በገላን ጉራ ፈለገ ግዮን ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከሰማይ ስለወረደው መስቀል

KeSemay Yeworedew Meskel

ከሰማይ ወረደ ተብሎ በጳጳሳት የተጎበኘው መስቀል ለሕዝብ ይታያል

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 13 ቁጥር 713፤ ቅዳሜ መስከረም ፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)

ዓለማየሁ አንበሴ

Addis Admas Logoበአቃቂ ቃሊቲ በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ፣ ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በቀስተ ደመና፣ በመብረቅ እና በነጎድጓድ ታጅቦ ከሰማይ እንደወረደ የተነገረው መስቀል፣ በጳጳሳት የተጎበኘ ሲኾን፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለሕዝብ እይታ እንደሚቀርብ ተገለጸ፡፡

መስቀሉን ከወረደበት ለማንሣት የሞከረ ወጣት ተስፈንጥሮ ከወደቀበት ለአራት ቀን ራሱን እንደሳተ የሚናገሩ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ፣ ከምሽቱ 9፡00 ከፍንዳታ ጋራ አካባቢው በብርሃን ተሞልቶ ስናይ የእሳት ቃጠሎ መስሎን ነበር ብለዋል፡፡ እያንጸባረቀ በኃይለኛ ግለት ያቃጥል ነበር የተባለው መስቀሉ፣ በጳጳሳት እና በማኅበረ ቅዱሳን መሪዎች የተጎበኘ ሲኾን የኢየሱስን ስቅለት የሚያሳይ ወርቃማ ቅርጽ ያለው ነው፡፡

ወደ አቃቂ ከተማ ከሚያስገባው ዋናው የአስፋልት መንገድ በስተግራ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ገላን ጉራ በሚባለው ስፍራ የዛሬ አምስት ዓመት የተቋቋመው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም [የቅድስት] ክርስቶስ ሠምራ ክብረ በዓል እየተከናወነ ሳለ ከሌሊቱ 9፡00 የኾነው ክሥተት ነው የዚህ ሁሉ መነሻ፡፡ ከባድ የፍንዳታ ድምፅ የሰሙና የቀስተ ደመና ቀለማትን የተላበሰ ብርሃን የተመለከቱ ነገሩን ከዝናባማው የአየሩ ኹኔታ ጋራ በማያያዝ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር የሚሉት የደብሩ መጋቢ፣ ‹‹በነጎድጓድና በኢትዮጵያ ባንዴራ የታጀበ መስቀል ከሰማይ ሲወርድ አይቻለኹ፤›› ብለዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ መስቀሉን ለማየት ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚጎርፉ ምእመናን በርክተዋል፡፡

ባለፈው ኀሙስ ከአቃቂ ከተማ በማለዳ ተነሥተን ከሁለት ሰዓታት የእግር ጉዞ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኑ ስንደርስ፣ ጥቂት ምእመናን በተገኙበት የዕለቱ ቅዳሴ እየተከናወነ ነበር፡፡ ከቆይታ በኋላ ቅጽሩ የመስቀሉን ታሪክ ሰምተው ከአቅጣጫው በሚመጡ ምእመናን ተሞላ፡፡ ‹‹መስቀሉ ከሰማይ ሲወርድ አይቻለኹ›› የሚሉት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፣ ስለ መስቀሉ አወራረድ ገለጻ ማድረግ የጀመሩት ከጸሎተ ቅዳሴው ፍጻሜ በኋላ ነው፡፡

በቅጽሩ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ መስቀሉ ወርዶ ያረፈበትን ስፍራ እያመለከቱ ይናገራሉ፡- ቦታው በቆርቆሮ ታጥሮ ድንኳን ተተክሎበታል፡፡ መስቀሉ ዐርፎበታል ከተባለው ስፍራ ‹‹አፈር›› እየተቆነጠረ የሚቀርብላቸው ምእመናን፣ ‹‹አፈሩን›› እየተመለከቱ የመጋቤ ሐዲስን ገለጻ ያዳምጣሉ፡፡

ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በዓል ነሐሴ ፳፫ ቀን የጸሎት ሥርዐት ከምሽቱ 5፡00 አካባቢ እንደተጀመረ የሚያስታውሱት መጋቤ ሐዲስ፣ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ አካባቢው በቀስተ ደመና ብርሃን ደምቆ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን ለዚህ ልዩ ክሥተት ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር፡፡ ከዝናባማው የአየር ጠባይ ጋራ አዛምደው አቅለለው ነው የተመለከቱት፤›› ብለዋል መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፡፡ የቀስተ ደመናው ብርሃን አንዴ ሲደምቅ፣ አንዴ ሲደበዝዝ መቆየቱን መጋቤ ሐዲስ ጠቅሰው፣ ‹‹ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ነፋስ ለማግኘት በካህናት መውጫ በር በኩል ስወጣ ግን ደብዛዛ የነበረው ብርሃን የበለጠ ደምቆ እንደ ቀን ብርሃን ወገግ ብሎ ታየኝ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሻቅቤ ስመለከት ሰማዩ በነጭ ደመና ተከቦ ተመለከትኩ፡፡ አፍታም አልቆየ፣ በኢትዮጵያ ባንዴራ ቀለማት የተጠቀለለ አንዳች ነገር በዝግታ ከሰማይ እየተገለባበጠ ሲወርድ አየኹ፡፡››

ከቤተ ክርስቲያኑ ቤተ ልሔም አጠገብ ያለውን የአገር አቋራጭ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መሥመር ተሸካሚ ማማ እያመለከቱ፣ ‹‹ከሰማይ እየተጠቀለለ የሚወርደው ነገር ከማማው አካባቢ ሲደርስ ነጎድጎዳማ ድምፅ ማሰማት ጀመረ›› የሚሉት መጋቤ ሐዲስ፣ ‹‹መሬት ላይ ሲያርፍ በከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ አካባቢው የእሳት ንዳድ የመሰለ ብርሃን ሞላው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ቤተ ልሔሙ ተቃጠለ እያልኹ ብጮኽም ድምፄን የሰማ ሰው አልነበረም፤ ለደቂቃዎች ያህል ለሰዎች እንዳይሰማ ኾኖ ታፍኖ ነበር፡፡ ድምፄ መሰማት ሲችል ግን፣ ካህናቱ ጩኸቱን ሰምተው ተደናግጠው ወደ ውጭ ወጡ፤›› ብለዋል፡፡ አንዳች አደጋ ደርሶ እሳት ተቀጣጥሎ ሊኾን ይችላል በሚል ድንጋጤ ሁሉም እሳቱን ለማጥፋት እንደተሯሯጠ ጠቅሰው፣ ነገር ግን ከአካባቢው ብርሃን በቀር የእሳት ቃጠሎ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል፡፡

‹‹አንድ የቤተ ክርስቲያናችን ወጣት አገልጋይ ወደ ደመቀው ብርሃን ተጠግቶ ለማየት ሞከረ፤ አንዳች ነገር ወደላይ አስፈንጥሮ መሬት ላይ ጣለው፤ ምእመናን ተደናገጡ፤ የኤሌክትሪክ መሥመር ተበጥሶ ኮንታክት ፈጥሮ ይኾናል የሚል ጥርጣሬ ነበር ያደረብን›› ሲሉም ተርከዋል፡፡ ‹‹የወደቀው ወጣት ምላሱ ተጎልጉሎ በወደቀበት ራሱን ስቶ ተዘርግቶ ነበር›› የሚሉት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፣ ከወደቀበት በጥንቃቄ አንሥተን ጠበልና ቅብዐ ቅዱስ ብናደርግበትም አልተሻለውም ብለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ካህናቱ እንደምንም ወደ ብርሃኑ ተጠግተው የተመለከቱት፡፡ እናም በብርሃን የታጀበ መስቀል መሬት ላይ ዐርፎ አዩ ብለዋል፡፡

ካህናቱና ምእመናኑ በአግራሞት ሲመለከቱ ቢቆዩም የእሳቱ ወላፈን ይፋጃል ያሉት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፣ በርቀት መጎናጸፊያ ተወርውሮበት እንዲለብስ እንደተደረገ ይገልጻሉ፡፡ የተቋረጠው ሥርዐተ ማሕሌት ከ10፡00 በኋላ የቀጠለ ሲኾን በካህናቱ ትእዛዝ መስቀሉ ወርዶ ካረፈበት ሥፍራ ላይ ማለዳ 12፡30 ድንኳን ተተከለ፤ ብፁዓን አባቶችም በስልክ እንዲያውቁ ተደረገ ብለዋል፡፡ ይኹን እንጂ በማግስቱ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ክብረ በዓል ስለነበር ብዙዎቹ ጳጳሳት ወደ ደብረ ሊባኖስ፣ ቀሪዎቹም ወደ የአድባራቱ ሄደው ስለነበር በዕለቱ መምጣት አልቻሉም ብለዋል፡፡

‹‹ከበላይ አካላት በተነገረን መሠረት ለወረዳው ፖሊስ ካሳወቅን በኋላ የፖሊስ ኃይል አካባቢውን ተቆጣጠረ፤›› የሚሉት መጋቤ ሐዲስ ቅዳሜ ዕለት የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መጥተው መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚያው ዕለት ከሰዓት በኋላ ለመምጣት ቀጠሮ የሰጡ ጳጳሳት ግን ከአንድ ሰዓት በላይ በረዶ የቀላቀለ ዝናም በመጣሉና ጭቃው የማያስገባ በመኾኑ ከመንገድ ተመልሰዋል፡፡ በማግሥቱ እሑድም አክራሪነትን ለመቃወም ሰልፍ የሚካሄድበት ቀን በመኾኑ መምጣት አልቻሉም፡፡

ሰኞ ዕለት፣ ነሐሴ ፳፯ ቀን በርካታ ጳጳሳት በቦታው ተገኝተው፣ መስቀሉ ዐርፎ ከቆየበት ስፍራ ተነሥቶና በበርካታ ምእመናን ታጅቦ ወደ መቅደስ እንዲገባ መደረጉን መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ ተናግረዋል፡፡ በደረሰበት አደጋ ራሱን ስቶ የቆየው አገልጋይ፣ በአራተኛው ቀን መንቃቱንና በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ ወጣቱ ሲጠየቅም፡- ሊያነሣው እጁን ሲሰነዝር ከኋላው አንዳች ሕፃን ልጅ የመሰለ ነገር ጎትቶ መሬት ላይ እንደጣለውና ከዚያ በኋላ የኾነውን እንደማያውቅ መግለጹን መጋቤ ሐዲስ ተናግረዋል፡፡

መስቀሉ ከወደቀበት መሬት ተነሥቶ ሲገባ ከፍተኛ ግለት እንደነበረውና [ያከበሩት] አባት ‹‹እያቃጠለኝ ነው›› እያሉ ሲናገሩ እንደነበር ተገልጧል፡፡ መስቀሉ የሰው ሥራ እንዳይኾን የተጠራጠሩ መኖራቸውን የጠቀሱት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፣ ‹‹መስቀሉ ከምን እንደመጣ የሚያውቀው ፈጣሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ እንግዳው የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ፣ መስቀሉ ከሰማይ ሲወርድ እንዳልተመለከቱ ጠቅሰው፣ ‹‹በጳጳሳቱ ካረፈበት ተነሥቶ ወደ መቅደስ ሲገባ ወርቃማ ብርሃን ነበረው›› ብለዋል፡፡ አንዳንድ የአካባቢው ሰዎችም ሌሊቱን ነጎድጓዳማ ድምፅ መስማታቸውንና በማግሥቱም ስለ ክሥተቱ ከቤተ ክርስቲያኑ ካህናት እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ለአካባቢው ጸጥታ በማሰብ መስቀሉ በየዕለቱ ለምእመናን እንዳይታይ ከቤተ ክህነት ትእዛዝ እንደተላለፈ ጠቅሰው፣ መስከረም ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር መስቀሉን ለእይታ ለማወጣት ቀጠሮ መያዙን መጋቤ ሐዲስ አስታውቀዋል፡፡

*            *           *

 ከሰማይ ወረደ የተባለውን መስቀል ለማየት ብዙ ሕዝብ ወደ ቡልቡላ እየተመመ ነው

(ኢትዮ ቻናል፤ ቁጥር 416፤ መስከረም ፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም)

ዮናስ አማረ

logo-transበአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በወረዳ 10 በተለምዶ ቡልቡላ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው ፈለገ ግዮን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከሰማይ በተኣምር ወረደ የተባለውን መስቀል ለማየት ሕዝቡ በብዛት እየተመመ ነው፡፡ ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በዓል በቤተ ክርስቲያኑ በሚከበርበት ሳይታሰብ አካባቢው በብርሃን መሞላቱን ተከትሎ መስቀሉ ከሰማይ እንደወረደ የዐይን እማኝ ነን ያሉ ሰዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡

ኹኔታውን ለማጣራት ወደ ቦታው አምርተን በነበረበት ወቅት መስቀሉ ወደ ማረፊያው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መግባቱንና በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ማንም ለማየት እንደማይፈቀድለት ቢነገረንም የዐይን እማኝ ነን ያሉ ካህናት ስለ ኹኔታው በዝረዝር ነግረውናል፡- ‹‹ኹኔታው የጀመረው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ነው›› ሲሉ ገለጻቸውን የጀመሩት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ አስረስ፣ በዚያ ምሽት ካህናቱ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ማሕሌት ቆመው እንደነበርና ከቤተ ክርስቲያኑ በስተምሥራቅ ባለው ቤተ ልሔም አካባቢ ከሰማይ ሰፊ ብርሃን መውረዱንና ነጎድጓድም መሰማቱን፣ ይህን ያዩ በደጅ የነበሩ ምእመናንም ቤተ ልሔሙ የተቃጠለ መስሏቸው ተደናግጠው በመጠራራት በአካባቢው መሰባሰባቸውን በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡

‹‹በቀስተ ደመና ብርሃን ተሞልቶ ከሰማይ እየተገለባበጠ ሲወርድና በቤተ ልሔሙ አካባቢ ሲያርፍ በዐይኔ አይቻለኹ›› ሲሉ የተናገሩት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ ክሥተቱ ፍጹም የእግዚአብሔር ተኣምር እንደኾነ የገለጹት፡፡

ሌላው የዐይን ምስክር ነኝ ያሉን የደብሩ አለቃ መጋቤ ሃይማኖት ኃይሌ መዝገቡ ሲናገሩ፣ በክሥተቱ ወቅት ቤተ ልሔሙ ሲቃጠል ቆሜ አላይም ያለ ደብሩን የሚያገለግል አቶ ነጋልኝ የተባለ ምእመን በብርሃን ወደተጥለቀለቀው ቦታ መግባቱንና ድንገትም እንደ ኳስ ተወርውሮ መውደቁን ጠቅሰው ምእመኑ ለአራት ቀናት ራሱን ስቶ መቆየቱን ነግረውናል፡፡ ‹‹መስቀል የሰላም ምልክት ነው›› ያሉት ካህኑ እግዚአብሔር እንዲህ ዐይነት ተኣምር ያውም በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ በዚህ ማውረዱ በጎ ምልክት እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡

ወረደ የተባለው መስቀል በአካባቢው የፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት ያለው ኃያል ብርሃን በረድ ሲል ራሳቸው በእጅ ስልካቸው ፎቶ እንዳነሡትና ከቤተ ክርስቲያን መጎናጸፊያ አምጥተው እንዳለበሱት መጋቤ ሃይማኖት ኃይሌ መዝገቡ ጨምረው ገልጸውልናል፡፡

ብርሃን የወረደበት የቤተ ልሔም አካባቢ በመታጠሩና ከካህናት ውጭ የተከለከለ ነው በመባሉ በቀስተ ደመና ተከቦ ከሰማይ ወረደ የተባለውን መስቀል በዐይናችን ለማየት ባይፈቀድልንም መስቀሉ በወረደ ሰዓት በሞባይል ካሜራ የተነሣ ፎቶ ግራፍ ነው ተብሎ በቤተ ክርስቲያኑ በ10 ብር ሲሸጥ ለመታዘብ ችለናል፡፡ ይህንኑ ፎቶ ግራፍ ሰሞኑን በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ሕዝቡ እየተቀባበለው የሚገኝ ሲኾን በርካቶች ክሥተቱን ፍጹም በማመን አስተያየት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

መስቀሉንና የተፈጠረውን ኹኔታ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና የአካባቢው ፖሊስ ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ እንደጎበኙት ያነጋገርናቸው ካህናት ገልጸውልናል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አስፈሪውን የቡልቡላ ወንዝ ድልድይ ተሻግሮ ጭቃው ሳይበግረው ሲተም አይተናል፡፡