ፎነት- በነጋዴዎችና በመንግስት የሌባና ፖሊስ ጨዋታዉ ቀጥሏል
የልጅነት ዕድሜን ለዛ ከሚያጣፍጥ መካከል የድብብቆሽ “ሌባና ፖሊስ ጨዋታ” አንዱነው፡፡ ይህ ጨዋታ አሁን በልጆች መካከል ብዙ እየተስተዋለ አይደለም፡፡ ይልቅ ቤተሰብን በተለይም ልጆችን በሚያስተዳድሩ ነጋዴዎችና ሀገርን በሚያስተዳድረው መንግስት መካከል ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ህፃናት በጨዋታው መካከል ሲገናኙ በመሀከላቸው መተማመን አለ፡፡ ምክንያቱም ጨዋታቸው ከልብና ከፍቅር የመነጨ ስለሆነ በነጋዴዎችና በመንግስት መካከል ያለው ግን ከዚህ የተለየ ይመስላል፡፡
በተለይም ከኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ ባለፉት ወራት በተለይም ከታህሣሥ 2003 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት “ምክንያት ናቸው” በማለት ነጋዴዎች ላይ ጣቱን ቀስሯል፡፡ በዚህም በ8 ወራት ውስጥ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ እልባት ባለመገኘቱም አዋጅ አውጥቶ እስከ ማፅደቅ ድረስ ተደርሶ አሁን ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም ነጋዴዎች በአዲሱ አዋጅ መሠረት በአዲስ መልክ ተመዝግበው ፍቃድ ማውጣት እንዳለባቸው ተወስኖ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን መንግስት በነጋዴዎች እንዳልተደሰተ ሁሉ፤ ነጋዴዎችም በመንግስት ደስተኛ እንዳልሆኑ በምሬት ይገልፃሉ፡፡
በተለይም የግብር አወሳሰኑ እና አሰባሰቡ ዙሪያ ላይ ቅሬታ እንዳላቸውና ለዚህም ሰሚ እንዳላገኙ በማውሳት፡፡ በተለይም በመርካቶ፣ በቄራ፣ በሳሪስ፣ በቦሌና በ22 ማዞሪያ አካባቢ የሚገኙ ነጋዴዎች እንደሚገልፁት ከሆነ፣ በግብር መክፈያ ቀን ክፍያ ለመፈፀም ሲሄዱ፣ ከቀድሞው ከሃያ በመቶ እጥፍ እና ከዚያ በላይ እንደተጠየቁ፤ ምክንያቱን ሲጠይቁ አሳማኝ የሆነ መልስ ከመስጠት ይልቅ “ወደህ ትከፍላለህ፣ ካልከፈልክ በህግ ተቀጥተህ ትከፍላለህ “አሊያም ንግዱን ማቆም ትችላለህ” በማለት አግባብነት የሌለው መልስ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ነጋዴዎቹ እኛ የሀገራችንን እድገት እንደማንፈልግና እንደማያገባን አስመስሎ ከማስገደድ ይልቅ በመግባባት ችግሮች ቢፈቱና የግብር ጉዳይ በድጋሚ ቢታይ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይም መንግስት በበኩሉ “ይህን እርምጃ እየወሰድኩ ያለሁት ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ነው” ቢልም አንዳንድ አስተያየት ሰጪ ነጋዴዎች በበኩላቸው የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ያሉት ከ30 የማይበልጡ የሀገሪቱ አከፋፋዮች ሲሆኑ እነኚህንም መንግስት ራሱ የሚያውቃቸው ከመሆንም በላይ እስካሁን ምንም ዓይነት እርምጃ እነርሱ ላይ ሳይወስድ እኛ ላይ ማተኮሩ “እኛን የእንጀራ ልጅ እያስመሰለን ነው” በማለት ሲያማርሩ፣ “ከዋና አከፋፋዮች ጀርባ ማን እንዳለ እና እንደሚነግድም መንግስት በከፍተኛ ምስጢር ማጥናት አሊያም ማስጠናት ከዚያም በይፋ ለህዝብ ግልፅ በሆነ መልኩ እርምጃ መውሰድ አለበት። ምክንያቱም መንግስት ቤቱን ሳያፀዳ ሌላው ላይ ጣት መቀሰሩ አግባብ አይደለም። ይህም መንግስትና ነጋዴው እስከመቼ ድረስ ሌባና ፖሊስ እንደሚጫወቱ ጥያቄ ምልክት ዉስጥ የሚያስገባን ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡ “ከዚህ ጨዋታ ይልቅ የእኛንም ችግር ሊያይና ጥያቄያችንን የሚያደምጥልን አካል የሚገኝ ከሆነ እንፈልጋለን። አለበለዚያ የባሰ ችግር ሊመጣ ይችላል” ሲሉም አስተያየታቸውን በተለይም ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡