የታሰሩ ጋዜጠኞችና የፓርቲ መሪዎች በድጋሚ ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸዉ
(ፎኖት) — ሽብርተኝነት” ተጠርጥረው በፌደራል ወንጀል ምርመራ ታስረው የሚገኙት የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ርዮት ዓለሙ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ/ኢብአፓ/ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚሐብሄርና የኢብአፓ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ደጀኔ ተፈራ ፓሊስ የምርመራ ጊዜን አለጣናከኩም በማለት በመጠየቁ በድጋሚ የ28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተስጥቶታል፡፡
ባለፈው ሐምሌ 11 ቀን 2003ዓ.ም የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት ውብሼት ታዬ፣ ዘሪሁን ገ/እግዚሐብሄር ደጀኔ ተፈራ በቀረቡበት ወቅት ችሎቱን ለመከታተል በርካታ ጋዜጠኞች የእስረኛ ቤተሰቦችና ወዳጆቻቸው በሥፍራው ተገኝተው ነበር፡፡
ሆኖም ግን እስረኞቹን ማነጋገርም ሆነ ችሎት ለመግባት አልተፈቀደም፡፡ እስረኞቹ ከችሎት በሚወጡበት ወቅት ጋዜጠኛ ውብሼት ታዬ ለጓደኞቹና ለቤተሰቦቹ “አይዞችሁ ልበወለድ ነው” በማለት ሲናገር ተደምጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአቶ ዘሪሁን ገ/እግዚሐብሄር ልጅ የሆነችው ሊዲያ ዘሪሁን ለዝግጅት ክፍላችን እንዳላቸው አባቴ እስር ቤት ለመጠየቅ በሄድንበት ጊዜ “አይዟችሁ ፍ/ቤቱ ስቀርብ በነጻ እንደሚለቀኝ እርግጠኛ ነኝ”በማለት ለቤተሰብ ሲናገር በስፍራው የነበረ መርማሪ ፖሊስ “ስለ ቤተሰብና ማህበራዊ ጉዳይ እንጂ ይህንን መናገር አትችልም” ብሎ ከልክሎታል” በማለት ገልጻለች፡፡
ሐምሌ 13 ቀን 2003ዓ.ም በ8 ሰዓት ፍ/ቤት ትቀርባለች ተብላ የነበረችው ርዮት ዓለሙ በዚሁ ዕለት ከሰዓት በፊት ጥዋት ችሎት ቀርባ ተመሳሳይ ቀጠሮ እንደተሰጣት መረዳት ተችሏል፡፡ ውብሼት ታዬ በሐዳር ጋዜጣ፣ በነጋድራስ ጋዜጣ፣ በመሰናዘሪያ ጋዜጣ፣ በጐግል ጋዜጣና በአውራምባ ታይምስ ጋዜጦች ላይ የሠራ ጋዜጠኛ ሲሆን ርዮት ዓለሙ በኤፍኤም ሬዲዮ 96.3፣ በአዲስ ፕሬስ ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኝነት ከመስራቷም በላይ በቼንጅ መጽሔት እና በፍትህ ጋዜጣ ላይ በአመዳኝነት የሠራች ጋዜጠኛ ናት፡፡
የፍኖት የመጀምሪያዉ እትም ጋዜጣን በሙሉ በፒ.ዲ.ዔፍ ለማንበበ ከዚህ ይጫኑ