የከፍተኛ ትምህርት ተቁዋማት የትምህርት ጥራት ደረጃ እጂግ አሳሳቢ ሆነ፣ ተመራቂዎች ምንም ቁም ነገር ሳንይዝ ለምረቃ በቃን አሉ
በያዝነው ዓመት እጂግ በርካታ ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን ተከታትለው በተለያዩ ደረጃዎች በመመረቅ ላይ ያሉ ሲሆን የግንቦት ሰባት ዘጋቢ ያነጋገራቸው ምሩቃን በሰጡት አስተያየት ምን እንደተማርን ሳናውቀውና እዚህ ግባ የሚባል እውቀት ሳንጨብጥ ለምረቃ በቃን፣ ይህም እኛን እያሳፈረንና እያሸማቀቀን ይኖራል በማለት ለዚህ ያበቃቸውን ሥርዓት አመራሩ።
ዘጋቢያችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት በመገኘት ካነጋገራቸው ተመራቂዎች ውስጥ በኢኮኖሚክስ ትመህርት መስክ በኤክስቴንሽን የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘት ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀች ወጣት፣ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ብቃት ያላቸው መምህራንና በቂ የማስተማሪያ መሣሪያዎች እጥረት ጎልቶ መኖሩን መንግሥት ተብዬው አገዛዝ እያወቀው ምረቃ በአላችን ላይ የተገኘው የወያኔ ሹም ጁኔዲን ሳዶ የትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶአል የሚል ድስኩር መልሶ ለኛው ለተጎጂዎች ማሰማቱ እጅግ የሚያበግን ነው ብላለች። ወጣቷ በመቀጠልም፣ አገራችን ውስጥ ስራ በመፈለግ ራስን ለማስተዳደር አንደኛው መንገድ ራስን በትምህርት የተሻለ ደረጃ ላይ ማስቀምነጥ እንደነበር ገልጻ ባሁኑ ወቅት ይህ ሁሉ ቀርቶ ስራ ማግኘት በፓርቲ አባልነት፣ በዘመድ አዝማድና በሌሎችም አሳዛኝ መንገዶች በመሆኑ ትምህርቷን አጠናቃ በዲግሪ መመረቁ በራሱ ምንም ትርጉም ሊሰጣት እንደማይችል በምሬት ገልጻለች። አገሪቷ ውስጥ በተንሰራፋው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምክንያት የተሻለ እውቀትና ልምድ ያላቸው አገራቸውን ጥለው እየተሰደዱ የትምህርት ጥራት እንዴት ማስጠበቅ እንደሚቻል ማወቅ ይቸግራል ያለቺው ወጣት እንደአሸን የፈሉ የዘመናችን ዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ታላላቆቻችን ከነበሩበት የሁለተና ደረጃ በ እጅጉ እንደሚያንስ ህብረተሰቡ ተገንዝቦታል ብላለች።
በሌላም በኩል በሶሺዮሎጂ የትምህርት መስክ የሁለተኛ ዲግሪዉን የያዘ ስሙ እንዳይጠቀስ ያሳሰበ ወጣት፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቁአማት የትምህርት ጥራት ደረጃ በአሳፋሪ መልኩ የወደቀው ዛሬ ሳይሆን ከበርካታ አመታት በፊት ነው። ይህ የትምህርት ጥራት ሲወድቅና እንዲህ ባለ አሳፋሪ ደረጃ ላይ ሲገኝ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ የሚገኙት ምሁራን ተብየዎች እጃቸውን አጣጥፈው ሲመለከቱ ቆይተዋል። አሁን ባለንበት ሁኔታ በምን መልክ ይህን ችግር መፍታትና ወደነበረበት ደረጃ መመለስ እንደሚቻል አይገባኝም። ይህቺ ሃገር በአይናችን እየተመለከትናት በሁሉም ዘርፍ ልተወጣበት ከማትችልበት አዘቅት ውስጥ እየገባች ነውና ችግሩን ለመቅረፍ ባለመጣራችን ሁላችንም በታሪክና በተተኪው ትውልድ ፊት በሃላፍነት ከመጠየቅ የምንድን አይመስለኝም ብሎአል።
በዘንድሮው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ላይ የተገኘው ሆድ አደሩ ጁነዲን ሳዶ የትምህርት ጥራት ችግር ከመምህራን ብቃት ጋር ተዳምሮ ተማሪዎችን በብቃት የማውጣቱ ሥራ ገና የሚቀረው ነው ፣ ድህነትን ልናጠፋ የምንችለው የምስክር ወረቀት ያላቸው ሥራ ፈላጊዎችን ማፍራት ሳይሆን፣ ሥራ ፈጣሪና ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች በማፍራት ነው በማለት መደስኮሩ ታውቁአል።
የግንቦት ሰባት ዘጋቢ ጁነዲን ሳዶ ባደረገው ንግግር ላይ አስተያየት እንዲሰጡት የጠየቃቸው የአንዲት ተመራቂ አባት በሰጡት አስተያየት፣ እንደ ጁነዲን ሳዶ ያሉት የወያኔ ሆድ አደሮች እኮ የሚናገሩትን የሚያውቁም አይመስለኝም፣ በሃገራችን ውስጥ እየታዩ ላሉ በርካታ ችግሮች መንስኤዎቹ እነሱ፣ ይህ መሆኑን እያወቁ ደግሞ፣ ልክ እንዳሁኑ የትምህርት ጥራት ደረጃ አሳቢ ነው በማለት ባደባባይ መናገር የወያኔ ባለስልጣናት ምንም አይነይት ይሉኝታና ሃፍረት ያልፈጠረባቸው መሆኑን ከማሳየት ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም ብለዋል።