ታይቶ ያልተወቀ የሰደድ እሳት በአዲስ አበባ
“የደላው ሙቅ ያኝካል” – የኑሮ ውድነቱ እንደቋያ እሳት ከዳር እዳር እየተንቦገቦገ ባለጊዜን ሳይጨምር ሕዝበ አዳምን ክፉኛ እየለበለበ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት የኢንተርኔቱ ጦርነት አፈ ሙዙን በኦነግ፣ በኦብነግና በግንቦት 7 ላይ አነጣጥሮ የደላቸው በብዕር እየተተጋተጉ ናቸው፡፡ ሰው በወደደው ይቆርባልና እንደጠቅላይ ሚኒስትራችን አባባል (ኦኦኦ ‹ሚኒስትሬ› ይባልልኝ እባካችሁ ተስቶኝ ነው) መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው፤ አድባርም ትከተላቸው፡ ለዬሚፈልጉትም ድል ታብቃቸው – አንድም ሳታዳላ፡፡ እኛ ባገር ቤት ያለነው ግን ያማረን የብዕር መትረየሳዊ ማፏጨት ሳይሆን ዳቦና ነጻነት ነው፡፡
ይልቁናም ታዲያን ሀገር ቤታዊ መርዶ ልንገራችሁ፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ መላዋ ኢትዮጵያ በአሁኗ ቅጽበት በድኝ እየተቃጠለች ናት፡፡ ይህ የድኝ እሳት በተለይ ከግንቦት 97 ወዲህ እያዋዛ ማንገቡገቡን ይዞ የነበረው ወያኔ ወለዱ የኑሮ ውድነት ነው፡፡ የኑሮ ውድነት ሲባል እንዲሁ የኑሮ ውድነት እንዳይመስላችሁ፤ አሜሪካ እንዳለው፤ ቦትስዋና እንዳለው፤ ሃይቲ እንዳለው፤ ሞስኮብ እንዳለው፤ኢራን እንዳለው፤ እስራኤል እንዳለው፤ … በጭራሽ እንደዚያ እንዳታስቡ፡፡ የኛ የኢትዮጵያውያን የኑሮ ውድነት እንደዚያ አይደለም፡፡ የኛ የሲዖል እቶን ነው፤ የኛ የገሃነም ፍም ነው፤ እኛን የገጠመን የኑሮ ውድነት በየትም ሀገር የሌለ አዲስ ስም ሊወጣለትም የሚገባው ልዩና ስሑል ነበልባላዊ የእሳት ሠይፍ ነው – ሌላ ቃል አጥቼ በተለመደው ‹የኑሮ ውድነት›ነቱ ቃለ ጥምረት እዚህ ላይ የምጠራላችሁ፡፡ ከዚህ ሠይፍ ሊተርፍ የሚችል ማን ነው ተብሎ ድንገት ቢጠየቅ እንዲሁ ባጭሩ እንዲህ ብሎ መመለስ ይቻላል፡፡
1. እህል ውኃ ሳይቀምስ፣ ልብስ ሳይለብስና መጠለያ ሳያስፈልገው በተዓምር ብቻ መኖር የሚችል ዜጋ፡፡
2. ደመወዙ በአራት አኀዝ የሚጠራ ሆኖ አፍ ላይ ከበድ የሚልና የቤተሰቡ ቁጥር አነስተኛ የሆነ፤ እንዲህም ሆኖ መጥፎ ሱስና ገንዘብ አባካኝ ባሕርይ የሌለው፡፡
3. የራሱ ገቢ ኖረውም አልኖረውም ወፈር ያለ ገንዘብ ከውጭ የሚላክለት(Remittance)
4. አከራይቶት ወፍራም ገቢ የሚያስገኝለት ቤት ወይም ሌላ ንብረት ያለው፡፡
5. በሥራው አጋጣሚ ራሱ በሙስና የተዘፈቀ ወይም ሞሳኝንና አስሞሳኝን በማገናኘት ሌሎችን ያስዘፈቀና በእግረ መንገዱ የራሱን ድርሻ የሚወስድ ሆድ አምላኩ ዜጋ፡፡
5. ለዓላማ (ብቻ) ሳይሆን ለጥቅም ሲል ኅሊናውን ለገንዘብ በመሸጥ የወያኔ አባል ሆኖ አቅሉን ስቶ መላ ትኩረቱን ዘረፋ ላይ ያዋለና በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰውን በማሳሰርና በማስፈታትም ጭምር ቢሆን ገንዘብ የሚያጋብስ፡፡
6. በንግድ ዘርፍ ተሠማርቶ ለወያኔ ቅን ታዛዥና አሸርጋጅ በመሆን ሕግ ሳይጠብቅበት ‹የሚነግድ›፡፡
7. በማንኛውም መንገድ በስርቆትና በማጭበርበር ካለድካምና ካለልፋት ሀብትና ንብረት የሚያግበሰብስ፡፡
8. ዋና ወይም የተጋቦት ወያኔ ሆኖ ከሁሉም የሀገሪቱ ሕጎች በላይ በመሆን – ከይስሙላው ሕገ መንግሥትም ጭምር – ያለቀረጥና ያለግብር ከሕግ ውጪ ‹እየነገደ› ወይም ‹እያስነገደ› በአየር ባየር ንግድ ከብሮ የሚያድር፡፡ (እዚህ ላይ ይህ የማፊያ ዓይነት አሠራር እንደየደረጃው በሕገ ወጥ መንገድ ግን ከዋናው ተለይቶ የማይታወቅ ብርን አሣትሞ ልዩ የመንግሥት ዕቃ በማስመሰል በማይፈተሸ ኮንቴይነር አጭቆ ወዳገር በማስገባት የሀገሪቱ ሕጋዊ ገንዘብ ዋጋ እስኪያጣ ድረስ ገበያውን እስከማግሸብ እንደሚደርስ ውስጠ ዐዋቂዎች እንደሚጠቁሙ ልብ ይሏል፡፡) ለነገሩ አንድን ሰው ለመጉዳት ወይም ለመጥቀም በአንድ ምሽት ሕገ መንግሥትን ያህል ነገር ንዶ ተለዋጭ ሕግ የሚያውጅ የሀገር መሪ ባለበት ሀገር ይህ ዓይነቱ ብልሹ አሠራር የማይጠበቅ አይደለም፡፡
እንግዲህ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት የገቢ ርዕሶች ሊካተቱ የሚችሉት የሀገራችን ዜጎች ስንት ሊሆኑ እንደሚችሉ አንባቢያን ራሳችሁ ገምቱና ቀሪውን በአንድ ቅርጫት ውስጥ ክተቱ፡፡ ምናልባት በግርድፍ ግምት እነዚህ በወንጀልም ይሁን አግባብ ባለው ሥራቸው ሆዳቸውን ሞልተው የሚያድሩና ስለሆዳቸው ለነገ የማይጨነቁ ዜጎች ቁጥር 20 ሚሊዮን ይደርሳል ብንል ቀሪውና ወደ 60 ሚሊዮን የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖረው ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆኖ ነው፡፡ የፈጣሪ ኪነ ጥበባዊ ረድኤት ባይታከልበት ኖሮ ሀገራችን በሚገርም ሁኔታ የለየላት የአሁኗ ሶማሊያ በሆነች ነበር፡፡ ግና ሳይደግስ አይጣላምና ያለው ለሌለው እየተራዳ የተገኘውን አብሮ በመቃመስ እስካሁን ቢያንስ በከተሞች የጎላ የርሀብ ዕልቂት አልተከሰተም፡፡ ሰው ሠራሹ የኑሮ ውድነት በዚህ ከቀጠለ ግን ወዮልን! ብዙዎቻችን ማለቃችን አይቀርም፡፡ እዚያ ማዶ ግንቦት 7፣ ኦነግና ኦብነግ ስትባባሉ በመሃል ቤት ኢትዮጵያውያን በኑሮ ውድነትና በእህል ምርት እጥረት ልናልቅላችሁ ነው፤ በአንዴ ማለቅስ ባልከፋ፡፡ መጥፎነቱ ርሀብና ኤድስ በቶሎ አይወስዱም፡፡ ክፉ የሰው ልጆች ባላጋራዎች ናቸው – ከወያኔ የማይተናነሱ መሠሪ ጠላቶች፡፡ ምነው ፈጣሪ እነዚህን ሠለስቱ አዋልደ ብዔልዘቡል ከሀገራችን ቢነቅልልን ጃል!
ጉድ በሉ እንግዲህ፡፡ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 10/2003 ነው፤ ግዴላችሁም ዘመኑ ዓመተ ፍዳም ቢሆን ዓመተ ምሕረት ልበለው – እናም የዘመን አቆጣጠሩን ላሻሽለውና ዛሬ 10/11/03ዓ.ም ነው፡፡ ባለቤቴ ሸዋርካብሽ ሰሞኑን በአልጫ ልትገድለኝ ይዛ ነበር – በርበሬ አልቋት፡፡ አሁን ቤት ስገባ ሁለት ኪሎ ዛላ በርበሬ ከነቅመሙ ገዝታ እያሰናዳች ደረስኩ፡፡ እናንተ ጋር ተገናኙ ሲለኝ ‹ኪሎውን በርበሬ በስንት ገዛሽው?› ብዬ መጠየቅ፡፡ ቀጠለች፤‹ እስኪ ተወኝ ነጹ – ራስህን ያምብኛል፤ ይቅርብህ፡፡› እንድትነግረኝ ችክ አልኩ፤ ‹ ላንተው ብዬ ነው፤ አንተም መታመም ከፈለግህ ምን ገደደኝ! አንዱን ኪሎ ዛላ በርበሬ 65 ብር፤ ለሁለቱ ኪሎ 130 ብር፤ ሁለቱነን ኪሎ ለማዘጋጀት የ60 ብር ቅመም፤ ለማስፈጨት ደግሞ አሁን ካልጨመሩ ለኪሎው አንድ ብር ነው ወንድማለም› ብላ በምሽቱ አረዳችኝ፡፡ የቀባጭ ምሴን አገኘሁና በብስጭት አንጎል እንደሆንኩ ወደናንተ መጣሁ እላችኋለሁ፡፡
የነገረችኝ ብዙ ነገር ነው፡፡ ራቴን የበላሁት ድፍን ምሥር ኪሎው 23 ብር ክኩ ቢሆን 30 ብር፣ አተር ክክ 28 ብር፣ በቆሎም ባቅሙ ጦፎ ኪሎው 7.50፣ ስንዴ 10.50፣ ጤፍ አንዱ ኪሎ 11.50፣ ሙዝ 10.00፣ አንድ ቢ 29 ሣሙና 16 ብር፣ ግማሽ ኪሎ ፓስታ 12.00፣ ግማሽ ሊትር ማማ ወተት 7.50፣ አይ ይቅርባችሁ፤ ብቻ ምን አለፋችሁ ባጭሩ ነገሩ ሁሉ ኳስ አበደች ዓይነት ሆኖላችኋል፡፡ የሚገርመኝ ሰው ሁሉ በጠቅልሎ አለማበዱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የዕብድና የሰካራም ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡ አንድ ሽሮ ፈሰስ 50 ብር የሚበላበት ቤት አለ አሉ፤ አንድ ኪሎ ጥብስም ይሁን ግንትር ሥጋ 120 ብር የሚበላበት ቤት ሞልቷል አሉ፤ ማበድ ታዲያ ይሄኔ ነው እንጂ ይህ ዘመን ካመለጠንማ መቼም ላናብድ ነው ማለት ነው – እንድናብድለት የሚቋምጥ አካል ካለ፤ እንዴ አለ እንጂ – ምድረ የወያኔ መንጋ ይህን አይደል አሰፍስፎ የሚጠብቅ? እንዲያ ባይሆንማና ፍቅርና መተሳሰብ ቢኖርማ ኖሮ ሀገሪቱ እንኳንስ ለ80 ሚሊዮን ከዚያ በላይ ለሚሆን ሕዝብስ አሳምራ ትበቃ አልነበር፡፡ የዐመል ነገር ግን በእጅጉ ይገርማል፡፡ በነሱ ጉሮሮ ማርና ወተት እየዘነበ፣ ጮማና ውስኪ እየተንዶለዶለ በብዘሀኃኑ ጉሮሮ ባልጩት እዬተሰነቀረ እስከ መቼ እንደምንዘልቅ ዕድሜ ሰጥቶን ማየት ነው፡፡ ለማንኛውም ማን መኖር ይቀጥላል ፤ ማንስ ተሸንፎ ሩጫውን ሳይጨርስ ባጭር ይቀጫል … ብዙም ሳንቆይ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ኑሮው በብርሃን ፍጥነት እንደመንኮራኩር ሽቅብ እየተወነጨፈ መሄዱ ስለማይቀር ተወደደም ተጠላ በጣም በቅርብ ጊዜ ውስጥ አንዳች ነገር መፈንዳቱ አይቀርም፡፡ አብዛኛው ሕዝብ የራሱን ኑሮ ሳይወድ በግድ እንዲተው ተደርጎ የኗሪ አኗኗሪ ከሆነ ብዙ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡
የኑሮ ውድነቱ ሕዝብን እንዲህ እያንገበገበ ሳለ ታዲያ የደላቸው በሌላ ነገር ተጠምደዋል፡፡ እናቱ ወንዝ የወረደችበትና የሞተችበት እኩል ያለቅሳሉ እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ይልቁንስ ጨርሰን በርሀብ ሳናልቅ ተባብራችሁ የምትደርሱልን ከሆነ ድረሱልን፡፡ አለበለዚያ ወርቃማ ዘመናችሁን በከንቱ እዬተነታረካችሁ አሳልፋችሁ ከሞትንና ግባተ መሬታችን ከተፈጸመ በኋላ በመቃብራችን ላይ ቆማችሁ ልታዝኑልን ብትሞክሩ አፅማችን እንዳይታዘባችሁ፡፡ ‹የነብር ዐይን ወደ ፍየል፣ የፍየል ዐይን ወደ ቅጠል› እንዲሉ አበው በአካልም በስሜትም ሳንገናኝ የአንዲት እናት ልጆች ባለመግባባት ሜዳ ላይ ያለእረኛ እንደተበተንን ብንለያይ ፀፀቱ ለሁላችንም ነውና በርግጥ ለኛ የሚያዝን ቢኖር አሁኑኑ ወደተግባራዊ እርምጃ ገብቶ ከኢኮኖሚያዊ ድህነትና ከፖለቲካዊ ጭቆና የምንወጣበትን መንገድ በጋራና ጉዳያችን ይመለከተኛል ከሚል ከሁሉም ወገን ጋር በመነጋገር መፍትሔ ያፈላልግልን፡፡ ሀገር ሳይኖርና ሕዝብ በርሀብና በኑሮ ውድነት እዬተቆላ የሕዝብ ወገን ነን ከሚሉ የአብራካችን ክፋዮች መስማት የምንፈልገው በአንተ ትብስ በአንቺ ትብሽ ላይ የተመሠረተ የወገን ደራሽነትን እንጂ የእርስ በርስ ባላንጣነትን አይደለም፡፡ እናም ሁሉም ወደየኅሊናው ተመልሶ ዛሬንና ነገን በማገናዘብ አመለካከቱን ቢያስተካክል ብዙም ሳይረፍድ ሁላችንንም ተጠቃሚ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ አጉል እልህ በጣም ጎጂና ለጥቃት የሚዳርግ መሆኑን መረዳት ከብልሆች የሚጠበቅ ነው፡፡ መቻቻልን እውን ለማድረግ ደግሞ መደማመጥ ይገባል፡፡ ከቂም በቀልና ከበቀል ንጹሕ የሆነ ስብዕናን መላበስ ተደማምጦ ለመግባባት ያስችላል፡፡ ሕዝብ በሞት የእንግዶች ጓዳ ውስጥ አሣሩን እየበላ በጣር ላይ ባለበት ሁኔታ ከዚህ አስደንጋጭ ትዕይንት ውጪ ያለን የሕዝብ አለኝታዎች ነን የምንል ወገኖች ለመጣላትና ለመካሰስ ጊዜ የለንም፡፡ አንዳንዴ – ሲቻለን- ትዝብትን መፍራትም አስተዋይነት ነው፡፡ የመግባባት ወጡ መደማመጡ እንበልና ለዛሬ እንለያይ ይሆን? …