አናብስት
ቀነኒሳን አንበሳ አሉት፡፡ ኃይሌንም አንበሳ አሉት፡፡ እንደምን ነው ቢሉ፡፡ አንድም አንበሳ ሲተኛ የሞተ፤ የደከመ፣ የታመመ ይመስላል፡፡ እንስሳት እየመጡ ይጎበኙታል፡፡ ያዩታል፤ አንዳንዶቹም ይራመዱታል፡፡ ሌሎቹም አንበሳው ደክሟል ብለው የአራዊት ንጉሥ እኛ ነን ይላሉ፡፡ እንደ ዝንብ ያሉትም ይወርሩታል ‹‹አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጨዋቻ ይሆናል›› እንዲሉ፡፡ እርሱ ግን የሚያደርገውን ያውቃልና ዝም ይላቸዋል፡፡
ታሪክ እንደ አንድ አንበሳና አይጥ፡፡ ታሪኩስ እንደምን ነው ቢሉ እንዲህ ነው፡፡ በአንድ ጫካ የሚኖር አንበሳ ደከመውና አፉን ከፍቶ ተኛ፡፡ እንደተኛም አንዲት አይጥ መጣች፤ መጥታም አልቀረች ትዞረው ጀመር፡፡ ወደ ወገኖቿም ሄዳ አንበሳ ደክሞ ተኝቷል ብላ በሰፊው አወራች፡፡ ተመልሳም መጣችና ተጠጋችው፡፡ እርሱም ዝም አላት፡፡ እርሷም ጠጋ ብላ ጅራቷን በአፍንጫው ከተተችበት፡፡ እንዳያነጥስ ችሎ ዝም አላት፡፡ አይጧም ጠጋ ብላ አፉን ተመለከተችው፡፡ ምቹ ዋሻ መስሎም ታያት፡፡ አሁንም ተጠጋች፡፡ በመጨረሻም ያንን የተከፈተ ዋሻ ልትጎበኝ ወደ አፉ ውስጥ ዘው አለች፡፡ ያን ጊዜም አንበሳ አፉን ግጥም አደረገው፡፡ ሲጥ ብትል ሚጥ መውጫ አልተገኘም፡፡
ቀነኒሳም እንዲሁ ነው፡፡ እርሱ ከውድድር ሲርቅ ደከመ፣ ሰለቸ፣ መከነ፣ ተወ፤ ተብሎ ነበር፡፡ ሌሎችም እኛ የትራክ ላይ ንጉሦች ነን፡፡ የጎዳና ላይ ነገሥታት ነን ብለውም ነበር፡፡ እንደ አይጧም ብዙ ወሬ አውርተው ነበር፡፡ አፈፍ ብሎ ሲነሣ ግን እነዚያን ሁሉ ድል ያደርጋቸዋልና ቀነኒሳን አንበሳ ብለውታል፡፡
አንድም አንዱ አንበሳ ሲያድን ሌላው አንበሳ በሦስት ነገር ይረዳዋል፡፡ አንድም አካባቢውን በመጠበቅ፣ አንድም ታዳኙን በማድከም፣ አንድም አዳኙን በማጀብ፡፡ ኃይሌም እንዲሁ ነው፡፡ ቀነኒሳን በለንደኑ ሩጫ በሦስት ነገር ረድቶታል፡፡ አንድም የሩጫውን ሂደትና ድል በመጠበቅ፣ አንድም ሞ ፋራህን በማድከም፣ አንድም ቀነኒሳን በማጀብ፡፡ አንበሳ ሲያጠቃ በቡድን ነው፡፡ ኃይሌና ቀነኒሳም በቡድን አጥቅተዋልና አንበሶች ተብለዋል፡፡ ኃይሌ ከቀናት በፊት ስለ ሞ ፋራህ የሰጠው አስተያየትና ለቀነኒሳ የሰጠው ምክር ለለንደኑ የቀነኒሳ ድል ረድቶታልና ኃይሌን አንበሳ ብለውታል፡፡
አንድም ኃይሌን በስፖርተኛ የዕርግን ዘመኑ ባስመዘገበው ውጤት አንበሳ ብለውታል፡፡ እንደምን ነው ቢሉ፡፡ አንበሳ ቢያረጅም እንኳን ፈጽሞ ካልወደቀ በቀር እንስሳት አይተው ይፈሩታል፡፡ እርሱም ተንቀሳቅሶ በዐቅሙ ያድናቸዋል፡፡ ኃይሌም ምንም በዕድሜ ቢገፋ ሯጮች አይተው ይፈሩታል፡፡ ሮጦም ድልን በዐቅሙ ያድናልና አንበሳ ብለውታል፡፡
ነገር እንደ ተረትና ምሳሌ
አንበሳ ተኝቶ ፍየል ዘለለችው
ንቆ ቢያሳልፋት ሞኝ አደረገችው
አንድም አንበሳ በሦስት ነገር ተፈርቶ ይኖራል፡፡ አንድ በድምጹ፣ ሁለት በግርማ ሞገሱ፣ ሦስት በክርኑ፡፡ በድምጹ እንደምን ነው ቢሉ አንበሳ ገና ከሩቁ ሆኖ ሲጮኽ ሲሰሙት እንስሳቱ ሁሉ ይርዳሉ፣ ይንቀጠቀጣሉ፡፡ በግርማ ሞገሱስ እንዴት ነው ብለው ቢጠይቁ አንበሳ ባይጮኽም ባይባላም በጫካው ውስጥ ጎምለል ጎምለል ሲል እንስሳቱ ፈርተው ይሸበራሉ፡፡ በክርኑስ እንደምን ነው ያሉ እንደሆን በእግሩ ርግጥ አድርጎ በክርኑ አድቅቆ ይመገባልና ነው፡፡ ቀነኒሳም አንበሳ ነው ሲሉ ምንም ባያሸንፍ እንኳን እዚህ ውድድር ላይ ሊወዳደር ነው፣ ሊሮጥ ነው ሲባል አብረውት የሚሮጡ ሁሉ ይፈራሉ ይርዳሉ፡፡ አንድም ምንም ባያሸንፍ እንኳን እርሱ በውድድሩ ውስጥ ገብቶ ሲሮጥ ሲያዩት ድል ይነሣን ይሆናል ብለው ብዙዎቹ ሯጮች ይሸበራሉ፡፡ አንድም አምርሮ የሮጠ እንደሆነ ደግሞ ኃያላኑን ከኋላው አስከትሎ ድል በኃያል ክንዱ ድል ያደርጋቸዋልና ነው፡፡
አንድም አንበሳ ከአፍሪካ ሄዶ በእንስሳት ማቆያ ውስጥ ካልሆነ በቀር በፈረንጅ አገር አይገኝም፡፡ እንደ ቀነኒሳ ያለ ሯጭም ከአፍሪካ ሄዶ ለሰው ሀገር ይሮጥ ይሆናል እንጂ በፈረንጅ አገር አይገኝምና ቀነኒሳን አንበሳ ብለውታል፡፡ አንድም አንበሳ የሀገራችን የጀግንነት፣ የአልበገር ባይነትና የድል አድራጊነት ምልክቷ ነው፡፡ ኃይሌና ቀነኒሳም በረሃብ፣ በችግርና በጦርነት ስሟ በክፉ የሚነሣውን ሀገራችንን በጀግንነት፣ በድል አድራጊነትና በአልበገር ባይነት እንድትታወቅ አድርገዋታልና አንበሳ ተብለዋል፡፡
ያሉንን አናብስት እያወደስን ሌሎች አናብስትን እናፈራለን፡፡