ለውጥ ሲመጣ እኛ ግን …! ሶሎሞን አ.
አንድን ስርዓት አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ሲደግፈው ያ ስርዓት ጠንካራ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። ነገር ግን አንድን ስርዓት ለረጅም ጊዜ የሚያቆየው ይህ ብቻ አይደለም፤ ለምሳሌ ሕዝብ ጠልቶት ነገር ግን ካልተቃወመው ወይም ደግሞ ሕዝብ ተቃውሞት ግን ሕዝቡ ሙሉ ለሙሉ ያልተሳተፈበት ተቃውሞ ከሆነ ያ ስርዓት ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። ስለዚህ አንድ አምባገነን ስርዓት እንደ ሕዝቡ ሁኔታ ሊወድቅም ላይውድቅም ይችላል። እንደእኛ ሁኔታ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ተንሰራፍቶ ያለው ጨቋኝ ስርዓት ገና ብዙ ጊዜ የሚቆይ ይመስለኛል።
ለዚህም ዋና ምክንያቶች እኛው ነን። የሚጠበቅብንን ማድረግ ቸል ብለን ጠንካራ ተቃዋሚ የለም! ሑሉም ተቃዋሚዎች ችግር አለባቸው!… በሚል በተለመደ እውቀት አጠር ምልከታ ተጠምደን ዛሬም ነገም እርሱን እንደጋግማለን። ይህ ምልከታ የሚዘወተረው በተለይ ሃላፊነታችንን ባለማወቅም ይሁን በመዘንጋት በማንወጣ ጥቂት በማንባል ለፖለቲካ ቅርብ ነን ብለን በምናስብ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲሆን ይህ አመለካከታችን ከራሳችን አልፎ በትጋት ለሚሰሩ ለጥቂቶች እንቅፋት ሲሆን ይስተዋላል።
በተለይ እዚህ በውጭው አለም በምንኖር ኢትዮጵያውያን ላይ ይሕ አስተሳሰብ ለአእምሮአችን ቅርብ ነው። እንደ እኔ ለዚህ ምክንያቱ ወደ ፖለቲካው የመጣንበት መንገድ ይመስለኛል። አገር ውስጥ እያለን በሃገሪቱ ውስጥ ምን እየተኪያሄደ እንዳለ ቀርቶ በአጋጣሚ እንኳን በቅርብ የምናገኛቸውን ጋዜጦች አንብበን የማናውቅ፤ እንዲሁ በእለት ተእለት የኑሮ ሂደት ተጠምደን ኖረን ልክ ከአገር ስንወጣ ወደ ፖለቲካው ጐራ እንቀላቀልና ለአባልነት እና ለሒስ እንጣደፋለን። ስለ ተቃዋሚዎች ድክመት በየተገኘንበት ስንለፈልፍ የጥንካሬም ሆነ የድክመት መሰረቶች እኛው እራሳችን መሆናችንን ለማሰብ ዳገት ይሆንብናል።
“ውሾቹም ይጮሃሉ ግመሎቹም ያልፋሉ” ሆኖብን እኛ ስንጮህ ደካማ የምንላቸው ተቃዋሚዎች ይሰራሉ፣ ስለሰሩም ለመለየት አስቸጋሪ እና የተለያዩ መልኮች የነበሩት ወያኔ አሁን ማንነቱ ተጋልጦ ቁልጭ ያለ አምባገነን እንደሆነ አለም አወቀ። የወያኔ አገዛዝ ድኅነትን፣ መሃይምነትን፣ ወንጀልን፣ ቢሮክራሲን፣ ለተፈጥሮ ሓብት እና ለቅርስ ግድ የለሽነትን ፈጥሯል። ይህንን ሁሉ ግን የሚታገሉት ጥቂቶች ናቸው እኛ ደካማ የምንላቸው ተቃዋሚዎች። ገዳይነቱን እና ጨቋኝነቱን አለም እንዲያየው እያደረጉ ያሉት እነዚሁ ጠንካራ አይደሉም የምንላቸው ተቃዋሚዎች ናቸው።
እኛስ ምን እየሰራን ነው? እከሌ ሪፖርት አወጣ፣ ከታሰረ እና ተፈታ፣ ከእከሌ እንዲህ አለ ከማለት የዘለለ ፋይዳ ያለው ነገር አድርገን አናውቅም። ዛሬም የምናወራው ወያኔ በሰጠን አጀንዳ ላይ ነው። ዛሬም የምንከተለው ለለውጥ ታገልን የሚሉትን ነገርግን ያለለውጥ ያረጁትን ሰዎችና ያስረጃቸውን ሓሳባቸውን ነው። ካላወቅን፣ ካልተቀየርን፣ ካልተባበርን የትም አንደርስም።
ከራስ ማንነት ግንዛቤ ማነስ የተነሳ ለመተባበር፣ ለመደጋገፍ፣ አብሮ ለመስራት፣ የሌላን ሃሳብ ለመቀበል እና የመሳሰሉትን ለማድረግ ድፍረት አንሶናል። እኛ አንድ ጠላት እያለን አንድነትን መፍጠር ከብዶናል። የምንታገለውን፣ የምንታገልለትን እያወቅን ወደ ተግባር ለመሸጋገር ተቸግረናል። እውነትን እውቀት ማድረግ ከብዶናል። እውነቱን ካወቅን ወደ ኋላ አንልም ግን ገና እውነቱ ወደውስጣችን አልዘለቀም። እውነቱን ማወቅ ጠንካራ ተቃዋሚ ያደርጋል። የሁላችን የጥንካሬ ምንጭ እውቀት ስለሆነ፣ ስለ ዴሞክራሲ ስለ ነፃነት ስለ ፍትህ ያለን እውቀት። ይህ እውቀት ሲያጥረን አላማ ቢስ እንሆናለን አላማ ቢስ ስንሆን እንደውሾቹ ፋይዳ ቢስ ጩሀት እንጮሃለን። እኛ እናወራለን እነሱ ይሰራሉ፣ እኛ ውሾች እነሱ ግመሎች።
ከወያኔ ጋር የሚደረገው ትግል የእለት አይደለም። የሂደት ትግል ነው። ይህ ትግል ለጊዜውም ቢሆን ወያኔን ከስልጣን ባያባርረውም የለበሰውን ጭምብል አስወልቆታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወያኔ በፍጥነት እየተቀየረ ነው፣ የዚህ ለውጥ ምክንያቶች ጥቂቶች ናቸው። ትግሉ ውስጥ እኛ ብንኖርበት ኖሮ ይህ ለውጥ እንዴት ይፈጥን ነበር? ወደድንም ጠላንም በዚህ ለውጥ ውስጥ ከሌለን እና ወያኔን የምንቃወም ከመሰለን ከንቱ ጩሀት እየጮህን ነው። እንደውሾቹ!!
ለውጥ ሲመጣ እኛ ግን አንለወጥም እንፈራለን በእምነት እና በራዕይ ተሰባስቦ መታገል እንደሚጠቅም እያወቅን ግን እንፈራለን። አዲስ ነገር አንወድም፣ ነገሮች ሲቀየሩ እኛ ባለንበት እንሄዳለን፣ ወጣ ብለን ብናይ ስንት ነገር ተቀይሯል እኛ ግን በለመድናት ጉድጓድ ውስጥ ተመቻችተን ተቀምጠናል። ከዚች ጉርጓድ መውጣት ያስፈራናል። እስቲ ባንፈራ ኖሮ ምን እንሆን ነበር? ምን አይነት አገር ይኖረን ነበር?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
ሶሎሞን አ.
[email protected]