዋጣ፤ሌላ መንገድ ቢከተሉ ነበር የሚሻላቸው፤›› ብለዋል።