ሶሪያ፣ አሜሪካ፣ አውሮፓና ኢትዮጵያ
እስክንድር ነጋ – (አዲስ አበባ)
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሰሞኑን ተወጥረው ሰነባብተዋል፡፡ የመንግሥታቸው ወጪ ከገቢው መንጥቆ ማምለጡ አዲስ ዜና አይደለም፡፡ ትንሹ ቡሽ እንደ እ.ኤ.አ. በ2ዐዐዐ ዓ.ም ከክሊንተን ስልጣን ሲረከቡ፣ የአሜሪካ መንግሥት በካዝናው ትርፍ ገንዘብ ነበረው፡፡ ገቢው ከወጪው ይበልጥ ነበር፡፡ በ2ዐ1ዐ፣ ዓመታዊ የባጀት ጉድለቱ ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሄዷል፡፡ በየዓመቱ የተጠራቀመው ጉድለትና ብድር ተደማምሮ ዘንድሮ ከ14 ትሪሊዮን ዶላር በላይ አሻቅቧል፡፡ ይሄ ነው ብሔራዊ ዕዳ ማለት፡፡ ሸክሙ አሜሪካን እያንገዳገዳት ነው፡፡