መገናኛ ብዙኃን ከፓርቲ ልሣንነት ነጻ ይውጡ! በታረቀኝ ሙጬ

NO, we do NOT agree with everything we post on the site. Some of it is utterly antithetical to our views. YES, we believe it is all worth reading. Know your surroundings; understand the positions of those with whom you disagree. Keep the dialogue and discourse free and open. And let the truth fall where it may.

Source: http://www.rense.com

የለም፣ በድረገፅ(-ኣችን) በሚወጣ ማንኛውም ሃሳብ ሁሉ አንስማማም፡፡ አንዳንዱ ጽሑፍ እንዲያውም ከእኛ አስተሳሰብና እምነት ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ ሁሉም ግን የመነበብ ዕድል እንዲያገኝ እምነታችን ነው፡፡ አካባቢን ማጤን ጥሩ ነው፤ በሃሳብ የማትስማማቸውን ወገኖች አቋም መረዳትም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ (መልዕክቱ ምንም ይሁን ምን) የሃሳብ ልውውጥንና የእርስ በርስ ውይይትን ለሁሉም ነጻና ክፍት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እውነት ተጣርታ ትውጣና ወዳሻት ታጋድል፡፡
ምንጭ፤ http://www.rense.com

ማንም ሰው የፈቀደውን ማንኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ንቅናቄ ወይንም ድርጅት የመደገፍ፣ አባል የመሆንና ሲያሻውም (በተቻለ መጠን በሰላማዊ መንገድ) የመቃወም፣ የመተቸትና ነቀፌታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ይህ ተፈጥሮኣዊ መብትም በምንምና በማንም ኃይል ሊገደብ ወይንም ሊሸረሸር አይችልም፤ አይገባምም፡፡ የማፍቀር፣የመውደድና የመቀራረብ መብት እንዳለ ሁሉ ያለማፍቀር፣ ያለመውደድና ያለመቀራረብ መብት እንዳለም ማንም አይዘነጋውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በፍቅር ደንብዞ አቅልን መሳትና ሁለንተናዊ ሚዛናዊነትን ማፋለስ እንደማይገባ ሁሉ በጥላቻና በቅድመ-አእምሮ ፍርድ(Bias and Prejudice) ተመርኩዞ ሊኖር የሚገባን መልካም ግንኙነት ማጠየም እንደማይገባም መረዳት በጣም ጠቃሚና ዘመናዊነትም ነው፡፡

ማንም ሰው ሲባል ደግሞ በቀለም፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በሙያ ወይም በሥራ ዘርፍ፣ በፆታ፣ በድንበርና በመሳሰሉት ተፈጥሮኣዊ ልዩነቶችና ሰው ሠራሽ አጥሮች ሳይገደብ በሰውነቱ ብቻ ሰው የሆነ ሁሉ ማለት መሆኑን ማንም አያጣውም፡፡ ዛሬ ዛሬ ሌሎች እንስሳት እንኳን እየሰለጠኑ ከሌሎች ዝርያዎች ጋር በሰላምና በፍቅር መኖር እየቻሉ ነው፡፡ ሰውማ ከእንስሳት እንዴቱንስ ያህል አይሻል?

በጋዜጠኝነት ሙያ የተሠማራም ሰው እንደማንኛውም ሰው የሚደግፈውና በክብር ወይም በሙሉ አባልነትም ተመዝግቦ አስፈላጊ ሆኖ የተገኘ ግዴታውን ሁሉ የመወጣት ኃላፊነትና ግዴታ የሚኖርበት ፓርቲ ሊኖረው እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና ይህን ሲያደርግ ሙያውንና ጊዜውን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በይፋ ለፓርቲው አገልግሎት ሊያውል ይጠበቅበታል እንጂ እንደእውነቱ ከሆነ በዴሞክራሲ ስም ወደነጻ ሚዲያ ገብቶ የሚዲያን ልጓም በመጨበጥ በነጻ ሚዲያ ሊገኝ ይችላል ተብሎ የሚጠበቅን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት እንዲያፍን አይጠበቅም፡፡ እንዲያ ካደረገ ራሱም በከፋ ባርነት ውስጥ የወደቀ ከመሆኑም በላይ ሙያውን ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ እንደጨመረ ይቆጠራል፡፡ ‹የቄሣርን ለቄሣር፤ የእግዜርን ለእግዜር› ማድረግ ሲገባ እንጀራንና የፖለቲካ እምነትን ማጫፈር በ‹ሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው› የኃጢያት ማስተስረያ ቀኖና ታጥቦ ሊጸዳ የሚችል ጥፋት አይደለም፡፡ የሀገራችን ጉዳይ ከዚህ መሠረታዊ ስህተት አንጻር ሲፈተሸ ብዙ የሚመዘዝ ነገር አያጣውም፡፡ በሌሎች ከፍ ያሉ የሚመስሉ ጥፋቶችና ስህተቶች እምቡር እንላለን እንጂ የእያንዳንዳችንን ጓዳ ጎድጓዳ ብንዳስስ ለአቅመ መዝገበ ጊነስ ሳይቀር ሊታጩ የሚችሉ ታላላቅ እንከኖችንና ህፀፆችን አናጣም፡፡ ምንጮች ወንዞችን፣ ወንዞች ሐይቆችን፣ ሐይቆች ባሕሮችን፣ ባሕሮች ውቅያኖሶችን እንደሚፈጥሩ ሁሉ እነዚህ የየግላችን ጉድፎች ተጠረቃቅመው ሞገድ የበዛበት የእሳት ባሕር በመፍጠር ሀገራችንን እያነገሏት መሆናቸውን ብዙዎቻችን የተረዳን አንመስልም፡፡ በምትኩ አንዳችን ወዳንዳችን ጣት እየተቀሳሰርን የማያልቀውን ጊዜ የምንጨርሰው ያህል እየተሰማን፣ ጊዜ ራሱን ሲያድስ እኛ ግን ከነልጅነታችንና ከነወጣትነታችን በከንቱ እያረጀን እንገኛለን፡፡ ፍርጃን ማምለጥ የሚቻለው በምን ዓይነት ዘዴ ይሆን?

የሌሊት ወፍ አጥቢ ናት፡፡ በሌላም በኩል ወፍ ናት፡፡ ወፍነትና አጥቢነት ደግሞ እንዲህ ሲገጣጠሙ በጣም የተለዬ ነገር ነው – ክስተተ ሃሊዮኮሜትን ያስቧል፤ በ76 ዓመት አንዴ እንደምትታየው ዓይነት፡፡ የሌሊት ወፍ ለአጥቢዎች ባዕድ ናት፤ ለአእዋፍ ዝርያም እንዲሁ ባዕድ ናት፤ ከሁለት ያጣ ጎመን እንደሆነች እስከ ዓለም ፍጻሜ ትኖራለች፡፡ ከሁለት ወዳንዱ እንዳትጠጋ የኔ ናት ብሎ አምኖ የሚቀበላት የለምና፡፡

ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ማንንም ወይንም ምንንም የመደገፍና የመቃወም ጉዳይ የግል መብት ሆኖ በነጻ ሚዲያ ረገድ ግን ፍጹምም ባይሆን አንጻራዊ ፍትሃዊነትና ከአድልዖ የራቀ መስተንግዶ እንዲኖር ሙያው ያስገድዳል፤ እንደመንግሥታት ሥልጣን እርሱም በመፈንቅለ – ጋዜጠኝነት ሙያው ካልተበረዘ፡፡ ‹ማጥፊያ ማብሪያው በጄ ውስጥ እስካለ ማን ምናባቱ ያመጣል?› የሚለው ከሙያዊም ከሰብኣዊም ሥነ ምግባሮች የራቀ እንደልቡነት ግን እንኳንስ ነጻ በሚባለው ሚዲያ በኢ-ዴሞክራሲያዊነታቸው ክፉኛ በምናብጠለጥላቸው የወያኔና መሰሎቹ ባለአንድ አቅጣጫ የመገናኛ ብዙኃንም አላማረም፡፡ ጀብደኝነትን ተላብሶ ነጻነትን መሻት መጸዳጃ ቤት ተቀምጦ የናርዶስ ሽቱን መመኘት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ በዞረ ድምር ውጤቱ ‹ካርማ›ን (የመንፈስ ንጽሕናን?) ከማጽዳት ይልቅ ይበልጥ የሚያቆሽሽና የምንቃወማቸው ወገኖች የሚጓዙበትን የበከተ ጎዳና በሌላ አቅጣጫ አቋርጦ በመቀላቀል ‹ከጎናችሁ ነን! ልዩነታችን አፍኣዊ እንጂ ልባዊ እንዳይመስላችሁ!› በማለት የአትርሱኝን መልእክት የማስተላለፍ ያህል ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ለውጥ የገደል ላይ ወይን እንደሆነች ትቀራለች እንጂ አትገኝም፤ ሱሚ ነው፡፡ ስለዴሞክራሲ የሚሰብክ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፤ ስለፍቅር የሚሰብክ አፍቃሪ መሆን አለበት፤ ስለመግባባት የሚሰብክ ተግባቢ መሆን አለበት፤ ያልሆኑትን መስሎ ሊሆኑ የማይችሉትን መመኘት ለቅስፈት ካልሆነ እውናዊ አይሆንም፡፡ ብዙ ችግሮች አሉብን በእውነት፤ ከሁሉ በፊት ሚዲያው ሱባኤ ይግባ፡፡ ጫፍ ላይ የተበላሸ ነገር ሥሩም ብልሹ ነው፡፡

በስሜት ፈረስ እየተጓዙ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ፍትህ የሚሻ ራሱ ቀድሞ ፍትሃዊ ይሁን፡፡ በደልን የሚጠላ ራሱ ቀድሞ ከበደለኛነት ነጻ ይሁን፡፡ በመጽሐፉ ‹በጓደኛህ ዐይን ውስጥ የሚገኘውን አነስተኛ ጉድፍ ለማውጣት ከመሞከርህ በፊት በራስህ ዐይን ውስጥ የሚገኘውን እርፍ እሚያህል ጉድፍ አውጣ› የተባለው ለቄንጥ ሳይሆን ሁላችንም የምንለውንና የምናደርገውን አመዛዝነን ወደተገቢው የጉዞ አቅጣጫ እንድንጓዝ ለመርዳት ነው፡፡ አለበለዚያ አለባብሶ እንደማረስ ነው፤ አረሙ ገበሬን ሊያደክም – ምርቱም ላያምር፡፡

ስለዚህ አማራጮችን ለይቶ ማወቅ በየትኛውም ደረጃ የፍትህ ሰዎች እንድንሆን ያስችለናልና ጊዜ ሳንፈጅ የሚበጀንን እንወቅ፡፡ ባለማወቅ በልማድና በይትበሃል የምንጓዘው ጉዞ አበሳችንን እያበዛው ከመሄድ ውጭ አንዳችም ነገር አይፈይድልንም፡፡ ለበርካታ አሠርት ዓመታት ተጓዝን፤ ምን አመጣን? ከሞላ ጎደል ምንም!

ያሉን አማራጮች እነዚህ ናቸው፡፡ አንድም የጋዜጠኝነትን የሙያ ሥነ ምግባራት በቅጡ ጨብጠን ለሙያዊ ሥነ ምግባር በመገዛት ግላዊ ጥቅምና ፍላጎታችን በሥራችን ጣልቃ እንዳይገቡና ትዝብት ላይ እንዳይጥሉን ማድረግ፤ አንድም ሙያውን አደጋ ላይ ላለመጣልና የእኛንም ሙያዊ ስብዕና ላለማጉደፍ በወደድነው ፓርቲ ሥር ገብተን የፓርቲውን ልሣን ማዘጋጀት፤ አንድም ከዚህ የተከበረ የጋዜጠኝነት ሙያ በጊዜ በመሰናበት ሌላ ሥራ መሥራት፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉት አማራጮች ብዙም የማያወላዱና በእንደእስካሁኑ የ‹መስቀል ከቀላጤ› ጉዞ የትም እንደማንደርስ መረዳት ተገቢ ነው፤ የጋዜጠኝነትን ሙያም ከተጨማሪ መጋጋጥና መፋፋቅ ማዳን የሚቻለው ከነዚህ የመፍትሔ ሃሳቦች ባንዱ ስንጸና ነው – ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ሁኔታ፡፡ የየት ሀገር ደብተራ እንደሆነ ለጊዜው ተዘነጋኝ እንጂ ቅኔው ቢጎድልበት ቀረርቶ ጨምሮ ምዕመናንንና ቀሳውስትን በቅኔ ማኅሌት ውስጥ አስቋቸዋል ይባላል፡፡ የጨነቀውስ እርጉዝ ያገባል ይባል የለም? – (ስትወልድበት ገደል ለመግባት)፡፡ መስቀል ከቀላጤ መባሉም እንደ አንዳንድ ‹ብሩካንና ብፁኣን› የዘመናችን አባቶች በመስቀል ሊባርኩ ዕጃቸውን ወደኪሳቸው ሲሰዱ በስህተት ሽጉጥ የማውጣታቸውን ‹ምሥጢረ ተክህኖ› ለማጠየቅ ነው፡፡ የመረገም ዓይነቱ ብዙ ስለሆነ የተሠማራንባቸውን ሙያዎቻች በአግባቡ ከመወጣት አኳያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በርካታ ዘርፎችም የሚታዩብን ማኀበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ነውሮችና ገመናዎችም እጅግ አሰቃቂ ናቸው፡፡ ትልቁ ችግር ደግሞ ችግር የለብንም ብለን ማመናችን ነው፡፡ ይህ ችግር ከአራት ኪሎ እስከ ዲያስፖራው ሰንጎ የያዘን የምዕተ ዓመቱ ወረርሽኝ ነው፡፡ ‹ አሃ! ይህች ሴት የምትለው ነገር ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም! እስኪ በወጉ ላዳምጣትና እኔም ልሞክረው› አንልም፡፡ ለምን? ለምንማ ለዘመናት የገረረው ባህላችን ራስን ወዳድና ሌሎችን ናቂ አድርጎ ኮድኩዶናላ – ብዙዎቻችንን፡፡ አያሳዝንም? እስኪ ፈረንጆችን ተመልከቱ፡፡ እንደኛ እንደብዙዎቻችን በትዕቢትና በዕብሪት የተወጠረ አለ? አይኖርም ባይ ነኝ፡፡ ያን ደረጃ ያለፉት ይመስለኛል – ከመነሻው ኖሯቸውም ከሆነ፡፡ የኛ እኮ ለየቅል ነው ትምክህታችን፤ አንዳንዶቻችን በባዶው፡፡ ታዲያ ሚዲያችን እንኳን ዐይኑን እየከፈተ መሄድ የለበትም ትላላችሁ?

እናም ይህ ወቀሳ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ የሚመለከታችሁ ወገኖች ራሳችሁን ካስቀመጣችሁበት የብቃት ማማ ለተወሰነ ጊዜ አውርዱና አሠራራችሁን ፈትሹ፡፡ እኔ ማንንም አትደግፉ ወይ አትቃወሙ የሚል አስተያየት የለኝም፤ ሊኖረኝም አይችልም፡፡ ነገር ግን በጋዜጠኝነት አምላክ ይሁንባችሁ ፍትሃዊ ሁኑ፤ የግል ስሜታችሁን እንደአንድ አንባቢ ወይ ተሳታፊ መግለጽ መብታችሁ ነው – በብዕር ወይም በራሳችሁ ስም፡፡ አንድ የሚዲያ አውታር ባለቤቱ እንደፈለገው የሚያሽከረክረው (የሚፈነጭበት ለማለት ሽቼ ከጨዋነት አንጻር መተዌን ተረዱልኝ) መድረክ ሳይሆን የተለያዩ ሃሳቦች ተፋጭተው አንዳች የጋራ መግባባት ይገኝ እንደሆነ የሚሞከርበት የጋራ መድረክ ነው፡፡ ያልገባን ነገር ሚዲያውን እንደራሳችን የግል ንብረት ማየታችን ነው፤ ያ ፍጹም ስህተት ነው፡፡ እንኳንስ የሚዲያ ተቋም በመርህ ደረጃ አንድ የሸቀጥ መሸጫ ሱቅ (ዐረብ ቤት) የተገልጋዩ ንብረት ነው፡፡ ሀበሻ ‹ባለጌ በቤቱ ይኮራል› የሚል ጥሩ ብሂል አለው፡፡ ሕጻናት ብቻ ናቸው የያዙትን ዳቦ ወይም መጫወቻ ነገር ‹እምቢዬው፤ አላቀምሽሽም› እያሉ ለንብረታቸው ንፉግ የሚሆኑት፡፡ እነሱ ካለማወቅና ካለማገናዘብ ነው፡፡ በሚዲያ አካባቢ ግን ሆደ ሰፊነት፣ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት ወሳኝ ግብኣቶች ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከመነሻው አድልዖዊ ሰው፣ አኩራፊ ሰው፣ ብዙ በማንበብ ዕውቀት ያላዳበረ ሰው፣ ሁልጊዜ በማንበብ የዕውቀት አድማሱን ለማስፋት የማይሞክር ሰው፣ የቂም በቀል ልክፍተኛ ሰው፣ በዘር – በቋንቋ – በቀለም – ባገር ልጅነት … የሚያመልክ ሰው፣ የጥላቻ ፖለቲካን የሚያራምድ ሰው፣ ሰጥቶ በመቀበል የማያምን ሰው … ወደ ጋዜጠኝት ሙያ ትውር ሊል አይገባውም፡፡ ይህ ሙያ በጣም ትልቅ የጨዋነትና የታጋሽነት ባሕርይ ይሻል፡፡ በአንድ በኩል እንደወታደር ማለት ነው – የብዕሩን ወላፈን መቼ ከአፎቱ እንደሚለቅ ሊያውቅ ይገባዋልና፡፡ በሌላም በኩል እንደካህን ነው – የሰማውንና ያየውን ሁሉ በጠማማ ሚዛን እዬሠፈረና በላይዳ እያዘራ አደባባይ ላይ ለዐውሎ ንፋስ አይበትንምና፡፡ ሙያው እጅግ ብርቱ ጥበብን የሚጠይቅ ነው እህቶቼና ወንድሞቼ፡፡

ከሁሉም ከሁሉም አንባቢ መከበር አለበት፡፡ በአንባቢያን በኩል ያለው ተራራ እሚያህል ችግር ለዛሬ ሳይነሳ ይቅርና በአጠቃላይ ግን እንደአካሄድ የሚዲያ ተቋማት አንባቢን ያክብሩ፤ ከአድልዖ ይታቀቡ ማለትን አስምሬበት ላልፍ እወዳለሁ፡፡ የሃሳብ ብፌ በሰፊ ገበታ በማቅረብም አንባቢያን የተለያዩ አማራጮችን እንዲያገኙ ዕድል መስጠት ተገቢ መሆኑን ይገንዘቡ፤ የግንዛቤ ችግር አለባቸው ብዬ አላስብምና ተግባራዊነቱ ላይ ይበርቱና ይሥሩ፡፡ የምንፈልገውን ብቻ ሳይሆን የማንፈልገውንም ለመውደድ እንሞክር፡፡ የማንወደውና የማንፈልገው ከሚመስለን ነገር ውስጥ ስንትና ስንት ዕፁብ ድንቅ ነገር እንደሚገኝ ከጋዜጠኛ በላይ የሚያውቅ አለ ብዬ አላምንም፡፡
ይህንን አስተያየት ለመሰንዘር ያበቃኝ ሰሞኑን የላክሁት አንድ ጽሑፍ በእስካሁኑ ሁኔታ ከሦስት ድረገጾች በስተቀር በሌሎቹ የውኃ ሽታ ሆኖ በመቅረቱና ለመቅረቱም አሳማኝ ሆኖ ያገኘሁት ምክንያት ስለሌለ ነው፡፡ እንደእውነቱ የኔ አስተያየት ወጣ አልወጣ በሀገር ነጻነት ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ መምጣት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊም ይሁን አወንታዊ ተፅዕኖ በጭራሽ የለም፡፡ ትርፉ ትዝብት ብቻ እንጂ ነው፡፡ እኔም የበኩሌን የተሰማኝን ለመሰንዘር እንጂ አነሳሴ ለክፋት አልነበረም፡፡ ለማንኛውም ግን ‹ከፊት የወጣ ጆሮ እያለ ከኋላ የወጣ ቀንድ በለጠ› እንዲሉ ሺዎች ዓመታትን የኖረች ኢትዮጵያ ተጋድማ በወያኔ እየታረደች ባለችበት ወቅት ትናንት የመጡ ንቅናቄና ግምባር ተብዬዎች በልጠውባቸው እኔን ሳይሆን የላክሁላቸውን ሀገር ምድሩ የሚያውቀውን እውነት ሳያወጡት መቅረታቸው ቢያሳዝነኝም ስልሳዎቹን እያጋመሰ ላለው ዘልዛላው ዕድሜየ ምሥጋና ይግባውና የወገኖቼን ባሕርይ ጠንቅቄ የማውቅ በመሆኔ እውነቱን ለመናገር ብዙም አልተከፋሁም፡፡ የሀገሬ ሁኔታ ሀገሬንም ያሳጣኝ በመሆኑ የነሱ ከዚህ አይብስምና ማቅ የሚያስለብሰኝ ነገር እስካሁን የለም፡፡ ይሁንና በዚህ አሠራር ስንቶች እየተበሳጩ ከሚዲያው እንደሚገለሉ በምናቤ ስለታየኝ ይህችን ጽሑፍ ጫጭሬ እንደገና ልልክ ተገደድሁ፡፡ ይህችኛዋንም ስንቶቹ እንደሚቀበሏት ገና ላይ ነኝ፡፡ መቼም አያርመኝ፡፡(‹ር›ን ላላ) አሁንም በለስ ከቀናኝ እመለስ ይሆናል፡፡ የገባብንን መግረሬ ፀር ፈጣሪ ይንቀልልን፡፡ ስደትንና እንግልትን በቃችሁ ብሎ ለሁላችንም በምትመች ሀገረ ኢትዮጵያ ዳግም ያሰባስበን፡፡ የ‘ለያቸው፤ ገነጣጥላቸው’ አባዜ ማርከሻው ተገኝቶ በአዲሱ የ2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ መሰባሰቢያችን ትሁን፡፡ በዘርና በጎሣ የሚያቧድነን ፀላኤ ሠናያት ተወግዶ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የቀድሞ ባንዲራችን ጥላ ሥር በፍቅር የምንመሰግበት ዘመን በቶሎ ይምጣልን፡፡ የትልቅ ሰው ምርቃት አይናቅምና ‘አሜን’ በሉ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

 በዚያኛው ጽሑፌ ያነሳሁት የኦነግ ጉዳይ አሳሳቢነቱ መቶ በመቶ ሆኖ የሚወራለት የትብብር መድረክ ምሥረታን በሚመለከት ደግሞ ‹ቂጣም ከሆነ ይጠፋል፤ ሽልም ከሆነ ይገፋል› በሚለው ልናሳድረው እንችላለን፡፡ ነግ ከነግ ወዲያ ቁርጡ ስለሚታወቅ ያኔ ለማማቱም ለማመስገኑም ያደርሰናል፡፡ በኦነግ ላይ ያለኝ አቋም ግን እኔንም አናቴን እየበጠበጠኝ ነው፤ ጥሩ ሰዎች አይደሉም በውነቱ፤ ያናድዳሉ፡፡ ኦሮሞዎቹ ቀ.ኃ. ሥላሴና መንግሥቱ ኃ/ማርያም የመሯት ኢትዮጵያ በምናብ የተፈጠረችዋን ኦሮሚያን ቅኝ ግዛት ሲያደርጓት እየታየኝ እንዴት ጤንነት ሊሰማኝ እችላለሁ?